አብሮ መብላትና አብሮ መጠጣት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን መገለጫችን ነው፡፡አኗኗራችንም ማኅበራዊ ነው፡፡በየዕለቱ ከሚፈላው ቡና ጀምሮ ማኅበር፣ በዓላት፣ ዝክር፣ ድግስና ግብዣ፣ ሰርግ፣ ለቅሶ፣ ዕድር…ነዋሪዎችን የሚያገናኙ፤ ለዘመናት ኅብረተሰቡን አስተሳስረው የኖሩና ያሉ ማኅበራዊነት ህያው ሆኖ እንዲኖር ያስቻሉ የኢትዮጵያውያን የአኗኗር ዘይቤ ልዩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ታዲያ በዚህ ሁሉ ማኅበራዊነት ውስጥ አብሮ የሚነሳው የኅብረተሰቡ የእርስ በእርስ የመተባበርና የመደጋገፍ ባህል ነው፡፡
አዎ ሰው በደስታ ጊዜ በጋራ ይደሰታል፣ በኃዘን ጊዜም አብሮ ያዝናል፣ በችግር ጊዜ ይተባበራል፣ ኃዘንና ደስታውን ይጋራል፡፡ይህ በእርግጥም ልንጠብቀው የሚገባ ወርቃማ ባህል ነው፣ መልካምም ነው! ይሁን እንጅ በግሌ እንደታዘብኩት በእኛ ሃገርና ባህል በደስታም ይሁን በኃዘን የምንረዳዳው አንዳች ልዩ ክስተት ወይም ጊዜያዊ ሁነትን ጠብቀን ነው፡፡የምንረዳዳው በኑሯችን ውስጥ አንዳች ችግር ሲገጥመን ነው፡፡ትብብራችን አንድ ችግር ከደረሰብን በኋላ ለዚያ ችግር ጊዜያዊ ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሌላው ይቅርና የምንልሰው የምንቀምሰው እንኳን አጥተን፤ ክፉኛ ተቸግረን ቢሆን ፤ መቸገራችን አይንኑን አፍጥጦ፣ ጥርሱን አግጥጦ፣ አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሶ፣ ችግራችን ከችግርነት አልፎ በሕልውናችን ላይ አንዳች ከባድ ስጋት ካልተጋረጠ፣ ገመናችን በአደባባይ ካልተገለጠ ሊረዳን የሚፈልግ የለም፡፡የመጨረሻው ተስፋ የመቁረጥ ደረጃ ላይ ደርሰን፣ በትግሉ ተሸንፈን፣ ለችግራችን እጅ ሰጥተን ካልታየን እጁን የሚዘረጋልን የለም፡፡
በሕይወታችን ውስጥ ችግር በርትቶ፣ በትግላችን የሚያግዘን አጥተን፣ ስቃያችን በዝቶ፣ ጉልበታችን ደክሞ፣ ጥንካሬያችን ተረትቶ፣ ሞራላችን ተመትቶ፣ ልባችን ተስፋ ቆርጦ ላንመለስ ተጎድተን በቁማችን ከሞትን በኋላ ግን አዛኝ ለመሆን የሚሽቀዳደም ይበዛል፡፡ከንፈራችንን እየመጠጥን “ውይ እከሌ/እከሊት እኮ እንዲህ ሆነ/ች” እያልን “እርዳታ” ለማሰባሰብ በራሳችን ተነሳሽነት ከሁሉም ቀድመን ከፊት እንቆማለን፡፡ችግሩ ወይንም በሽታው ተባብሶ እስከወዲያኛው የሚሞት ካለም የወገናችንን ቀብር “ለማሳመር” ለዘመናት በቆየውና በዳበረው የ“ትብብር” ባህላችን በዕድራችን አማካኝነት ሟችን “ለመርዳት” ሆ ብለን እንነሳለን፤ ያውም ከብዙ ኃዘንና ደረት መድቃት ጋር፡፡
ዋነኛው የትብብር ባህላችን ወካይ መገለጫ የሆነው የዕድር ዓላማም ይኸው ነው – በሞት ወይም በችግር ጊዜ መተባበር፡፡ዳሩ ምን ያደርጋል የሚረዳው አጥቶ በችግር ብዛት ተስፋ ቆርጦ ላይመለስ የተጎዳን የቁም ሟች ወይም በቁሙ እያለ የሚደርስለት ወገን አጥቶ በችጋርና በድህነት አልያም በበሽታ ተሰቃይቶ ሳያልፍለት ያለፈን ሟች መርዳት የይምሰል ነውና ከዚህ በኋላ የሚደረገው እርዳታ በከንቱ የሚቃጠል የቃየል መስዋዕት ይሆናል፡፡ከሞተ በኋላ ሰውን መርዳት አይቻልምና!
በመሆኑም ዛሬ በዚህ መጣጥፌ ላነሳው የፈለኩት ዋነኛው ጉዳይ “መተባበር የሚገባን በችግር ጊዜ ብቻ ነው ወይ?” የሚለውን የትብብር ባህላችንን መሰረታዊ ህፀፅ ነው፡፡ምክንያቱም መልካም ስለሆነው ባህሌ የበኩሌን የማበርከት፣ ህፀፁን የማሳየት፣ ጉድለቱን የመሙላት በዚህም ወርቃማው የማኅበራዊ ኑሮና የትብብር ዕሴት የበለጠ ለኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን መንገድ የማመላከትና የተሻለ የምለውን ሁሉ የማሳየት ሞራላዊ ግዴታ አለብኝና፡፡
እናም እጠይቃለሁ፤ ለመሆኑ ዓለም ያደነቀውና አንደኛው የኢትዮጵያችን መለያ የሆነው ወርቃማው የትብብር ባህላችን በኅብረተሰባችን ውስጥ ለዘመናት አብሮ የቆየ ከመሆኑ አኳያ ለምን የሚገባውን ያህል ለዕድገታችን አስተዋፅኦ አላበረከተም? ይሄ ለምን ሆነ ብየ ስመረምር የደረስኩበት መደምደሚያ ለዘመናት የቆየው የማኅበራዊነትና የትብብር ባህላችን የዕድሜውን ያህል ለሃገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያላገለገለበት ምክንያት የትብብር ባህላችን በጊዜያዊ ሁነት ላይ እንጅ በቋሚ ዕውነት ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን ነው፡፡
የችግሩ ዋነኛ መንስኤም የትብብር ባህላችን ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ምላሽ መስጠትን እንጂ ችግሮች ከመከሰታቸውና ሰዎችን ከጥቅም ውጭ ከማድረጋቸው በፊት በሰላም ጊዜ ማገዝን፣ መልካምም ይሁን ክፉ አጋጣሚዎችን ተከትለው የሚመጡ ጊዜያዊ ሁነቶችን እንጂ የኅብረተሰቡን ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታና መሠረታዊ የዕድገት ዕውነቶችን መሠረት ያላደረገ መሆኑ ነው፡፡ከእኛ አልፎ በዓለም ደረጃ የምንታወቅበትና ማኅበራዊነት ላይ የተመሠረተው መልካሙና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው አንጋፋው የትብብር ባህላችን መጥቀም የሚገባውን ያህል ያልጠቀመን ለዕድገታችንም ያላገዘን ከእውነታ ይልቅ በጊዜያዊ ክስተትና ችግር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ወይም ችግር-መር በመሆኑ ነው፡፡
እንደአንድ ሃገሩንና ባህሉን እንደሚወድ ዜጋ ስለችግሩና ስለ መንስኤው ብቻ ሳይሆን የዚህ ወርቃማ የትብብር ባህላችን ጉድለቶች ስለሚሞሉበትና በቀጣይ ዕሴቱ ለላቀ የህብረተሰብ ጥቅም ስለሚውልበት፣ ስለመፍትሔውም ያለኝን ሃሳብ እያካፈልኩ ልቀጥል፡፡“የዕድሜ ባለ ፀጋው” የትብብር ባህላችን የዕድሜውን ያህል በሥራውም ታላቅ እንዲሆን፣ እውነተኛ ፋይዳው በተግባር ተገልጦ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ለጋራ ብልጽግና ጥቅም ላይ እንዲውል በዕድሜ ታላቅ መሆን የሚያስገኘውን ዋጋ ሳይረሱ ቁም ነገሩም ታላቅ እንዲሆን ዝቅ ብሎ በትህትና ቀና ብሎ በድፍረት መጠየቅ ይገባል፡፡
ይህንን ስናደርግ በማኅበራዊ ኑሯችን ውስጥ ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ የሚታመነው የትብብር ባህላችን በተመለከተ ካስቆጠረው ረጅም ዕድሜ እና ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማምጣት ካለው ከፍተኛ ፋይዳ አኳያ መጥቀም በሚገባው ልክ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑ አንዳች መሠረታዊ ችግር እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡የችግሩን መንስኤ ስንገነዘብ ደግሞ “የአንድን ችግር ዋነኛ መንስዔ ማወቅ ችግሩን ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመጓዝ ነው” የሚለውን አባባል ትክክለኛነት አውቆ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን ዕድል እንፈጥራለን፡፡
በዚህ ረገድ በበኩሌ ለህሊናዬ ታምኜ፣ የሃገሬን ጥቅም መነሻና መድረሻ አድርጌ በአቅሜ በመረመርኩት መሠረት ወርቃማው የትብብር ባህላችን ከዘመናት የችግር-ተኮርነት የቆየ ልማዱ ተላቅቆ ለሃገርና ለሕዝብ የሚገባውን ያህል መጥቅም እንዲችል መፍትሔ ሆኖ ያገኘሁት ችግሩ መኖሩን አምኖ ተገቢውን ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንን ነው፡፡ለዚህም ባህል የሚሻሻል፣ የሚለወጥና የሚያድግ መሆኑን ዘንግቶ፣ ጎጂ መሆኑንም እንኳን እያወቀ እንደ ዘመኑ ጭፍን ብሔርተኞች “የእኔን ባህል ሊያጠፉ፣ የራሳቸውን ሊጭኑብኝ፣ ሊውጡኝ…ቅብጥርስ …” ከሚል የውሸት ተቆርቋሪትና አጉል ግብዝነት ወጥቶ በንጹሕ ሕሊና ጥቅምና ጉዳቱን መመርመር ያስፈልጋል፡፡
ይህን ለማድረግ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከዕውቀትም የበለጠ ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ነገሮችን በዕውቀትና በቅንነት ከመመርመር በተጨማሪ ዕምነት ትልቅ ኃይል አለውና ራስንና ሌሎችን ማመን፣ መታመንና እርስ በእርስ መተማመንን ከነገር ሁሉ በፊት ከሁሉ አስቀድመን ሁላችንም ልንመራበት፣ ልንኖርበትም ይገባናል፡፡ያኔ ከከንቱ የባህል ተቆርቋሪነትና ከጭፍን የባህል ጠባቂነት ተላቅቀን የማይጠቅምን ልማድ በመለወጥና በአዲስ በመተካት፣ ዕድሜ ጠገቡንና ወርቃማውን የትብብርና የማኅበራዊ ኑሮ ባህላችንን ጉድለቶች በማረምና በአዳዲስ ጠቃሚ ሃሳቦች በማጎልበት ለሚፈለገው ሁለንተናዊ ዕድገትን የማምጣት ዓላማ ማዋል እንችላለን፡፡
በዚህም ሰዎች ችግር ደርሶባቸው ከተጎዱ በኋላ ሳይሆን ገና ችግሩን የማሸነፍ አቅም ላይ እያሉ እገዛ የሚያገኙበትንና ከችግራቸው በቀላሉ መውጣት የሚችሉበትን አዲስ የማኅበራዊ እሴትና የትብብር ባህል መፍጠር እንችላለን፡፡ለችግር ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ሰዎች የችግር ሰለባ ከመሆናቸው በፊት አግዞ ወደ ዕድገት ማምጣት የሚያስችል፤ ችግር ተኮር ሳይሆን “ዕድገት-መር” የትብብር ባህልና ማኅበራዊ ዕሴት መገንባት እንችላለን፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም