ግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ወደ ኋላ መለስ ብለን በ1960ዎቹ የታተሙትን የአዲስ ዘመን ጋዜጦች በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን ለመዳሰስ ሞክረናል። በወቅቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከተመን በላይ ዋጋ በመጫን ሲሸጡ የነበሩ ነጋዴዎች መቀጣታቸውን የሚነግረን አንድ ዘገባ አሁን ካለው የዋጋ ንረት አኳያ በዚያ ዘመን የነበረውን ለማየት እንዲያስችለን መርጠነዋል፡፡ በአዋሳ እና በአካባቢው አሉባልታ በመንዛት ሁከትና ሽብር ለመፍጠር የሞክሩትን ለመቆጣጠርና የአካባቢ ፀጥታ ለመጠበቅ መወሰኑን እንዲሁም በልማት ረገድም ሕዝብ በመተባበር በጐባ መንገድ ማሠራቱን በሚመለከት የተዘገቡትን ዜናዎች አካተን እንደሚከተለው ለንባብ አቅርበናል፡፡
ዋጋ ያስበለጡ 605 ብር ተቀጡ
ጅማ፤ ዲላ (ኢ/ዜ/አ/) በከፋ ክፍለ ሀገር በሰኮሩና በመሐል ማጂ ወረዳዎች ኗሪ የሆኑ አራት ነጋዴዎች ከዋጋ በላይ ጨምረው ሲሸጡ በመገኘታቸው ተከሰው በጠቅላላው ፮፻፭ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል በ ፲፫ ብር ከ፶ ሳንቲም መሸጥ የሚገባቸውን አንድ ቁምጣ ጨው ከ፳፰ ብር እስከ ፵ ብር ሲሸጡ የተገኙት አቶ ናጂ አሊ ፫፻ ብር ሲቀጡ፤ አቶ መሐመድ ጀማልም ተመሳሳይ ጥፋት በመፈጸማቸው ፪፻፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተበይኖባቸዋል፡፡
አቶ አደም መሸሻና አቶ የሱፍ ትኩዬ የተባሉት ነጋዴዎች፤ በመሐል ማጂ ወረዳ አንድ አሞሌ ጨው ከዋጋው አስበልጠው በ፫ ብር ሲሸጡ በመገኘታቸው ተከሰው አድራጎታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠ፤ እያንዳንዳቸው ፶፭ እንዲከፍሉ ባይከፍሉ ግን በ፴፰ ቀናት እሥራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን የየወረዳው ፍርድ ቤት ዳኞች ገልጠዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሰሎሞን በርሔ የሕዝብ ማመላለሻ ሹፌር ከማዘጋጃ ቤት የሚጠየቀውን ግብር ላለመክፈል ሲል ሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ከተከለከለው ሥፍራ ውጪ ሕዝብ ሲያሳፍርና ሲያወርድ በመገኘቱ ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍል የዲላ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰሞኑን በዋለው ችሎት በይኖበታል።
ተከሳሹ ቅጣቱ የተበየነበት መንገደኞችን ከአዋሳ ከተማ ዲላ ካደረሰ በኋላ ለመነሻና መድረሻ በተከለለው ሥፍራ በማውረድ ፈንታ፤ መንገደኞቹን ባልተለመደበት ቦታ ደብቆ ሲያወርድ፤ ሌሎችንም ሲያሳፍርና ሲያወርድ መገኘቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት ነው፡፡
ሰሎሞን ከአሁን በፊትም ለመኪናዎች መነሻና መድረሻ ከተከለለው ቦታ አላቆምም በማለቱ ተከሶ ፲፭ ብር የተቀጣና ማስጠንቀቂያም ተሰጥቶት እንደነበር ተገልጧል፡፡
ከዚህም ሌላ ዋለልኝ ደሚ የተባለው የከባድ የጭነት መኪና ሹፌር አለደረጃው የ፫ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ይዞ በመገኘቱ ይኸው ፍርድ ቤት የ፶ ብር ቅጣት የበየነበት መሆኑን የደራሳ አውራጃ ፖሊስ ትራፊክ ክፍል ሹም የ ፲ አለቃ ነጋሽ አብዲ ገልጠዋል፡፡
(ግንቦት 10 ቀን 19 68 ዓ.ም ከወጣው
አዲስ ዘመን)
የጀምጀም ከተማ ነዋሪዎች አወናባጅ አድኃሪያንን ለመደምሰስ ወሰኑ
አዋሳ፤ (ኢ.ዜ.አ.) በጀምጀም አውራጃ በክብረ መንግሥት ከተማ የሚገኘው የ፳፫ መ/ቤቶች ተጠሪዎችና ሠራተኞች በከተማው የተቋቋሙት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሊቀመናብርትና የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት ባለፈው እሁድ በአውራጃው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በአደረጉት ጠቅላላ ስብሰባ የተሳሳተ ወሬ በማውራት የሚያወናብዱትን አድኃሪያንን ለመደምሰስ ስምምነት አደረጉ፡፡
በዚሁ የውይይት ስብሰባ ላይ ከተማው የኅብረት ሥራ ማኅበር የጥቃት ጠባቂዎችም ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር ፀጥታውን እንዲጠብቁ ስምምነት መደረጉን አንድ የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ቃል አቀባይ በሰጠው ዜና ገልጧል፡፡
ከዚህም ሌላ ስብሰባው የየቀበሌው ማኅበራት አብዮታችንን ለመቀልበስ የሚሞክሩትን አወናባጆችና አድኃሪያኖችን በየቀበሌያቸው ነቅተው መጠበቅ ያለባቸው መሆኑን አሳስቧል፡፡ የጀምጀም አውራጃ የሚገኘው በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ውስጥ ነው ፡፡
( ግንቦት 10 ቀን 1968 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)
የጐባ ከተማ ነዋሪ መንገድ ሠራ
ጐባ ፤ (አ.ዜ.አ.) በባሌ ጠቅላይ ግዛት የሚገኘው የጐባ ከተማ ኗሪ ሕዝብ በዚሁ ከተማ ባለው የ፬ኛ ክፍለ ጦር መሐንዲስ ሻምበል ጋር በመተባበር በከተማዋ ውስጥ ፲፯ ኪሎ ሜትር የመገናኛ መንገዶች አሠርቶ በአገልግሎት ላይ አዋለ፡፡
በ፳፪ ቀናት የተሠሩት እነዚሁ ፲፯ ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለፈው ሳምንት ክቡር ጃጋማ ኬሎ የባሌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ተዘዋውረው በመጐብኘት ሕዝቡንና የመሐንዲሱን ክፍል አባላት አመስግነዋል፡፡
በሕዝብ መዋጮ የተገነባው መንገድ በነዳጅና የጉልበት ርዳታ የተሠራ ነው፡፡ መንገዱ ከጠቅላይ ግዛቱ ጽሕፈት ቤት እስከ ባማ ገፈርሳ ድረስ ፪ ኪሎ ሜትር ከሥላሴ ቤተክርስቲያን ድልድይ እስከ ቡርቂቁ ት/ቤት ድረስ ፬ ኪሎ ሜትር በቂጣበል ሠፈር የውስጥ ለውስጥ መገናኛ መንገድ ፪ ኪሎ ሜትር፣ከዶሮ ተራ እስከ ሚጫ ት/ቤት ድረስ ፪ ኪሎ ሜትር ከአውቶቡስ ጣቢያ እስከ ጀማሪ ት/ቤት ድረስ ፪ ኪሎ ሜትር፤በነጋዴ ሠፈር አካባቢ የውስጥ ለውስጥ መገናኛ መንገድ ፫ ኪሎ ሜትር መሆኑን የጐባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ አብርሃም ዘለቀ በዚሁ ጊዜ አስታውቀዋል፡፡
በከተማው ሕዝብ በማዘጋጃ ቤቱና በ፬ኛ ክፍለ ጦር የመሐንዲስ ሻምበል ትብብር የተሠራው ይኸው ፲፯ ኪሎ ሜትር የመገናኛ መንገድ ከግራ ቀኙ የውሃ መውረጃ ቦይ ያለው ሲሆን፤ በማከታተል ጠጠር የሚለብስ መሆኑን አቶ አብርሃም ዘለቀ በተጨማሪ አስረድተዋል፡፡
ክቡር እንደራሴው ከዚሁ ጉብኝታቸው ሌላ ማዘጋጃ ቤቱ በከተማው ውስጥ በሚገኙ ዋና ዋና መንገዶችና ግራና ቀኝ ቱቦ ቀብሮ ያሠራቸውን ፲፬ ኪሎ ሜትር መንገዶች በመመልከት የተጓደሉት ተሟልተው እንዲሠሩ መምሪያ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
(የካቲት 27 ቀን 1966 ዓ.ም ከወጣው
አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/ 2015 ዓ.ም