መንግሥት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው። በእርግጥም ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የስራ እድል በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለአገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም ትስስር የሚፈጠርባቸው መሆናቸው ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም ሰፊ የሰው ኃይል ያለ መሆኑና በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መኖሩ፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ተክለው እንዲሰሩ ጥረቶች ተደርገዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። እነዚህ ተልዕኮዎቻቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በተጠናቀረ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ መሰረት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በቀጥታ በምርት ተግባራት ላይ 81ሺ ሰራተኞች ተሰማርተዋል። ይህ ቁጥር ከፓርኮቹ ውጭ ያሉና ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች አይጨምርም። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ከፓርኮቹ ውጭ ካሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የስራ ትስስር ስላላቸው በዚህ ሂደትም በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፓርኮቹ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ፣ ለውጭ ገበያ የቀረበውና በተኪ ምርቶች የተገኘው ገቢ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ከዚህ ገቢ ውስጥ፣ 930 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ነው።
በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል። በተለይም እንደ አገር የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ በሚያስፈልግበት በእዚህ ወቅት እንደ አንድ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ከእነዚህ ፓርኮች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። በ279 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ፓርኩ፣ የፋርማሲዩቲካል ምርቶችን የሚያመርቱ ባለሀብቶች እንዲሰማሩበት የተገነባ ነው። በአሁኑ ወቅት 17 ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው በተለያዩ ደረጃዎች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል። ወደ ፓርኩ የገቡት አምራቾች ኢትዮጵያን በየዓመቱ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ከሚዳርጓት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነውን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ግዢ ፍላጎት በአገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገውን ጥረት እያገዙ ይገኛሉ።
የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ ረጋሳ፣ ፓርኩ ለአምራች ኩባንያዎች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ አምራቾችን እየተቀበለና ሌሎች አምራቾችንም እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ወደ ፓርኩ የገቡት ባለሀብቶች በማምረት ላይ፣ በግንባታ ላይ እና በዲዛይን/ጥናት ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ አምራቾች የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። በቀጣይ ወራትም ወደ ምርት የሚገቡ አምራቾች አሉ። ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ወደ ፓርኩ ገብተው ለመስራት ፍላጎት ያሳዩ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ፓርኩ ገብተው እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ አስራት እንደሚሉት፣ ባለሀብቶቹ በዘርፉ ኢንቨስት ሲያደርጉ የታክስ ክፍያ የእፎይታ ጊዜ፣ ከውጭ ለሚያስገቧቸው ግብአቶች የቀረጥ ነፃ ድጋፍና ሌሎች ማበረታቻዎች ይደረጉላቸዋል። ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለሚሰማሩ ባለሀብቶች፣ በተለይም ተኪ ምርቶችን በማምረት ላይ ላተኮሩ አምራቾች፣ የመሬትና የማምረቻ ሼድ ኪራይ ክፍያን በብር እንዲከፍሉ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። ባለብቶቹ ወደ ፓርኩ ገብተው በፈለጉት ዲዛይን ገንብተው እየሰሩ እንደሚገኙና በግልም ሆነ በጋራ በመሆን የሚያለሙበት መንገድ እንደሚመቻችላቸው ገልፀዋል።
ባለሀብቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ለዘላቂ የአገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተም ‹‹የአገር ውስጥ አቅም ለመፍጠር የሚያግዙ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከምቹ ሁኔታዎቹም መካከል የታክስ ክፍያ እፎይታ፣ አምራቾች ከውጭ ለሚያስገቧቸው የምርት ግብዓቶች የሚደረጉ ድጋፎችና ሌሎች ማበረታቻዎችም አሉ። ባለሀብቶች የመሬት ሊዝ ክፍያው በዶላር መሆኑ አሁን ባለው የምንዛሬ ዋጋ አስቸጋሪ ስለሚሆን የሊዝ ዋጋው በኢትዮጵያ ብር ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የሊዝ ዋጋው በዶላር ስሌት በብር የሚከፈልበት መንገድ እየተመቻቸ ይገኛል›› በማለት ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያዎች አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ ለማ ገብረየስ በበኩላቸው፤ ፓርኩ የመብራትና ውሃን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ተግባራት ምቹ እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹ፓርኩ የውሃ፣ የመብራት፣ የደህንነትና ሌሎች አግልግሎቶች አሉት። ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከባንኮች፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ባለሀብቶች ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር በሽርክና እንዲሰሩና ወደ ፓርኩ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ጥሬ እቃዎችን አምጥቶ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ፓርክ ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መቀነስ ይቻላል። ለባለሀብቶቹ የሚደረጉት ማበረታቻዎችም ትልቅ ፋይዳ አላቸው›› ይላሉ።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት አገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል።
የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል። ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለባለሀብቶች ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ ትኩረት የሚሻው ሌላው ጉዳይ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ማበረታታት ነው። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ለዘላቂ የአገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉ የልማት አንቀሳቃሾች ናቸው። በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። እነዚህ አገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ የሰሩት ስራ የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሏቸዋል።
የበለፀጉት የዓለም አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን ቀደም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሳይሆን አሁንም ከፍተኛ ድጋፍና ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። አገራቱ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለባለሀብቶቻቸው የተለየ የድጋፍ መርሃ ግብር አላቸው። የበለጸጉት አገራት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከሚያደርጉት ድጋፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሰረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የውስጥ አምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይታወቃል።
የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይገባል። ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል።
በተለይ ኢትዮጵያ በስራ አጥነትና በዋጋ ንረት እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። መንግሥት ለባለሀብቶቹ የሚያደርገው ድጋፍ ምጣኔ ሀብቱን በማነቃቃት፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የገቢ ንግድ እቃዎችን በመተካት፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ አገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል።
ኢትዮጵያውያን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም። አገሪቱን በየዓመቱ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ከሚዳርጓት ዘርፎች መካከል አንዱ የመድኃኒት ግዢ በመሆኑ የሕክምና መገልገያዎችን በአገር ውስጥ በማምረት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን በመደገፍ የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንዲሁም የአገሪቱን የጤና ዘርፍ ማሻሻል ያስፈልጋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2015