በሩጫው ዓለም አሸናፊነትን መታወቂያቸው ካደረጉ ብርቱ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። በጎዳና ላይ ሩጫዎች በተለየ የምትታወቀው ኮከብ አትሌት በቀጣይ የማራቶን ውድድሮች የበላይነትን የመቀዳጀት እድሏ ሰፊ ስለመሆኑ የቀደመው ስኬቷ አመላካች ነው። በወጣትነቷ በበርካታ ስኬቶች መታጀቧም ጠንካራ አትሌት መሆኗን ያሳያል። በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ በብዙ ተስፋ የተጣለባት ይህቺ ወጣት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ትባላለች። ባለፈው እሁድ የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ አትሌት የስፖርት ሕይወት በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ተዳሷል።
ያለምዘርፍ በ1992 ዓ.ም በጎጃም ፍኖተሰላም የተወለደች ሲሆን፤ በ12 ዓመቷ ሩጫን እንደጀመረች መረጃዎች ያመላክታሉ። እንደ አብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ አገራት አትሌቶች ሩጫን በ5ሺ እና 10ሺ ሜትሮች በመጀመሪያም በሂደት የጎዳና ላይ ሩጫዎችን ለመቀላቀል ችላለች። በዚህም በተለይ የታወቀችበትና ዝናን ያተረፈችበት ርቀትም የግማሽ ማራቶን ውድድር ነው። በዚህ ርቀት ከአትሌቲክስ ቤተሰቡ ጋር ይበልጥ የተዋወቀችውም እአአ በ2019 በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አገሯን ወክላ በተካፈለችበት የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ነበር። በወቅቱም የውድድሩ ክብረወሰን የሆነ ሰዓት (1:10:26) በማስመዝገብ ጭምር ድርብ ክብርን ለማግኘት ችላለች።
በዚያው ዓመት ደግሞ በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ላይ የውድድሩን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ስኬቷን ለማጣጣም በቅታለች። ከአገር ውስጥ ውድድር ባለፈ ዓለም አቀፍ ተሳትፎዎችን በማድረግም በህንድ (ዴልሂ) እና በቻይና (ዚመን) ግማሽ ማራቶን የብር እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ከመነሻው በርቀቱ ያላትን ብቃት ማስመስከር ችላለች። በቀጣዩ ዓመት በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና አገሯን ወክላ የተሳተፈችው ያለምዘርፍ በግሏ የነሃስ በቡድን ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ነበር ያገኘችው። በግሏ ባካሄደቻቸው ውድድሮችም ውጤታማ ከመሆን ወደኋላ አላለችም። የዴልሂ ግማሽ ማራቶን በድጋሚ የሮጠችው ያለምዘርፍ አሸናፊ የሆነችው ቀድሞ ከገባችበት ሰዓት በሁለት ደቂቃ ማሻሻል ችላለች። በስፔን የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫም በተመሳሳይ አሸናፊ ሆናለች።
ለስኬታማዋ አትሌት እአአ 2021 እንደተለመደው ድሏን ያጣጣመችበት ዓመት ነበር። በቱርክ ግማሽ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ በአየርላንድ የአንትሪም ኮስት ግማሽ ማራቶንም በተመሳሳይ ባለድል ለመሆን ችላለች። ይሁንና ይህ ውድድር ሁለት ተቃራኒ ስሜቶችን ያስተናገደ በመሆን በይበልጥ ይታወሳል። ይኸውም ርቀቱን የሸፈነችበት 1ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ44ማይክሮ ሰከንድ የሆነ ሰዓት የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ሆኖ መቆየት የቻለው ለጥቂት ጊዜ ብቻ በመሆኑ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በውድድሩ ላይ በድጋሚ በተደረገው ማጣራት የውድድሩ አዘጋጆች ርቀቱን በለኩበት ወቅት በፈጸሙት ስህተት ፈጣኑ ሰዓት እንደማይመዘገብ ይፋ በመሆኑ ነው። በዚህ ሁኔታ ተስፋ ያልቆረጠችው ታታሪዋ አትሌትም በቫሌንሺያ በተካሄደ ሌላ ውድድር ተካፍላ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ለመፈጸም ችላለች።
የተያዘው የፈረንጆቹ ዓመትም ለያለምዘርፍ የስኬት ዓመት ሲሆን፤ ከግማሽ ማራቶን ሯጭነት ወደ ማራቶን የተዘዋወረችበት መሆኑም ሌላኛው የስኬቷ ማሳያ ነው። አትሌቷ የዓመቱን ስኬት ማጣጣም የጀመረችው በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ላይ ነበር። በድጋሚ በስፔን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይም 24 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ ከ14 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመሮጧ የዓለም ክብረወሰኑን ከእጇ ማስገባት ችላለች። ቀጣዩ ውድድሯም ቀድሞ የማትታወቅበት የማራቶን ሩጫ ነበር። በጀርመን የሃምቡርግ ከተማ በተካሄደው ማራቶን ላይም አሸናፊ የሆነችበት 2:17:23 ሰዓት የግሏ እና የውድድሩ ፈጣን በሚል ሊመዘገብላት ችሏል። ይኸውም እአአ በ2016 በአገሯ ልጅ መሰለች መልካሙ ተይዞ ከነበረው ሰዓት ደቂቃዎችን የፈጠነ በመሆኑ የቦታው የክብረወሰን ባለቤት ሊያደርጋት ችሏል።
ሁለተኛው የማራቶን ሩጫዋን ደግሞ ባለፈው ሳምንት ለንደን ላይ ነበር ያካሄደችው። የፕላቲኒየም ደረጃ ካላቸው ጥቂት ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የለንደን ማራቶን ያለምዘርፍ፤ ቀዝቃዛውን አየር ተቋቁማ ከመሮጧ ባለፈ ከተፎካካሪዎቿ ጋር በነበረ ትግል ወድቃ በመነሳት ነበር አሸናፊ ለመሆን የቻለችው። ይህም አስደናቂ ውጤት ሲሆን፤ የለንደን ማራቶንን ያሸነፈች ወጣቷ አትሌት አድርጓታል።
ያለምዘርፍ ታዋቂና ስመጥር አትሌቶችን ባቀፈው የ‹‹ኢኤንኤን ራኒንግ ቲም›› አባልና ከፍተኛ አቅም ካላቸው ሴት አትሌቶቹ መካከል አንዷ ናት። በአሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ የምትሰለጥነው አትሌቷ በግማሽ ማራቶን ከ10 ጊዜያት በላይ በመሮጥና በማሸነፍ በርቀቱ ያላትን ብቃት አስመስክራለች። በቅርቡ በተቀላቀለችው ማራቶንም በተመሳሳይ አዲስ የውጤታማነት በር የተከፈተላት መሆኑን ከመነሻው አንስቶ እያሳየች ትገኛለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015