መካንነት ማለት ከአንድ አመት በላይ ያለ እርግዝና መከላከያ በተደረገ የግብረስጋ ግንኙነት ለመፀነስ ያለመቻል ሲሆን፤ በዚህ መካከል ግን የሴት ዕድሜ 35 እና ከዛ በላይ ከሆነ መካን ለመባል የሚያስፈልግበት ጊዜ እስከ ስድስት ወር ነው፡፡
መካንነት 10 እስከ 15 በመቶ በሆኑ ጥንዶች ላይ የሚታይ ችግር ነው የሚሉት የተለያዩ የዘርፉ ጥናቶች ይህ ማለትም ዕድሜያቸው ከ 20 እስከ 45 ዓመት የሆኑት ጥንዶች ላይ በጣም የተለመደ ችግር ነው ። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አብዛኞቹ ጥንዶች ሙሉ ጤነኛ ከሆኑ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እርግዝና ይፈጠራል፡፡
የመካንነት ምክንያቶች
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛውን ጊዜ በተለይም በሴቶች ላይ ለመካንነት መንስኤ ሆኖ የሚገኘው እድሜ ነው ።በመሆኑም የሴት ልጅ ዕድሜ ትልቅ ተፅዕኖ አለው ፤ በተለይ ወደ 30 እና 40ዎቹ የደረሱ እንስቶች ከፍ ያለ ጫና ያለው መሆኑንም ጥናቶቹ ይናገራሉ ። ለጤነኛ ሴት በ20ዎቹ ዕድሜ ወይም የ30 መጀመሪያ አመታት እርግዝና የመፈጠር እድሉ በየወሩ ከ 25 እስከ 30 በመቶ ሲሆን፤ በ40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለች ሴት ግን የማርገዝ ዕድሏ 10 በመቶ ወይም ከዚያ ያነሰ ስለመሆኑ ይነገራል ።
እድሜዋ ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ሴት በወር ውስጥ አንዴም እንቁላል (የሴት ዘር) ካልለቀቀች የማርገዝ ችግር ያጋጥማታል ።ይህንን ችግር ሊያመጡ ከሚችሉ ችግሮች መካከል ደግሞ የእንቅርት ህመም፣ የሆርሞን ችግሮችና polcystic ovary syndrome (PCOS) የሚባል በሽታ መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪ የወር አበባ በትክክል በየወሩ የማያዩ ሴቶች ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም ከመጠን በላይ ውፍረት መጨመርና ክብደት መቀነስ የየራሳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል፡፡
የማህፀን ቱቦ መጎዳት ወይም መዘጋት
የማህፀን ቱቦዎች ከማህፀን ጋር የተገናኙ ሲሆን፤ የወንድ ዘር እና እንቁላል የሚገናኙበት ቦታ ነው ።የማህፀን ቱቦ መዘጋት ወይም መጎዳት መካንነት ወይም ከማህጸን ውጭ እርግዝናን ሊያስከትል ይችላል፡፡
የማህጸን ጫፍ ችግሮች
የማህጸን ጫፍ ችግሮች መካንነት ከሚያመጡ ነገሮች መካከል ተጠቃሾቹ ሲሆኑ፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ መካን የማድረግ እድላቸውም አናሳ ነው ።የማህፀን ጫፍ ችግር ፅንስ የማህፀን ግድግዳ ላይ ተለጥፎ እድገቱን እንዳይጀምር ያደርጋል ።
የሆድ እቃ ችግሮች
ሆድዕቃ ችግሮች የሚባሉት ሆዳችን ውስጥ ያሉት የሰውነት ክፍሎች ( ኦርጋንስ)የሚሸፍን ጠባሳ ወይም Endometriosis (ኢንዶሜትሪዮሲስ) ማለት ሲሆን ማህጸን ላይ የሚገኘው ቲሹ ( tissue ) በሌላ ቦታ ላይ ሲበቅል ነው ።ይሄ ቲሹ (pelvis) ፔልቪስ ውስጥ በሚገኘው በማንኛውም አካል ላይ ኦቫሪም ላይ ሊበቅል የሚችል ነው ።በመሆኑም እነዚህ ነገሮች በሴቶች ላይ በሚከሰቱበት ጊዜ መካንነትን ያስከትላሉ ።
የወንድ መካንነት
አንድ ሶስተኛው የሚሆነው የጥንዶች መካንነት ችግር በወንዶች ምክንያት ሲሆን፤ ሌላው አንድ ሶስተኛው ደግሞ የመካንነት ችግር ደግሞ በሁለቱም ጥንዶች በአንድ ላይ የሚከሰት ችግር ነው ።ወንዶች መካን የሚሆኑባቸው ምክንያቶች የወንድ ዘር አለመስራት ወይም የወንድ ዘር አለማመንጨት ናቸው፡፡
ምክንያቶቹ ያልታወቀ የመካንነት ችግር
ከ10 በመቶ እና ከዛ በላይ የሚሆኑ መካኖች የሚታወቅ ምክንያት የላቸውም፤ ይህም ምክንያቱ ያልታወቀ የመካንነት ችግር ይባላል ።አልፎ አልፎም እነዚህ ችግሮች በህክምና ሊታገዙ ይችላሉ፡፡
የመካንነት ችግር በጥንዶች ላይ ተከሰተ የምንለው በየጊዜው የወሊድ መከላከያ ሳይጠቀሙ ለአንድ አመት ግንኙነት ቢያደርጉም ጽንስ መፈጠር ካልቻለ ነው ።ይህ ችግር የወንድም ሆነ የሴት ችግር ሊሆን ይችላል ። ከዚህ ጋር ተያይዞ እድሜያቸው ከ40 ዓመት እድሜ በላይ በሆኑ ጥንዶች ላይ ይህ ችግር የማጋጠም እድሉ የጨመረ ነው፡፡
አጋላጭ ምልክቶች ለመካንነት ችግር ለመጋለጥ የዘረመል ችግር (genetic problem) ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል ።ይህ ደግሞ ምንም አጋላጭ ምክንያቶች ሳይኖሩ ሊፈጠር የሚችል ነው ።ይህ አይነት መካንነት (primary infertility) ወይም እርግዝና ተከስቶ የማያውቅበት አይነት የመካንነት አይነቶች ውስጥ ዋናው ነው፡፡
በሌላ በኩልም የዕንቁላል ማጠራቀሚያ ወይም ዕንቁላል ችግር፣ የወንድ የዘርፍሬ አፈጣጠር፣ መጠን እንዲሁም የዘርፈሳሽ አወራረድ ችግር፣ በተለያዩ ምክንያቶች የማህፀን ቱቦ መደፈን፣ በሰውነት እድገት (hormone) መዛባት ምክንያት እርግዝና ያለመከሰት እድሉ ይሰፋል፡፡
የመካንነት ምልክቶች
በእድሜ ከ40 ዓመት በላይ መሆን ፣ የወርአበባ መብዛት ሲከሰት ፣ በቤተሰብ መውለድ ወይም የመካንነት ችግር ሲኖር፣ የማህፀን ኢንፌክሽን ተከስቶ ከነበረ፣ የአባላዘር በሽታ ካጋጠመ ፣ ለማንኛውም ዓይነት ካንሰር የጨረር ወይም ኬሞቴራፒ ህክምና ከተደረገ፣ የማህፀን እንዲሁም የዘርፍሬ ሳንባ ነቀርሳ (Tb) ተይዘው ከነበረ እንዲሁም ያልታከመ ሳንባ ነቀርሳ ተይዘው ከነበሩ፣ በወንዶች የፕሮስቴት የዘር ፍሬ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የስንፈት ወሲብ ችግር ካለና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እንደመንስኤ ይጠቀሳሉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው ከዘር ወይም ዘረመል ችግር አንዲት ሴት ወይም አንድ ወንድ ጽንስ መፍጠር ያለመቻል የሚመጣ መካንነት ውጪም በተለይ እርግዝና ተከስቶ የሚያውቅ አይነት (secondary infetlity) የሚያመጡ ምክንያቶችም አሉ፡፡
እነዚህ ምልክቶች በወንዶች ላይ ስኳር ፣ የአባላዘር በሽታ፣ ጆሮ ደግፍ እንዲሁም ኤች አይቪ ኤድስ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዘር ፍሬ ማስተላለፊያ ችግር የሚያመጡ በሽታዎች እንደ ቲቢ፣ባክቴሪያና ኢንፌክሽን፣ አልኮል መጠጥ መጠጣት ሲጋራ ወይም አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም ፣አንዳንድ ለደም ግፊት እንዲሁም ለኢንፌክሽን የሚሰጡ መድሀኒቶች በተደጋጋሚ መውሰድ፣ ፀረተባይ መድሀኒትና ጨረር የካንሰር መድሀኒቶች አካባቢ ተጋላጭ መሆን ይጠቀሳሉ ።
እነዚህ በሴቶች ላይም የራሳቸው መገለጫዎች ያሏቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል እንቁላል ከእንቁላል የማጠራቀሚያው ወደ ማህፀን እንዲመጣ እንዲሁም ከወንድ የዘር ፍሬ ተጣምሮ በማህፀን እንዲቀበር የሚያደርጉ ሆርሞንስ (hormone) ችግሮች፣ የማህፀን እጢና የማህፀን የእንቁላል የማጣራቀሚያ ካንሰሮች፣ በተደጋጋሚ እንዲሁም በህክምና ተቋም በተገቢው መንገድ ያልተደረገ ውርጃ፣ ከእንቁላል ማጠራቀሚያ ወደ ማህፀን በሚወስደው ቱቦ ችግር (በኢንፌክሽን ፣በውርጃ እንዲሁም ቀዶ ጥገና ጊዜ የሚመጣ ጠባሳ)፣ ከሚጠበቅባት እድሜ በፊት አንዲት ሴት ቀድማ የማረጥ ጊዜዋ ሲመጣ፣ ማጨስ፣ አደንዛዥ እፅ መጠቀም፣ ፀረ ተባይ ጨረርና የካንሰር መድሀኒቶች መውሰድ፣ የክብደት በጣም መጨመር ወይም መቀነስ፣ ሀይለኛና አቅም የሚጠይቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠቀሳሉ። በአጠቃላይ ከዚህ የምንረዳው ብዛት ያላቸው ጥንዶች በተለያዩ ምክንያቶች የመካንነት ችግር ሊመጣባቸው ስለሚችል ያሉትን ችግሮች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መታየት፣ ምርመራዎችን ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ነው ።
አንዳንዴ ሁሉም ነገር ጤናማ ሆኖ እርግዝና ላይፈጠር ይችላል። ይህ የማይገለፅ መካንነት [Unexplained Infertility] ይባላል። ይህ ማለት ቴክኖሎጂ ያልደረሰባቸው ችግሮች አሉ ማለት ነው። 20 በመቶ የሚሆኑ ጥንዶችም ይህ ችግር የሚያጋጥማቸው ሲሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና ሊደረግላቸው ይችላል።
መካንነት በተለይ አፍሪካ ውስጥ የተለመደ ችግር ነው ። በተለይ በአባላዘር በሽታዎችና በሌሎች ኢንፌክሽኖች የመካንነት ችግር ተንሰራፍቷል። የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከ15 እስከ 20 በመቶ ጥንዶች የዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው። ሴቷም ሆነ ወንዱ በእኩል ደረጃ በመካንነት ሊጠቁ ይችላሉ፤ በመሆኑም በማኅበረሰቡ ሴቷ ላይ ብቻ ጣት የሚቀስረው በተሳሳተ አመለካከት ነው።
በአውሮፓዊያኑ 2016 የወጣው የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የውልደት መጠን እየቀነሰ መሆኑን ያመለክታል። በከተሞች ደግሞ በ2000 ከነበረው 3ነጥብ 0 በ2016 ወደ 2ነጥብ 3 ዝቅ ብሏል።
በአጠቃላይ አንዲት ሴት መውለድ ካለባት አማካይ የውልደት መጠን በ2000 ከነበረው 5ነጥብ 5 በ2016 ወደ 4ነጥብ 6 መቀነሱን የዳሰሳ ጥናቱ ያመለክታል።
በአገራችን ይህንን የብዙ ጥንዶች ችግር የሆነውን የመካንነት ሁኔታ በህከምና ለመፍታት ከሚሰሩ የጤና ተቋማት አንዱ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ ነው ።ሆስፒታሉ የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግር ለመፍታት የመካንነት ሕክምና ማዕከል አስመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ 2011 ዓ.ም ነው።
አገልግሎት መስጠት በጀመረ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ከ 60 ሺህ በላይ ጥንዶች የመካንነት ሕክምና የተከታተሉ መሆናቸውን በሆስፒታሉ የሥነ ተዋልዶ ማዕከል የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ከእነዚህ መካከል 1ሺ 400ዎቹ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና ለማግኘት የተመዘገቡም ነበሩ። ቀሪዎቹ ደግሞ ወደዚህ ሕክምና ከመግባታቸው በፊት ሌሎች ሕክምናዎችን በመከታተል ሂደት ላይ ነበሩ ።ጥንዶች በተለያየ ኑሮና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የመጡ ናቸው።
በዚህ መንገድ እናቶች ልጃቸውን ሲያቅፉ በደስታ ያለቅሳሉ። በጋብቻ መሃል ልጅ አላዩም ነበር። ልጅ ይናፍቁ ነበር። ልጅ ለማግኘት በዕምነት ቦታዎችና የባህል መድሃኒት ፍለጋ ሲንከራተቱ ነው የቆዩት። ከማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው ጫናም ቀላል አልነበረም። ይህን ሁሉ አልፈው ልጅ ሲያቅፉ የተሰማቸውን ሊቆጣጠሩት የማይችሉት የደስታ ስሜት ነው። በደስታ ሲፈነጥዙ ነው የሚታየው በማለት ከሆስፒታሉ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ሕክምናው የሚሰጠው በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ባስተማራቸው የሕክምና ባለሙያዎች ነው። ይህ የሕክምና አገልግሎት መሰጠት ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
“በማኅበረሰቡ ልጅ መውለድ፣ ቤተሰብ መመሥረት እንደ ሕይወት ግብ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ፤ መካንነት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከትላል። በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩም ሆነ በሌላ መልኩ መፍትሔ ሲያገኙ ጥንዶች ደስተኛ ይሆናሉ” ። ይህ የሕክምና አገልግሎት መጀመሩም መልካም ጅምር ነው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም