መምህርት እፀገነት ከበደ ትባላለች። መምህርት፤ ደራሲና የሚዲያ ባለሙያም ነች። በግጥም ምሽቶች መድረኮች ላይ ትታወቃለች። ሳታየር ተረቶችን በዚህ መድረክ ታቀርባለች።
‹‹ ፈጣሪ ወደዚህ ዓለም የመጡ ፍጡሮቹን እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንዳስተምራቸው የመረጠኝ በመሆኔ በስነጽሑፉ ዓለምም ሆነ በመገናኛ ብዙሃኑ ሙያ ዘርፍ መሰማራት የሚያስችል አማራጭ ቢኖረኝም ከማስተማር መነጠል አልችልም›› የሚል ዕምነት አላት። ራሴን ፈትኜ አውቃለሁ። ግን ማስተማር ሱስ የሆነበት ሰው ዓይነት ነኝ። ልጆች ላይ መሥራትና ማስተማር ሕልሜም ፍላጎቴም ነው ስትል ስለ ራሷ ትገልፃለች። ቀድሞ በነበራት ልምድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ታስተምር የነበረች ቢሆንም አሁን እያስተማረችበት ያለችበት ‹ላይነርስ› አካዳሚ የውጭ ዜጎች ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ብቻ ስለሚያስተናግድ አሁን ላይ የምታስተምረው እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ልጆችን ነው። በትምህርት ቤቱ የአማርኛ ቋንቋ መምህርትና የአማርኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊም ናት። ልጆች ላይ መሥራትና ማስተማር ስጦታዬ ነው ትላለች።
በመምህርነት ሙያ መሥራት ከጀመረች 13ኛ ዓመቷን ጨርሳ 14ኛውን የያዘችው መምህርት እፀገነት ባለቤቷም እንደ እሷ በመምህርነት ሙያ የተሰማራ ነው። ወላጆቻቸው የተለያዩባቸውንና በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የአካባቢያቸው ልጆችን ትምህርትን ተቀብለው በወደፊት ሕይወታቸው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በማድረጉ ረገድ መኖሪያ ቤታቸውን ሳይቀር መስዕዋት አድርገው በጋራ በነፃ እያስተማሩ ነው። እሷ ትምህርት ቤት ስታስተምር ውላ ስትመጣ ባለቤቷ በቤታቸው ውስጥ የአካባቢውን ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ በተለይም ትምህርት ቤት ዝግ በሚሆንበት ጊዜ በነፃ ሲያስተምር ይቆያታል። የልጆቹን የትምህርት አቀባበል ሁኔታም ሪፖርት ያደርግላታል።
መምህርቷ ልጆች በትምህርት ውጤታማ የሚሆኑበት በርካታ መጽሐፍቶች እያዘጋጀች ስትገኝ አንድ የልጆች መጽሐፍና አንድ የአዋቂዎች መጽሐፍትም አሳትማለች። አንደኛውና የ‹‹እንጎቻ ታሪኮች›› የሚለው የተረቶች ስብስብ ነው። ተረቶች ለሁለት ጉዳይ ይዘጋጃሉ። አንደኛው የንባብ ክሎታቸውን ለማዳበር ሲሆን ሁለተኛው ሞራላቸው ስነ ልቦናቸው እንዲገነባ የሚሰሩ ናቸው። ሞራላቸውን ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ማህበረሰብ ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈለጉና የማይፈለጉ ነገሮችን ወደ ልጆች በማስተላለፍ እንዲቀረፁ የሚደረገው በተረቶች አማካኝነት ነው። አባቶቻችንም ሲያደርጉ የነበረው ይሄንኑ ነው።
ማህበረሰቡን ቅርጽ እያስያዙ አሁን ድረስ ያመጡት በተረቶች፤ በተረትና ምሳሌዎች፤ በእንቆቅልሾች እና በስነ ቃሎች ነው። እስከ አሁን የመጣነው በዚህ መንገድ ነው። የእኛ ማህበረሰብ ዝም ብሎ ዱብ ብሎ የተገኘ ሳይሆን ብዙ የተለፋበት ነው። ‹‹የኔ ተረት ትንሽ የሚለየው ሲዲም ጭምር አለው›› የምትለው መምህርት እፀገነት የሚነበቡ ብቻ ሳይሆኑ የሚደመጡም እንደሆኑ ታብራራለች። ይሄን ያዘጋጀችው ፈረንጆች ከመተኛታቸው በፊት ወላጆቻቸው ተረቶች ታሪኮች ያነቡላቸዋል። ይሄ አንድም ልጆቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያላቸውን ቅርበት ይጨምረዋል። በተጨማሪም ምናባቸው ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይሄን ነገር እኛ ባህል አላደረግነውም። ወይም ከአያቶቻችን ብንወርሰውም ዘንግተንና ትተነዋል። ምንድነው ምክንያቱ ብላ የተወሰኑ ወላጆችን እንዳስተማሪ ጠይቃ ያገኘችው መልስ ቀን በሥራ እናሳልፋለን ደክሞን ነው የምንገባው የሚል ነው። ይሄ ልጆች ላይ ችግር የሚፈጥር ከሆነ በዚህ መተካት ይቻላል ብላ ነው ሲዲውን ያዘጋጀችው። ሲዲ በዚህ ዓይነት መንገድ መጽሐፉ ከሲዲ ጋር ተጋግዞ እንዲሰራ አድርገው ነው ያወጡት። ባለቤቷም በሲዲ ዝግጅቱ የተሳተፈ ሲሆን 10 የሚሆኑ ተረቶች ይዟል። ሁሉም መደረግ ያለበትንና የሌለበትን ልጆች እንዲለዩ የሚያደርጉ ናቸው።
ለምሳሌ አንዱ ሁለቱ እህትማማች ዳክየዎች የሚል ተረት ሲሆን ውሃ ለመጠጣት የሚሄዱበት መንገድ ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን አንደኛዋ ዳክየ ለሌለኛዋ ቀበሮ እንዳየችና በዛ መንገድ መሄድ እንደሌለባቸው ትነግራታለች። ሌላዋ ዳክየም ከለመድኩት ውጭ በሌላ መንገድ መሄድ አልፈልግም ትላለች። ብትለምናትም አልሰማቻትም። በመጨረሻ አብረው ይሄዳሉ። በዚህ መካከል ያለችው ተኩላ አጋጠማቸውና ከመበላት ለጥቂት ተረፉ። ይሄን ተረት ያመጣችው ሕይወት ውስጥ ብዙ አማራጮች መኖራቸውንና ይሄን ባለመጠቀማችን ችግር ውስጥ እንደምንገባ ለማሳየት ነው። አንዱ ሳይሆን ሲቀር ሌላውን መሞከር ተገቢ መሆኑን ለመጠቆምም ነው። ሌላውን መሞከር እንጂ ተስፋ መቁረጥ ለሕይወታቸው እንደማይበጅ ለማሳየት ነው።
ሌላኛው መጽሐፏ ‹‹ማለዳን መናፈቅ›› የሚልና ለአዋቂዎች የተጻፈ ሲሆን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አሉብን። ችግሮቻችንንና ራሳችንን የምናይበት የተለያየ መንገድ እንደሚያስፈልገን ያስተምራል በማለት በውስጡ 20 የሚደርሱ ታሪኮች ስላሉት መጽሀፏ ትናገራለች።
‹‹ልጆች በትምህርትም ሆነ በየትኛውም መንገድ ግንዛቤ መጨበጥ ያለባቸው በዕድሜያቸው መጠን ነው›› በዕድሜያቸው መጠን ቃላትን አውቀው ችግር ሲገጥማቸው ችግሮችን መፍታት ይችላሉ ባይ ናት፤ ለምሳሌ ኳስ ሲጫወቱ የሚያጋጥሙ ግጭቶችንና ኢፍትሃዊ የሆነ አካሄድ የሚፈቱበትን መንገድ ማወቃቸው ይጠቅማቸዋል ይህንን ሳይዙ ማደጋቸው ግን ምንልባት ዳኛ ሲሆኑ እንኳን በገንዘብ ሊታላሉ ሚዛናዊ ፍርድን ላይፈርዱ ይችላሉ ። በመሆኑም ፍትሃዊነትን ከልጅነታቸው ጅምሮ ማስተማር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ። ይህንን ለማስተማር የሚያግዘው ዘዴም በመጽሐፉ ተካቷል እንደ መምህረት እፀገነት ገለጻ።
‹‹በልጆች በኩል ብቻ ሳይሆን በመምህሩም በኩል የምፈልገውን ሀሳብ ምን ያህል አስተላልፊያለሁ የሚለው መመዘን አለበት›› የምትለው መምህርቷ በመጻፉ ባሉት ታሪኮች መጨረሻ ላይ ልጆቹ የሚያደርጉት ተግባር እንዳለም ታወሳለች።
መምህርቷ የህፃናት መፃፉን ልትጽፍ የቻለችው ፈጣን ግንዛቤ የሚያስጨብጡትን የውጭዎቹን መጻፎች የማንበብ ዕድሉን ስላገኘችና የእኛም ሀገር ልጆች በዚህ መንገድ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መነሳሳትና ከፍተኛ መንፈሳዊ ቅናት ስላደረባት እንደሆነም ትናገራለች። የእኛን ሀገርና የውጭውን የህፃናት መጽሐፍ በንጽጽር ስታየው ርቀቱ ሰፊ እንደሆነ ነው የምትገልፀው። የሕፃናት መፃፍ ሲፃፍ ያለውንና የደረስንበትን የስልጣኔ ደረጃ ታሳቢ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ታነሳለች።
በውጭው ዓለም ታዲያ እያንዳንዱ ለህፃናት የሚሆን መጽሐፍ የሚዘጋጀው ጥናትን መሰረት አድርጎ ነውም ትላለች። ሆኖም በእኛ ሀገር ብዙ የህፃናት መጽሐፍትም ሆኑ ሌሎች የማስተማሪያ ግብዓቶች የሚዘጋጁት በፍላጎትና በተነሳሽነት ነው ትላለች። ብዙ ጊዜ በተማሪዎቻችን ላይ ውጤታማነታቸውን ማየት የማንችልበት ምክንያት ይሄው መሆኑንም ታክላለች። መጽሐፍቶቻችንን፤ የምናሳትምበት መንገድን፤ የትምህርት ስርዓቱ፤ የመምህራን የሙያ ጥራት ማስጠበቅ ያልቻልነው በዚህ አካሄዳችን ነው ባይ ናት። አካሄዱ ልጆችን አለማብቃት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ ለመምህራን ክብርም እንዳይሰጥ አድርጎታል። ሌላው ቀርቶ ልጆችን ወደፊት ምን መሆን ነው የምትፈልጉት ሲባሉ መምህር እሆናለሁ ብሎ የሚመልስ ጥቂት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ልጆችንም ጨምሮ በጆሯቸው በመስማት በቀላሉ መማር የሚችሉ እንዳሉ ሁሉ በዓይን በማየት በቀላሉ መማር የሚችሉም ብዙ ናቸው። ለምሳሌ በቀላሉ በዓይን መማር የሚችሉትን እንዲያዳምጡ የምናስገድዳቸው ከሆነ ውጤታማ አይሆኑም። ልጆቹ ትምህርቱን እንደ ዕዳ ነው ይቆጥሩታል ‹‹እኔ በግሌ ተማሪ ረባሽ ነው ብዩ አላምንም። የሚረብሸው የሚማረው ነገር ሳያገኝ ሲቀር ነው›› ትላለች።
እንደ እሷ ይሄ የሚሆነው የሚማረው ነገር ወይ ከአቅሙ በታች ወይም ከአቅሙ በላይ ሲሆን ነው። አንድ ክፍል ውስጥ ሆኖ የሚሳተፍበት ነገር ከሌለ መረበሽ የሚሻለው መሆኑን ለአስተማሪው ማሳየት አለበት። አንድ ተማሪ ልጅ የሚረብሸው ደደብ ስለሆነና ስለማይገባው አይደለም። አንድ ክፍል ሆነው የሚሳተፉበት ነገር ከሌለ መረበሽን ይመርጣሉ። ሁላችንም ተመሳሳይ አእምሮ ቢሰጠንም አእምሯችንን የምንሞላበት መንገድ ልክ እንደ ተፈጥሯችን ይለያያል። በመሆኑም በተወሰነ ደረጃ ከፋፍሎ በምን መማር ይችላል የሚለውን ከለየን በኋላ በዚህ መንገድ በማስተማር ልጆቹን ውጤታማ ማድረግ ይቻላል በሚለው በምታስተምርበት ትምህርት ቤትም ሆነ ከባለቤቷ ጋርም ትሰራለች።
ይሄን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የማስተማር መንገድ በመደበኛው መንገድ ተምረውና ፈጥነውም ሆነ ዘግይተው ግንዛቤ መያዝ ለማይችሉ በኢትዮጵያ ላሉ ልጆችም አምጥቶ መጠቀም ይቻላል። ባለቤቷና ልጆቿ በቤት ውስጥ አቅም የሌላቸውን የአካባቢውን ልጆች ሰብስበው በሚያስተምሩበት ወቅት እንዲህ ዓይነት የትምህርት አቀባበል ያላቸው ልጆች ሲገጥሟቸው ለእሷ ሪፖርት ያደርጉላታል።
ለምሳሌ ችግር ሲኖር ይሄም ልጆቹን ቁጭ አድርጎ ለልጆቹ ቃለ መጠየቅ በማድረግ የሚያደርጉት በማየት ልጆቹ ምን ዓይነት ችግር እንዳለባቸው ጥናት ይሰራል።
ብዙዎች የሚያጋጥሟቸው ረጅም ሰዓት ትኩረት ማድረግ ያለመቻል ነው። እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ልጆች በመደበኛው መንገድ የሚማሩ ልጆች በሚማሩበት መንገድ አስተምሮ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም። በመሆኑም ሌላ የተለየ መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ትኩረታቸውን ለማራዘምና ለማስተማር የሚረዱ ሥራዎችን ትሰራለች። ይሄ ታዲያ የተለያዩ የስነ ልቦና ችግር ያለባቸውን ልጆች ለምሳሌ እናትና አባት የተለያዩባቸው እንደገና በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉ ልጆችን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል። ችግሮቹንና ቀውሶቹን ተቋቁሞ ትምህርት ቤት ውሎ ውጤታማ መሆን በጣም የሚከብድበትን ሁኔታ ያቀልላቸዋል። የምታዘጋጀውም የስነ ልቦና ቀውስን ተቋቁሞ እነዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ግብዓት ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/ 2015 ዓ.ም