ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አቶ ፍቅሩ ባደረባቸው ህመም በሚኖሩበት ሃገር ፈረንሳይ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከትናንት በስቲያ ሌሊት ላይ በ88 ዓመታቸው ማረፋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አረጋግጧል።
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ በስፖርት ጋዜጠኝነት፣ ቀዳሚ በመሆን እና በአለም አቀፍ ተቋማት በስፖርት እና በተለያዩ ዘርፎች በሀላፊነት እንዲሁም በከፍተኛ ሙያተኛነት በማገልገል እውቅናን የተጎናፀፉት የአንጋፋው የስፖርት ሰው አቶ ፍቅሩ ስርአተ ቀብር መቼና የት እንደሚፈጸም እስከ ትናንት አመሻሽ የተገለጸ ነገር የለም።
አቶ ፍቅሩ በህይወት በነበሩ ጊዜ በተለይም የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እንዲመሰረት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ እንዲጎለብት በማድረግም ለበርካታ ወጣቶች አርአያ መሆን ችለዋል። ከስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያቸው ጎን ለጎን በታላላቅ በአለም አቀፍ ተቋማት በሰሩባቸው ወቅቶች አገራቸውን በማስጠራት ታላላቅ ሽልማቶችን ለመቀበል በቅተዋል።
‹‹የፒያሳ ልጅ›› መፅሀፍ ደራሲ የሆኑት አቶ ፍቅሩ፣ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ፈር ቀዳጅ ከሚባሉ ግለሰቦች አንዱ ከመሆናቸው ባሻገር የእግር ኳስ ጨዋታን በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላለፍ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ነበሩ። አቶ ፍቅሩ በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት ያስተላለፉት ጨዋታም እኤአ በ1957 የኢትዮጵያና የሱዳን ብሔራዊ ቡድኖች አዲስ አበባ ስቴድየም ላይ ያደረጉት ጨዋታ እንደነበር በታሪክ ማህደሮች ተሰንዶ ይገኛል።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በተለያዩ ቋንቋዎች የስፖርት ዘገባዎችን በማቅረብም ይታወቃሉ። ኦሊምፒክ፣የአለም ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫና የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን በመሳሰሉ ታላላቅ የአለማችን የስፖርት መድረኮች ላይ በአካል በመገኘት የተለያዩ ዘገባዎችን ሰርተዋል። ከጋዜጠኝነት ህይወታቸው ባሻገር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፣ በካፍ እና በኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራርነት ፣ በጋዜጠኞች ማህበር መስራችነት እና አመራርነትም ከፍተኛ ግልጋሎት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ስማቸው በቀዳሚነት የሚነሳው ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በ1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን የአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የተመዘገቡ የልብ ደጋፊ መሆናቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
አቶ ፍቅሩ በተለይም የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በ1961 ዓ.ም ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ቴኒስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል። በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ እንደነበሩም ይታወሳል።
ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ በሀገሪቷ ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የአለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን መስራት የቻሉት ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።
የአቶ ፍቅሩን ከዚህ አለም በሞት መለየት አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ሌሎች የስፖርት ተቋማትና የስፖርት ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በአንጋፋው የስፖርት ሰው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰባቸው ፣ ለሙያ ባልደረቦቻቸው እና ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ይመኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2015