ፍሪ ስታይል በዓለም ላይ ቀልብ ከሚስቡ የስፖርት እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው። የፍሪ ስታይል ስፖርታዊ ትእይንት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ቢተገበርም የፉትቦል ፍሪ ስታይል እግር ኳስን በመጠቀም ማራኪ ጥበብ ታክሎበት የሚሰራ ተወዳጅ እንቅስቃሴ ነው። በበርካታ አገራትም እውቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ይህን እንቅስቃሴ ህዝብ በተሰበሰበበት ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል ለእይታ ሲያቀርቡ ማየት የተለመደ ነው። ከዚህ ባለፈም የስፖርቱን እንቅስቃሴ በቋሚነት በመስራት በበርካታ አገሮች ታዋቂና ፕሮፌሽናል ግለሰቦች በርካታ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን ይህን ስፖርት ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ስራዬ ብለው የሚያዘወትሩትና እድገቱም እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ እናገኘዋለን።
በኢትዮጵያ ይህን ተወዳጅ ስፖርት በማዘውተር እውቅና እያገኙ ከመጡ ግለሰቦች መካከል ወጣት ምንተስኖት ነጋሽ (ምንቴ ካርሎስ) ዋነኛው ነው። ስፖርቱን በትልቅ አላማና ራእይ ስራው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ይህ ወጣት የፍሪስታይል ጥበበኛ ከዚህ በፊት የተሳካ ባይሆንም በተለያዩ ክለቦች እግር ኳስን ተጫውቷል። ገና በታዳጊነት እድሜው ወደ ዋና ቡድኖች አድጎ መጫወት ቢችልም ከቡድን ይልቅ ወደ ግል ክህሎት የሚያደላ በመሆኑ በተጫዋችነት ብዙ መግፋት አልቻለም። ብራዚላዊው የኳስ ጥበበኛ ሮናልዲኒሆ ጎቾ ከኳስ ጋር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና በሚያሳየው ጥበብ እየተማረከም ወደ ግል ጥበብ ያደላ ነበር። እግር ኳስ ደግሞ የቡድን ስራ ስለሆነ የእሱ እንቅስቃሴና ከኳስ ጋር ቄንጥ ማብዛቱ በአሰልጣኞች እንደማይወደድ ይናገራል።
“ፍሪስታይል ፉትቦል እግር ኳስ ላይ ጥበብን መጨመር ነው” የሚለው ይህ ወጣት እንቅስቃሴውን ያዩ ሰዎች ከእግር ኳስ ይልቅ ወደ ፍሪ ስታይል ቢገባ እንደሚሻለው በሚሰጡት አስተያየት ከዚያም በፊት ስፖርቱን በቅርበት ስለሚከታተለው ኳስ ገዝቶ ሙሉ በሙሉ ገባበት።
ምንቴ ካርሎስ ወደዚህ ስፖርት ሲገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ስላተለመደ ከሰራሁበት አዋጭ ይሆናል ብሎ በማሰብ እንደነበር ያስታውሳል። እግር ኳስ መጫወት አቁሞ ይሄንን ጥበብ በጎዳናዎች ላይ ማሳየት ሲጀምርም ከተመልካች ጥሩ ምላሽ ይሰጠኝ ነበር። “አድናቆትን እያገኘሁ ስመጣም ሙያውን ከፍ አድርጌ ተንቀሳቃሽ ምስሎች (ቪዲዮዎችን) መስራት ጀመርኩ፣ በዚህም አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ እገኛለሁ” ይላል።
በሌላው ዓለም ይህ ስፖርት ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝና እንደ አንድ ስራ ጥበበኛውን ማኖር የሚችል ነው። በእኛ አገር ግን እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ እንደሚቀረው ምንቴ ይናገራል። በእርግጥ በእኛ አገር ብቻም ሳይሆን እንደ አፍሪካም ስፖርቱ ያለበት ደረጃ ገና ነው፣ ስፖርቱ በፕሮፌሽናል ደረጃ አድጎ ወደ ቢዝነስ የመቀየር እድሉ ግን ሰፊ እንደሆነ ያምናል። “እኔ አሁን በአጭር ጊዜ ወደ ቢዝነስ ቀይሬዋለሁ ማለት እችላለሁ፣ ይሄንን ስፖርት በተመለከተ በተለያዩ ሚዲያዎች ቃለመጠይቅ የሰጠሁትም እኔ ነኝ፣ ጥራት ያላቸው ቪዲዮዎች እየሰራሁ ለማህበረሰቡ እያደረስኩም ነው” የሚለው ምንቴ ይሄ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናል ደረጃውን ጠብቆ እንዲያድግ ትልቅ ፍላጎት አለው። ይህን እንቅስቃሴ ከሚሰሩ ካንዳንድ ልጆችም ጋርም በጋራ በመስራት ሙያውን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ውድድሮችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያስረዳል። ውድድሮች ካሉ ስፖርቱን ወደ ቢዝነስ መቀየር እንደሚቻልም ያምናል።
እንደ ወጣቱ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ስፖርት የሚያዘወትሩ ግለሰቦች በዓለም ፍሪስታይል ፌዴሬሽን እውቅና እንዲያገኙ በአገራችን አቻ ፌዴሬሽን ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ አገርን ወክለው በዓለም መድረኮች የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ማፍራ ይቻላል። ከስር የሚሰለጥኑ ስፖርተኞችም ያንን አላማ አድርገው ለመስራት ይነሳሳሉ። እንዲህ አይነት እድሎች ሲገኙ ወደ ገበያው የመግባት አጋጣሚውም ይሰፋል፣ እይታዎችም ይጨምራሉ። ይህ እድል ባለመኖሩ ግን ከዚህ በፊት በዚህ ስፖርት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሙያውን በትርፍ ሰዓታቸው ለመስራት ይገደዱ እንደነበር ያስታውሳል። “እኔ የሙሉ ሰዓት ስራዬ ይሄ ነው፣ ሙያውን ከፍ አድርጌ በተለያዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለመምጣት ጥረት እያደረኩ ነው፣ በስፖርቱ ተሰጥኦ ያላቸው ልጆችን አሰልጥኖ የማውጣት ሃሳብም አለኝ፣ ነገር ግን ልጆቹን አሰልጥኜ አንድ የሚያርፉበት አላማና ግብ ከሌለ ቤተሰብም ፍቃደኛ አይሆንም” ይላል። ስፖርቱ ብዙ ቦታ አይፈልግም በየትኛውም ቦታ ላይ ሊሰራ ይችላል። አንዱ ችግር አንድ ልጅ ቢያንስ መለማመጃ አንድ ኳስ የሚያስፈልገው መሆኑ ነው። በእኛ አገር ደግሞ ያለው የኳስ እጥረት ይታወቃል። እንደ አማራጭ ግን ወጣቱ ጥበበኛ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ፍላጎት ላለው ሁሉ በያለበት አጫጭር ስልጠናዎችን የመስጠት ሃሳብ አለው።
እንደ አገር ፌዴሬሽን ለመመስረት በቅድሚያ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው መድረኮች ሊኖሩ እንደሚገባ የሚጠቁመው ምንቴ፣ ለዚህ ብዙ ሂደቶችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።
“በአገራችን አሁን ላይ በዚህ ስፖርት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማሰባሰብ አንዱ ፈተና ነው፣ የት እንዳሉ አይታወቅም” የሚለው ይህ ወጣት፣ ስፖርቱ በጣም ተወዳጅ እንደመሆኑ በደንብ ቢሰራበት ማደግ እንደሚችል እምነት አለው።
ይህ ስፖርት ከእግር ኳስ በተለየ አንድ ሰው አገርን ወክሎ በአለም ዓቀፍ መድረኮች መሳተፍ የሚቻልበት ቢሆንም እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ ያስረዳል። “በዚህ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ የራሴን አሻራ ማሳረፍ እፈልጋለሁ” የሚለው ምንቴ አርቆ በማሰብ በትልቅ አላማና ራእይ ጥረቱን ቀጥሏል። በዚህ ስፖርት ተሰጥኦው ያላቸው ታዳጊዎችን በማፍራት አገርን እንዲወክሉ በሚያደርገው ጥረት የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ከቁሳቁስ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉለት ይጠይቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም