የልጅ አስተዳደግ
ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? መቼም ጥሩ ነው የሚል መልስ እንደሰጣችሁኝ አልጠራጠርም ። ጎበዝ ተማሪዎችና አስተዋይ ልጆች ቀናቸው ሁልጊዜ ብሩህ ነው ። ምክንያቱም ነገሮችን ሲያከናውኑ ተጠንቅቀውና አስተውለው ነው ። ስለዚህም ችግሮች እንኳን ቢያጋጥሟቸው በቀላሉ መፍትሄ በመስጠት ያሳልፉታል ። እናንተም በዚህ መልኩ ህይወታችሁን ስለሆናችሁ ጊዜያችሁ ያማረ እንደነበር እገምታለሁ ። ለማንኛውም ልጆች ዛሬ ለእናንተ ሳይሆን ለወላጆቻችሁ የሚሆን ምክረሀሳብ ነው ይዘን ብቅ ያልነው ። ምንጫችን ዶክተር ዮናስ ላቀው የጻፉት ጽሑፍ ነው ።
ዶክተር ዮናስ ላቀው ስለ ልጆች አስተዳደግ ይነግሩናል። እናም ወላጆችን ይህንን ጽሁፍ ቢያነቡት በጣም ጥሩ ነው። በእርግጥ ልጆችም ቢያነቡት ብዙ ዕውቀት ያገኛሉ ።
ወደ ጉዳዩ ስገባ ጸሐፊው እንደሚለው፤ ልጆች የሚያድጉበት መንገድ ከፍ ሲሉ ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ የፍቅር ጓደኛ ምርጫ፣ ስኬት፣ በራስ መተማመን ላይ ትልቅ ሚና አለው ። እንደ የስነ-ነልቦና ባለሙያዎች አባባል ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉባቸው መንገዶች በደንብ የተጤነ መሆን አለበት ። በዚህም መሰረት ዶክተሩ የልጅ አስተዳደግን በአራት አይነት ከፍለው ያስቀምጡታል።
1. አምባገነን (ኮስታራ) ፦ ይህ አይነት የልጅ አስተዳደግ በአለማችን በይበልጥ ደግሞ በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የነበረ የማሳደጊያ መንገድ ነው ። ከእናቶች ይልቅ ደግሞ አባቶች ላይ ይስተዋላል ። እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ‘ኮስተር’ ብለው ይነግሩና ልጆች ‘ወለም ዘለም’ ሳይሉ እንዲከተሉ ይጠብቃሉ ። እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች ደግሞ በአብዛኛው ስኬታማ ለመሆንና ‘ትክክል’ የሆኑ ነገሮችን ለማድረግ የሚጣጣሩ ናቸው ። ነገር ግን አዲስ ነገር ለመሞከር ወይም ያልተለመደ ስራ ለመስራት ይከብዳቸዋል ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከቤተሰብ ሲርቁ የማያምኑባቸውን ነገሮች ለማድረግ ጭምር የሚገፋፉት ለዚህ ነው ።
2. የሚያሞላቅቁ (ሁሉንም የሚፈቀዱ)፦ ይህ አይነት የልጅ አስተዳደግ በቅርብ የተጀመረ ሲሆን፤ በተለይ በከተማዎች አካባቢ በጣም እየተስፋፋ የመጣ ነው ። እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ያለ ገደብ እንደፈለጉ እንዲሆኑ ይፈቀዳሉ ። ልጆቻቸው ያለ ከልካይና ያለ ገደብ እንደልባቸው እንዲሆኑ ከመፍቀድ ውጪ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አይነግሯቸውም ። ልጆቻቸው እስከፈለጉ ድረስ ከቤተሰቡ አቅም በላይ ቢሆኑም እንኳን ለማሟላት ይጣጣራሉ ። ይህ ደግሞ ልጆችን በተለያየ መልኩ ባህሪያቸው እንዲቀየር ያደርገዋል ።
አንደኛው ቤት ሁሉም ነገር ተሟልቷል በሚል ከቤት ውጭ እንደፈለጉ ወጥተው እንዲጫወቱ አይፈቀድላቸውምና ጭንቀት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ሌላው ደግሞ የተወሰኑትን ቢሆንም ለምንም ነገር ኃላፊነት የማይሰማቸው እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል ። ምክንያቱም ብዙ ነገራቸው በቤተሰባቸው አማካኝነት የሚሞላላቸው ልጅ ሆነዋል ።
3. ግድ የለሽ፦- እነዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ግድ የሌላቸው አይነት ናቸው ። ቁጣም ሆነ አድናቆትን ለልጆቻቸው አያሳዩም ። ልጆቻቸው እነሱን እስካላስቸገሩ ድረስ የትም ቢውሉ፤ የፈለጉትን ቢያደርጉ ግድ አይሰጣቸውም ። ዋና ፍላጎታቸው ቤተሰብ እንዳያስቸግሩ ማድረግ ብቻ ነው ። በዚህ አስተዳደግ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች የተወሰኑት የቤተሰብ ኃላፊነት የሚሸከሙ ይሆኑና ልጅነታቸውን ይነጠቃሉ ።
ሲያድጉ ደግሞ ብቸኝነት የሚሰማውና ሰውን ማመን የሚከብደው ልጅ ይሆናሉ ። በራስ መተማመናቸውም በዚያው ልክ ዝቅተኛ ይሆንባቸዋል ። እናም ያለፈውን ጊዜያቸውን ለማካካስ በጣም ከፍተኛ ኃይል እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ ።
4. በልክ (ነጻነት በወሰን የሚሰጡ)፦ ይህንን አስተዳደግ የሚከተሉ ወላጆች ለልጆቻቸው ወሰን አስቀምጠው ነጻ እንዲሆኑ የሚፈቅዱ ናቸው ። የልጆቻቸውን ምርጫ ያከብራሉ፤ የልጆቻቸውን ሀሳብ፣ ስሜትና አስተያየት ያዳምጣሉ ። በጣም ጠቃሚ ነገሮች ላይ አስተያየታቸውን ይቸሯቸዋል ። ከባድ ነው ብለው ሲያስቡና ሕይወታቸውን የሚጎዳ እንደሆነ ሲያምኑበትም አሳምነዋቸው በልጆቻቸው ጉዳይ ይወስናሉ ። በአቅማቸው የሚችሉትን ያደርጉላቸዋልም ። ስለሆነም በዚህ መንገድ የሚያድጉ ልጆቸ ከሌሎች ጋር ተባብረው መስራት የሚችሉና በራሳቸው የሚተማመኑ ስኬታማ ሰዎች ይሆናሉ ። ለራሳቸው የተለየ ዓለም ለመፍጠር የሚጥሩ ልጆችም ይሆናሉ ። በተለይም ደስተኛና ለሌሎች ደስታ የሚጨነቁ መሆናቸው ከሌሎቹ አስተዳደጎች የተለየ ያደርጋቸዋል ። ስለዚህም ከዚህ ሁሉ ተመራጭ የልጆች አስተዳደግ አይነት ተደርጎ ይወሰዳልም ።
የአንድን ሰው የወደፊት ባህሪ የሚወሰነው ከአስተዳደግ ባሻገር በጣም ብዙ ነገሮች ቢሆኑም ከላይ የተገለፀው አስተዳደግ ሊኖረው የሚችለውን ተፅእኖ ግን በምንም መልኩ የሚዘነጋ መሆን የለበትም ። ምክንያቱም የነገውን ፍሬ የሚያሳየን የዛሬ አበባ ነው ። ከአበባው በፊት ዛሬ ላይ የዘራነው ዘርና ያደረግነው እንክብካቤ ነው ። እናም ለልጆቻችን የምናስብ ነን ካልን የእኛን ቦታ ዛሬ ላይ ማወቅ ይጠበቅብናል ። ዘሩ ምን አይነት ነው፤ እንክብካቤውስ በምን መልኩ ቀጥሎለታል የሚለውን ማጤንና ከተሳሳትን ከስህተታችን መታረም አሁኑኑ አለብንም ።
ልጆቻችንን ወደፊት ደርሰውበት እንድናየው የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የዛሬው ድርጊታችን ወሳኝነት አለው ። ሰው የዘራውን ያጭዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። እናም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አስተዳደጋችን የተበላሸ ከሆነ ዛሬን አርመን ነገን እናብራላቸው በማለት ጽሁፋችንን ቋጨን ። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም