የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ከሃምሳና ስልሳ ዓመታት በፊት የታተሙ ጋዜጦች ይዘው የወጡትን ዘገባዎች ያስታውሰናል። የደብረ ዘይት የከብት ሕክምና ኢንስቲትዩት የተለያዩ የእንስሳት በሽታ መከላከያ መድኃኒት እየቀመመ ለእንስሳት ሕክምና በሥራ ላይ ማዋሉ ለትውስታ ከመረጥናቸው ዘገባዎች ተጠቃሽ ነው። ሌሎች በተለይም የመዝናኛ ይዘት ያላቸው ዘገባዎችንም መራርጠን እንደሚከተለው አቅርበናል።
ለ፮ ሚሊዮን እንስሳት የሚበቃ መድኃኒት ተቀምሟል
ደብረ ዘይት፤(ኢ.ዜ.አ.)፤ ደብረ ዘይት የሚገኘው የከብት ሕክምና ኢንስቲትዩት፤ በዚህ ዓመት ለ፮ ሚሊዮን ፬፻፴፫ሺህ ፭፻፺፭ እንስሳት የሚበቃ ልዩ ልዩ የእንስሶች በሽታ መከላከያ የሚሆን መድኃኒት መቀመሙን አንድ የኢንስቲትዩቱ ቃል አቀባይ ገለጠ።
ቃል አቀባዩ ከዚህ አያይዞ እንዳስረዳው፤ የተቀመመው መድኃኒት ፭ ሚሊየን፫፻፴፰ ሺህ ፪፻ ዶዝ ለቀንድ ከብቶች፣ ለአሳማዎች በሽታ መከላከያ መሆኑን ገልጧል።
እንደዚሁም፤ በተለይ የተዘጋጀ ፓስቴውሪላ ፩፻፸፯ ሺህ ፬፻፳፭ ዶዝ ፣አባ ጎርባ ለተባለው በሽታ መከላከያ፤ ፩፻፸፩ ሺህ ፪፻፶ ዶዝ፣ ለአባ ሠንጋ በሽታ መከላከያ ፬ሺህ ዶዝ፣ ፋውል ታይፎይድ ማለት(የዶሮ በሽታ) ፭ሺህ ፭፻ ዶዝ፣ ፋውል ኮሌራ (የዶሮ) በሽታ መከላከያ የሆኑ መድኃኒቶችን ቀምሞ በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል።
ቃል አቀባዩ አቶ ጌታሁን አበጀ ከዚህም በማያያዝ፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ መድኃኒቶችን ቀምሞ በየጠቅላይ ግዛቶቹ ታድለው በሥራ ላይ መዋላቸውን ከገለጡ በኋላ፤ የመከላከያ መድኃኒቱን ከውጭ ሀገር ስናስመጣ እዚሁ ስለሚቀመምና ስለሚዘጋጅ የከብት ሕክምና ዋና መምሪያ በሽታውን ለመከላከልም ሆነ፤ ፈጽሞ ለማስወገድ በየቦታው ያሠማራቸው ሠራተኞቹ መከላከያ መድኃኒት የማነስም ሆነ የማጣት ችግር አይገጥማቸውም።
የመከላከያ መድኃኒቶቹን በላቦራቶሪ ውስጥ ቀምመው የሚያዘጋጁ አንድ ኢትዮጵያዊ ዶክተርና ሦስት የውጭ አገር ዶክተሮች ይገኛሉ። ከዚህም ሌላ በቂ ትምህርት ያላቸው ቴክኒሺያኖችና የዶክተሮቹ ረዳቶች መኖራቸውን ገልጠዋል።
(ነሐሴ 11ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
፪ ጭንቅላት ያለው ጥጃ ሞቶ ተወለደ
ጐባ (ኢ.ዜ.አ.) በባሌ ጠቅላይ ግዛት በገናሌ አውራጃ በዶዶላ ወረዳ ግዛት አቤና አንሻ በተባለው ቀበሌ ባለፈው ግንቦት ፳ ቀን ፷፩ ዓ/ም ንብረትነቷ የአቶ ጂሎ ጊጐ የሆነች ላም ልዩ ተፈጥሮ ያለው አንድ ወንድ ጥጃ ወለደች።
ይኸው የተወለደው ጥጃ ሁለት ጭንቅላት፤ ፬ ጆሮ ፤ ሁለት አፍ፤ ፬ ዓይን ሁለት ጭራ ያለው ሲሆን የእበት መጣያ ሥፍራ ደግሞ ድፍን መሆኑ ታውቋል። ጥጃው ከላይ በተጠቀሱት የአካል ክፍሎች ከሌሎች እንስሳት የተለየ ቢሆንም፤ እግሮቹና ብልቱ ትክክለኛውን የእንስሳት ተፈጥሮ የያዙ ናቸው።
ይኸው ልዩ ተፈጥሮ ያለው ጥጃ ከመወለዱ በፊት በእናቱ ማህፀን ሞቶ ስለነበር በመንደር ወጌሻ እርዳታ የወጣ መሆኑን የአውራጃው ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ ሙላት ሙሉነህ ገለጠ።
(ሰኔ 1 ቀን 1961 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ወንዝ ውስጥ ገቡ
የመቶ አለቃ ታደሰ ዱባለ የተባሉ የክቡር ዘበኛ ባልደረባ ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም፤ ከምሽቱ ፫ ሰዓት ከሐያ ደቂቃ ሲሆን፤ የሰሌዳው ቁጥር ፮ሺህ ፰፻፹ የሆነ ሠራዊት ጂፕ መኪና ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኮከብ ወደ ሚያዝያ ፳፯ አደባባይ እየነዱ ሲሔዱ ራስ መኮንን ድልድይ ሲደርሱ፤ ወደ ግራቸው ተጠምዝዘው የድልድዩን ድጋፍ ከሰበሩ በኋላ፤ ወንዝ ውስጥ ገብተው አደጋ ደርሶባቸዋል።
አደጋ መሆኑ እንደተሰማ፤ የትራፊክ ፖሊሶች ከሥፍራው ደርሰው በእሳት አደጋ ወታደሮች ዕርዳታ ቁስለኛውን ከድልድዩ ውስጥ ካወጡ በኋላ፤ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ወስደዋቸው የመጀመሪያ ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ፤ የደረሰባቸው ቁስል ከባድ በመሆኑ ወደ ክቡር ዘበኛ ሆስፒታል ተዛውረው በዚያ ተኝተዋል።
እድልድዩ የገባው ጂፕ ትናንት በክቡር ዘበኛ መኪና ተጐትቶ ከወንዙ ውስጥ ወጥቷል።
(ሐምሌ 7 ቀን 1953 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ኢትዮጵያ በፀጥታ ምክር ቤት መቀመጫ እንዲሰጣት ጠየቀች
ከተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያና ሞሪታንያ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አሁን በተባበረው ዓረብ ሪፑብሊክ የተያዘ የመካከለኛው መሥራቅ (ሥፍራ መቀመጫ) ለእኛ ይገባል ሲሉ ውድድር አቅርበዋል በማለት ከኒውየርክ የተገኘ ወሬ አስታውቋል።
ለምዕራበውያኑ አውሮፓ ክፍልና ለመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሆኑ ጠቅላላ ስምምነት ተደርሶባቸው የነበረው መቀመጫዎች፤ ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ለማግኘት በመከራከር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ሌሎች መቀመጫውን ለመያዝ የሚወዳደሩ አገሮች ኢራን ሞሮኮና አፍጋኒስታን እንደሆኑ ታውቋል።
(ነሐሴ 24 ቀን 1954 ዓ.ም. ከወጣው አዲስ ዘመን )
ዝንጀሮ ሰው በላ
ጅማ፤ (ኢዜአ)፡- በከፋ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ ኮሣ ወረዳ ግዛት በርቄ በተባለው ቀበሌ አንድ ዝንጀሮ የ፪ ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጅ መብላቱ ተነገረ።
ዝንጀሮው ሕፃኑን ልጅ ከበላ በኋላ በተጨማሪ አንዲት የ፫ ዓመት ዕድሜ ያላት ልጅ ለመብላት ሲሞክር ሰው ደርሶ አድኗታል። ሆኖም ልጅቷን ለመብላት መሬት ጥሎ በመቦጫጨቅ የመቁሰል አደጋ ያደረሰባት መሆኑ ከቀበሌው መልከኛ ተገልጧል ሲል የወረዳው ግዛት ጸሐፊ አቶ ለማ አዱኛ ገለጡ።
ዝንጀሮው አንዱን ልጅ በልቶ ሌላዋን ልጅ ያቆሰለው ልጆቹ በቤታቸው አቅራቢያ ሲጫወቱ አግኝቷቸው መሆኑን ዋና ጸሐፊው በተጨማሪ አረጋግጠዋል።
ይኸው ዝንጀሮ ልጆቹን ከመብላቱ በፊት፤ ከ፴ ያላነሱ በጐችና ፍየሎች በልቶ ወደ ጫካ እየተሸሸገ የኖረ መሆኑ ታውቋል።
(መስከረም 1 ቀን 1962 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/ 2015 ዓ.ም