ድምጽ እንዴት ሊቆጠር ይችላል? ምላሹ አስቸጋሪ ይመስላል። ለዛሬው ተቆጥረው የሚገኙ ሁለት ድምጾችን እንመለከታለን። የምናብ ታሪካችን “ሁለቱ ሰዎች” በማለት ይጀምራል። ሁለቱ ሰዎች አብረው ይራመዳሉ፤ በተመሳሳይ ፍጥነት፤ በተመሳሳይ ዝግታ፤ በተመሳሳይ ቁመት፤ ነገርግን በተለያየ እርቀት ።አንዱ ሲቀድም ሌላው ይከተላል። አንዱ ዋና ሆኖ ሲገኝ ሌላኛው ጥላ ሆኖ ይታያል። ጥላውም ዋናውም መሬቱ ላይ እኩል ሲሄዱ ይታያሉ፤ ሁለት ሰዎች፤ አንዱ ሰው በሁለትነት ።
ልጆቹ እንደወትሯቸው ግለሰቡን እያዩ ይጠቋቆማሉ። ግለሰቡ የአእምሮ ህመምተኛ መሆኑን ማህበረሰቡ ደምድሞ “እብዱ” እያለ የሚጠራው ። በሰፈሩ ውስጥ ያለውን ግሳንግስ ሁሉ ተሸክሜ ካልዞርኩ የሚል ። እናቱ ጋር ሲደርስ ግን የተለመደውን መልእክት በትኩረት የሚያስተላልፍ፤ የሁሌ መልእክቱን።
እናቱን በጥሞና ትኩር ብሎ ያያቸውና “እማዬ ሌላስ የምሸከመው ነገር ይኖር ይሆን?” ይላል ።እናቱም “ልጄ የተሸከምከው ከበቂ በላይ ነው፤ እባክህ ሸክምህን አራግፈው።” ይሉታል ።የእናቱን ምላሽ ሳይጠብቅ ፈጥኖ ወደ መንገድ ይወጣና ሌላ ሸክምን ይፈልጋል ። ተመሳሳይ ጥያቄ፤ የእናትም የዘወትር ተመሳሳይ መልስ። ቀኑን ሙሉ ሰፈሩን ሲያስስ የሚሸከመውን ሲመርጥ፤ የተሸከመውን ይዞ ጉዞ ሲያደርግ ይውልና አንዱ ጋር ይተኛል ። በሃያ አራት ሰዓት አንድ ጊዜ ግን እናቱ ካሉበት ቤት መጥቶ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ፤ የተሰጠውን ምላሽ ሳይሰማ በመጣበት ፍጥነት ይመለሳል ።
ሌላው የዘወትር ተግባሩ የገበያ መሃል ንግግሩ ነው። በአካባቢው በሚቆመው በሰኞ ገበያ ቀን ድንገት ይመጣና የሚሸከመውን ተሸክሞ በገበያው መሃል ቆሞ “ሸክሙ የእኔ ብቻ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፤ ሸክሙ የሁለታችንም ነው”ይላል ።እብድ ተብሎ ስም የወጣለት ሰው ሊቀርበው የማይፈቅደው አይነት ሰው ነውና “ሁለታችሁ” ማን እና ማን ናችሁ ብሎ የሚጠይቀው ሰው ግን የለም ።አንድ ቀን ግን ከገበያተኞቹ መካከል አንድ ሰው ቀርቦ “ሁለታችሁ ግን ማን እና ማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ፤ ምላሽ ሳይሰጠው አፍጥጦበትም ብቻ ሄዳ ።
ጥያቄ አቅራቢ ገበያተኛው ወደ ውስጡ ሲያዳምጥ በእርሱ ውስጥ ሸክም ተሸክመው የሚኖሩት ሁለቱ ሰዎች ታዩት፤ በሁለት አይነት ድምጽ ዘወትር የሚገኙቱ። ግለሰቡ ራሱን ሲያይ አንዳንዴ ራሱ ሁለት ሰው ሆኖ ያገኘዋል፤ ኧረ ለብዙ ጊዜ እንጂ ።በአንድ ሰው ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ።ተራ በተራ ሁለቱ የሚያወሩ፤ አንዳንዴ የሚጨቃጨቁ ግፋ ሲልም የሚጣሉ፤ የሚኮራረፉም፤ ሁለት ሰዎች ።እኒህን ሁለት ሰዎች በአግባቡ ማድመጥ መቻል አስፈላጊ እንደሆነ ገበያተኛው እያሰበ ወደ ገበያው ተመለሰ ።ወደ ተለመደው የገበያ ወግ፤ ወደ ጭቅጭቁ፤ የገዢና የሻጭ ጭቅጭቅ ።
የገበያ ውበቱ የገዢና ሻጭ ጭቅጭቅ ሆኖ እንዲሳል ያደረገ ጭቅጭቅ ዘወትር ይደረጋል ።የተለመደ መንገድ ነውና ጭቅጭቁ ቀጥሎ ሁሉም እንደ መሻቱ ገበያውን ፈጽሞ ይመለሳል ።ገበያው የሰመረለት አትርፎ ወደ ቤቱ ሲመለስ፤ ያልሰመረለት ከስሮም ሊወጣ ይችላል። እያንዳንዱ የገበያ ቀን ትርፍና ኪሳራ አለው፤ አንዳንዴም በመሰረቅም ሆነ በሌላ ሁኔታም ታጅቦ የሚውል ሰራተኛውም ሆነ ሌባውም የሚሰማሩበት ።
ገበያተኛው ጠያቂ ከገበያ ውስጥ ገበያ ተኮር ጭቅጭቅ በላይ አሻግሮ ያደመጠው እያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥ ስላለው ጭቅጭቅ ነበር ።የማይሰማው፤ በለሆሳስ የሚሆነው፤ መነሻውም ሆነ መድረሻው ግለሰቡ ውስጥ የሆነው፤ በአግባቡ ካልተያዘ ጨርቅ አስጥሎ ወደ አደባባይ ሊያስወጣ ስለሚያስችለው የአንዱ ሰው ሁለትነት የሚያሳየው ጭቅጭቅ ።
አሸናፊው ማን እንደሆነ የማይታወቀው በመንታ መንገድ ውስጥ የሚፈጠረው ጭቅጭቅ ህይወትን ባልተገባ አቅጣጫ ሊመራ መቻሉ ግን እሙን ነው። ምነው ያቺን ቀን የሚሉ ሰዎች ለአፍታም ቢሆን በውስጣቸው ተፈጥሮ የነበረውን ጭቅጭቅ አይረሱትም። በቀጣይም ቀን በውስጣቸው ተሸክመው የሚሄዱት የትናንቱ ህይወታቸው ተጽእኖው ቀላል አይደለም። የቆጠርናቸውን ሁለት ድምጾች በመመልከት ውስጥ ሁሉም ስለተሸከመው ሸክም እንመልከት ።
አንደኛው ድምጽ፤ በትናንት ውስጥ የሚገኘው
አንተ ውስጥ የትናንት ሰው አለ፤ አንቺ ውስጥ ትናንት ላይ የሚኖር ሰው አለ፤ በሁሉም ሰው ውስጥ ከትናንት የተነሳ የተፈጠረ ሰው አለ፤ ድምጽ የሆነ ።በጊዜ ውስጥ እንደ ህጻናት መሆን አንችልም ።ቀን በቀን እንደ ህጻን ከመሆን እንደ አዋቂ እንሆናለን ።እንደ አዋቂ በመሆን ውስጥ ትርፍም እንዳለው ኪሳራም አለው ።ህይወት እንደ ህጻን መሆን በምትፈልግበት ነገር ላይ እንደ ህጻን መሆን ሲሳነን እናገኛለን ።ለምን?ምክንያቱም በትናንት ጉዞ ውስጥ የተፈጠረ ድምጽ እንደ አዋቂ እንድንቀሳቀስ ከውስጣችን ሆኖ ስለሚነግረን ።
ትናንት አንድን ነገር ሞክሮ ያልተሳካለት ሰው፤ ዛሬ አንድን ነገር ለመሞከር ሲያስብ ምን ሊያስብ ይችላል? ትናንት በሙሉ ነጻነት ቃላትን እየተጠቀመ ሲናገር የነበረ፤ በነጻነት በመናገሩ ዋጋን ከከፈለ በኋላ ዛሬም በዚያው መንገድ ሊገኝ ይችል ይሆን? ትናንት ከሰዎች ጋር በግልጽነት በመቅረብ ዋጋን የከፈለ ሰው ዛሬ በተመሳሳይ መንገድ ላይ የሚገኝ ይሆን? ምላሹ ለአንባቢው ቢተው ከአንባቢው ምላሽ ጋር ስምም የመሆን እድላችን ሰፊ ነው።
በትናንት ውስጥ ያለፍንበት ነገር በዛሬ ላይ ጥላ ማጥላቱ አይቀሬ ነው ።ይህን ሰው እንዴት እንያዘው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ህይወትን በጥበብ ለመምራት ወሳኝነት አለው ።በትናንት እስረኛ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔው አንድ የሚዋጥ ኪኒን ነው ቢባል ኪኒኑን ለማግኘት የሚሰለፈው ሰው ሰልፍ የትየለሌ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ።
በትናንት ውስጥ ሆኖ የሚመክረው በውስጣችን ውስጥ ያለው አንደኛው ድምጽ ሌላኛውን ሰው የሚገነባ እንጂ የሚያፈርስ እንዳይሆን ማሰብ ያስፈልጋል ። የሰው ልጅ እድገት ውስጥ ዘወትር ቢያልፍ ይመርጣል። ባለበት ቆሞ መቅረትን የሚፈልግ ማንም የለምና። እድገት ደግሞ ወደፊት መራመድን ይጠይቃል። ወደፊት መራመድ ደግሞ በትናንት በመቆዘም ውስጥ አይሆንም፤ በተግባር መንቀሳቀስ በመቻል ውስጥ እንጂ ።
ያለፍንበት ትናንት ትምህርት ቤት ሆኖን የምንራመድበት እንጂ ወደ ኋላ የምንልበት ከእድገት የምንቀርበት እንዳይሆን ማሰብ ይኖርብናል ።ወደፊት መራመድ ነጻ ሆኖ ማሰብን፤ ያሰቡትን ወደ እቅድ መቀየርን፤ እቅድ ያደረጉትን መተግበር እንደሚችሉ መረዳት መያዝን፤ ወዘተ ይጠይቃል ።በትናንት ውስጥ በመቆዘም፤ እንደማይሆንልን በማሰብ፤ እጅና እግርን አጣጥፎ በመቀመጥ ውስጥ የትናንት ድምጽ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በትናንት ውስጥ ሆኖ ተስፋ አስቆራጭ መንፈስ እንደሚዋጋን ሁሉ በትናንት ውስጥ ትእቢትም ይዋጋናል። በትናንት ውስጥ አልጋ በአልጋ የሆነላቸው ሰዎች በውስጣቸው ሁሉንም ነገር እንዳሻቸው ማድረግ እንደሚችሉ የሚያስቡ ናቸው። እንዳሻቸው ማድረግ መቻላቸው ከህግም ከሞራልም ውጪ እንዲኖሩ የሚገፋፋቸው ሆኖ የትእቢት እስረኛ ይሆናሉ። የዛሬው ሰው በትናንቱ ሰው አማካኝነት መራመድን መፍራት እና በትእቢት መራመድ መፈለግን ሊያዳብር ይችላል። ትናንት ውልድ የሆነውን ድምጽ መግራት መቻል የጥበብ መንገድ ነው፤ በማይለወጠው ትና ንት በመልካም ሊሰራ የሚገባውን ዛሬን አለማበላሸት ።
ሁለተኛው ሰው፤
ወደ ነገ መራመድ የሚፈልገው በነገ ውስጥ ማድረግ የማንፈልገው ምን አለ ።ብዙ ነገር ገና ከፊታችን የሚሆን እንደሆነ ቆጥረን ትኩረታችንን ከፊታችን አድርገን እንኖራለን ።ወደ ፊታችን እንመለከታለን፤ ከፊታችን ምላሽን ለማግኘት እንፈልጋለን ።ያላገበው ሰው ከፊቱ ትዳርን ያስባል፤ ልጆች ሲወልድና ሲያሳድግ ወዘተ ።በሥራ ላይ ያለ ሰው ወደፊት ስለሚሰራበት ትልቅ የስራ ቦታ በማሰብ ትኩረቱን በነገው ውስጥ አድርጎ ጉዞን ያደርጋል ።ስራን በመፈለግ ላይ ያለው የሚፈልገው አይነት ስራ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ውስጥ እንቅስቃሴ ያደርጋል ።በነገ ውስጥ ሞትም አለ ።ከሞት ባሻገር ያለውን ህይወት የሃይማኖት መንገድ በሚለው በኩል ለማግኘት ሁሉም በየመንገዱ ይራመዳል ።በነገ ውስጥ እድገት እንዲሁም ሞትም አለ ። ሞትን በመፍራት፤ በተቻለው መጠን ከሞት ለማምለጥ ጥረት በማድረግ እድገትን ለማግኘት የሰው ልጅ ስራው ነው ።ሁሉም በየአቅጣጫው ያለው ስምሪት እድገትን ለማምጣትና ሞትን ለመሸሽ ነው ።የሞት ሽሽቱ በህክምና መስጫ ቦታዎች ላይ ሰዎች እንዲገኙ ያደርጋቸዋል፤ ባለመድሀኒትነት ይፍለጋል ።እድገትን ለማምጣት ደግሞ ተማሪው በትምህርት ቦታው፤ ሠራተኛው በስራው ቦታ ይገኛል። ሁሉም በየፈርጁ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ድምር ውጤት የምድራችንን ህይወት ይህን ያስመስለዋል።
ሁለተኛው ሰው ወደፊት ከመቆም ራሱን መልሶ ጉዞ ማድረግ ይፈልጋል። ከጉዞው የሚያደናቅፈው አይፈልግም። ጉዞውን ዳር ማድረስ ይፈልጋል ።ጉዞው ላይ እንቅፋት እንዳይኖር ይፈልጋል። እንቅፋት ሲገጥመው ይበሳጫል፤ እንቅፋቱን ገለል ለማድረግ በህግም በሌላም መንገድ ይሄዳል። በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ወደ አመራር የሚመጡ ግለሰቦች በመንገዳቸው ላይ የሚመጣውን በብልጠትም ሆነ በጡጫ ወደ ጎን በማድረግ መድረስ የፈለጉበት ጋር ለመድረስ ጉዞ የሚያደርጉ መሆኑን መጽሐፍት ይነግሩናል ። በሌሎች ሀገሮችም ተመሳሳዩ መንገድ በብዙ የተተገበረ ነው። ከስልጣኔ ወደ ኆላ በቀሩት ሀገራት ደግሞ አሁንም መተግበሩ የጨመረ ነው። ወደ ግለሰብም ጉዳዩን ስናመጣው ነገ ውስጥ ማየት ከሚፈለገው አንጻር አንዱ በሌላው ላይ መጨካከንም ይስተዋላል ።ሃሳብን በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ጡጫን መጨመር አዲስ ነገር አይደለም፤ እስከ ህይወት ማጥፋት።
ዛሬ በውስጣችን ያለውን በነገ ውስጥ እድገትን ማምጣት የሚፈልገውን ሰው በጥንቃቄ እንድንመለከተው ያስፈልጋል። በውስጣችን ያለው ሰው ወደ ውጤቱ ለመድረስ እየተከተለው ያለው ምን አይነት መንገድ መሆኑን መመርመር አለብን። ወደ ውጤት የሚያደርሰን መንገድ ላይ ለመገኘት ራስን መግዛት አስፈላጊው ነገር ነው። ወደ እድገት፤ ወደ ውጤት፤ ወደ መሳካት፤ ወደ ህልምን መጨበጥ ወዘተ ላይ መድረስ የሚፈልገው ውስጣችን ያለው ሰው ከትናንቱ ሰው ጋር የሚያደርገውን ግጭት በአግባቡ መመርመር፤ ምርመራውን ወደ ውጤት ማድረስ እንዲቻል የሚቻለውን ሁሉ ማድረግን ይፈልጋል ። ልማት የሚያስከፍለው ዋጋ እንዳለ የልማት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለአሁኑ ትውልድ የሚሆን ልማት መጪውን ትውልድ የሚጎዳ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግንም ይጠይቃል። ነገን ታሳቢ አድርጎ ጉዞ የሚያደርገው ሰው ወደ ውጤት እንዲደርስ ልማት ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ዋጋ መክፈል ተረድቶ ለዋጋ መክፈሉ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም