የችግሩ ሰለባ የሆነ ሰው ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ የአካል ጉዳትን የበለጠ ይረዳል። በተለይ ዓይነስውራን ሴቶች እናትነት ከሴትነት ጋር ተዳምሮ የሚጎዱበት ጊዜ ቀላል አይደለም። ፈተናቸው እጅግ ከባድ ነው። ይሄን መሻገሩ ለችግሩ ሰለባዎች ቀላል አይደለም። በአራት ዓመታቸው አንድ ዓይናቸውን የወላጆቻቸው የቤት ሠራተኛ በእንጨት መትታ ያጠፋቻቸውና ሌላውን ዓይናቸውን በኩፍኝ በሽታ ያጡት ወይዘሮ የወይንእሸት በዙ ፈተናውን ከራሳቸው አልፈው ሌሎች ዓይነስውራን እንዲሻገሩት እያገዙ ይገኛሉ። ከራሳቸው አልፈው 17 ዓይነስውራን ሴቶችን በቀን ሦስቴ እንዲመገቡ፤ መጠለያ እንዲያገኙ ማድረግና እየደገፉ ማኖር ችለዋል። የፍኖተ ተሐድሶ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ወይዘሮ የወይንእሸት ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ።
ወይዘሮ የወይንእሸት በዙ የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ሊጋባ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ሲሆን ሲወለዱ ከተማዋ መብራትና ውሃ ባይኖራትም ውብ ነበረች። በበራቸው የምታልፍ ቦይ መሰል ወራጅ ውሃ በመኖሯም በውሃ እየተጫወቱና ቀድተው ቤተሰባቸውን በማገልገል ነው ያደጉት። ከተማዋ ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ነዋሪው ሕዝብ እርስ በእርሱ ይተዋወቃል። ይሄ ሁኔታ ደግሞ አንዱ ዓይናቸው የአራት ዓመት ሕፃን ሳሉ በቤት ሠራተኛቸው ሁለተኛው ደግሞ በኩፍኝ ለጠፋው ለወይዘሮ የወይንእሸት ወላጆች ልጃቸውን ከነዚህ ጉዳቱን የእግዚአብሔር ቁጣ አድርገው ከሚቆጥሩ ነዋሪዎች ደብቀው በቤታቸው ውስጥ እንዲያስ ቀምጡ ምክንያት ሆኗ ል።
በአራት ዓመታቸው ትምህርት ቤት ቢገቡም በኩፍኝ ምክንያት ሁለተኛው ዓይናቸው የጠፋው ወይዘሮ የወይንእሸት በሁለተኛው ዓይናቸው መጥፋት ወላጆቻቸው ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡና ከቤት እንዳይወጡ አደረጓቸው። በቤት ውስጥ ተኝተው እንዲውሉና ከአልጋ ላይ እንዳይወርዱ ያደርጓቸው ነበር። የሚያበሏቸው፤ የሚያጠጧቸው እንዲሁም የሚያፀዳዷቸው ወላጆቻቸው ነበሩ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የአባታቸው እናት አያታቸው በፀና ይታመማሉ። ይሄ አጋጣሚ ለወይዘሮዋ መልካም ነገር ይዞ ነበር የመጣው። አያታቸውን አዲስ አበባ አምጥተው ለማሳከም ከአዲስ አበባ ወደ አርሲ የወይዘሮ የወይንእሸት አክስትና የአክስታቸው ልጅ መጡ። በዚህ አጋጣሚም ዓይናቸው መጥፋቱን ተረዱ። አክስታቸውና የአክስታቸው ልጅ ወይዘሮዋንም ጨምረው ለማሳከም ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው መጡ። ሆኖም ዓይናቸው መዳን ስላልቻለ ሰበታ መርሐ ዕውራን ትምህርት ቤት እንዲገቡ ሆነ። እዚህ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የመማር ሰፊ ዕድል አገኙ። በተለይ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት ወቅት በየበዓላቱና ሊጠይቋቸው በሚሄዱበት አጋጣሚ በሚዘምሩላቸው መዝሙር፤ በትምህርት አቀባበላቸውና በጉብዝናቸው አክስታቸውንና የአክስታቸውን ልጆች እንዲሁም ወላጆቻቸውን በአግራሞት ያስደምሙ ያዙ።
ወይዘሮዋ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንደአጠናቀቁ ፈጥነውም ወደ ሥራው ዓለም ገቡ። እዚህ እየሠሩ በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ማህበር በሴቶች ዘርፍ መመረጣቸው ደግሞ የሴት ዓይነስውራንን ችግር የበለጠ እንዲረዱ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸው። በራሳቸው ከደረሰው ጋር አዳምረው የሴት ዓይነስውራንን ውስብስብ ችግር የበለጠ መፍታት የሚችሉበት ዕድል ማሰብ ጀመሩ። በዚህም ሥራቸውን ለቀው በግላቸው ለመንቀሳቀስና የሴቶቹን ችግር ለመፍታትም እንቅስቃሴዎችን ጀመሩ፡፡
መጋቢት 24 ቀን 1999 ዓ.ም ሥራውን መሥራት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አወጡ። ፈቃዱን ያወጡት አምስት ሰዎች ይዘው ሲሆን ሁለቱ ለረጅም ጊዜ ከዓይነስውራን ጋር የሠሩ ሲሆኑ ሦስቱ ዓይነስውራን ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜም በጎዳና ላይ የሚኖሩና የሚለምኑ ሴት ዓይነስውራንን ሰብስበው ብሬል በማስተማር ወደ ሥራው ገቡ። ለሌሎቹም በኤች አይቪ ኤድስ እንዲሁም በተለያዩ ከአካል ጉዳት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትም ይሰጡ ነበር። ለአብነትም ለሴቶች የስነተዋልዶ ጤና፤ አካል ጉዳትን በፀጋ ተቀብሎ ስለመኖር፤ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ምርታማ መሆን እንደሚቻል፤ ከትዳር በፊት ያለ አባት ልጆች ወልደው እንዳያሳድጉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከሚሰጧቸው ውስጥ ይጠቀሱ እንደነበር ያወሳሉ።
ባህታዊ ገብረመስቀል ጋር ለአንድ ዓመት ያህል በፕሮጀክት አስተባባሪነት የሠሩት ወይዘሮ የወይንእሸት ቢኤስኦ የተባለ ድርጅትና ባህታዊው ሥራውን ለማስኬጃ መጠነኛ ድጋፍ አድርገውላቸዋል። በተለይ ፊላንድ አገር የሚኖር ድርጅት ቀርፀው ባቀረቡለት ፕሮጀክት መሠረት አካል ጉዳተኛ ሴቶችን በተለይም ዓይነስውራንን እንዲያሰለጥኑና እንዲያቋቁሙ ደግፏቸዋል። 40 ጉዳተኞች በተለያየ የራሳቸው ንግድ ዘርፍ ተሰማርተው እንዲቋቋሙ አድርገዋል። ከዓይፓስ ድርጅት ጋር በመሆንም ዓይነስውራን ለመረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ ሠርተዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም እንግሊዝ አገር ከሚኖሩ ሁለት ባልና ሚስቶች ጋር ማታ ማታ ከምሽቱ አምስትና ስድስት ሰዓት ላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እያሰባሰቡ ይመግቡም ነበር ። ‹‹ሁለት ዓይነት ወጥ ከአንድ እንጀራ ጋር በፌስታል እየቋጠርን እንመግባለን›› የሚሉት ወይዘሮዋ ምገባው ከምሽቱ አምስትና ስድሰት ሰዓት የሆነው ቀን ቀን የጉልበት ሠራተኛውም ሆነ ሌላው ሰው ሊቀላቀልና ሊመገብ ስለሚችል ትክክለኛ የጎዳና ነዋሪዎች ለመለየት ጭምር እንደነበረም ያስታውሳሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ የዓይንና ሌሎች የአካል ጉዳት የነበረባቸው ሴቶች ነበሩና እነሱንም ለመለየት አግዟል። የታመሙትን ደግሞ አልጋ ብርድ ልብስ በማሟላት ቤት ተከራይተው ሲንከባከቡና ሲያስታምሙ ቆይተዋል። ከነዚህ መካከል በዘላቂነት ሊደግፉና ሊያቋቁሟቸው የሚችሉ ዓይነስውራን ሴቶችን ሲመርጡ ከርመዋል።
ወይዘሮዋ ትክክለኛ ሴቶችን ለመምረጥ እግረመንገዳቸውን የሚያደርጉት የምገባም ሆነ ግንዛቤ የማስጨበጥ ትምህርትና ሌላ ድጋፍ ውጤታማ አልሆነላቸውም፤ በተለይ አስታመውና ሌሎች ድጋፎችን አድርገው ወደየመጡበት ከሚሸኟቸው መካከል ስኬታማ የሆኑ ቢኖሩም አብዛኞቹ በተለይም ወንዶቹ አርሰው መኖር ስለማይፈልጉ ከስድስት ወር በኋላ ተመልሰው ወደ ጎዳና የሚወጡበት አጋጣሚ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ የተማረሩት ሁለቱ ባልና ሚስት እንግሊዛውያን ድጋፋቸውን አቁመው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ወይዘሮ የወይንእሸትም ብቻቸውን ቀሩ።
‹‹ዓይነስውርነት ከሴትነት ጋር እጅግ ከባድና ፈታኝ ነው። እናትነትም አብሮት መኖሩ ደግሞ ፈተናውን የበለጠ ያከብደዋል›› የሚሉት ወይዘሮ የወይንእሸት ሁለትና ሦስት ልጅ ይዘው በምፅዋት የሚተዳደሩት ዓይነስውራን ሴቶች ሕይወት ላይ ጥናት አደረጉ። ለምንድነው እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ለዓይነስውራን ሕፃናት ድጋፍ የማይደረግላቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። በግላቸው በጀት በተለያየ መንገድ ሲለይዋቸው የነበሩ ዓይነስውር ሕፃናትን ሰብስበው ወደ ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ሥራ ገቡ። ዶሮ ማርባት፤ የሥጋ ዶሮና እንቁላል መሸጥ፤ የባልትና ውጤቶች ሱቅ በመክፈትና በመስራት ገቢያቸው ልጆቹን በመንከባከቡና 10 ሺህ ብር የቤት ኪራይ በመክፈሉ ረገድ የሚያስፈልጋቸውን ገቢ ሸፍኖላቸው ነበር።
ሥራውን የጀመሩት ሰባት ዓይነስውራን ልጃገረዶችን በመቀበል ሲሆን መጠለያን ጨምሮ ሙሉ ወጪያቸውን ይሸፍኑ ነበር። ልጃገረዶቹን ሽሮ ሜዳ በሚገኙት ድል በትግልና እንጦጦ አምባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያስተምሩም ነበር። እዚህ አካባቢ ልጃገረዶቹ ይኖሩበት የነበረው ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ቤት ያፈስ የነበረና ጣውላዎቹም የተሰባበሩ በመሆናቸው ለዓይነስውራን ልጃገረዶቹ አልተመቿቸውም። አከራዮቻቸው የሚኖሩት ከኢትዮጵያ ውጪ ስለነበር በስልክ ቢወተውቷቸውም ሊያድሱላቸው አልቻሉም። በየጊዜው በራሳቸው ወጪም ማደሱ አድክሟቸው ቆይቷል።
ይሄን የሚያዩ የውጭ ዜጎች ነበሩና ለምን ደህና ቤት ተከራይተሸ አትንከባከቢያቸውም አሏቸው። ለዚህ ከመረጡላቸው አካባቢ መካከልም ለትራንስፖርት፤ ለትምህርት ቤት፤ ለሆስፒታል ቅርብ የሆነውንና አራት ኪሎ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጀርባ የሚገኘውን የአሁኑን ቢሮና የልጃገረዶቹን መኖሪያ ነው። ቤቱ አምስት መኝታ ክፍሎችና ስድስት መታጠቢያ ቤቶች ሁለት ምግብ ማብሰያ፤ ሳሎንና ቢሮ ያለው ነው። ለዚህ ቤት በየወሩ 50 ሺህ ብር ይከፍላሉ።
በዚህ ቤት ውስጥ 17 ዓይነስውራን ልጃገረዶችን እያኖሩ፤ እየተንከባከቡና እያስተማሩ ይገኛሉ ወይዘሮ የወይንእሸት። ልጃገረዶቹ የመጡት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲሆን ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ የመጡ ይገኙበታል ። ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 18 ዓመት ይደርሳል። ብሬል የሚማሩትን ጨምሮ ዘንድሮ ለተለያየ የክፍል ደረጃና 12ኛ ክፍል የደረሱላቸውም አሉ።
ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና የምትወስደው ቤተልሄም እሸቱ አንዷ ስትሆን ተወልዳ ያደገችው ጅማ እንደሆነ ትናገራለች ። በሕፃንነቷ ወላጆቿ አዘውትረው ቤተክርስቲያን ይወስዷት ነበር ። ቤተክርስቲያን ውስጥ እየተሯሯጠች ስትጫወት ያም ይሄም የሚስማት ቆንጆና ዓይናማ ልጅ ነበረች። በዚህ መካከል አንዱ ሰርቋት ይሄዳል። ሁለት ዓይኖቿን በማጥፋትም ብዙም ከአካባቢው ሳይርቅ እናቷ ጉሊት ትሸጥበት ከነበረው አካባቢ በስተጀርባው በነበረ አንድ መስጂድ በመውሰድ ያስለምናታል። እናት ልጇን ፈልጋ ስታጣ አእምሮዋ ይነካል። ልጇን በመፈለግም ስትባዝን ውላ ስትባዝን ታድራለች። ልጅቱን የሰረቀው ግለሰብ የገቢ ምንጭ አድርጎ ለብዙ ዓመታት ሲያስለምናት ይቆያል። በሕፃንነቷ ስለወሰዳትና አባቷ ስለሚመስላትም አባዬ እያለች ትጠራዋለች። በዚህ መሃል ትታመማለች። ግለሰቡ ሆስፒታል ሲወስዳት የልጅቱ እናት ጎረቤት የሆነችው ነርስ ልጅቱን ታውቃታለች። «ነገ ይዘሃት ና» ትለውና ቀጠሮ ትሰጠዋለች፡፡ በቀጠሮው ቀን ሲመጣም ፖሊስ ይዛ ትጠብቀዋለች። ግለሰቡ ወደ እስር ቤት ይሸኛል። ነርሷ ልጅቱን ትረከባለች። ወላጆቿ ልጃቸውን ያገኛሉ። ቤተልሄም የአካል ጉዳት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ጉዳትም ደርሶባት ስለነበር ፍዝዝ ትላለች። ወይዘሮዋ እንደነገሩን 24ቱን ሰዓታት ሙዚቃና ሬድዮ በመስማት ነው የም ታሳልፈው።
በዚህ ምክንያት ነው ከጅማ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ፍኖት ተሐድሶ ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር የገባችው። ትምህርቷን ተከታትላ 12ኛ ክፍል መድረስ የቻለችው በስነ ልቦና ሐኪምና በወይዘሮ የወይንእሸት እገዛ መሆኑም ራሷም ትናገራለች።
ሌላዋ ከያቤሎ አካባቢ የመጣችውና በማህበሩ የምትደገፈው ታዳጊ ሕፃን ደፊ አዳሙ ናት ። 10 ዓመቷ ነው። መስማት ብትችልም ማየት፤ መራመድ በራሷ መመገብና መፀዳዳት አትችልም። አባቷ አምጥቶ ለማህበሩ ካስረከባት በኋላ አንድም ቀን ብቅ ብሎ አይቷት አያውቅም። ቆይቶ ቆይቶ ሲደውል ምነው ልጅህ አይደለች እንዴ እንዴት ትጠፋለህ ስለው «ውሰዳት ትይኛለሽ እኔ ወስጄ ምን አደርጋታለሁ አለኝ›› ይላሉ ወይዘሮ የወይንእሸት። በእርግጥ ስትመጣ ትጮህና ታለቅስ ነበር። አሁን ላይ ለቅሶዋን ትታለች። ተረጋግታለችም። በመሆኑም በቅርቡ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ጊቢ የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች መማሪያ ሊያስገቧት ዝግጅት አጠናቀዋል። ትምህርትን በብሬል እያሰለጠኗት ነው። ስልጠናውን እንዳጠናቀቀች ትምህርት ቤት ያስገቧታል።
ወጣት የውብነሽ አድምጠው ማህበሩን የተቀላቀለችው ከጎንደር መጥታ ነው። እንደነገረችን ወደ አዲስ አበባ ያመጣቻት ላስተምራት በማለት አክስቷ ነበረች። ሆኖም ትምህርት ቤት ሳታስገባት ሀብታም ዘመዷ ጋር ታስቀጥራታለች። ደመወዝ ይኑራት አይኑራት የምታውቀው ነገር ባይኖርም በራስ መተማመን እንዳይኖራት አድርገው ለዓመታት ጉልበቷን ሲበዘብዟት ቆዩ። በኋላ ትምህርት ቤት ቢያስገቧትም ጥቁር ሰሌዳው ላይ የሚፃፈውን ማየት አልቻለችም። ብዙ ቦታ ቢሞከርም ዓይኗ አላይ አላት። ምስራች ማዕከል ብሬል እንድትማር አደረጓት።
‹‹እዚህ ስማር ውዬ ስመጣም እንዲሁ ሥራ ይበዛብኛል›› የምትለው ውብነሽ ትንሽ ትንሽ እንደሚታያትና ቀጣሪዎቿ እርጃት ብለው ወደ ወይዘሮ የወይንእሸት ማህበር ያመጧት መሆኑንም ታወሳለች። ወደ ማህበሩ ከገባች በኋላ በትምህርቷም ጎበዝ ሆነች ደፍሮ የመናገር ሐሳቧን የመግለጽ ክህሎት ማዳበር ችላለች። ውብነሽ ትምህርት ቤታቸው ለመኖሪያቸው ቅርብ ቢሆንም ከመኪና አደጋዎችና ከሌሎች መሰናክሎች ለመጠበቅ ማህበሩ በሰርቪስ የሚያደርሳት መሆኑን ገልፃልናለች። የትምህርት ቤት ምገባን ከሌሎች አቅም ከሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ልጆች ጋር አትሻሙም ተብሎ ምሳ ተቋጥሮላቸው ትምህርት ቤት እንደሚሄዱም ትናገራለች። በቂና ተመጣጣኝ ምግብ በቀን ሦስቴ መመገብ መቻሏንም አልሸሸገችን፡፡
ወይዘሮ የወይንእሸት በዚህ መልኩ ለዓይነስውራን ሴቶቹ የሚያደርጉት ድጋፍ ዘላቂ በመሆኑ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ሥራውን በስፋት በማስኬዱ ረገድም የገንዘብ ችግር እየገጠማቸው ነው። ለቤት ኪራይ የሚከፍሉት 50 ሺህ ብር በርካታ ዓይነስውራን ሴቶች መርዳት ይችላል። በመሆኑም መንግሥት አሁን ላይ ቤት በረጅም ጊዜ ሂደት ደግሞ መሬት ሰጥቶ ግንባታ አከናውነው ትኩረት የሚሹ ሴት ዓይነስውራንን መርዳት የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ይጠይቃሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/ 2015 ዓ.ም