ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ ስፖርት ከስኬት ጋር እንድትተዋወቅ ያደረጉት የሚሊተሪ መሠረት ያላቸው ክለቦች ስለመሆናቸው ታሪክ ያወሳል። ከእነዚህ ክለቦች መካከል አንዱ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ነው። ይህ አንጋፋ ክለብ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ታሪክ በቀድሞ ወርቃማ አትሌቶቹ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ እና ጥሩነሽ ዲባባ ብቻ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስገኘት ከፍተኛውን የወርቅ ቁጥር ያስመዘገበ የአገር ባለውለታ ነው።
ይህ ታሪካዊ ክለብ በዚህ ወቅት በአትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች 105 አትሌቶች ያሉት ሲሆን፤ በሴት ቮሊቦል (12)፣ በወንድ ቦክስ(11)፣ በወንድ እጅ ኳስ(12) በአጠቃላይ 140 ስፖርተኞችን በስሩ ይዞ ይንቀሳቀሳል። በውጤታማነትም በተለይ የቮሊቦል እና ቦክስ ስፖርቶች የአትሌቲክሱን ያህል ስኬታማ የሚባል ታሪክና ቡድኖችን አፍርቷል። ይሁን እንጂ ይህ ስመ ጥር ክለብ ከዓመታት ወዲህ በገጠመው ችግር ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለማለፍ ተገዷል።
በክለቡ የመካከለኛና ረጅም ርቀት አሰልጣኝ የሆኑት ረዳት ኮሚሽነር ጀኔራል ሁሴን ሸቦ፤ ክለባቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በነበረበት ሁኔታ እየቀጠለ አለመሆኑን በቅሬታ ስሜት ይገልጻሉ። ምክንያቱ ደግሞ በደርግ ዘመነ መንግሥት እርሳቸውን ጨምሮ ሰራዊቱ ገንዘብ በማዋጣት ያቋቋሙት የመዝናኛ ክበብ (ካራ ሎጅ የተባለ) በማከራየት በሚገኘው ገቢ የስፖርት ክለቡ ሲደጎም የቆየ ቢሆንም ከአራት ዓመት በፊት ግን ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመሰጠቱ ህልውናው አደጋ ላይ እንደወደቀ ይጠቁማሉ።
ላለፉት ዓመታትም ለአትሌቶቹ ለላብ መተኪያ የሚሆን ገንዘብ በማጣቱ ምክንያት በሞራል፣ በሹመትና በትጥቅ ከማበረታታት በቀር እንደሌላው ክለብ የተሟላ ነገር አልነበረውም። ክለቡ በተወሰደበት ክበብ ምትክ ባለማግኘቱ እንዲሁም የገንዘብ ካሳ ባለመቀበሉ ምክንያትም አስቸጋሪ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ክለቡ በሚጠበቀው ልክ ለመቀጠል ተቸግሯል። ለዚህ ችግሩ መፍትሄ የሚሆን መልስ ካገኘ ግን ወደ ውጤታማነቱ እንደሚመለስ አሰልጣኙ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ምክትል ኮማንደር ወንደሰን ማንደፍሮ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የስፖርት ክለቡ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ የአገርን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ማውለብለብ የቻሉ አትሌቶች ስላፈራው ታሪካዊ ክለብ ይናገራሉ። ክለቡ አሁንም አትሌቶችን እያፈራ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ አንጻር መቀነስ ማሳየቱን ይገልጻሉ። ለማሳያም በአንድ ዓለም አቀፍ ውድድር 11 የሚሆኑ አትሌቶችን እስከማስመረጥ የደረሰበትን ጊዜም ያስታውሳሉ። በእርግጥ በኦሪጎኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል ሁለቱ የተገኙት በዚህ ክለብ አትሌቶች ነው። ይህም እጅግ መልካም የሚባል ውጤት ይሁን እንጂ በግልጽ ሊታይ በሚችል መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክለቡን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ቁጥር ግን መቀነሱን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
ለዚህ ምክንያት ሆኗል የሚሉት ደግሞ ከዚህ ቀደም የስፖርት ክለቡ ይተዳደርበት የነበረው ካራ ሎጅ የተባለ የመዝናኛ ክበብ ለሌላ ተቋም ተላልፎ መሰጠቱን ነው። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ይህ ክበብ አባላቱ በራሳቸው ገንዘብ ያቋቋሙት ሲሆን፤ ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በማከራየት ገንዘብ ሲገኝበት ቆይቷል። ነገር ግን ከአራት ዓመታት አስቀድሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሁም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ መሠረት በተሳሳተ ግንዛቤ ክበቡ የመንግሥት በመሆኑ ያለክፍያ እንዲገለገሉበት በሚል ከክለቡ እጅ ወጥቷል። ነገር ግን ክበቡ የመንግሥት ሳይሆን በአባላቱ የተቋቋመ በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል። ፍርድቤቱም አግባብ አለመሆኑን በማመላከቱ ክለቡ ለአራት ዓመታት በሽምግልና ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሁም ኪራይ ቤቶች ጋር በክርክር ላይ ቆይቷል።
ያለፉትን ዓመታትም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ለክለቡ በጀት መያዝ ስለማይችል በተለያየ መንገድ ድጎማዎችን እያደረገ እስካሁን ሊቀጥል ችሏል። በዚህ ሁኔታ ውስጥም በክለቡ የታቀፉ ስፖርተኞች ለክለቡ ባላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ አብረው ከመቀጠል ወደኋላ አላሉም። በእርግጥ የመዝናኛ ክበቡን የጠቀለለው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ቦታውን እጅግ ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ለኩላሊት ንቅለተከላ ማዕከልነት ማዋሉ አገራዊና አላማ ያለው መሆኑን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ክለቡም በተወሰደበት ቦታ ምትክ እንዲሰጠው ጥያቄውን አቅርቧል። ከዓመታት ክርክር በኋላም በተጠየቀው መሠረት አንደኛ ደረጃ የሆነ ምትክ ቦታ እንዲሁም የአንድ ዓመት ኪራይ የሚሆን 6 ሚሊዮን ብር እንዲሰጠው ተወስኖ እንደነበርም ዳይሬክተሩ ያስታውሳሉ። ይህንን ተከትሎም ጉዳዩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ ተዘዋውሯል። በመሆኑም ክለቡ እስካሁን የተወሰነለት ምትክ ቦታ ባይሰጠውም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እየሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ክለቡ ያለፉትን ዓመታት በዚህ ሁኔታ ሲያሳልፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እና ኦሊምፒክ ኮሚቴን የመፍረስ አደጋ እንደገጠመው በመጥቀስ ድጋፍ መጠየቁንም ዳይሬክተሩ ያስታውሳሉ። ነገር ግን ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱ በክለቡ ላይ ቅሬታ አሳድሯል። በቀጣይ ግን ክለቦች የሚቋቋሙት አገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ እንዲሁም ታሪካዊው ክለብ ወደ ቀድሞ አቋሙ እንዲመለስ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት ዳይሬክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም