የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ሩጫ ከስፖርትም በላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል። በእርግጥም አትሌቲክስ ከስፖርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ማረጋገጥ ይቻላል። አትሌቲክስ ኢትዮጵያን ለዘመናት በመልካም ሲያስጠራና ገጽታዋንም ሲገነባ የኖረ ስፖርት ሲሆን፤ የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ማሰሪያ ሆኖም ያገለግላል። ሩጫ ለብዙዎች ሥራ ሆኖ የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፤ መተሳሰብና የመረዳዳት መንገድ መሆኑንም አሳይቷል።
ኢትዮጵያ ስማን ካስጠሯት ብርቱ አትሌቶቿ እንዲሁም ለስፖርቱ ምቹ ከሆነው ድንቅ ተፈጥሮዋ ባሻገር የወርቃማ አትሌቶች አገር መሆኗን በታላቁ የሩጫ በኢትዮጵያ እያስመሰከረች ትገኛለች። ያለፉትን 22 ዓመታት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ታዋቂ አትሌቶችን በማሳተፍ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ከማግኘት ባለፈ የአገርን መልካም ገጽታ በመገንባት ላይ የሚገኘው ይህ እንደ ስሙ ታላቅ የሆነ የጎዳና ላይ ውድድር ለአገር እያበረከተ የሚገኘው ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዓለም ምርጥ አስር እንዲሁም ከአፍሪካ ቀዳሚ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የሆነው ግዙፉ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ዕውቅና ሰጪ ተቋም አባልም ነው። ይህም ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች አገራት ዝነኛ አትሌቶች ውድድሩን እንዲመርጡት በማድረግ በስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።
ይህ በሩጫ ስፖርት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ተቋም መርሃ ግብሩን ከውድድርነት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮችን በመከወንም መልካም ስም መገንባት ችሏል። 40ሺ ሯጮች የሚሳተፉበት የዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ሊካሄድ ሳምንታት ብቻ የቀሩት ሲሆን፤ ከሩጫ ባሻገር ያለ ተግባሩን በዚህ ዓመትም አጠናክሮ ይቀጥላል። ከሩጫው ጎን ለጎን ከሚያካሂዳቸው ማህበራዊ ጉዳዮች መካከልም በዓመታዊ ሩጫው ላይ ሁለቱን ተግባራት በመደበኛነት ይመራቸዋል። እነዚህም ትኩረቱን በትውልዱ ላይ ያደረገው የሕፃናት ሩጫ እንዲሁም ‹‹ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ›› የሚለው የእርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ናቸው።
ከ2005 ጀምሮ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከመካሄዱ አንድ ቀን አስቀድሞ የሕፃናት የሩጫ ውድድር ይካሄዳል። ዕድሜያቸው ከ3-11 ዓመት ድረስ የሆናቸው ሕፃናት እርስ በእርስ የሚያደርጉት ይህ የሩጫ ውድድር ስፖርትን ባህላቸው ያደረጉ ታዳጊዎችን የመፍጠር ዓላማን ያነገበ ነው። ይህም ውድድር በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፤ ዘንድሮ ‹‹ፕለይማተርስ›› በሚል ሃሳብ የሚቀጥል መሆኑን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስውታቋል። ይህ ውድድር ከፕላን ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ሲካሄድም፤ ጨዋታን መሠረት ያደረገ ተማሪ ተኮር የመማር ማስተማር ሥነዘዴን ያስተዋውል። ፕሮጀክቱ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች እየተገበረ ሲሆን፤ 250ሺ ሕፃናትን ለማስተማርም እቅድ አለው።
በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሚያደርገው የመሮጫ ካኒቴራም (ቲሸርት) በ250ብር እየተሸጠ መሆኑን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ አስታውቋል። ሽያጩም ከትናንት (ጥቅምት 02/2015ዓ.ም) ጀምሮ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ ይደረጋል። ሕፃናቱ ከሩጫው በኋላም ሜዳሊያ የሚበረከትላቸው ይሆናል።
ሌላኛው ከሩጫው በተጓዳኝ የሚካሄደው መልካም ተግባር ደግሞ ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ የሚለው የበጎ አድራጎት ዘመቻ ነው። ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመተባበር የሚካሄደው ይህ መርሃ ግብር በ80ሺ ብር ድጋፍ ተጀምሮ አሁን ላይ 19 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ባለፉት ዓመታትም በዚህ ዘመቻ 31 የሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የገንዘብ ተጠቃሚ ሊሆኑ ችለዋል። የትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሁም የሕፃናት ፓይለት ፕሮጀክቶች ምስረታም ከዚህ በተጓዳኝ የሚነሳ ነው። ድጋፉ የሚደረገውም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያወጣው መስፈርት መሠረት ለሚመረጡ ተቋማት ነው።
በዘንድሮ ውድድር ላይም ምሽሽጓ ሎካ፣ አክሽን ፎር ዴቨሎፕመንት እና ኢማጅን ዋን ደይ የተባሉት ሦስት ተቋማት መመረጣቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ ገልጸዋል። የመሮጫ ቲሸርቶቹ አስቀድመው የተጠናቀቁ ቢሆንም ለዚህ በጎ ዓላማ እንዲሆን የተወሰኑ ቲሸርቶች የቀሩ በመሆናቸው ተሳታፊ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች በ900 ብር መግዛት እንደሚችሉም ታውቋል። በዚህም 1ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ሲታቀድ ቲሸርቱን መግዛት ያልቻሉ ሰዎች ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም