የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፤ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተቻችለውና ተከባብረው፣ ባህላቸውንና ማንነታቸውን ጠብቀው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ምድረ ቀደምት፣ የስልጣኔ መነሻ፣ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ሃይማኖቶች የሚገኙባት መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ የህዝቦችን አንድነትና አብሮ የመኖር ጥበብ ማግኘት እንችላለን። ያልተበረዘና ያልተከለሰ ንፁህ ማንነት፣ ቱባ ባህል፣ በደስታና በሃዘን አብሮ መቆም፣ መረዳዳትና ተካፍሎ መብላት ሌላው የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። ከዓመት ዓመት በህዝብ ተናፍቀው የሚጠበቁትና ሁሌም በድምቀት የሚከበሩት ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም ጭምር እንድትታወቅ አድርጓታል።
እነዚህ በዓላት የተለያዩ ማንነቶች፣ ብዝሃነትን የሚያስተናግዱና የየራሳቸው መገለጫ ያላቸው ናቸው። የአዲሱን አመት ሁለተኛ ወር ለመያዝ የአንድ ቀን እድሜ በቀረው መስከረም ወር ብቻ እንኳን መላው ኢትዮጵያውያን የሚደምቁበት ከቀሪው የዓለም ክፍል የሚመጡ ጎብኚዎችም ሳይቀሩ በአገራችን የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ የቱሪዝም ሃብቶች የሚደነቁበትና ሀሴት የሚያደርጉበት ነው።
ለአብነትም መስከረም 1 የዘመን መለወጫ፣ የወላይታ ህዝብ ክብረ በዓል ጊፋታ፣ በዓለም የቱሪዝም ሃብትና ቅርስነት የተመዘገቡት የመስቀል በዓልና የኢሬቻ የምስጋና ቀን ኢትዮጵያን የሚያደምቁና ቀሪውን ዓለም ከሚያስደምሙ አያሌ ክብረ በዓላትና የቱሪዝም ሃብቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚነህ በተጨማሪ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትናንት በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ያለፈው 1497ተኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) ሌላኛው የወሩ ተወዳጅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓትን መጥቀስ ይቻላል።
በሃይማኖቱ አስተምሮት አንዱ መንዙማ እንደሆነ ይታወቃል። ከሃይማኖት አለፍ ሲልም ከሃይማኖት የሚቀዳ ባህላዊ ስርዓትን የሚያንፀባርቀው መንዙማ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። በተለይ መንዙማ ትናንት ተከብሮ ባለፈው የመውሊድ በዓል ላይ ልዩ ድምቀትን የሚሰጥ ዜማ ነው። የፎክሎር ባለሙያው ዶክተር መሀመድ ዓሊ እንደሚናገሩት፣ መውሊድን ለሚያከብሩ ሰዎች ነብዩ
ሙሐመድ ለተወለዱበት ወር የተለየ ክብር አላቸው። ይህ ወር ‹‹ረቢእ›› ተብሎ ይጠራል። ወሩ ነብዩ የተወለዱበት፣ ከፈጣሪ ወህይ መቀበል የጀመሩበት፣ ተልዕኳቸውን አድርሰው፣ ለሕዝባቸው አደራ ሰጥተው ያለፉበት ነው። እናም በመንዙማ ወሩን የነብዩ ሙሐመድ ማወደሻ፣ ማስታወሻ አድርገው እንደሚከተለው ይገልጹበታል።
የአከባበር ስነስርዓት
በኢትዮጵያ የመውሊድ በዓል አከባበር ከአካባቢው የሙስሊም አገሮች በተለይም ከሱዳን፣ ከግብፅ፣ ከሶማሊያና ከጅቡቲ ጋር በአብዛኛው ይመሳሰላል። በእስላማዊ ቅርሶችና ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው ተሾመ ብርሃኑ ከማል በኢትዮጵያ የመውሊድ የአከባበር ስርዓትን አስመልክተው የሚከተለውን ሃሳብ አጋርተውናል።
ኢትዮጵያ የነብዩ ሙሐመድ ልደት ቀን ከሚከበርባቸው ስፍራዎች መካከል በትግራይ ነጋሺና በሆጂራ ፎቂሳ (ራያ)፣ ሰሜን ወሎ ዳና፣ በደቡብ ወሎ በጃማ ንጉሥ፣ በባሌ በድሬ ሸኽ ኹሼን በሚከበርበት ጊዜ ከስፍራው ተገኝቶ የመመልከት ዕድል ገጥሟቸዋል። እርሳቸው እንዳሉት ከአገሪቱ አራት አቅጣጫዎች የሚመጡ ሙስሊሞች በመስጊዶች ዙሪያ መሰባሰብ የሚጀምሩት በዓሉ አንድ ሳምንት ሲቀረው ነው። በዕለቱም የእንስሳት እርድ ይከናወናል።በሥፍራው የተሰባሰቡ የበዓሉ ታዳሚዎች እንዳይቸገሩ ውሃና የማገዶ እንጨት ይዘጋጃል። የበዓሉ ታዳሚዎችም ቢሆኑ በዓሉን ወደሚያከብሩበት ሥፍራ ሲሄዱ አቋርጠው ከሚያልፏቸው ወንዞች በእቃ ውሃ ቀድተው፣ ከደን ደግሞ ለማገዶ ደረቅ
እንጨት ለቅመው ይዘው የመሄድ ልማድ አዳብረዋል። ለበዓሉ ማድመቂያም ድቤ ስለሚመታ ድቤው ጥሩ ድምጽ እንዲያወጣ በፀሐይ ብርሃን በደንብ ሲመታ ይሰነብታል። ወይንም ሙቀት እንዲያገኝ ይደረጋል። በዚህ መልኩ ከተዘጋጀ ድቤው ከብረት እንደተሠራ ብረት ወይም የብረት ድምፅ ያለው በሃ ድንጋይ «ኪው፣ ኪው» የሚል ድምፅ እንዲያወጣ ያስችላል።
በመስጊዱ ወይም በመስጊዱ ዙርያ የሚቀመጡት የታወቁ የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮቻቸው ናቸው። ምርጥ ጫት እስከሚያምር ዛላው ይታደላቸዋል። በዚህ ወቅትም ፈጣሪንና ነብዩ ሙሐመድን የሚያወድሱ ዜማዎች መውረድ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜም ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ ስሜት ውስጥ በመግባት ዓለማዊ የሆነውን ነገር ሁሉ የሚያስረሱ ስለፈጣሪ ፍቅር፣ ስለነብዩ ፍቅር ይወሳል። እንዲህ ባለው መንፈሳዊ ስሜት ውስጥ ሆነው ምስጋና የሚያቀርቡ ሰዎች አካላቸው ሲወዛወዝ በማሳ ላይ በንፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሰውን የደረሰ ጤፍ ይመስላሉ። እንዲህ በተመስጦ የሚከናወነው ሃይማኖታዊ ሥርአት በአምስቱ የሰላት ሰዓቶችና በምግብ ሰዓት ካልሆነ ያለእረፍት ይቀጥላል።
ከሚመታው ድቤ የሚወጣው የደወል አይነት ድምፅ፤ በቅርበት ላይ የሚገኘውን ሰው መንፈሳዊ ደስታ ይሰጠዋል። በሩቁ ያለን ደግሞ «ና ወዲህ» በማለት የሚጣራ ይመስላል። ድቤ እንዲህ የሰውን ቀልብ መያዝ የሚችል ሲሆን፣ ስፍራውም ፍቅር በፍቅር ይሆናል። ቀኑና ሌሊቱን በጸሎትና በምህላ፣ ቁርዓን በመቅራትና ሐዲሶችን በማንበብ ያሰለፉት ምዕመናን በዕለቱ በሕይወት ወደሌሉ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ሙስሊሞች የመቃብር ሥፍራዎች በመሄድ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት እንዲያስቀምጥ ጸሎት አድርገው ይመለሳሉ። ረፋድ ላይ ደግሞ የነብዩ መሐመድ ልደት ማክበር የተፈለገበትን ምክንያት ለምእመኑ ገለጻ ይደረጋል። ከነዚህ ሁሉ ሥርአቶች በኋላ ኢትዮጵያና ሕዝቧ በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ በመጸለይና በመመረቅ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖ ይለያያሉ።በእግሩና በአጋሰስ፣ በመኪና ተጓጉዞ በስፍራው የተገኘው ምእመን ሁሉ ጸሎት አድርሶ ወደቤቱ በመመለሱ መንፈሱ በደስታ ይሞላል።
“በኢትዮጵያ መውሊድን ማክበር በአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ እና ከሱፊዝም መስፋፋት ጋር እንዳደገ ይታመናል። ሱፊዎች መውሊድን የአምልኮ ተግባሮቻቸውና የመንፈሳዊ ንቃታቸው ማበልጸጊያ የአንድነታቸው ማጠናከሪያ መሳሪያ አድርገው ይገለገሉበታል” የሚሉት የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ተሾመ ብርሃኑ በአገራችን የመውሊድ በዓል ከአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ አንስቶ ህዝባዊ ክብረ በዓል ሆኖ ቢቀጥልም እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የአገሪቱ ይፋዊ ክብረ በዓል እንዳልነበረ እና ከ1967 ዓ.ም ወዲህ ግን፣ በህዝበ ሙስሊሙ የቀደመና ተከታታይ ጥያቄ የአገሪቱ ይፋዊ በዓል ሆኖ፣ በረቢ አል አወል አስራ ሁለተኛው ቀን መከበር መጀመሩንም ያብራራሉ።
የመውሊድ በዓል በበርካታ ድርጊቶች ይደምቃል። ከእነዚህም መካከል የሰደቃ ወይም የምጽዋት፣ የጀባታ፣ የተመረጡ የቁርአን ክፍሎችና የመውሊድ ምንባብ፣ የመንዙማ ፕሮግራሞች እንደሚገኙ በዓሉን የሚያከብሩት አማኒያን ይናገራሉ።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
በእስላማዊ ቅርሶች፣ ትውፊቶች፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ ስርዓቶች ላይ ሰፊ ዳሰሳ ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው ተሾመ ብርሃኑ ከማል ክብረ በዓላቱም ሆነ በተለያዩ አስተምሮቶች ምክንያት በውስጥም ሆነ በውጭ ሰፊ ግንኙነቶች ይደረጋሉ። አማኞች ስርዓታቸውን እንዲከውኑ ከማድረጉም ባሻገር በባህል እና በቱሪዝም ዘርፍ ውጤታማ ግንኙነት እንዲፈጠር ያስችላል። ይህንን ተከትሎ የታሪክ ተመራማሪው የግንኙነቶቹን ዳራ እንደሚከተለው ያብራሩታል።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከጥንት ጀምሮ ከጂቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን፣ ከግብፅ፣ ከየመንና ከሳዑዲ ዓረቢያ ሙስሊሞች ጋር መልካም ግንኙነት ሲኖራቸው በተለይም ወደ ግብፅና ሱዳን ሄደው
የእስልምና ትምህርት የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከአጎራባች ሙስሊም አገሮች የሚጋሯቸው ኢስላማዊ እሴቶች በስምምነትና በመተሳሰብ እንዲኖሩ ያደረጓቸው ሲሆን፣ በተለይም ተመሳሳይ የሱፊ ስርዓት በመቀበላቸው አንደኛው ተማሪ ወደ ሌላው ሄዶ ትምህርት እንዲቀስም አስችሎታል።
በአገር ውስጥም ቢሆን የአንዱ ክልል ሙስሊም ተማሪ (ደረሳ) ወደሌላው ክልል ሸኽ ሔዶ መማር የተለመደ ሲሆን፣ በሶማሌ ውስጥ የቃዲሪያ፣ የአሕመዲያ-ኢድሪስያ፣ የሳሊሕያ፣ የራፊዒያ፣ ጦሪቃ የነበረ ከመሆኑም በላይ ወደነ ሸኽ አብዱራሕማን አል-ዘይላዊ፣ የሸኽ ኢብራሂም ሐሰን ጀብሮ ከሐረርጌ፣ ከባሌ፣ ከአፋር ሄደው ይማሩ እንደነበረ ሁሉ ከሶማሌም ወደ ሐረር መጥተው ይማሩ ነበር። ከነዚህም መካከል የአሕመዲያ-ኢድሪስያ ጦሪቃ የተመሠረተው በአህመድ ኢብን ኢድሪስ ሲሆን፣ ይህም ከ1760- 1837 እንደዘለቀ ይታወቃል። የአሕመድያ ኢድሪስያን ጦሪቃ የማይከተሉት የሳሊሐን ጦሪቃ በ1887 አካባቢ የመሠረቱ ሲሆን፣ ይህም ጠሪቃ በተለይ በኦጋዴን ተስፋፍቶ እንደነበር ይታወቃል። የታወቁት የሱማሌ ሸኽ ዓዌስ ሙሐመድ ባራዊ (1909 አረፉ)፣ የሳሊሕያና የአሕመዲያ-ኢድሪስያ ጠሪቃ በሸበሌና በጁባ ወንዞች አካባቢ ጀምዓት ፈጥረው እንደነበርም ይታወቃል። ሸኽ ዓብዱራሕማን ዓብዱላህ (ሞቃዲሹ) የኡጋዴን በተለይም የሙስታሂል፣ የፈርፌር፣ የጎዴ ደረሶች እየሄዱ ትምህርት ይቀስሙባቸው ነበር።
በኢትዮጵያ ውስጥ መውሊድ በዓል እንደሚከበረው ሁሉ በሌሎች የዓለም ክፍል በሚገኙ የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በተመሳሳይ በልዩ ልዩ ስነ ስርዓት ተከብሮ ይውላል። በዓሉን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማክበር ከውጭ አገራት የሚመጡ ጉብኚዎች ሲኖሩ በተመሳሳይ ወደ ተለያዩ አገራት በመጓዝ ይህንኑ በዓል የሚያከብሩ ኢትዮጵያውያንም በርካቶች ናቸው።
እንደ መውጫ
መስከረም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ፀጋና በርካታ በረከትን ይዞልን ይመጣል። ሁሌም የያዝነው ዓመት ተገባዶ አዲሱን ስንቀበል በወጋገን ፈክተን በልምላሜ ተከበን በአደይ አበባ አጊጠን ነው። እኛ የራሳችን የዘመን መቁጠሪያ፣ የራሳችን ፊደልና ከተፈጥሮ ጋር የምንግባባበት ልዩ ቀመር ያለን ህዝቦች ነን። ለዚያ ነው ጉሙና ጨለማው ሲገፍ አበቦች በፍካት ሲፈነድቁ በራችንን ከፍተን በልዩ ተስፋ ተውበን ዘመኑን የምንቀበለው።
መስከረም ሲጠባ የአሮጌው ዓመትን ሽኝት የምናደርግበት ብቻ አይደለም። ልዩ ልዩ በዓላትን የምናከብርበት ለቀጣዩ ወራት እቅድ አውጥተን የሕይወት ስኬት ለማስመዝገብ የምንሰናዳበት ጭምር እንጂ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የመውሊድ በዓል አንዱ ነው።
እነዚህን መሰል በዓላት ስናስታውስ አዲስ ዓመት ሁሌም ይናፈቃል። ሁሉም የአገሬ ሰው በዚህ ጊዜ በደስታ ይቅበጠበጣል። ከላዩ ላይ እርጅና የሚለውን ስሜት ገፍፎ ደምቆና አምሮ ይታያል። በሸኘው ዓመት ያገኘውን ድል በአዲሱ ደርቦ ደራርቦ ስኬታማ ለመሆን ያቅዳል። ማንፀባረቁ የፊት ገፅታው ላይ ሲገለጥ፣ ማማሩ ደግሞ ከባህላዊ እሴቱ በተቀዳው ማራኪ አልባሳት በማጌጡ ላይ ይታያል። በአጠቃላይ አዲስ ዓመት ሁሌም አዲስ ሁሌም ፍካትን የሚሻበትና “አሃዱ” ብሎ ዳግም የሚነሳበት ወቅት ነው።
መስከረም ለእኛ ብቻ አይጠባም። ወሩን ጠብቀው ውብ ባህላችንን፣ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን እንዲሁም ልዩ ልዩ መገለጫዎቻችንን ለመጎብኘት ከተለያዩ የዓለም ክፍለ አገራት ወደ ውቢቷ አገራችን የሚጎርፉ አያሌ የውጭ ዜጎች አሉ። እኛ ልዩና ውብ ባህል፣ ማንነት ያለን ህዝቦች ነን። በዚህ ምክንያት ደግሞ ብዙዎች ያሉንን እሴቶች ለማየት ይናፍቃሉ። እኛም እንግዳን ተቀብለን “እሽሞንሙነንና” ዳግም ደጃችንን እንዲናፍቁ አድርገን መሸኘት የምንችል ኢትዮጵያውያኖች ነን። 1497ተኛው የመውሊድ በዓልም በዚህ መንፈስ ነው ተከብሮ ያለፈው። የዓመት ሰው ይበለን!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015