ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በተለይም በአዲስ አበባ በድምቀት እየተከበረ የሚገኘው የኢሬቻ በአል የፋሽን አልባሳት ዲዛይነሮችን ቀልብ በስፋት እየሳበ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዚህም ባለፉት በርካታ ዓመታት ተዘውትረው ሲለበሱ ከማይታዩ በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አልባሳት መካከል ውስጥ አንዱ የነበረው የኦሮሞ ባህል አልባሳት የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንደስትሪ በስፋት እንዲቀላቀሉ አድርጓል። የአገሪቱ የፋሽን ኢንዱስትሪ አልባሳቱን በተለያየ ስልት ሸምነው በማቅረብ በርካቶች እንደየ ፍላጎቶቻቸውና እንደምርጫቸው በተለይም በኢሬቻ በአል ወቅት እንዲደምቁበት አስችለዋል።
ይህ አዲስ የኦሮሞ ባህል አልባሳት የፋሽን አብዮት ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተስተዋለ ቢገኝም ከሳምንት በፊት በተከበረው የኢሬቻ በአል ላይ ግን በስፋት ታይቷል። በዚሁ ክብረ በዓል ላይ በእነዚህ ባሕል አልባሳት ተውበው የሚታዩ የተለያዩ ግለሰቦች ቁጥርም በርክቶ ተስተውሏል። ለዚህም የተለያዩ የፋሽን ዲዛይነሮች ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ማስተዋል ይቻላል።
ቀይ፣ ጥቁርና ነጭ ቀለማት ያላቸው የኦሮሞ ባህል አልባሳት ወትሮም የነበሩ ናቸው። አዲሱ ነገር እነዚህን ሶስት ቀለማት በአንድ ላይ በህብር አድርጎ በዘመናዊ መልክ ውብና ምቹ ሆነው በተለያዩ ዲዛይኖች እንዲቀርቡ መደረጉ ነው።
የ27 ዓመቷ ዲዛይነር ሴናክቤኪ ግርማ በኦሮሞ ባህል አልባሳት ላይ ያየችውን ለውጥ “ማይታመን” ስትል ለቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ በሰጠችው ቃለምልልስ የሰሞኑን የፋሽን አብዮት ትገልፀዋለች። “ሰዎች የበለጠ በማንነታቸው እየኮሩ መምጣት ጀምረዋል’’ የምትለው ወጣት ዲዛይነር እነዚህ የባህል አልባሳትም ከበዓል ቀናት ውጪ ሰርክ የሚለበሱ እንዲሆኑ ምኞቷ ተናግራለች።
በየዓመቱ በአሉ ከሚከበርባቸው ቀናት ቀደም ብሎ “የኢሬቻ ፋሽን ትርኢት እና የባህል ፌስቲቫል” እንዲሁም የሞዴሊንግ ውድድሮች በአዲስ አበባ፣ አዳማና ሌሎች ከተሞች መካሄዳቸው ዲዛይነሮች የበለጠ እንዲነቃቁና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ይዘው ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ምክንያት ሆኗል። ይህም በፋሽን ገበያው ትስስር ለብዙዎች ትልቅ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ኢሬቻ ለፋሽን ኢንዱስትሪው እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ እንደሆነ ተነግሮለታል።
አልባሳቱን በማዘመን ረገድ ትልቅ ድርሻ ከነበራቸው ዲዛይነሮች የኬቲ ፋሽን ባለቤት አቶ ዘሩ ዓለማየሁ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ፣ “ኢሬቻ በአልባሳት ሽያጭ እና ዲዛይን ሥራ ላይ የሚታይ ለውጥ ስለማምጣቱ” ይጠቁማሉ። “በበዓሉ ዕለት ደምቀው ለመታየት የሚሆኗቸውን አልባሳት የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በማሻቀቡም ትዕዛዝ መቀበል አቁመናል” ሲሉ በዚህ ፋሽን ላይ ያለውን ሰፊ የገበያ ፍላጎት ያብራራሉ።
የፋሽኑ መስፋፋት የኦሮሞን ባህል ከማስተዋወቅ ያለፈ ጥቅም እንዳለው ብዙዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሃሳብ ሲለዋወጡ ነበር። በርካታ ድረ ገጾችና ማህበራዊ ሚዲያዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው የተለያዩ ዘገባዎችን አሁንም ድረስ እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ የፋሽን አብዮት በእርግጥም ባህልን ከማስተዋወቅ ባሻገር ወጣቶች ባህላቸውን እንዲወዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ለማንም ግልጽ ነው። የበዓሉ ሕዝባዊነት ወደሌሎች አካባቢዎችም ተስፋፍቶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያከ ብረው እንዲሆንም የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም። ለዚህም የፋሽኖቹ ውበትና ሳቢነት ከኦሮሞ ማህበረሰብ ባለፈ የሌሎች ብሔረሰቦችንም ቀልብ እየሳበ እንደመጣ መታዘብ ይቻላል። ወደ ፊትም የዲዛይነሮች ትጋትና አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ታክሎበት በአፍሪካ ብሎም በሌሎች አለማት ሰፊ ተቀባይነት የሚያገኝበት እድል እንዳለው መናገር አይከብድም።
ይህ የፋሽን አብዮት በብዙ መልኩ ያለውን ጥቅም ያህል የራሱ ጉዳት እንዳለውም ስጋታቸውን የሚገልጹ አልጠፉም። ይህም ስጋት ባህላዊ አልባሳት በአዳዲስ ዲዛይኖች በዘፈቀደ እንዲዘምኑና የቀደመ ይዘታቸውን እንዲለውጡ ከመደረጋቸው ጋር የተያያዘ ነው። በባህል ተሟጋቾች ዘንድ እንዲህ አይነት የፋሽን አብዮቶች የልዩ ልዩ ባህሎችን (አካባቢዎችን) አለባበስ መቀላቀል፣ በሽመና ወቅት የቀለም ድርድሮችን ወይም መስመሮችን ማዛባት፣ የጥራት ደረጃን ማሳነስ ወይም ከባህሉ ውጭ ያሉ ጨርቆችን መጠቀም፣ በአጊያጊያጥ ወይም አለባበስ ላይ ያለውን ባህላዊ ስርአት ሊያፋልሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።
በኦሮሞ ባህል ውስጥ የባሌ፣ የአርሲ፣ የቦረና፣ የጉጂ፣ የሐረርጌና የጅማ አካባቢዎች የተለያዩ የአልባሳት አይነቶች የራሳቸው መገለጫ ያላቸው አለባበሶች ሲዘምኑ የቀደመ ታሪካቸውን ባልለቀቀ መልኩ መሆን እንዳለበት ሁሉንም ያስማማል። ይህም የአንዱን አካባቢ አለባበስ ከሌላው ጋር በመደበላለቅ የባህል መዘበራረቅ እንዳይኖር በማሰብ የሚሰነዘር አስተያየት ነው።
ይህንን ስጋት ለማስቀረትም ወጣቶችን እና ዲዛይነሮችን ባህልና ወጉን ጠንቅቆ በማስተማር ፋሽኑን በአዳዲስ ጥበብ አዘምኖ ማሳደግ እንደሚቻል ይታመናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም