ኢትዮጵያ በዘመናዊ ስልጣኔ ወደፊት ትራመድ ዘንድ ብዙ የሰሩ፤ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በስልጣን የቆዩት ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንግስት ዘውዲቱ በስልጣን እያሉ ከአልጋ ወራሽነታቸው በተጨማሪ የንጉስነት ስልጣን የተቀዳጁት በዚሁ ሳምንት መስከረም 24 ቀን 1921 ዓ.ም ነበር። እኛም የንጉስነት አክሊል የደፉበትን ታሪካዊ እለት በማስመልከት ስለ ንጉሱ ጥቂት ማለትን ፈለግን።
በብዙዎች ከ1923 እስከ 1966 ያለውን ጊዜ አስልተው የአፄ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን ይበሉት እንጂ አፄ ኃይለስላሴ እራሳቸው ባዘጋጁት 1923 ዓ.ም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት ላይ “ንጉሰ ነገስት” ብለው ከመሰየማቸው ቀደም ብሎም እርሳቸው የአገሪቱን ሲመሩ ቆይተዋል። በተለይ ንግስት ዘውዲቱ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው አመታትም ከንግስቲቱ ያልተናነሰ ስልጣንና ቤተ መንግስት ውስጥ ከሁሉም የተሻለ ተሰሚነት እንደነበራቸው ይነገራል።
ውልደት
እናት ወይዘሮ የሺእመቤት አሊ ከ6 በላይ ልጆች ቢወልዱም አንዱም ለፍሬ ሳይበቃ ሁሉም ሞቶባቸው በሀዘን አመታት አሳልፈዋል። ለ7ኛ ጊዜ የወለዱት ልጃቸው ሌሎች ልጆቻቸው የገጠማቸውን እንዳይገጥመው ሰጉ። አዲስ የሚወለደው ልጅ ትልቅ ተስፋ እንዲሆናቸው አጥብቀው ተመኙ፤ አምላካቸውንም ተማፀኑ። እናት ልጃቸውን በስስትና በስጋት አምጠው ወለዱት።
ይህ ለቤተሰቡ ሰባተኛ ሆኖ የተወለደው ህፃን ልጅ ተፈሪ ነበር። በኋላ ላይ ለፍሬ እንዲበቃ የጸለዩት ለወግ ማዕረግ እንዲበቃላቸው እጅጉን የጓጉት እናት የልጃቸው ሁኔታ ለማየት ባይታደሉም ልጅ ተፈሪ ግን ታላቋ አገር ኢትዮጵያ ላይ ነግሶ ለዘመናት ቆይቷል።
ውልደታቸው ከሐረር 30 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ያለ አካባቢ ኤጀርሳ ጎሮ ነው። ወቅቱ ደግሞ ክረምት ዝናብ የሚበረታበት ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም ነበር። በሰባተኛ ወር የተወለዱት ልጅ ተፈሪ ከእናታቸው የተለዩ ገና በጨቅላነታቸው ነበር።
በወቅቱ በተደጋጋሚ ልጅ የሚሞትባቸው የልጅ ተፈሪ እናት አዲስ የተወለደው ልጅ እንዳይሞትባቸው በአካባቢው ልማድ መሰረት ከወላጆቹ ተነጥሎ ዘመድ ቤት እንዲሆን ተወስኖ ከእናቱ መነጠል ግድ ሆነ። በዚህም ዘመድ ጋር እንዲያድጉ ሆነ። እዚያም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማሩ።
የቀድሞ መጠሪያ ስማቸው ልጅ ተፈሪ በኋላም ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ በአባታቸው ብርቱ ጥበቃ ዘመድ ቤት በምቾት አደጉ። አባታቸው ራስ መኮንን የአፄ ምኒልክ የአክስት ልጅ ናቸው። ልጅ ተፈሪ ከአጎታቸው ደጃዝማች ብሩ ኃይለማሪያም ጋር ነበር ያደጉት። የ10 ዓመት ልጅ ሳሉ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአፄ ምኒልክ ጋር ተዋወቀው ወደ ሐረር ተመልሰዋል።
አባታቸው ራስ መኮንን “ተከታዩ ልጄ ራስ ተፈሪ ነው” በማለት ለህዝብ አወጁ። ልጅ ተፈሪ በ14 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ አገኙ። ከቆይታ በኋላ መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ራስ መኮንን ሞቱ። በዚህ ጊዜ አፄ ምኒልክ ወደ አዲስ አባባ አስመጥተዋቸው ደጃዝማችነቱን አፅንተው የሰላሌ ግዛት እንዲያስተዳድሩ ልጅ ተፈሪን ሾሟቸው።
ልጅ ተፈሪ ለግዛቱ እንደራሴ ተወክለው ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው ቀጠሉ። በኋላም ደጃዝማች ተፈሪ የባሶ በጌ ቀጥሎም ሲዳሞን አስተዳደሩ። መልሰው ወደ አባታቸው ግዛት ወደ ሐረርጌ በማቅናት እዚያ ማስተዳደር ጀመሩ። 1903 ዓ.ም ወይዘሮ መነንን አገቡ። ከምኒልክ ሞት በኋላ የነገሰው ልጅ እያሱ 1907 ደጃዝማች ተፈሪን ከሐረርጌ ግዛት ሽረው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አደረጉ። በ1909 ልጅ እያሱ ከስልጣን ወርደው ንግስት ዘውዲቱ ሲነግሱ ደጃዝማች ተፈሪ ‹‹ራስ›› በመሰኘት አልጋ ወራሽ በመሆን ተሾሙ።
በቤተ መንግስት ቆይታቸው የተለያዩ መንግስታዊ ስራዎችን በማቀድና በመምራት ስልጣናቸውን አጠናከሩ። እንዲሁም ንግስት ዘውዲቱ በስልጣን በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ጉዳዮች ላይ በመወሰንና በማስተዳደር ተሰሚነታቸውን ከፍ አደረጉ።
ንግስት ዘውዲቱ ካረፉ በኋላ ስልጣን በመረከብ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን በንጉሥነት መርተዋል። በዚህም ኢትዮጵያን በተለያየ መስክ ከውጭው ዓለም ጋር በማገናኘት እንዲሁም በአገሪቱ ስልጣኔ እንዲስፋፋና አዳዲስ አሰራሮች እንዲተገበሩ በማድረግ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ታላቅ አሻራን ትተዋል።
አፄ ኃይለስላሴ እስከ 1966 ድረስ ስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በምትካቸው የጊዜያዊ ወታደራዊ ምክር ቤት (ደርግ) ስልጣን ይዞ ወታደራዊ አመራር ተመሰረተ። በደርግ የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይ 59 ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ምሁራን፣ ሚኒስትሮች፣ ጀነራሎችና ንጉሳዊ ቤተሰቦች፣
ሲገደሉ ንጉሱም በ1967 ዓ.ም በቤተ መንግስት ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የንጉስ ኃይለስላሴን አሟሟት በተመለከተ የተለያዩ የታሪክ ምሁራን እና ፖለቲከኞች የየራሳቸውን ግምታዊ ሀሳብ ከመስጠት ውጭ እስካሁን በትክክል እንዲህ ነው የሚል ማስረጃ የለም።
ንጉሱ መስከረም ሁለት ቀን 1966 ዓ.ም ደርግ ከቤተመንግስታቸው እንዲወጡ በጠየቀበት እለት ከቤተመንግስት እንዲለቁ ሲጠየቁ የተናገሩ ታሪካዊ ንግግር በብዙዎች ይታወሳል። እኛም በዚሁ ታሪካዊ ንግግር የዛሬው ታሪካዊ ትውስታችን ቋጨን።
“ያነበባችሁትን ሰምተናል፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም። ቢሆንም በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ደግሞ ላገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት … የኢትዮጵያን ታሪክ ጠብቃችሁ ማልማት ከቻላችሁ የእኛ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃል፤ ካልቻላችሁ የእናንተ ታሪክ ያበቃና የእኛ ይቀጥላል፤ አገራችንንና ሕዝባችንን በምንችለው አገልግለናል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እድል የእኛን መወገድ የሚጠይቅ ከሆነ ሥራችንን አቁመን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ‹አሁን ተራው የእኛ ነው› ካላችሁ ኢትዮጵያን ጠብቁ ”
“የኢትዮጵያ ታሪክ” ከተክለ ፃዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1947 -1983” ባህሩ ዘውዴ የተሰኙ የታሪክ መጽሐፍትና የተለያዩ ድረ ገፆችን በዋቢነት ተጠቅመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015