እናትነት ፍፁም በማይተካ ደስታ ልጅን በጥልቀት መውደድ ነው። የደግነት፣ የሩህሩህነት፣ የሁሉን ቻይነት…መገለጫ ጭምር ነው። ልጅን በማህፀን ውስጥ ለወራት መሸከም፣ ከዚያም መውለድ፤ ጡት አጥብቶና ተንከባክቦ ማሳደግ ነው። የዕድሜ ልክ ትስስር የሚፈጥር በህይወት ዘመን ሁሉ የሚቀጥል ጠንካራ የፍቅር መተሳሰሪያ ገመድ ያለው ነው።
እናትነት ከፈጣሪ ለሴቶች ብቻ የተሰጠ ልዩ ፀጋ ነው። ፍሬያማ ትውልድ ማፍሪያና የጠንካራ ቤተሰብ መመሥረቻ ማዕከል የሚገነባበት ዋናውን ምሰሶ ማቆም ነው። ልጅን ተንከባክቦ አሳድጎ አስተምሮ በስነምግባር አንጾ ለቁም ነገር ማብቃት ላይ የእናት ድርሻዋ ከፍ ያለ ነው። ገመና ሸፋኝም እናት ናት። በማህበራዊ ኑሮ፤ በቤት ውስጥ ሞላ ጎደለ ተጨንቃና ተጠባ ልጆቿን የምታሳድግ ናት። አብስላ የምትመግብ፣ ስታጣም ያላትን ለልጆቿ አከፋፍላ የራሷን ፍላጎት ገድባ የምትቆራመድ፣ ለሌሎች የምትኖር ናት። እናት ለልጆቿ፣ ለቤተሰቦቿ የተሰጠች ልዩ ስጦታ ብንላት አይበዛባትም። ከሩህሩነቷ ጋር ተያይዞም እናት ብዙ የተነገራላት፣ ብዙ የተዘፈናላት ናት። በእውነቱም ስለተባለው ብቻም ሳይሆን ከዛም በላይ ናት። ዘጠኝ ወር ሙሉ ምቾትና ጤናን አጥቶ፣ ስለምቾቱ እና ጤናው ተጨንቀው የሳሱለት ውድ ልጅ ከማሕፀን ወጥቶ ቀኑንም ሌሊቱንም እቅፍ ውስጥ ሲያሳልፍ ከመመልከት የላቀ ምን ስጦታ ሊገኝ ይችላል።
ከማሕፀን ወጥቶ እቅፍ ውስጥ ያለው ልጅ ከማንም በላይ ለእናት ቅርብ ነው። ጨቅላ ህጻናትም አስቀድመው የሚያወቁት እናታቸውን ነው። የእናታቸውን ጡት እየጠቡ በእናታቸው እቅፍ ሆነው ምቾታቸውን ያረጋግጣሉ። እናትም ጨቅላ ህጻናትን በጤና ለማሳደግ በደስታና በሰቀቀን ውስጥ ሆና የእናትነት ጥንቃቄና እንክብካቤ በማድረግ ታሳድጋለች።
ገና በማህፀን ውስጥ ሲገላበጥ ጀምሮ የሆነ ነፍስ የሚያሳሳ ስሜት ከመሰማቱም በላይ ዘና ብለው በእቅፍ ውስጥ ውለው የእናታቸውን ፊት እየነካኩ ሲጠቡ ያለው ስሜት በዓለም ላይ ካለው ሁሉ ደስታ በላይ ነው። ከፍ እያሉ ሲሄዱ የድክድክ ሩጫቸው ላይ ወደቁ ተነሱ ሰቀቀኑ የእናት ነው። ሙሉ አካል ይዘው በጤና እንዲያድጉ የእናት ውለታዋ የላቀ ነው።
እናት በማይመች ትዳር ውስጥ ሆና እንኳን የምታስበው ስለወለደቻቸው ልጆች ነው። በእቅፏ አቅፋ በጀርባዋ አዝላ ሁሉን ትሆናለች ለልጇ። እነሱን አሳድጌ አስተምሬ ለቁም ነገር አብቅቼ ብላ። “ ልጄ አንዴ ቁምነገር እስኪደርስለኝ ልታገስ..” በማለት ዓመታትን የልጅን ቁምነገር ለማየት በትእግስት ስታሳልፍ፤ የማይቻለውን ችላ ለዛች ለልጇ ስኬት ጎንበስ ብላ ቀን ታሳልፋለች። እናትነት ሸከም፤ እናትነት ተስፋ፤ እናትነት የዓለም ደስታም ሀዘንም የሁሉ ነገር መገለጫ ነው።
ታዲያ ይሄን ውብ ፀጋ የታደለችው እናት፤ እንኳን ለሰው ለቤትና ለዱር እንስሳ ሳይቀር ‹‹ላም ቀንዷ አይከብዳትም፤ ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች ››የተባለላት ምን አንጀቷን አስጨክኖት፣ ምን ከባድ ችግር ገጥሟት ይሆን እንጃ ብቻ የእናት አንጀቷ በልጇ ላይ ለመጨከን ያበቃት የሚያስብል አንድ አጋጣሚ ለማየት ችለናል።
የኑሮን ሸክም የፈተናት እናት
ወይዘሪት ሰብሪያ ወይንም በሌላ ስሟ ፋይዛ በድሩ ሽፋ ትባላለች። በጉልት ንግድ የምትተዳደር ወጣት ናት። ማልዳ ተነስታ ከአትክልት ተራ አትክልት አምጥታ በመቸርቸር ኑሮዋን ትገፋ ነበር። ለእለት ጉርሷና የራሷን ህይወት ለማሸነፍ ታትራ የምትሰራው ወጣት ከአንድ በቀን ስራ ከሚተዳደር የጉልት ደንበኛዋ ጋር የፍቅር ግንኙነት ትመሰርታለች። በእራሷ መንገድ እራሷን እያስተዳደረች የምትኖረው ወጣት ከአንድ ሁለት ይሻላል በማለት ሶስት ጉልቻን መስርታ የትዳርን መንገድ ትጀምራለች። በመካከል ባለቤቷ የኮንስትራክሽን ስራ በመዳከሙ የተነሳ ቤት ውስጥ ተኝቶ መዋል የዘወትር ተግባሩ ያደርጋል።
ከሌሊት እስከ ሌሊት የምትለፋው ወጣት ተጋግዘን የኑሮን ዳገት እንገፋለን ብላ የገባችበት ህይወት ባላሰበችው ሁኔታ ሸክም ሲሆንባት መከፋት ጀመረች። ራሷን ለማስተዳደርና ህይወቷን ለመለወጥ ያሰበችው ሁሉ ሌላ ተጨማሪ ሸክም ትከሻዋ ላይ ወደቀባት።
የተከፋ ተደፋ ይሉት ነገር ደርሶባት ነው መሰል በሆዷም ጽንስ ተቋጠረ። እንደ በፊቱ መስራት መሮጥ ቢሳናትም አቅሟ እስከቻለ ትታትር ጀመር። ኑሮ ጫናና እርግዝና ተደራርበው አመል የነሷት ወጣት ስትወጣ ስትገባ ከፍቅር ጓደኛዋ ጋር መነታረክ ጀመረች። ስራ ማጣት ብሎም የሚስቱ ጭቅጭቅ ያስመረረው ባል አንድ ቀን ለስራ ወጥታ ስትመለስ ቤቱን ጥሎ መሄዱን ተገነዘበች።
ያኔ ሰማይ ምድሩ ተደፈባት፤ በዚህ ላይ ልጅ ሊያውም ያለ አጋር በጣም ተከፋች። ያን ጊዜ የቅርብ ጓደኛዋ ቀለል ያለ ቤት አብረን ተከራይተን እየተጋገዝን እንኖራለን በማለት በጋራ ቀለል ያለ ቤት ተከራይተው የመውለጃ ቀኗን ይጠባበቁ ጀመር።
ጓደኛዋ ሰብሪያ እንዳይከፋት የተቻላትን በሙሉ እያደረገች ልታስደስታት ትሞክራለች። ቀኑ ደርሶ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ የታቀፈችው ወይዘሪት ሰብሪያ ልጅ በማግኘቷ ብዙም ደስተኛ አትመሰለም ነበር። ልጇን ይዛ ወደ ቤት ከገባች በኋላ ለአራት ቀናት ጓደኛዋ ከጎኗ ሳትለይ ስትንከባከባት ቆየች።
የእለት ጉርስ ማግኘት ግድ የሆነባት የሰብሪያ ጓደኛ አይዞሽ ቶሎ እመለሳለሁ በማለት ጥላት ትሄዳለች። ያኔ ነው እንግዲህ ሰብሪያ ትናንት ያሳለፈችውን ሰቆቃ ዳግም ከልጇ ጋር ልታሳልፍ መሆኑን ስታስበው አእምሮዋን ክፉ ክፉ ነገሮችን ማሰብ የጀመረው።
አሳዛኙ ውሳኔ
ቀን አልፎ ቀን ሲተካ የኑሮ ውጣ ውረድ እንደሚቀል ነገን በተስፋ ማየት የ ተሳነችው እናት ከራሷ ጋር ውዝግብ ጀምራለች። “ በጨርቅ ጠቅልዬ ልጣለው?…….. አይ ይቅርብኝ….” “ ወይስ አፉን ላፍነው….. ውይ ልጄን…” ታዲያ ምን ልሁን?” በማለት ከራሷ ጋር ጠብ፣ ለህሊናዋ ጋር ሙግት፣ ደግሞ ክርክር ትጀምራለች።
ከብዙ ከእራስ ጋር ውይይት በኋላ የማያዳግም ውሳኔ ወስና ወደተግባር ትቀይራለች። በውሳኔዋም የ5 ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ልጇን በሻሽ አንገቱን በማነቅ ህይወቱ እንዲያልፍ ታደርጋለች።
ነገሩ እንዲህ ነው። ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ዓለም ባንክ አካባቢ ከጓደኛዋ ተከራይታ በምትኖርበት ቤት ውስጥ የጓደኛዋን ወደ ስራ መሄድ ተጠቅማ የአብራኳ ክፋይ በሆነው ልጇ ላይ እጇን አንስታለች።
በክስ መዝገቡ ላይ በዝርዝር እንደተብራራው፣ በፆታ ወንድ የሆነውንና የ5 ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ልጇን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሻሽ አንገቱን አንቃ ህይወቱ እንዲያልፍ ካደረገች በኋላ በብርድ ልብስና በፍራሽ ጠቅልላ በማስቀመጥ ቤቱን ዘግታ ከአካባቢው ብትሰወርም በተደረገባት ክትትል በቁጥጥር ስር ውላለች።
የህፃኑ አባት
የወይዘሪት ሰብሪያ ፍቅረኛ በዚህ ከባድ ወቅት ብቻዋን ጥሎ መሄዱ ተገቢ እንዳልሆነ ያምንና ይፀፀታል። ከዛም በብዙ ጥረት ስራ አግኝቶ ከጀመረ በኋላ የመጀመሪያ ሳምንት ደሞዙን ይዞ ቀድሞ ተከራይተው ይኖሩበት ወደነበረው ቤት ይሄዳል። እዛ ሲደርስ ግን የፍቅር ጓደኛው ቤት መልቀቋ ሰማ። ስራውን እየሰራ ሁለቱንም የሚያውቋቸውን ሰዎች አይተዋት እንደሆነ በማለት ሲያጠያይቅ ከጓደኛዋ ጋር እየኖረች መሆኗን ይሰማል። በቀጣዩ ቀን አለች ወደ ተባለችበት ቤት ሲሄድ ወጣት ሰብሪያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆና ድርጊቱን እንዴት እንደፈፀመች ታስረዳለች።
ቤቱ በአካባቢው ሰዎችና በህግ አካላት ተሞልቷል። ምን እንደተፈጠረ ጠጋ ብሎ ሲመለከት የሆነውን በሙሉ ይረዳል። ሰማይ ምድሩ ዞረበት፤ ለዚህ ህፃን መጥፋትም ራሱን ተጠያቂ አድርጎ እጅግ በጣም አዘነ። “ ምናለ ትንሽ ቀን ታግሻት በነበር ..? ምነው ሲሄድ እግሬን በሰበርው…?” በማለት በለቅሶ ለያዥ ለገናዥ አስቸግሮ ቆየ። የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ ነገር ሆነበት ሁሉ ነገር ካከተመ በኋላ በቦታው ቢደርስም ከማልቀስ ያለፈ ሌላ መፍትሄ አጣ።
የፖሊስ ምርመራ
ህፃኑን የተኛ አስመስላ ከቤት ከወጣች በኋላ ርቃ ለመሄድ እየተንቀሳቀስች የነበረችው ወይዘሪት ሰብሪያን አንድ ጎረቤት ትመለከታታለች። “አራስ ሆና እንዴት
ወጣች? ልጇንም አልያዘችም” በማለት ጎረቤት ደውላ ቤት ያለውን ነገር አጣርተው እንዲነግሯት ታደርጋለች። እሷ ግን ሰብርያን በርቀት መከተል አላቆመችም ነበር። ጎረቤት ቤቱ ክፍት መሆኑን ህፃኑ በህይወት አለመኖሩን ደውለው ይነግሯታል። ያን ጊዜ ፖሊስ ጠርታ እንድትያዝ ታደርጋለች።
ፖሊስም የዐይን ምስክሮችና የሆስፒታል የምርመራ ወረቀትን በመመልከት ወንጀለኛዋ ላይ ተጨማሪ ምርምራ ሲያካሂድ ቆይቶ የሰነድ ማሰረጃ ማጠናቀር ጀመር። የወንጀል ምርመራ ተደርጎባት ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ተረጋግጦ በግለሰቧ ላይ ክስ ተመስርቶባታል።
የወንጀል ምርመራ ቡድን ኃላፊው ኢንስፔክተር ግርማ ስለሺ እንደሚናገሩት አእምሮን ተቆጣጥሮ ማሰብ ቢቻል የአብራክን ክፋይ ከማጥፋት የተሻሉ አማራጮች በሞሉባት አገር ስለምን ጥፋትን ምርጫ ማድረግ እንመርጣለን። ህፃናትን የሚያሳደጉ ድርጅቶችና በርካታ ሰዎች እያሉ ልጅን ማጥፋትን ማሰብ አንድ በትክክል የሚያስብ አእምሮ ካለው ሰው የማይጠበቅ መሆኑን ተናገረዋል።
ውሳኔ
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሽ ወይዘሪት ሰብሪያ ወይንም በሌላ ስሟ ፋይዛ በድሩ ሽፋ ትባላለች። ከመስከረም 10 እስከ 11/2014 ዓ.ም ባለውና ወንጀሉ የተፈጸመበት ሰዓት በውል በማይታወቅበት ጊዜ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 540 ስር የተመለከተውን ተላልፋ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ዓለም ባንክ አካባቢ ከጓደኛዋ ጋር ተከራይታ በምትኖርበት ቤት ውስጥ የጓደኛዋን ወደ ስራ መሄድ ተጠቅማ የአብራኳ ክፋይ በሆነው ልጇ ላይ የጭካኔዋን ጥግ አሳይታለች።
በክስ መዝገቡ ላይ በዝርዝር እንደተብራራው ተከሳሽ፣ በፆታ ወንድ የሆነውንና የ5 ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ልጇን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሻሽ አንገቱን አንቃ ህይወቱ እንዲያልፍ ካደረገች በኋላ በብርድ ልብስና በፍራሽ ጠቅልላ በማስቀመጥ ቤቱን ዘግታ ከአካባቢው ብትሰወርም በተደረገባት ክትትል በቁጥጥር ስር ውላ የወንጀል ምርመራ ተደርጎባት ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ተረጋግጦ በግለሰቧ ላይ ክስ ተመስርቶባታል።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ በመሰረተው ክስ ፍርድ ቤት ቀርባ ክርክር ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል።
በዚሁ መሰረት ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015