በየዘመኑ ተተኪ የሚሆኑ የአትሌቲክስ ጀግኖችን የምታፈራው ኢትዮጵያ፤ አሁን ደግሞ ከመም ወደ ማራቶን ውድድሮች የተሸጋገሩ አዳዲስ ከዋክብቶችን አግኝታለች። እጅግ ፈታኝ በሆነው የማራቶን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፈው ውጤታማ የሆኑት ድንቅ ድንቅ አትሌቶችም ከመላው ዓለም አድናቆት እየጎረፈላቸው ይገኛል። ታሪካዊ በሆነውና በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው የአምስተርዳም ማራቶን በኦሊምፒክና ሌሎች የመም ውድድሮች የለመዱትን በክብር ላይ ክብር መደረብ ደግመው አሳይተዋል። በሁለቱም ጾታ ከተፎካካሪዎቻቸው ልቀው በመገኘት የበላይነቱን በመውሰድ የአገራቸውን ስምም አስጠርተዋል።
ይህ ውድድር አስቀድሞ የተጠበቀው በተለይ በሴቶች በኩል ነበር። ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ በረጅምና መካከለኛ ርቀት የመም ውድድሮች የስፖርቱን ቤተሰብ ያስደመሙት ጀግኖች በእኩል ወቅት ፊታቸውን ወደ ማራቶን በማዞራቸው ነው። ስኬታማ እንደሆኑበት የመም ውድድር ሁሉ በጎዳና ላይም ስኬታማ ይሆናሉ የሚለውም በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቅ ጉዳይ ነበር። በውድድሩም ላይ በማራቶን ልምድ እንዳላቸው አትሌቶች አብዛኛውን ርቀት ሲመሩ የቆዩት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሲሆኑ፤ በግማሽ ማራቶን በተደጋጋሚ በመሮጥ ልምድ ያላት ጸሃይ ገመቹ እስከ 33ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ውድድሩን ስትቆጣጠር ቆይታለች። ከ35 ኪሎ ሜትር በኋላ ግን የሪዮ ኦሊምፒክ ጀግናዋ አትሌት አልማዝ አያና ወደፊት በመስፈንጠር የመሪነቱን ቦታ በመያዝ አሸናፊ ለመሆን ችላለች።
አልማዝ ፍጥነቷን በመጨመርም የርቀቱን የመጨረሻ መስመር በቀዳሚነት ስትረግጥ፤ የገባችበት 2:17:20 የሆነ ሰዓት የአምስርተርዳም ማራቶን ፈጣኑ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ሶስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ በሃምቡርግ ማራቶን ከገባችበት ሰዓት በሶስት ሰከንዶች የፈጠነና የኢትዮጵያን ክብረወሰን የግሏ ለማድረግ ያስቻላት ነው። ከዓለም ደግሞ ሰባተኛው ፈጣን ሰዓት በመሆኑ አትሌቷ የማራቶን ጉዞዋን በስኬት መጀመሯን አስመስክራለች። እአአ የ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትርን ለረጅም ዓመታት ሳይደፈር የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አድናቆትን ያተረፈችው አልማዝ፤ በ1ሺ500 ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ በማጥለቅም ስኬታማ ነበረች። ይሁንና በጉዳትና በወሊድ ምክንያት ለረጅም ጊዜ በውድድሮች ላይ ሳትታይ ቆይታለች።
እአአ የ2015 እና 2017 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎችን በ5ሺ እና 10ሺ ሜትሮች ስኬታማ አትሌት ስትሆን፤ በዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ አትሌትነት ተመራጭ መሆኗም የሚታወስ ነው። ከዓመታት በኋላም ባለፈው ወር የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ከተሳተፈች በኋላ ማራቶንን ሮጣለች። አትሌቷ ከድሏ በኋላም ‹‹ቃላት የለኝም፤ ይህ የተለየ ነገር ነው ደስ ብሎኛል። ከ2016ቱ ኦሊምፒክ በኋላ በጉዳት ምክንያት አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። በባለቤቴ፤ ልጄ እና በስልጠና ቡድኔ እገዛ ለዚ በቅቻለሁ›› በማለት ገልጻለች።
ሌላኛዋ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ በመሮጥ ስኬታማነቷን ከወዲሁ ያረጋገጠችው ገንዘቤ ዲባባ ናት። አልማዝን ተከትላ በመግባት 2:18:05 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀችው አትሌቷ ከዓለም 20 ምርጥ የማራቶን አትሌቶች መካከል አንዷ ለመሆን የሚያስችላትን ጅምር አሳይታለች። ብርቱ ተፎካካሪ የነበረችውና ሩጫውን ስትቆጣጠር ቆይታ የአገሯ ልጆች አሸናፊዎች እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና የተጫወተችው ጸሃይ ገመቹ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። 2:18:59 በሆነ ሰዓት የገባችው አትሌቷ ከግማሽ ማራቶን ወደ ማራቶን ያደረገችው ሽግግር በስኬት የታጀበ መሆኑንም አረጋግጣበታለች።
በወንዶች በኩልም ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አንደኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ በውድድሩ የነበራቸውን የበላይነት አሳይተዋል። በርቀቱ እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ በአሯሯጭ የታገዙት ኬንያውያን አትሌቶች በመሪነት ቢቆዩም ኢትዮጵያውያኑ ብርቱ አትሌቶች ለአምስት ጊዜ በተቀናቃኞቻቸው የተያዘውን የውድድሩን አልሸነፍ ባይነት ሰብረው በማለፍ ለአሸናፊነት በቅተዋል። 40ኛው ኪሎ ሜትር ላይም አትሌት ጸጋዬ ጌታቸው አፈትልኮ በመውጣት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረገ ሲሆን፤ 2:04:49 በሆነ ሰዓት በመግባት አሸናፊ ሊሆን ችሏል። ከውድድሩም በኋላ ‹‹ጥሩ ውድድር ነበር፤ አየሩም ሆነ ድጋፍ ሰጪዎቹም መልካም ነበሩ›› ብሏል።
ኬንያዊው አትሌት ቲቱስ ኪፕሩቶ አሸናፊ ለመሆን ጠንካራ ፉክክር ቢያደርግም በአምስት ሰከንዶች በመዘግየቱ ሁለተኛ ለመሆን ተገዷል። እጅግ ጠንካራ የአሸናፊነት ፉክክር በታየበት ውድድር ሶስት ሰከንዶችን ብቻ በመዘግየቱ ኬንያዊውን አትሌት ተከትሎ የገባው ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት ባዘዘው አስማረ ነው። ብርቱው አትሌት ኬንያውያኑ አትሌቶች ቡድን ሰብሮ በመግባት የማሸነፍ ውጥናቸውን ለማክሸፍ ችሏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/ 2015 ዓ.ም