የሀገር አንድነት የሚወሰነውም የሚጠበቀውም በህዝቦች ስምምነት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የተሰባጠረ ህዝብ በያዙ ሀገራት ውስጥ የህዝቦች አንድነት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ሀገርን በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ልማቶች ለማሳደግ የህዝቦች መተማመንና አብሮ የመኖር ፍላጎት አስፈላጊ ነው፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር ያሰቡ እንደ አሸባሪዎቹ ትህነግ እና ሸኔ ያሉ አካላት በተደራጀ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ደርሷል፡፡ ሀገሪቱ ከገባችበት ሁኔታ እንድትወጣ ለማስቻል ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ሀገራዊ አለመግባባቶችን፣ ግጭቶችን ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውል አንድ አይነት የግጭት መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ድርድር የተለያየ ጥቅምና ፍላጎት የሚወክሉ አካላት በሰጥቶ መቀበል መርህ ልዩነቶቻቸውን የሚፈቱበት ዘዴ ነው፡፡ ሌላው ዘዴ እርቅ ሲሆን የደረሰ በደል ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረግና በመተማመን ይቅር በመባባል ስምምነትን ማስፈኛ ዘዴ ነው፡፡ በመጨረሻም የማስማማት የግጭት መፍቻ ዘዴ በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ልዩነትን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ ከግጭት መፍቻ ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ እንዲቻል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 አውጥቷል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጥቅም በዋናነት ግጭትን ለማስወገድ፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚጠቅም ነው፡፡ በተለይም ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለማስተዳደር እና ለመፍታት አይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃም በበርካታ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ መነሻ ምክንያቶች ሀገራዊ ምክክሮችን አካሂደዋል፡፡ የተወሰኑት የተሳካላቸው ሲሆን፤ የተወሰኑት የሚፈለገውን ግብ ሳያሳኩ ቀርቷል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ከሚያልፍባቸው ሂደቶች ውስጥ መነሻ፣ ዝግጅት፣ ምክክር እና ትግበራ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም የኮሚሽኑ የዝግጅት ምእራፍ ተጠናቆ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፤ ከዚህ አንፃር አዋጁ ያካተተው ጉዳይ የኮሚሽኑን ተግባርና ሀላፊነት በሚመለከት በገለልተኛነት እና በነፃነት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ የምክክር አጀንዳዎችን፣ አወያዮች አመራረጥን፣ የምክክር ስነ ስርአትን፣ የተወያዮች አመራረጥን እና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በነፃነትና በገለልተኝነት በራሱ እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡ ምክክር የሚደረግባቸው ደረጃዎች፣ ሂደቶች፣ አካባቢዎችን መወሰን እና ምክክሩንም በአመቻችነት መምራት አለበት፡፡
በዚህ ረገድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስራውን ሲጀምር ከክልል አስተዳደሮችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱም ግብዓት ከመሰብሰብ በተጨማሪ ለክልሎችና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነቶችን ሰጥቷል፡፡ ኮሚሽኑ ከክልል አመራር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። በመድረኮቹ ኮሚሽኑ የያዘው ዓላማ ኢትዮጵያውያንን የጋራ አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሁሉንም ህዝቦች ባሳተፈ መልኩ በማካሄድ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመግባባት በራሳቸው ጉዳይ መክረው መፍትሔ እንዲያስቀምጡ የሚያግዝ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልል መንግስታት ሁለንተናዊ ድጋፍ አስፈላጊ ነው፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ያወጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን በየመድረኮቹ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ በተለይ በክልሎች አካባቢ የሚታየውን የእርስ በርስ አለመግባባት በመፍታት ሀገራዊ አንድነት እንዲፈጠር ሊተጉ፤ የኮሚሽኑን አላማ ከግብ እንዲደርስ የሚጠበቅባቸውን ሊያበረክቱ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ክልሎች እርስበርስ የመደጋገፍና አብሮ የመስራት ሁኔታዎች ባሳደጉ ቁጥር በውስጣቸው የሚኖሩ ህዝቦች ተግባብተው ለአንድ አላማ መቆም ይችላሉ፡፡
ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ በህዝቦች መካከል መቃቃርን የፈጠሩ ትርክቶችን የማስተካከል ስራ ነው፡፡ በተለይ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ያለው የእርስበርስ ጤናማ ያልሆነ ፉክክር የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲወጡ በር ከፍቷል፡፡ እነዚህ ትርክቶች በህዝቡ ዘንድ መቃቃርን ከመፍጠር ባለፈ ጥላቻን አምጥቷል፡፡ ይህ ጥላቻ ታድያ የእርስበርስ ግጭቶች እንዲበዙ አድርጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክር መድረኩ መሳካትና ለውጥ ለማምጣት ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ በተለይ የተዘሩ የጥላቻ ትርክቶች እንዲሻሩ ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምክክር መድረኮችም በሚዘጋጁበት ወቅትም የነቃ ተሳትፎ በማድረግና ገንቢ ሃሳቦችን በመሰንዘር መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በውይይቶቹ የሚሳተፉት አካላት ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችን በመያዝ እና አንድነትን የሚያመጡ ጉዳዮችን በማንሳት ውይይቶች ላይ መሳተፍ አለበት፡፡ የምክክር መድረኮቹ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ተገቢውን ውጤት ለማምጣት እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ለአብነት ያክል ሀገሪቱ ያለፈችባቸውን መንገዶች በመገምገም በቀጣይ እንደ ህዝብ ሊተኮርባቸው የሚገቡ ሁነቶች ላይ የጋራ መግባባት እገዛ ያደርጋል፡፡
ዜጎች በምክክሩ ለሀገር እድገትና ተጠቃሚነት ፋይዳ በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜያቸውን ከማባከን ይልቅ በኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋ ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን የቀደመ ጠንካራ አንድነት ለመመለስ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ሁሉም ራሱን ለውይይት ዝግጁ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይ ላለፉት 27 ዓመታት በብሔር ተኮር የፖለቲካ እሳቤ ሲፈጸም የነበረው ሴራ በዜጎች መካከል ልዩነቶች እንዲሰፉ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። በዚህም የማህበረሰቡ የመተባበር፣ የመከባበርና ተቻችሎ የመኖር እሴቶች በተለያየ መንገድ ተሸርሽረው የነበረ ሲሆን፤ ይሄን መመለስ የምክክሩ አንደኛው አላማ መሆን አለበት።
በርካታ የሚያግባቡና አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እያሉ ባለፉት ዓመታት ልዩነቶች በሚያጎሉ ጥቃቅን አጀንዳዎች ላይ የእኔነት ስሜት ላይ እንድናተኩር ተደርጓል። ይህ ሴራ የሀገሪቱ ሀብት በውስን አካላት እጅ እንዲወድቅና ለዝርፊያ እንዲዳረግ ምቹ አጋጣሚ ከመፍጠር ባለፈ ሥራ አጥነትና መሰል ችግሮችን አበራክቷል። በኢትዮጵያዊያን የጋራ ተጋድሎ የመጣው ለውጥም በተፈለገው ልክ እንዲሄድና በህዝቦች መካከል የነበረው ጠንካራ አንድነት እንዲመለስ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል አለበት። ለውጡን በጠንካራ መሰረት ላይ በማቆም የተፈለገውን ሀገራዊ መግባባትና አንድነት ለማምጣት የመንግስትና ህዝብ መተማመን ወሳኝ ነው። ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሰሚ ያጡ የህዝብ ቅራኔዎችና አለመግባባቶችን በነባሩ እሴቶች መሰረት መለየት ይገባል፡፡ ለዚህም ኮሚሽኑ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ የተግባር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል ውጤታማ የሆነ የውይይት መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል፡፡
ከአለበል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም