የታሪክ መዛግብት ቅኝታችን ማጠንጠኛ ጉዳይ ይሆን ዘንድ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት በዚች ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ከሆኑ አበይት ሁነቶች መካከል አንዱን መረጥን ። የታሪክ ትውስታችን ወደ ጥቅምት 2 ቀን 1888 ላይ አድርሶ ያኔ የሆነውን ያሳየናል ። ከዛሬ 126 ዓመት በፊት በዚያ ታሪካዊ ቀን የሆነውን እንዲህ አቀረብነው ።
ያኔ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን መደፈር ሰምተው ቁጭት ውስጥ የገቡበት ወቅት ነበር ። ጣሊያን የአገራቸውን ዳር ድንበር ተሻግሮ ሉዓላዊነታቸውን ሊነጥቅ መሆኑን ተረድተው፤ በአንድነት ቆሞ ለመፋለም ‹‹ሆ!›› ብለው የተነሱበት ጊዜ ነበር ። የጥቁር ህዝብ ነፃነት ፋና ወጊ ኢትዮጵያዊያን ለፍትህ፣ ለአገራቸው ክብርና ለባንዲራቸው እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት በጊዜው አስፈሪ የነበረውና ዘመናዊ ጦር የታጠቀው የጣሊያን ወራሪ ድል ለማድረግ የተነሱበት ጅምር ። አድዋ! የጦርነቱ ዘመቻ ጅማሮ አዲስ አበባ ላይ የሆነው በዚህ ሳምንት ነበር።
ጥቅምት ሁለት ቀን 1888 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጉልህ የሚጠቀስ ታላቁ የአድዋ ጦርነት ዘመቻ ጅማሮ ቀን ነው ። ዛሬ ፒያሳ ጊዮርጊስ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ነው አርበኞች የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ተሰባስበው የተነሱበት ታሪካዊ ስፍራ ። ጥቅምት ሁለት ደግሞ የአድዋ ጦርነት ዘመቻ ጉዞ የተጀመረበት ዕለት ነበር።
የዘመቻ ጥሪው አዋጅ የተነገረው መስከረም 17 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር ። የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በመውረር በቅኝ ግዛቱ ስር ለማዋል ማሰቡን በማረጋገጣቸው፤ በቁጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ያሳሰቡበትን የክተት አዋጅ አስነገሩ ። አዋጁም የሚከተለው ነበር።
“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላትን አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ ። እንግዲህ ብሞትም ሞት ለሁሉ ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፤ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም።
አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬ ከብት ማለቁንና የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ።
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም ። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም ። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ ። አልተውህም ማርያምን፤ ለዚህ አማላጅ የለኝም ።
ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከትተህ ላግኝህ ። ”
በእርግጥ አዋጁ የወጣው መስከረም 17 ቀን 1888 ዓ.ም ቢሆንም፤ ሁሉም በጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ እንዲከትም ነበር የተነገረው ። በየክፍለ አገሩ ያሉት የኢትዮጵያ ልጆች የእናት አገራቸውን መወረር ከሰሙ ዕለት ጀምሮ ለመዝመት ቆረጡ ። አገራቸውን ከራሳቸው የሚያስበልጡት ኢትዮጵያዊያን የአገራቸው መደፈር አስቆጭቷቸው ለጦርነቱ መሰናዶ በማድረግ ቆዩ ።
አፄ ምኒልክም የሩቁን አካባቢ ሰው አገሩ መወረሯን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ እንዲነሳ አዘዙት ። ሩቅ አካባቢ ያሉት በተባለው ጊዜ ለመድረስ ቀድመው ጉዞ ጀመሩ። የጎጃም፣ የደንቢያ፣ የቋራ፣ የበጌምድር፣ ከጨጨሆ በላይ ያለውን አካባቢ ሁሉ አሸንጌ ድረስ ክተት ተብሎ ተነገረው።
በሰሜን የአገራች ክፍል ያሉት እንደ ወልቃይት ጠገዴ እና አካባቢው ያለው ሰው መቀሌ ድረስ ክተት ተብሎ መልዕክት ተሰደደለት ። እዚያም ያለው አንዱ ከሌላው ጋር እየተቀናጀ የአገሩን ነፃነት ሊያረጋግጥ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች ሊያንበረክክ ተሰናዳ ። በተባለው ቦታ ለመገኘትም ትጥቅና ስንቁን አዘጋጅቶ ጉዞ ጀመረ ።
የምዕራብ፣ ምስራቅና ደቡብ ሰው ከሸዋው ጋር አብሮ ሊተም ወደ አገሪቱ መናገሻ አዲስ አበባ ተሰበሰበ። የየክፍለ አገራቱ ገዥዎች ጦራቸውን ይዘው ተገኙ ። ከምስራቅ ራስ መኮንን የሐረርጌን ጦር ይዘው በመስከረም እኩሌታ አዲስ አበባ ገቡ ። ከጊቤ በታች ያለውን አካባቢ ጦር የወለጋው ሹም ፊታውራሪ ተክሌ ጦራቸውን ይዘው አዲስ አበባ ተገኙ ።
አፄ ምኒልክ አዋጃቸውን በመስከረም ወር ካስነገሩ በኋላ ለአገር ጥበቃ አጎታቸውን ራስ ዳርጌ ሣህለሥላሴን ሾመው እርሳቸው የጊዮርጊስን ታቦት አስከትለው በሸዋ የጦር መኮንኖች ታጅበው በጠንካራ ወኔ ከአዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ ። ይህ የሆነው ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ነው ። አፄ ምኒልክ ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች ከተሰባሰቡ ጀግኖች አርበኞች ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ተነስተው በጊዳ በኩል አድርገው ጥቅምት 18 ቀን ወረኢሉ ገቡ ።
ከዚያም ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን የጦር መሪዎች እነ ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ወሌን፣ ራስ መኮንንን፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላን፣ ዋግሹም ጓንጉልን፣ ደጃች ወልዴን፣ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኛዝማች ታፈሰን ‹‹ቀድማችሁ ወደ አላጌ ዝመቱ የሚቀላችሁ ከሆነ ጠላትን ውጉት ። የሚከብዳችሁ ከሆነ ላኩብኝ፤›› ብለው አስቀድመው መላካቸውን ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ በመፅሀፋቸው ሲጠቅሱ፤ በሌላ በኩል አንዳንድ ጸሐፊዎች ስለ ሁኔታው ሲገልፁ አፄ ምኒልክ “እኔ እስክመጣ ድረስ ከባችሁ ተቀመጡ እንጂ አትዋጉ” በማለት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ያመለክታሉ።
አውሮፓዊው ፓውሎቲ ስለ ኢትዮጵያ ጦር ጉዞ በጻፈው ጽሁፉ እንዲህ ሲል ዘመቻውን ገልፆታል ። “የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲጓዙ በደንብ ተመልክቻለሁ። ዳገቱን ሲወጡ፣ ቁልቁለቱን ሲወርዱ፣ ሸለቆውን ሞልተው ሲሄዱ በታላቅ ወኔ እየጩኹ፣ እየፎከሩና እየሸለሉ ነው። ለውጊያ የሚሄዱ አይመስሉም ። ወንዶች፣ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ቄሶችና መነኮሳት… ሁሉ ሳይቀሩ በአንድነት ሲጓዙ እኔ እንዳሰብኩት ለጦርነት የሚሄዱ አይመስሉም ። ሕዝብ በሙሉ ተነቅሎ ለወረራ የሚሄድ ይመስላል” ብሏል ።
ጣሊያናዊው ካፒቴን ሞልቴዶ ደግሞ “….አሕያው፣ በቅሎው፣ ፈረሱ፣ ሰው ሁሉ በአንድነት ይጓዛል ። መንገድ ሲጠብ መንገድ ይሰራሉ ። በአንድ ጊዜ በግራ ወይም በቀኝ ይሰማሩና የጠበበውን መንገድ ይሰራሉ። ሠራዊቱም ባለፈበት መንገድ እርጥብ የሳር ዘር እንኳን አይገኝም።ምክንያቱም በመቶ ሺ የሚቆጠር እግር ረጋግጦ ስለሚያቦካው ነው።…”በማለት በወቅቱ የነበረውንና ያየውን ሁሉ መስክሯል ።
ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በዘመቻው ላይ ሳሉ አንድ አዲስ ደስ የሚያሰኝና በኢትዮጵያዊነት የሚያስመካ ዜና ተሰማ ። ወሩ ህዳር 24 ቀን 1988 ዓ.ም ነበር ። አስደሳቹ ዜናም ደጅ አዝማች ጓንጉል ጸጋዬ በአፄ ምኒልክ ላይ ሸፍተው ከምኒልክ ጋር በጦርነት የተፈታተኑ ሰው በተመለከተ የተሰማ ነበር ።
ደጅአዝማች ጓንጉል ጸጋየ በዚህ ወቅት በአፄ ምኒልክ ሸፍተው በረሃ እንደገቡ ነበር። ምኒልክ ህዳር 24 ቀን መርሳ ላይ ሰፍረው ሳሉ የደጃዝማች ጓንጉል መልዕክተኛ ከአፄ ምኒልክ ዘንድ መጣ ። መልዕክተኛውም “ ጃንሆይ ከእርስዎ ተጣልቼ በረሃ ገብቻለሁ ። አሁን ግን በአገሬ ላይ የውጪ ጠላት ስለመጣባት፤ የርስዎና የኔ ጉዳይ ቀርቶ ይማሩኝና ወጥቼ ከእርስዎ ከጌታዬ ጋር ሆኜ የአገሬን ጠላት ልውጋ ብለዋል።” ብሎ ተናገረ ።
የእኚህ ደጃዝማች ሀሳብ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ አንድ ጉዳይ መኖሩን የሚያሳብቅ ነበር ። ምንም እንኳን በውስጥ ጉዳይ ላይ አለመግባባት ቢኖርም ኢትዮጵያን ሊዳፈር በመጣ ጠላት ላይ አንድ ሆኖ በመነሳት ድል ማድረግ ልማድ መሆኑ ። ከየትኛውም የግል ፍላጎትና መሻት በላይ የሆነችውን ኢትዮጵያ ላይ ማንም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል እንደማይደራደር ማሳያም ነው ።
በዚህ ቀን ደጅአዝማች ጓንጉል ጸጋዬ በላኩት አጼ ምኒልክ ተደስተው “ይምጣ ምሬዋለሁ” ብለው መልዕክተኛ ላኩ። ደጃዝማች ጓንጉልም መጥተው ከአፄ ምኒልክ ጋር ተገናኙ ። ሠራዊቱም መኳንንቱም በእንዲህ ያለ ወሳኝ ጊዜ ከጌታዬ ጋር ልሙት በማለታቸው አይተው እጅጉን ደስ ተሰኙ ።
የዘማቾች ብዛት
በጊዜው ካለው የመረጃ ሁኔታ መነሻነት ወደ አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ቁጥር ብዛቱ በትክክል አይታወቅም ። የታሪክ ጸሐፊዎችም የጻፉት የተለያየ ቁጥር ነው ። ቶኪ የተባለው ጸሐፊ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥር ከ70,000 እስከ 80,000 ይደርሳል ይልና ከእነዚህ ውስጥ ጠመንጃ ያላቸው 25,000 ሰዎች ብቻ ነበሩ በማለት ታሪካዊ ሁኔታውን ይዘረዝራል ።
በሌላ በኩል አንቶኔሊ ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ከ110,000 እስከ 120,000 ይደርሳል ሲል፣ ባራቴሪ እንደጻፈው ደግሞ ከ75,000 እስከ 80,000 ይደርሳል ብሏል ። ኢልግ 150,000 ነው ሲል ዌልድ የተሰኘ ፀሀፊ ደግሞ በምኒልክ ጥሪ የተሰበሰበው 200,000 ሰው ነው፤ ነገር ግን ሁሉም ሰራዊት ወደ ጦርነቱ ቦታ ሳይደርስ ጦርነቱ በኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት እንደተጠናቀቀ ይዘረዝራል ።
በርከት ያሉ ፀሀፊዎች የተስማሙበት የዘማቾች ቁጥር ግን እንደሚከተለው ነው ። አጼ ምኒልክ 30,000 እግረኛ 1,200 ፈረሰኛ፣ እቴጌ ጣይቱ 3,000 እግረኛ 6,000 ፈረሰኛ፣ ራስ መኮንን 15,000 እግረኛ፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ 12,000፣ ራስ ሚካኤል 6,000 እግረኛ ራስ አሉላ 3,000 እግረኛ፣ ራስ መንገሻ አቴከም 6,000 እግረኛ፣ ራስ ወሌ 10,000 እግረኛ ወደ አውሳ የዘመቱ ነበሩ ።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከየአቅጣጫው ‹‹ሆ!›› ብለው ተነስተው በዘመቱበት በዚህ ጦርነት፤ ኢትዮጵያ ድል ተቀዳጀች ። የድሉ ቀን የካቲት 23 1888 ዓ.ም ሆነ ። በዚህም ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ከውጪ ወራሪ ሃይል ነፃ በማድረግ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ችቦ አበሩ ። ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም የተጀመረው ዘመቻ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በድል ተጠናቀቀ፤ ኢትዮጵያም ለኢትዮጵያ በተዋደቁ ጀግኖች ልጆቿ ተጠብቃ ኖረች ። ጀግኖች አባቶቻችን አገራቸውን አሸናፊ አድርገው በታሪክ ማህደር ውስጥ ሰፈሩ ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም