በመጪው ጥር በአልጄሪያ አዘጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ(ቻን) ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሚሳተፍ ይታወቃል። ዋልያዎቹ ለሶስተኛ ጊዜ በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክና ሊቢያ ጋር የምድብ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ቀደም ብለው መደልደላቸው ይታወቃል። ከትናንት በስቲያም ዋልያዎቹ የምድብ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ቀን እና ሰዓት ይፋ ሆኗል። በዚህም መሰረት ጥር 5 ቀን ምሽት 1 ሰዓት ላይ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሞዛምቢክ ጋር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ጥር 9 – ምሽት 4 ሰዓት ከአልጄርያ ጋር ሁለተኛውን ጨዋታ ያከናውናሉ። ቀሪውን አንድ የምድብ ጨዋታም ጥር 13- ምሽት 4 ሰዓት ከሊቢያ ጋር እንደሚጫወቱ ከወጣው መርሃግብር ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን ዋንጫን ጨምሮ በቀጣይ ወራት ለሚያደርጋቸው አህጉራዊ ውድድሮች ይረዳው ዘንድ ከወዲሁ የወዳጅነት ጨዋታዎችን እየፈለገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። በዚህም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ከአፍሪካ ይልቅ ፊቱን ወደ አውሮፓ በማዞር በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከምትገኘው ከአየርላንድ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጥያቄ እንዳቀረበ ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።
ዋልያዎቹ እኤአ ከ2013ቱ የደቡብ አፍሪካ የቻን ዋንጫ ጀምሮ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን በቀጣይም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመሩ ለሁለተኛ ጊዜ በመድረኩ ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በሁለቱም ተሳትፏቸው ከምድብ ማለፍ ሳይችሉ ደካማ ውጤት በማስመዝገብ ነበር ከውድድሩ የተሰናበቱት። ዘንድሮ ደቡብ ሱዳንን በደርሶመልስ ጨዋታ ውጤት 5ለ0 እንዲሁም ርዋንዳን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለሶስተኛ ዋልያዎቹን ለቻን ያበቁት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ካለፉት ሁለት ተሳትፎዎች የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል። አሰልጣኙ ባለፈው ወር ከዋልያዎቹ ጋር ለመቀጠል የሁለት አመት ኮንትራት ሲሰጣቸውም ቡድኑን በዘንድሮው የቻን ዋንጫ ከምድብ ጨዋታ የማሳለፍ ሃላፊነት እንደተሰጣቸው ይታወሳል።
በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በጥር ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው ሰባተኛው የቻን ዋንጫ የተሳታፊ አገራትን ቁጥር በመጨመር ከዚህ ቀደም በቻምፒዮናው የሚሳተፉ 16 አገራትን ወደ 18 ማሳደጉን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከወር በፊት አሳውቋል።
በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የራሳቸው የአፍሪካ ዋንጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ በማመን የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮና (ቻን) የሚባለውን ውድድር እንደ ዋናው የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ ማዘጋጀት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዘንድሮ በሚካሄደው ውድድር አስራ ስምንቱ ተሳታፊ አገራት በአምስት ምድብ ተከፍለው የሚጫወቱ ይሆናል።
አስራ ስምንቱ አገራት በሚሳተፉበት የቻን ውድድር አዲስ ይዘት ከአምስቱ ምድብ በሦስቱ ምድቦች አራት አራት አገራት የሚፋለሙ ሲሆን፣ በሁለቱ ቀሪ ምድቦች ሦስት ሦስት አገራት የሚፋለሙ ይሆናል። በአዲሱ የውድድር ሕግ መሰረትም አራት አራት አገራት ከሚፋለሙበት የመጀመሪያ ምድብ ሁለት ሁለት አገራት ወደ ሩብ ፍጻሜ ሲያልፉ ሦስት ሦስት አገራት ከሚፋለሙበት ሁለቱ ምድብ አንድ አንድ አገር ብቻ ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላል።
የውድድሩ ሃሳብ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በካፍ የተጠነሰሰ ሲሆን እኤአ 2009 ላይ የመጀመሪያው ውድድር በኮትዲቯር አስተናጋጅነት መካሄዱ ይታወቃል። የመጀመሪያው ውድድር በስምንት አገራት መካከል ቢካሄድም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመሳተፍ ፍላጎታቸው በመጨመሩ በሁለተኛው ውድድር በቀጥታ ወደ አስራ ስድስት ሊያድግ ችሏል። ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሞሮኮ ይህን ዋንጫ ሁለት ሁለት ጊዜ በማንሳት ስኬታማ ሆነው የሚጠቀሱ ሲሆን ሊቢያና ቱኒዚያ አንድ አንድ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት በመሆን ታሪክ አላቸው።
በአልጄሪያ የሚካሄደው የቻን ዋንጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቀድሞ ሊካሄድ ከነበረበት ጊዜ ተራዝሞ የሚካሄድ ሲሆን፣ አልጄሪያ ውድድሩን ለማስተናገድ በይፋ ኃላፊነቱን የወሰደችው በ2018 እንደነበር ይታወሳል። ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ ይህን በአፍሪካ ሁለተኛውን ትልቅ የእግር ኳስ ውድድር በአራት የተለያዩ ስቴድየሞቿ ለማስተናገድ ዝግጅቷን ከጀመረች ቆይታለች።
ውድድሩን የሚያስተናግዱት ስቴድየሞችም በመዲናዋ አልጄርስ፣ በኦራን ከተማ የሚገኘው ኦሊምፒክ ስቴድየም፣ በአናባ የሚገኘው ቻሂድ እንዲሁም በሃምሎይ የሚገኘው ኮንስታንቲን ስቴድየሞች ውድድሩን ለማስተናገድ ተመርጠዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምተ 9 ቀን 2015 ዓም