ትውውቅ
የአዊ ብሔረሰብ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት 3 የብሔረሰብ ዞኖች አንዱ ነው። ዞኑ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር በደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ በ122 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። የብሔረሰብ ዞኑ መቀመጫ የሆነችው እንጅባራ ከተማ ደግሞ ከአዲስ አበባ ባህርዳር መንገድ በ435 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኛዋ ነው።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በምስራቅ- የምዕራብ ጐጃም ዞን፣ በምዕራብ- የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በሰሜን- የሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጐጃም ዞኖች፣ በደቡብ- ምዕራብ ጐጃምና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ያዋስኑታል።
የአዊ ብሔረሰብ ዞን የበርካታ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ መስህብ ሀብቶች፣ የባህል እሴቶችና ማህበራዊ ኩነቶች ባለቤት ነው። የተለያዩ ውሃማ አካሎች በጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ትልልቅና መለስተኛ ወንዞች፣ ምንጮች፣ እርጥበት አዘል ባህር ሸሸ መሬቶች፣ ፏፏቴዎችና ሐይቆች የተመልካችን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ ውብና ማራኪ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች መገኛ ነው።
ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ በርካታ ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት፣ መካነ-መቃብሮችና ዋሻዎች፣ የብራና መጽሐፍት እንዲሁም ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደኖች፣ በርካታ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ ዝርያዎች መገኛ ነው። ለአብነት የዘንገናና የጥርባ ሃይቅ፣ የትስኪ፣ የዶንደር፣ የፋንግና የጋርቾ ፏፏቴ፣ የዳንጉላ ዋሻና የወለተ ጴጥሮስ ገዳምን በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል።
ብሔረሰቡ ተቀድቶ የማያልቅ ባህል፤ የራሱ ቋንቋና በኢትዮጵያ ታሪክ አስተዳደራዊ ድርሻ የነበረው ቀደምት ህዝብ ነው፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከአዊኛ ቋንቋ በተጨማሪ አማርኛ በስፋት፤ ጉሙዝኛና ሽናሽኛ በጥቂቱ የሚነገርበት እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተከባብረው የሚኖሩበት ነው፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩን ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ የሚያስተዋውቅ የአዊ ባህልና ኪነ-ጥበባት ማህበር ተቋቁሞ «እንተዋወቅ ቁጥር 1 እና 2» የኦዲዮና ቪሲዲ አልበሞች ተሠርተው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባህሉን አስተዋውቀዋል፡፡ እኛም የብሔረሰቡን ቱባ ባህሎች የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ያወጣቸውን መረጃዎችን በማጣቀሻነት በመጠቀም፤ ከዞኑ የባህል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪን በማናገር ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡
የባህል አምባሳደሮቹ ፈረሰኞች
የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር የብሔረሰቡን ባህልና ትውፊት በማስተዋወቅ ረገድ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡ ማህበሩ የሰባት ቤት አገው የሚለውን ስያሜ ያገኘው በአንድ ወቅት «አንክሺ፣ ባንጂ፣ ዘጋሚ፣ አዚኒ፣ ኳኩሪ፣ ቻሪና ሚቲክሊ» የተባሉ ሰባት ወንድማማቾች ከዋግ ኸምራ አካባቢ እንደመጡና፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡና ለአደን ምቹ መሆኑን ስለተገነዘቡ በአካባቢው በመስፈራቸው ነው። በመሆኑም የዘር ግንድ አመጣጡን ለመዘከር ሲባል እንደሆነ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አንድ ሰው ፈረሰኛ ለመባል ፈረስ፣ ኮርቻ፣ ፋርኒስ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ምቹና ግላስ ለፈረሱ ያስፈልገዋል። ለራሱ ደግሞ አለንጋ፣ ዘንግ፣ ገንባሌ፣ ሳርያን ኮት፣ ጀበርና ሊያሟላ ይገባል። ጦር፣ ጋሻና ሌሎች የአባቶቻችን የዘመቻ ቁሶች ካሉት ደግሞ ተመራጭ ነው።
አገውና ፈረስ ተለያይተው አያውቁም ወደፊትም አይለያዩም። በአገዎች ዘንድ ፈረስ የታመመን ወደህክምና ያደርሳል፤ የተጋቡ ጉብሎችን ያንሸራሽራል፤ በዓልና ሃዘንን በማድመቅም ትዝታው እንዲታወስ ያደርጋል። ፈረስ መሬቱን አርሶ ጎተራ ሙሉ እንዲሆን ያደርጋል። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማጓጓዣ ሆኖም ያገለግላል። ለእነሱ ፈረስ ሁሉም ነገራቸው ነው ማለት ይቻላል። ሰባት ቤት የአገው ፈረሰኞች ማህበር የብሔረሰቡን ትውፊት በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የ «ፊፊ ጨዋታ»
«ፊፊ» ቆየት ያለ በጃዊ ወረዳና አካባቢው በሚኖሩ አዊዎች የተለመደ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በጥንት ጊዜ ጠላትን ለመከላከል የተጠቀሙበት መግባቢያ መሣሪያ እንደሆነ የአካባቢው ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡
«ፊፊ» የአዊኛ ቋንቋ ሲሆን «ውጣ እንውጣ» እንደማለት ነው፡፡ «ፊፊ» በአሁኑ ወቅት ባህላዊ የትንፋሽ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ አምስት አይነት ዜማዎች እና ሰባት የተለያዩ ድምፆች ያሏቸው መሣሪያዎች አሉት፡፡ ከቅርቀሃ ተክል የሚዘጋጅ ሲሆን ሰባት ወንዶች በጋራ ይጫወቱታል። ሴቶቹ ደግሞ ዙሪያውን እየዞሩ በዕልልታ ያደምቃሉ፡፡
የፊፊ ጨዋታ ከሐምሌ 5 እስከ መስከረም 18 ምሽት እስከ አምስት ስዓት ድረስ ይዘወተራል፡፡ ባህሉን ለትውልድ ለማስተላለፍ የመሣሪያው ተጫዋቾች፣ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች እንዲሁም ባህልና ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ የ «ፊፊ»ን ባህላዊ ጨዋታ ለማሣደግ እና ለማስተዋወቅ ብዙ ባለመሰራቱ ወደፊት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታቅዷል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኘው የጃዊ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤትም በዓሉ በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን በወረዳ ደረጃ እንዲከበርም ወስኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በወረዳው የ «ፊፊ» ባህላዊ የኪነ ጥበብ ቡድንም ተቋቁሟል፡፡
የ«ፊፊ» ባህላዊ መጫወቻዎች ከሽመል ተክል ይሰራሉ፡፡ ጨዋታው በራሱ ቅንጅትና ልምድን ይፈልጋል፡፡ከቁመትና ከውፍረት የተነሳ የድምፅ ልዩነት ይፈጥራሉ፡፡ መሳሪያዎቹ ሰባት አይነት ሲሆኑ የየራሳቸው ስያሜና ሚና አላቸው፡፡ በሰባቱ የትንፋሽ መሣሪያዎች እና በሴቶች ድምፅ ጥምረት አምስት አይነት ዜማዎችን ይፈጥራሉ፡፡
የመጀመሪያው ዜማ «ጊኝ ጊኝ» ይባላል፡፡ ትርጉሙም «ጠላቶች ሲመጡ ሮጠህ ተሰብሰብ» የሚል መልዕክት ነው፡፡ ሁለተኛው ዜማ «አጎተኒ» ይሰኛል፡፡ ትርጓሜውም «አይዞህ በርታ ደርሰንልሃል» ነው፡፡ ሶስተኛው «ወሴ አዴሌ» ይሰኛል፡፡ «ጠላትህን ተከላከል ፣ የአፀፋ መልስ ስጥ» የሚል ፍች አለው፡፡ «ይማንጀ ቲኪሊ» የተሰኘው ደግሞ «በሄድንበት አካባቢ ሁሉ ጥረን ግረን እንስራ» የሚል ሃሳብ አለው፡፡ ጠላትን ድል ካደረጉ በኋላ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ባህላዊ ጨዋታ የአካባቢውን ብሎም የብሔረሰቡን ቱባ ባህል በማስተዋወቅ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
ማስተዋወቅ
አቶ ለይኩን ሲሳይ የአዊ ብሔረሰብ አሰተዳደር ዞን የባህል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ከባህልና ቱሪዝም መሥሪያ ቤት ሶስት ተግባራት መካከል አንዱ የብሔረሰቡን ባህል፣ ታሪኩን ቋንቋውን መጠበቅ፣ ማሳደግና ማጥናት ላይ አትኩሮ የሚሰራበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከ2000ዓ.ም በኋላ የብሔረሰቡን ባህሎችን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ስራ ተሰርቷል። በተለይም ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ስራ በመሰራቱ ከፍተኛ የሚባል ለውጥ መጥቷል። አዊኛ ሙዚቃ በሀገሪቱ ሙዚቃ ላይ እንደ አንድ ስልተምት ሆኖ የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በመሆኑም የብሔረሰቡን ባህል ለማስተዋወቅ ሙዚቃዎችን መስራቱ ዋናው የስኬቱ ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። በአልበም ደረጃ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ተሰርተዋል። ቁጥር ሶስትን ለመስራት በዝግጀት ላይ ናቸው። የሁለቱም ሙዚቃዎች ፕሮዲዩሰር እርሳቸው ናቸው። ሙዚቃዎቹን ሲሰሩ በጥናትና በጥንቃቄ የብሔረሰቡን ባህል ለማስተዋወቅ ጥረት መደረጉን ይናገራሉ፡፡
በአዊ ብሔረሰብ በሙዚቃ ረገድ የባህል አብዮት እየተቀጣጠለ ነው። በክሊፕ ደረጃ ሙዚቃችንን በማስተዋወቅ ደረጃ ተዋጥቶለታል። የመጀመሪያው ሙዚቃ ሲወጣ ሁለት ዓላማ ይዞ ነበር። ቀዳሚው ያልታወቀውን የአዊን ባህል ማስተዋወቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው ታዋቂ ዘፋኞች አዊኛ ዘፈኖችን እንዲዘፍኑ ማስደረግ ነበር። ከውጭ አገር ሳይቀር ብዙ ሙዚቀኞች እየዘፈኑት ነውና ተሳክቶላቸዋል።
በሙዚቃው በኩል የተሳካላቸውን ያህል ሌሎች ባህላዊ ትውፊቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ እንደሚቀራቸው ያምናሉ። የመስቀል፣ የሰርግ፣ የፋሲካን፣ የገና በአላት ባህላዊ ክዋኔዎችን በሚገባ አስተዋውቀዋል። ስለ ባህላዊ ቁሶችም ብዙ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ ስለ ፈረሱ፣ ከቀንድ ስለሚሰሩ ጥበቦች፣ ከቀርከሃ ስለሚሰሩት መገልገያዎች፣ ስለ ጭራ፣ ስለ ባህላዊ አለባበሱ ብዙ እንደሰሩ ቢያምኑም አሁንም ተሳክቶልናል ብለው እንደማይዘናጉ አጫወተውናል።
የተለያዩ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግም የአዊ ባህል ማዕከል ለማሰራት በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ባህላዊ ትውፊቶችን በመጽሐፍ መልክ በመሰነድ ለአጥኚ አካላት እንዲተላለፍ እየተደረገ ነው። በተለይ ወጣቱ ባህሉን እንዲያውቅና በባህሉ እንዲኮራ በማድረግ በኩል ሰፊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ይናገራሉ።
ባህልን ለማስተዋወቅ ሙዚቃ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል፡፡ በመሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ በብሔረሰቡ ባህሎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሙዚቃዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የብሔረሰቡን አለባበሱን፣ የአኗኗር ስርዓቱን፣ የእደ ጥበብ ውጤቶችና ማጊያጊያጫዎችን ለማስተዋወቅ እየተጠቀሙበት ነው።
በተለይም የአዊ ፈረሰኞች ማህበር 78ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት የብሔረሰቡን ትውፊቶች ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል። የፈረሰኞች ማህበር ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ለማድረግም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ከጥረቱ መካከል 20 በላይ ጋዜጠኞችን በመጋበዝ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚገኙ ባህላዊ ክዋኔዎች ማስተዋወቁ አንዱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ለይኩን፤ በክልሉ ካሉ ባህሎች የጎላ ልዩነት ባይኖርም በቋንቋው መለየት ምክንያት የተፈጠሩትን ባህሎች ላይ ትኩረት አድርገው ለማስተዋወቅ እየሰሩ ነው።
የባህል ብረዛ
አቶ ለይኩን በብሔረሰቡ ሙዚቃ ውስጥ በጥናት ላይ ተመስረተው የማይሰሩ ሙዚቃዎች አጋጥሟቸዋል። ሙዚቃው ከሙዚቃዊ ፋይዳው ባለፈ ባህሉን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ቢታመንም ብዙ ጊዜ የባህል ስራዎችን ሲሰሩ ጥንቃቄ ያለማድረግ ክፍተቶች ታይተዋል። ሙዚቀኞቹ ባህሉን ከሚያውቁ መጠየቅ ቢገባቸውም በድፍረት ነው የሚሰሩት።
ስህተቱ ከቋንቋ አጠቃቀም ሊጀምር ይችላል። አንድ ገበያ ላይ የዋለ የአዊኛ ሙዚቃ ቃሉ ሲተረጎም ፀያፍ ሆኖ ተገኝቷል። አገውኛ ብቻ የሚሰማው የህብረተሰብ ክፍል ያንን ሙዚቃ ሲሰማ ያፍራል። ችግሩ የተከሰተው ቋንቋውን ባለማወቃቸው የተነሳ ቃላቱን አስተካክለው ባለመናገራቸው ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ለተናጋሪው ምንም አይነት ትርጉም የሌላቸው ይሆናሉ።
ለምሳሌ ‹‹አጋላይ›› የሚለውን ‹‹አንጋላይ›› ተብሎ ይዘፈናል። «እንች እንካ» የሚለው ዘፈን ደግሞ አገውኛ ዘፈን ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ነገር ግን አማርኛ ቃል ነው የሚጠቀሙት። በአገውኛ ትርጉሙ ከታየ በጣም ፀያፍ ትርጉም ነው የሚኖረው። ስልተ-ምቱን ተጠቅመው በራሳቸው ቋንቋ መዝፈናቸው ችግር አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ቋንቋውን የሚጠቀሙ ከሆነ ለትርጉሙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
ቃላት ላይ፣ ጭፈራው ላይ፣ አለባበስ ላይ ብዙ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ። አንዳንዶቹ ከወላይትኛ ጭፈራ ጋር ተቀላቅለው የቀረቡም አጋጥመዋቸዋል። የትኛው ባህል እንደሆነ የማይለዩ፤ በባህሉ ውስጥ የሌሉ አለባበሶች፣ አጨፋፈሮች ተስተውለዋል።
እንደሚታወቀው ባህልን በማስተዋወቅ ረገድ ፊት መሪው የኪነጥበብ ሰው ነው፡፡ የባህልን መዘወሪያ መሪ የያዘው የኪነጥበብ ሰው ነው፡፡ በዛ ላይ መተዳደሪያውም ጥበብ ነው። በመሆኑም ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ካልተወጣ አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ባህል አንድ ጊዜ ከተበረዘና ከተበላሸ መልሶ ለማስተካከል አስቸጋሪ ይሆናል።
አቶ ለይኩን ማህበረሰቡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስህተት የሆነውን ነገር ስህተት ነው ብሎ መናገር እንዳለበት ያምናሉ። የጥበብ ሰውም ከሚያገኘው ገንዘብ ይልቅ ባህሉን ማክበር ላይ ማተኮር አለበት። ባህል ሲበረዝ የባህሉ ባለቤቶች እየናቋቸው ይመጣሉ። ተቀባይነት ይታጣል፤ ጥቅማቸውም ይቀራል። በመሆኑም የባህል ሙዚቃ ሲሰራ ቦታው ድረስ ሄዶ ባህሉን ማጥናት ይገባል። በድፍረት መሰራት የለበትም። ባህል ባለበት ተወስኖ የሚቀር ጉዳይ ሳይሆን ማደግ እንዳለበት ይታመናል። ይደግ ሲባል ደግሞ መበላሽት የለበትም። ባህል ዘመናዊ አድርገው ሲሰሩ መሰረታዊ የሆነውን ህግ ጥሰው መስራት እንደሌለባቸውም ይመክራሉ።
ባህልን ከብረዛ ለመከላከል
የባህል ብረዛዎችን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ለይኩን፤ «በሙዚቃው በኩል ከእኛ መረጃዎችን አግኝተው ትክክለኛውን መልእክት ለማስተላለፍ ለሚፈልጉ አካላት በራችንን ክፍት አድርገን እናስተናግዳቸዋለን። ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲሰራና በትክክለኛው ባህል ላይ ተመስርተው የሰሩትን በመሸለምና በማበረታታት አስተዋፅኦ አድርገናል።
በተለያዩ ጊዜያት የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ሲምፖዚየሞችን እናደርጋለን። በዚህ ሲምፖዚየም ላይ በብሔረሰቡ ላይ የተሰሩ ስራዎችን እወቅና በመስጠትና በመሸለም እያበረታታን ነው። ምሁራን ጥናት እያደረጉ እያገዙን ነው» በማለት ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ። ይህ ጥረት መልካም ቢሆንም ባሕልን በመበረዝ ስህተት የሚሰሩትን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ስህተቱ በመገናኛ ብዙሃን ተደጋግሞ ሲነገር ትክክል ሊመስል ይችላልና ያለውን ክፍተት ለመድፈን ከብሔረሰቡ ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት ብዙ ይጠበቃል።
የባህል ትዕይንቶች ፋይዳ
በሀገር አቀፍ፣ በክልል ከዛም ወረድ ብለው በዞንና በወረዳ ደረጃ የባህል ትእይንቶች ይዘጋጃሉ፡፡ በዚህም ትክለኛውን ባህል ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡ በተጨማሪም የባህልና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የአዊ ብሔረሰብም በክልሉ በሚዘጋጁ የባህል ትእይንቶች ላይ በመሳተፍ የአካባቢውን ቱባ ባህሎች የማሳየትና የማስተዋወቅ እድል ተፈጥሮለታል፡፡ አቶ ለይኩንም በባህል ትዕይንቶች ላይ የታዘቡትን ይናገራሉ፡፡
ባህልን ለማሳደግና ለማስተዋወቅ የባህል ፌስቲቫሎች ፋይዳቸው ትልቅ ነው። ምክንያቱም ባህሉን ለማስተዋወቅ መድረክ ማግኘት ወሳኝ ነውና። ይሁን እንጂ በውድድር መንፈስ መዘጋጀቱ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ «በመሰረቱ ባህልን ከባህል ማወዳደር አይቻለም። ነገር ግን ሁሉም አካባቢዎች ባህላቸውን በትክክል ማስተዋወቅ ወይም ማቅረብ ችለዋል ወይ? የሚለው ነው መነሳት ያለበት። ባህል ማለት ውዝዋዜው፣ አለባበሱና አጨፋፈሩ ብቻ አይደለም። በመሆኑም የባህል ፌስቲቫል ተብለው የሚያቀርቡት ወጣቶች በፀጉር አቆራረጣቸውና ባለባበሳቸው እንዲሁም በአኗኗ ራቸው መስለው መቅረብ አለባቸው፡፡
ነገር ግን በባህል ትእይንቶች ላይ ያልሆነ ነገር እያየን ነው። ባህሉን ለሚያውቅ ሰው ግራ ያጋባሉ። ብዙ ወጭ ተደርጎባቸው የሚቀርቡ የባህል ፌስቲቫሎች በጥንቃቄ የሚከወኑ አይደሉም። ዓላማው ባህልን ለማስተዋወቅ ተብሎ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ባህሉ ከተበላሸ ለገንዘብ ተብለው በሚዘጋጁ ክሊፖች ላይ ባህል ቢበላሽ ምንም አይገርምም። የሚመለከታቸው አዘጋጆች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል» በማለት ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
አቶ ለይኩን እንዳሉት የባህል ውድድር ሲደረግም ባህሉን የማይወክሉ አለባበሶች፣ የፀጉር አቆራረጦችና አጊያጊያጦች እንዳይካተቱ ትኩረት መደረግ ይኖርበታል። እንደ ውድድር መስፈርት ሆኖ ባህሉን ያልጠበቁ አቀራረቦች ከውድደር ውጭ መደረግ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ስህተታቸው ሊነገራቸውና ሊማሩበት ይገባልና።
የባህል ተወዳዳሪዎቹን ይዘው የሚመጡ ባለሙያዎችም በትርኢቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ትኩረት ማድረግ ያለባቸው በፀጉር አቆራረጣቸውና በአለባበሳቸው ላይም ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ትክክለኛ ብሔረሰቡን የሚወክሉ ሰዎችን ይዘው መቅረብ አለባቸው። የሚወክሉትን ህዝብ ማክበር እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ በርካታ ታሪክ፣ የባህል፣ የጥበብ ሀብቶች አሉት። ይሁን እንጂ ብዙ አልተዋወቁም። በሀብቶቹም የቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው አልተረጋገጠም፡፡ በመሆኑም የተወሰኑ ሁነቶችን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የማስተዋወቂያ ስልቶችን በመጠቀም የተደበቁ የባህል ሀብቶችን ማስተዋወቅ ይገባል። ሰላም!
ዳንኤል ወልደኪዳን
I am constantly impressed by the depth and detail in your posts You have a gift for making complex topics easily understandable