የስነ አእምሮ ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይም በህጻናት ላይ የሚከሰቱ የስነ አእምሮ ችግሮች አብዛኛውን ጊዜ ከተፈጥሮ ሂደት መዛባት ጋር የሚከሰቱ ሲሆን በህክምናም ሙሉ በሙሉ መዳን ባይችሉም ክትትል እየተደረገባቸው ለውጦችን ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። ህጻናት በእርግዝናና በውልደት ወቅት በሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ነገሮች የእድገት ውስንነትን ጨምሮ ኦቲስቲክና ሌሎች ችግሮች ሊስተዋሉባቸው ይችላል።
በመሆኑም ወላጆች እንዲሁም አሳዳጊዎች የልጆችን እድገት በአግባቡ መከታተል፤ ችግሮች ሲታዩም ነገ ዛሬ ከማለት ይልቅ በቶሎ መፍትሔ እንዲያገኙ ወደ ህክምና ተቋማት መውሰድም ከሚመጡት ውስብስብ ችግሮች እንደሚያድን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
የካቲት 12 ሆስፒታል በተለየም በህጻናት ስነ አእምሯዊ እድገት ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ክፍል አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሆስፒታሉ በተለየም በመንግስት ሆስፒታል ደረጃ በብቸኝነት በሚሰጠው የህጻናት ስነ አእምሯዊ ህክምና ኦቲስቲክን ጨምሮ የአእምሮ እድገት ውስንነት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች በባለሙያዎች እየታዩና እየተፈተሹ የመፍትሔ እርምጃ እየተወሰደባቸው በርካታ ልጆችና ወላጆችም ከችግሩ እየወጡ ስለመሆኑ አይተናል፡፡
ልጆች በማዕከሉ በሚደረግላቸው የንግግር ልምምድና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም ነገሮችን እንዲለዩ በራሳቸው መብላት መጠጣት መልበስ እንዲሁም መጸዳዳት እንዲለምዱ በሚሰጣቸው ስልጠና ብዙዎች ለውጥ አምጥተዋል የሚሉን ደግሞ በሆስፒታሉ የስነ አእምሮ ህክምና ክፍል ሃላፊ የስነ አእምሮ ስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አሸናፊ ነጋሽ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር አሸናፊ ገለጻ የአእምሮ ህክምና ሲባል አብዛኛውን ነገር የሚሸፍን ነው፤ ነገር ግን እንደሁኔታው ሊለያዩ ይችላል፡፡ ነገር ግን ማናቸውንም ዓይነት የአእምሮ ህመሞችን የማከም ስራ ይሰራል፡፡ የካቲት 12 ሆስፒታልም የሚታወቀው በህጻናት ስነ አእምሮ ህክምና ነው፡፡ ይህ ሲባል ኦቲዝም የአእምሮ እድገት ውስንነት ከትምህርት ጋር በተያያዘ ወደኋላ የመቅረትና የመሳሰሉት ስለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር አሸናፊ ገለጻ በልጆችና በአዋቂዎች ላይ የሚከሰቱ ማናቸውንም አይነት የአእምሮ ህመሞችን ይታከማሉ፡፡ ነገር ግን ከሌሎች ሆስፒታሎች በተለየ መልኩ የየካቲት 12 አገልግሎት ህጻናት ላይ ያመዝናል። ብቸኛው ነውም ማለት ይቻላል፡፡
የህጻናት የአእምሮ ጤና ችግር በርካታ ናቸው የሚሉት ዶክተር አሸናፊ የእድገት ውስንነት ኦቲዝም መዘግየትና ሌሎችም አሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ ቤተሰብ የልጆቹን ሁኔታ በቶሎ ያለመረዳት ከተረዱም በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ወደህክምና ተቋም ያለማምጣት ይስተዋላል፡፡
ነገር ግን ለህክምና ውጤታማነት ልጆች ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ቢመጡ ተመራጭ ነው የሚሉት ዶክተር አሸናፊ እያጋጠመን ያለው ነገር ግን ከዚህ ፍጹም በተቃራኒው በ20 እና 25 ዓመት እድሜ ላይ የሚመጡ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡
የህጻናት አእምሮ ችግሮች ሰፊ ናቸው፡፡ ህብረተሰቡም ችግር ያለባቸውን ልጆቹን ቶሎም ይዞ የመምጣቱ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ነው፡፡ ነገር ግን ህክምናው በጣም ብዙ ሂደቶች ያሉት ትዕግስትና ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች ቀጣይነቱ ላይ ችግር ይሆንባቸዋል ብለዋል፡፡
የአእምሮ ህክምና እንደ ኢንፌክሽን ችግር በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ህክምና መድሃኒት ተወስዶ የሚዳንበት አይደለም የሚሉት ዶክተር አሸናፊ ወላጆችም የሚቸግራቸው ነገር ህክምናውን ማስቀጠል ነው፡፡ ከተሞች አካባቢ ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው ትንሽ ምልክት ሲያዩም ላማክር በማለት የመምጣት ልምዶች እየተስተዋሉ ነው ይህ ሊዳብርም ይገባዋል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር አሸናፊ አብዛኞቹ ከህጻናት ጋር የሚያያዙ የአእምሮ ችግሮች የሚለኩት ከእድገታቸው ጋር ነው ፤ በመሆኑም ማንኛውም ቤተሰብ ማየት ያለበት ቆሞ መሄድ ላይ መዘግየት ካለ ይህ ሲባል ደግሞ አንድ ልጅ በአንድ ዓመት ከሁለት ወሩ ወይም ሶስት ወሩ ቆሞ መሄድ ካልቻለ ይህ ሁኔታ ደግሞ እስከ ሶስትና አራት ዓመት የሚቀጥል ከሆነ፤ ንግግርን በተመለከተም እማማ አባባ ከሚለው ቃል ጀምሮ በሂደት ዓረፍተ ነገር እየሰራ መሄድ ካልቻለ በተለይም እስከ ሶስትና አራት አመት ድረስ ምንም ቋንቋ የማያወራ ከሆነ የእድገት መዘግየት ችግር ታይቷል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከልጆች ጋር ሲደባለቅ የሚያሳያቸው ነገሮች እንደ እኩዮቹ የመግባባት ችግር ካጋጠመው ትምህርት ቤት ገብቶም ከክፍል ጓደኞቹ እኩል የነቃ ተሳትፎን የማያደርግ ከሆነ እድገቱ ላይ የሚስተዋል ችግር በመሆኑ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ፡፡
ዶክተር አሸናፊ ማብራሪያቸውን በመቀጠልም ልጆች ሊኖራቸው የሚገቡ መሰረታዊ ክህሎቶች ለምሳሌ አንድ ልጅ ከተወለደ ከወራት በኋላ ቤተሰብ ያበላዋል፤ ያጠጣዋል፤ ንጽህናውን ይጠብቅለታል፤ ያለብሰዋል ከዛ በኋላ ግን በሂደት ልጁ ይህንን ነገር መስራት ካልቻለ አስር አመቱ ሆኖ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን እገዛን የሚሻ ከሆነ ችግር በመሆኑ ወላጆች አስፈላጊውን ክትትል ማድረግና በተገቢው ሁኔታ የህከምና እርዳታን መጠየቅ ይገባቸዋል።
እነዚህ መዘግየቶች ምናልባትም ኦቲስቲክ ህጸናት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ላይ ሊገኙ የሚችሉ ናቸውና ምልክቶቹ ሲታዩ ወደህከምና ተቋም አምጥቶ ችግሩ በትክክል የቱ ነው ምን ዓይነት እንክብካቤስ ያስፈልገዋል የሚለውን መወሰንም አስፈላጊ ነው ይላሉ ዶክተር አሸናፊ።
እዚህ ላይ ግን ሊስተዋል የሚገባው ሁሉም ልጆች ተመሳሳይ እድገት ይኖራቸዋል ማለት አለመሆኑን ነው ያሉት ዶክተር አሸናፊ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያነጻጽሩም የወራቶች ልዩነት ከሆነ ያን ያህል ችግር አይኖረውም። ነገር ግን መዘግየቱ በዓመታት የሚገለጽ ከሆነ ግን አስፈላጊውን እርዳታ ማግኘት እንደሚገባም ይመክራሉ።
በአብዛኛው ከእድገት ጋር የተያያዘ ህመም ያለባቸውን ህጻናት ይዘው ወደማዕከላችን ለሚመጡ ቤተሰቦች መጀመሪያ የምናደርገው ስለ ችግሩ እንዲማሩ ግንዛቤ መፍጠር ነው፤ በዚህም ከእድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ይታከማሉ ግን ደግሞ ሙሉ በሙሉ የሚጠፉ አለመሆናቸውን የማሳወቅ ስራ እንሰራለን፤ ሌላው ደግሞ ምክያቶቹን ግልጽ የማድረግ ስራ ይሰራል፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ ወላጆች ለልጆቻቸው ችግር አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ተጠያቂ ስለሚያደርጉ መንስኤዎቹን ግልጽ የማድረግ ስራ ይሰራል፤ ይላሉ።
እንደ ዶክተር አሸናፊ ገለጻ መንስኤዎቹን ካስተማርን በኋላ ችግሩ ከልጆቹ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚጠፋ እንዳልሆነና ህክምናውም ባህሪያዊ እንጂ በመድሃኒት የሚሰጥ አለመሆኑን እናሳውቃለን ይላሉ። በመሆኑም ልጆች ወደማዕከሉ ሲመጡ እያንዳንዷን ባህሪያቸውን ሊያስተካክል ብሎም መዘግየታቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ትምህርታዊ ስራዎችን እንዲሰሩ ይደረጋል። ይህ ደግሞ በማዕከሉ ብቻ ተሰርቶ የሚያበቃ ስላልሆነና በቶሎም ለውጥ ላይታይበት ስለሚችል ስራዎቹን ወላጆች ቤት ሄደው እንዲያሰሯቸው የቤት ስራ ተደርጎ ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ብቸኛው የንግግር ህክምና የሚሰጥበት እንደመሆኑ የእድገት ችግር ያለባቸው ህጻናት ቀጠሮ እየተያዘላቸው በመምጣት ንግግርን እንዲለማመዱ ቋንቋ እንዲያወጡ በማድረግ ክትትል ይደረግባቸዋል፤ በሌላ በኩልም ሃይለኝነት የሚታይባቸው ልጆች ካሉ ለምሳሌ ሰውና ራስን መጉዳት ከአቅም በላይ የሆነ መንቀዥቀዥ ሲኖሩ ግን መድሃኒት ሊታዘዝ ይችላል የሚሉት ዶክተር አሸናፊ ነገር ግን አንድ ልጅ መናገር እንዲችል አልያም ቆሞ እንዲሄድ በራሱ እንዲበላ የሚያደርግ መድሃኒት አለመኖሩንና ይህንን ማስተካከል የሚቻለው በሚሰሩ ተግባራዊ ስራዎች መሆኑንም ያብራራሉ።
ልምምዱ ስኬታማነቱ የሚለካው በሚያሳየው ደረጃ ነው የሚሉት ዶክተር አሸናፊ ምናልባት ችግሩ ያለበት ህጻን ከፍ ባለ ችግር ውስጥ ሆኖ ከመጣ ብዙ ጥረት ሊጠይቅ የሚመጣው ለውጥም በጣም የዘገየ ሊሆን ይችላል ፤ በመሆኑም ውጤቱን ለመለካት የመጣበት የእድሜ ደረጃ የህመሙ መጠን ይወስነዋል በማለት ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ህጻናቱ የሚታይባቸው የእድገት ችግር ነው ወይስ ሌሎች ተዛማጅ ህመሞች አሉባቸው የሚለውም ሊጤን የሚገባው ነገር ነው ካሉ በኋላ ምክንያቱ ደግሞ አሁንም ውጤቱን የሚለካው ከዛ አንጻር በመሆኑ እንደሆነም ይናገራሉ።
ህጻናትን በማከም በተለይም መሰል የስነ አእምሮ ህክምናዎች ሲያጋጥሙ ትልቁ ችግር የቤተሰብ ብርታት ነው የሚሉት ዶክተር አሸናፊ ወላጆች ይሰላቻሉ ከማዕከሉ የሚሰጧቸውን የቤት ስራዎች ተከታትለው ማሰራቱ ላይ ይደክማሉ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህክምናው ዓመታትን የሚወስድ በመሆኑ ተሰላችተው ወደማዕከሉ መምጣታቸውን ያቆማሉ ይህ ደግሞ ልጆቹ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ያደርጋል እኛም የምንቸገረው ከዚህ አንጻር ነው በማለት በህክምናው ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ይናገራሉ።
ህክምናው ሰፊ ከመሆኑና የታካሚው ቁጥርም ከመጨመሩ ብሎም በንግግር ህክምና ብቸኛ ሆስፒታል እንደመሆኑ የአቅም ውስንነት አለ፤ በባለሙያም በኩል የተሟላ አይደለም፤ ለአንድ ታካሚ ምናልባት አንድ ሰዓት ተኩል እንወስዳለን ይህ በሌላ ህክምና ብዙ ታማሚዎች የሚተያዩበት ነው ይህ ደግሞ ከባለሙያዎች ቁጥር ማነስ ጋር ስራዎች ይደራረባሉ አገልግሎት ፈላጊዎችን በአጭር ቀጠሮ ማስተናገድ በጣም እንቸገራለን በማለት ይናገራሉ።
ይህም ቢሆን ግን ተናበን በመስራት ቀጠሮ ስንሰጥም ጥንቃቄ በማድረግ ሁሉንም አገልግሎት ፈላጊዎች ለማስተናገድ እየሞከርን ነው ነገር ግን ሰዎች ምናልባት ወረፋው እስከ ስድስት ወርና አመት ድረስ ላይደርሳቸው ይችላል ይላሉ።
“ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያዩትን ምልክት ችላ ሳይሉ በቶሎ ወደማዕከሉ እንዲሁም ወደሌላ የጤና ተቋማት ቢመጡ ችግሩ ሳይብስ መፍትሔ ከማግኘታቸውም በላይ የእኛንም ስራ ያቀሉልናል። በመሆኑም ልጆች የሚያሳድጉ ሰዎች በሙሉ የልጆቻቸውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተል ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ህክምና ተቋም የመጣ ህጻን ህመሙ ሙሉ በሙሉ አይጥፋለት እንጂ በከፍተኛ ሁኔታ የመሻሻል ሁኔታ ስላለው ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም” በማለት ምክራቸውን ያካፍላሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015