ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችሉ ለዘርፉ የሚውሉ ግብዓቶች እምቅ አቅም እንዳላት ይታወቃል:: እነዚህ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶችና ብዛት ያለው ወጣት ኃይሏ ለአምራች ኢንዱስትሪም ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ይጠቀሳሉ::
ዘርፉ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በመንግሥት ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተብለው ከተለዩት ዘርፎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም፣ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደሚያስችሉ ታምኖባቸዋል:: ለዚህም ነው ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ዘላቂ ተወዳዳሪነትንና ምርታማነትን የሚያረጋግጥ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው::
ወደ ተግባር ከተገባ በኋላም በኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ለውጦችና መሻሻሎች ታይተዋል:: ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር 47 በመቶ የነበረው የማምረት አቅም ዘንድሮ 61 በመቶ ደርሷል:: ይህ በጣም ትልቅ እምርታ ነው፤ አሁንም ማደግ አለበት፤ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ሥራ ገብተዋል:: በዚህ ዓመት ብቻ ከ55 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል:: ከ120 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች አዳዲስ ፍቃድ አውጥተዋል::
የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ አልፎም ተርፎ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል:: ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለሌሎች ዘርፎች እድገትና መነቃቃትም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፡- ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚውል አንድ ዶላር ለሌላው ዘርፍ የሶስት ነጥብ ስድስት ዶላር አበርክቶ ይኖረዋል። በዘርፉ የሚፈጠር አንድ ቀጥተኛ የሥራ ዕድል በሌሎች ዘርፎች ከሰባት እስከ ዘጠኝ ለሚደርሱ ሰዎች ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ በዚህም ዘርፉ የዕድገት ሞተር ሆኖ ያገለግላል::
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት በማስቀረት ለብክነት የተዳረገን ሀብት ማዳን የተቻለበት ነው::
ባለፈው ሳምንት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ተገምግሟል::
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤቶችን ማምጣት ተችሏል:: ይህም ያለፉት ዘጠኝ ወራት የማምረት አቅም ወደ ተሻለ አፈጻጸም እንዲመጣ አድርጓል:: በክልሎች መካከል ያለው የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምም እንዲሁ እያደገ መጥቷል::
የአንዳንድ ክልሎች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከሚጠበቀውም ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅም 64 በመቶ ያህል የደረሰበት ሁኔታ እንዳለም አስታውቀዋል:: ይህም አቅማቸው ከፍ እያለ መሆኑን እንደሚያመላክት ይጠቁማሉ:: ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስኬት ሊመዘገብ የቻለው አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ከማስገባት አኳያ ውጤታማ ሥራ በመሠራቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል::
ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ረገድ ውጤታማ ተግባሮች መከናወናቸውንም ያመላክታሉ:: በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሶስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል:: ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት የተመረቱት ተኪ ምርቶች አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ እንደነበሩም አስታውሰዋል::
ተኪ ምርቶችን ከጨርቃጨርቅ፣ አልባሳት፣ ከምግብና መጠጦች ባለፈ ማሽነሪዎች ጭምር በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል::
በሌላ በኩል ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች አንጻርም የእቅዱን ያህል ማሳካት ባይቻልም፣ የባለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ በላይ ብልጫ ማሳየቱን አመላክተዋል:: አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በማስገባት የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ በቀሪዎቹ ወራት የአምራች ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አስታውቀዋል::
በመድረኩ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የዘንድሮው በጀት ዓመት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የተጀመረበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የበጀት ዓመቱን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል:: ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተተግብሯል ሲባል ከኢኮኖሚ ፖሊሲው አንጻር ለየት ያለ ትርጉም እንዳለውም ይገልጻሉ:: በዚህም የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ በነፃ ገበያ እንዲወሰን መደረጉን ጠቅሰው፣ ገቢያችንን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረግን ባለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማ መሆኑን አመልክተዋል:: በመደበኛ ሥራዎች አፈጻጸምም በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው እና በማዕድን ዘርፎች በጣም ጥሩ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ጠቅሰዋል።
በተለይ ደግሞ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካኝነት የሚካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› የሚመራባቸው የስትራቴጂ ማሕቀፎች በደንብ ጠርተው የወጡበትና ዘርፉ የተቀናጀና የተደራጀ አመራር እየተሰጠበት መሆኑን ያነሳሉ:: የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሻሻልና ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በጣም ጥሩ ውጤቶች እያመጡ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አመላክተዋል::
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ዓባይ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በፖሊሲ ደረጃ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ብዙ እየተሠራ ይገኛል:: በዚህም በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ተቀዛቅዞ የኖረውን የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በማነቃቃት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል::
‹‹በኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በተከናወነው ውጤታማ ሥራ ኤክስፖርት አቁመው የነበሩ 24 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል:: ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ምርት ወደ ውጭ መላክ የጀመሩት አምራች ኢንዱስትሪዎች 14 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል::
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ እንዳለው የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ በቀጣይ አስር ዓመታት ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ይገልጻሉ። በተጨማሪም የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል:: የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ በየዓመቱ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉት፡- በኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለፉት አራት ዓመታት የንቅናቄና የሪፎርም ሥራዎች በመከናወናቸው በአምራች ኢንዱስትሪ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከዚህ በፊት ወጪ ምርቶች ላይ ብቻ ይደረግ የነበረውን የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር ተኪ ምርቶችንም የሚያበረታታ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
በዚህም በ2016 በተኪ ምርት ለማሳካት ታቅዶ የነበረው ሁለት ነጥብ 31 ቢሊዮን ዶላር ማዳን እንደነበረ አስታውሰው ፤ ሁለት ነጥብ ስምንት አራት ቢሊዮን ዶላር በማዳን ውጤታማ አፈጻጸም ሊመዘገብ መቻሉን ያመላክታሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በቀጣይ ኢንዱስትሪው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ በአስተማማኝነት ለማሳደግ ይሠራል። ለዚህም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ በመቀጠል ተኪ ምርት ላይ ትኩረት ይደረጋል:: ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የመሳብ እና ያሉትን በማጠናከር የሥራ እድል ፈጠራውን በሚጠበቀው ደረጃ የማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አብራርተዋል::
ባለፉት ዓመታት በተለይ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙና በአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ መንግሥት ትልቅ አቅጣጫ አድርጎ ከወሰዳቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ኢንዱስትሪ ነው የሚሉት የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ መላኩ አለበል፤ በፖሊሲ ፣ በስትራቴጂ እንዲሁም በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› እንደ ሀገር ለዘርፉ ምቹና ጠንካራ መዋቅር እየተዘረጋ መሆኑን አመላክተዋል:: ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በተቋቋመው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ካውንስል አማካይነት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል::
ሚንስትሩ እንዳብራሩት፡- የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በዘላቂነት እንዲያድግና ተወዳዳሪ እንዲሆን የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ ነው:: ኢኮኖሚያችን በዘላቂነት ተወዳዳሪ እንዲሆን ካስፈለገ ከሎጀስቲክ ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮችም በፍጥነት መፍታት አለባቸው::
ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የባሕር በር አስፈላጊ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት ከኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ጋር በተያያዘ መሆኑን አመልክተዋል:: አምራች ኢንዱስትሪዎች ለምርት የሚጠቀሟቸው ግብዓቶች ለማስገባትና ምርታቸውንም በቀላሉ ኤክስፖርት ለማድረግ እንዲችሉ እንደ ሀገር ያለውን የባሕር በር ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው::
‹‹ኢንዱስትሪ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ፤ በጣም ውስብስብና ከባድና ከመሆኑም በላይ ልክ መርከብ እንደማዞር ያህል ነው›› የሚሉት ሚንስትሩ፤ በዚህ የተነሳ ውጤቱ በአንድ ጊዜ አይታይም›› ሲሉ አስገንዝበው፣ እንዲያም ሆኖ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ በአብዛኛው መስመር እየያዘ መምጣቱን ያመላክታሉ:: ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኢንዱስትሪው የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ልክ ተቋማዊ አቅምን ለመገንባትና ለማጠናከር ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል::
የታሪፍ ጭማሪን በተመለከተ ያብራሩት ሚንስትሩ እንደ ሀገር የኛን ዓይነት ምርት አምርተው በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች /ሀገራት/ ከተጫነባቸው አዲስ ታሪፊ አኳያ እንደሚታይ አስታውቀዋል:: ‹‹የእነ ህንድ፣ ቬትናምና ቻይና ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከእኛ ሀገር በላይ ከፍ ያለ ታክስ የተጨመረባቸው መሆናቸውን ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ እነርሱ ላይ የተጣለው ታሪፍ 40 እና 50 በመቶ መሆኑ የኛ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ የመወዳዳር አቅማቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል ሲሉም አብራርተዋል:: እንዲያም ሆኖ ተወዳዳሪነትን በውስጣችንን ካላሳደርን፣ የምርት ጥራትን ካላረጋገጥንና አዳዲስ ነገሮችን እስካላመጣን ድረስ በተወዳዳሪነት መጠቀም አንችልም›› ብለዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የዘርፉ የኢንቨስትመንት ፍሰት እያደገ መጥቷል፤ በ2017 በጀት 202 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል፤ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በተሰጠው ልዩ ትኩረት አሁን ላይ ካለው አምራች ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገር ውስጥ ባለሀብት እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።
ሀገሪቱ ካላት እምቅ የማልማት አቅም እና ከ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ግቦች አንጻር አሁንም ትኩረት የሚሹና የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በተለይ የኢንዱስትሪ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት በብዙ ማነቆዎች ውስጥ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ኢተገማች እየሆነ መምጣቱን ተናግረው፣ በየሰዓቱ የተለያዩ ክስተቶች ይፈጠራሉ ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል:: ለዚህ እንደ ሀገር ያለበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ተወዳዳሪነትን ማሳደግና ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጠውን ድጋፍም ይበልጥ ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል:: ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል
ከዓመቱ እቅድ አኳያ ቀሪዎቹ ወራት በጣም አጭር ጊዜያት መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በእነዚህ ቀሪ ወራት በቁርጠኝነት የመሥራት ሀገራዊ ኃላፊነት አለብን ሲሉ አስገንዘበዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም