የዛሬው የ‹‹ዘመን እንግዳ›› በትህነግ ዘመነ መንግስት ከሚወዷት አገራቸው በግፍ ከተሰደዱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው። ትውልዳቸውም ሆነ እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ መሿለኪያ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጋዚያን እና ፈለገ-ዮርዳኖስ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል። ሽመልስ ሃብቴ እና ልዑል መኮንን ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉባቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው። እንግዳችን ነፃ የትምህርት እድል አግኝተውም በወቅቱ የራሺያ አካል በነበረችው ዩክሬን ግዛት ተልከው ለአምስት ዓመታት ወታደራዊ ሳይንስ አጥንተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ወደ አገራቸው በ1981 ዓ.ም ሲመለሱ አገሪቱ ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ስለነበረች በቀጥታ ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ይመሩት ወደነበረው አዋሽ አርባ ግንባር ተመደቡ። ብዙም ሳይቆዩ ግን ወደ መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) ተዛወሩ። በዚያም አሰብ የራሺያውያኖች አማካሪ ሆነው መስራት ጀመሩ። በተጓዳኝም የመኮድ የትራንስፖርትና ስምሪት ሃላፊ ሆነው እስከ 1983 ዓ.ም አገለገሉ። ወያኔ አገሪቱን መቆጣጠሩን ተከትሎም ወደ ኬኒያ ተሰደዱ። በኬኒያ በአንድ የትራስፖርት ኩባንያ ተቀጥረው እስከ 1988 ዓ.ም ከሰሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ‹‹ጌትሽ ትሬዲንግ›› የተባለ የራሳቸውን የትራንስፖርት ኩባንያ ከፈቱና ለብዙዎች የሥራ እድል ፈጠሩ።
ከዚሁ ጎን ለጎን የተለያዩ የንግድና ማህበራዊ ስራዎችን ሲሰሩ የቆዩት እንግዳችን በተለይም እንግሊዝ አገር የተካሄደውን ሁለተኛውን የህዝብ ለህዝብ ጉዞ በማስተባበር ስማቸው ጎልቶ ይነሳል። ይሁንና ለአገር ያላቸው ፍቅርና የቀድሞ ሰራዊት አባል መሆናቸው ብዙም ያልተመቻቸው የወያኔ አመራሮች ሰበብ እየፈለጉ ይተንኩሷቸውና ይጠልፏቸው ነበር። በዚህ ምክንያት የሚሰሩት ስራ ተጀምሮ የሚቋረጥበት አጋጣሚ እየተበራከተ መጣ። ከስርዓቱ መሪዎች ጋር ያለው አለመግባባት እየተካረረ በመሄድ ለእስርና ለስደት ዳረጋቸው።
ላለፉት 14 ዓመታት በኬኒያና በካናዳ በስደት የኖሩት እኚህ ሰው በኖሩባቸው አገራት ሆነውም የወያኔን ስርዓት እንዲያበቃለት ብርቱ ትግል ሲያደርጎ ቆይተዋል። የዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤትን ከመሰረቱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን መካከል አንዱ ሲሆኑ በምክር ቤቱ አማካኝነት የአገራቸውን ገፅታ በመገንባት ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ነው የሚገኙት።
ከሰሞኑ ደግሞ ወደሚወዷት አገራቸው መጥተዋል። በአገር ቤትም ከ15 ዓመት በፊት ወጥነውት የነበረውንና አሁንም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን እውን የማድረግ አላማ ሰንቀዋል። በዚህና በሌሎች ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኮር ዳዊት ጌታሁን ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ከአገር የወጡበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ኮር ዳዊት፡- ከአገሬ የወጣሁት በነበረው የፖለቲካ ስርዓት ምክንያት ሥራ መስራት ባለመቻሌ ነው። እኔ አገሬንም ሆነ ህዝቤን የምወድና አገሬን የማሳደግ ብዙ እቅዶች የነበሩኝ ቢሆንም የወያኔ ሰዎች ፈፅሞ ሊያስቀምጡኝ አልቻሉም፤ የምሰራውን ሁሉ እያበላሹ ፈታ ነሱኝ፤ በኩባንያዬም ሆነ በእኔ ላይ ብዙ ጫናው ሲበረታ መቋቋም ባለመቻሌ ጥዬ ለመሄድ ተገደድኩኝ። ስወጣ ደግሞ ዝም ብሎ አይደለም፤ ከእስር ጀምሮ እኔን ለመግደል ብዙ ነገር ተሞክሮ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ከመንግስት ጋር አላግባባ ያሎዎት ምን ነበር?
ኮር ዳዊት፡– በአጠቃላይ እኔ አገር ወዳድና የማምንበትን ሁሉ ያለአንዳች ፍርሃት የምናገር ሰው መሆኔ በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎችን አያስደስትም ነበር። ደግሞም የቀድሞ ሰራዊት አባልና በኢትዮጵያዊነቴ የማልደራደር በመሆኔ እኔ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው ያደረገ ይመስለኛል። የሚገርምሽ እንደዚያ እየጠመዱኝም ቢሆን በርካታ ለአገር የሚጠቅሙ ስራዎችን ሰርቻለሁ። ከዚህም ውስጥ ሁለተኛውን የህዝብ ለህዝብ ጉዞ በእንግሊዝ አገር ያዘጋጀሁት እኔ ነኝ።
ከህዝብ ለህዝብ ጉዞ ስመለስም ከሰባት እስከ አስር ሺ ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር በማለም አዲስ አበባ ያሉትን የአውቶብስ ፌርማታዎችን ግራና ቀኝ መቀመጫ፤ ጫማ ማሳመሪያ ቦታ ያላቸው በራሴ ገንዘብ ወጪ አድርጌ በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች ሰርቼ አስመረቅኩ። ይሁንና ሌሎች ቦታዎች ላይ ሊቀጥል ሲሉ በጊዜው ስልጣን ላይ በነበሩ ሰዎች ምክንያት ፕሮጀክቱ ተቀምቶ ለሌሎች ባለሃብቶች ተሰጠ።
በዚህ ግን አልተወሰንኩም፤ ከ250 ፋብሪካዎች ላይ ጥናት በማካሄድ ሌላ 8፣3፣3 የተባለ ትልቅ ፕሮጀክት ነደፉኩኝ። ይህም ፕሮጀክት 8 ሰዓት ይሰራል፤ በሶስት ፈረቃ ሶስት እጥፍ ፋብሪካዎች እንዲያመርቱ የሚያደርግ ነው። ይህ ስር ነቀል በሆነ መልኩ የአገሪቱን የስራ ባህል የሚለውጥ ፕሮጀክት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ ቢቀርብም ስልጣኑን የተቆጣጠሩ ባለጊዜዎች ግን ይህ አዲስ ሃሳብ አልጣማቸውም። ስለዚህም በሰበብ ባስባ እንዳይተገበር አደረጉት። እንዳውም ይህንን ሃሳብ ከጅምሩ እንዳቆም ማስፈራሪያ አዘል ትዕዛዝ ተሰጠኝ።
ይህ ጉዳይ ከባለስልጣናቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከተተኝ፤ በመጨረሻም በሌሊት አፍነው ‹‹ጓታናማ›› ይባል በነበረና ምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ ይገኝ በነበረ ወህኒ ቤት ለሶስት ወራት ጨለማ ቤት ውስጥ ከተው አሰሩኝ። ከሶስት ወር በኋላ አውጥተው ሌሊት ሳሪስ ቀለበት መንገድ ላይ ጆንያ ውስጥ ከተው ጣሉኝ። ሌሊቱን ሙሉ ስጓዝ አድሬ ቤቴ ገባሁ። በጣም የሚያሳዝነው ግን ‹‹እናቴ ልጅሽ ሞቷል›› ተብላ ስለነበር ሃዘን ለሶስት ወራት ተቀምጣ ነበር፤ እድርም በልታለች። ቤተሰቦቼ ሲያገኙኝ ከፍተኛ መደናገጥ ነበር የተፈጠረው። ከዚያ በቀጥታ ዳግመኛ ወደ ኬኒያ ተሰደድኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ኬኒያ ሳሉ አንድ አስገራሚ ነገር እንደተፈጠረ ሰምተናል፤ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ያጫውቱን?
ኮር ዳዊት፡- ነገሩ የሚጀምረው እዚህ ጓንታናማ እስር ቤት ሳለሁ ነው። ምን መሰለሽ፤ እዚህ የታሰርኩበት ወህኒ ቤት ውስጥ 14 ኬኒያውያን ነበሩ፤ በ1997 ዓ.ም ምርጫ በተመሳሳይ ኬኒያ ውስጥ ምርጫ ነበርና ከኪባኪ ጋር ክርክር ውስጥ ስለነበር የኬኒያ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እስረኛ የሚቀያየሩበት አሰራር ስለነበራቸው እነዚያ ኬኒያውያን እዚህ እኔ የታሰርኩበት ወህኒ ቤት አምጥተው አሰሯቸው። ከ14ቱ ውስጥ ስድስቱ የት እንደገቡ ባላውቅም ስምንቱ ኬኒያዎች ግን ታማኝ እስረኞች ስለነበሩ ከእኔ የተሻለ የመውጣት የመግባት ነፃነት ነበራቸው።
ከእነሱ ጋር የምንገናኝበት አጋጣሚ ስለነበረ ጓደኞች እስከመሆን ደርስን። እናም ቀድሞ የተፈታ በሕይወት ስለመኖራችን ለየቤተሰቦቻችን ለማስታወቅ ቃል ተገባብተን ነበር። እድለኛ ሆኜ እኔ ቀድሜ ተፈታሁ፤ እንደአጋጣሚ ኬኒያ ሄጄ የአንደኛው ኬኒያዊ ስልክ ስለነበረኝ ለባለቤቱ ደውዬ በሕይወት ስለመኖራቸው ነገርኳት፤ የእነሱን በሕይወት መኖር ስነግራት ግን ልታምነኝ አልቻለችም። ምክንያቱም እሷም ሆነ የሌሎች ቤተሰቦች ራሳቸው መሞታቸውን ነበር የሚያውቁት። እንዳውም የሁለቱ እስረኞች ሚስቶች ባለቤቶቻቸው የሞቱ መስሏቸው ሌላ ትዳር መስርተው ነበር።
በኋላም አለመሞታቸውን ስነግራት እሷ ከሞብሳ እንዲሁም የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ የነበሩት ግለሰብ ሰምተው ከኡጋንዳ ድረስ እውነታውን ለማጣራት መጡ። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግስታት ጋር ተፃፅፈው በአውሮፕላን ጭነው ኬኒያ አስመጧቸው። በእኔ ምክንያት በመፈታታቸው መላው ኬኒያዊ ሰምቶ እኔን እንደንጉስ ይንከባከቡኝና ያከብሩኝ ጀመር። በየጋዜጣው ፊት ገፅ ላይ ስለሰራሁት ነገር ተጻፈ። እናም በእነዚህ ኬኒያውያን እስረኞች ምክንያት ረዱኝና ወደ ካናዳ መሻገር ቻልኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- በስደት ሆነውም ስርዓቱን በፅኑ ሲታገሉ እንደነበር ይታወቃል፤ ስለዚህ የትግል ሕይወት በጥቂቱ ያስታውሱን?
ኮር ዳዊት፡- ካናዳ እንደገባሁኝ ኑሮ አልጋ በአልጋ አልሆነልኝም፤ በጣም ከባድ ነበር። ምክንያቱም ኬኒያም እያለሁ ጀምሮ በቀጥታ ኑሮዬ ፖለቲካ ነበር፤ ያንን ሃገር አጥፊ ስርዓት እንዲወገድ መታገል ነበር ዋነኛ ትኩረቴ። እንደሄድኩኝ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ጋራዥ ከፈትን ግን እኔ ባለሙያ ሳልነበርኩኝና ቀጥሮ ማሰራት ስለማይቻል ብዙም ውጤታማ መሆን አልቻልኩም። ከዚያም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ቢሮ ከፍተን ጉዳይ የማስፈፀም ስራ እንሰራ ነበር። ትልቁ ስራዬ ግን ፖለቲካው ነበር። በአጠቃላይ ላለፉት 15 ዓመታት ሕወሓትን ስታገል ነው የቆየሁት።
አሁን የመጣሁት 8፣3፣3 የተባለውን ፕሮጀክቴን እውን ለማድረግ ነው። ይህንን ፕሮጀክት እውን ማድረግ ከተቻለ ለምሳሌ መተሃራ ስኳር ፋብሪካ በቀን የሚመርተው 10 ሺ ኩንታል ስኳር ቢሆን ይህንን ፕሮጀክት ማስጀመር ከተቻለ ፤ በሶስት ፈረቃ 30 ሺ በማምረት 30 ሺ ሰው የስራ እድል ያገኛል ማለት ነው። ይህንን ሁሉም ድርጅቶች ላይ ማድረግ ከተቻለ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ አጥ ይጠፋል። የስራ ባህሉንም ስርቀል በሆነ መልኩ ነው የሚለውጠው። በመሰረቱ ምዕራብያውያኑ የሚከተሉት ይህንን አይነት ዘዴ ነው። እርግጥ ይህንን ስራ ያለጥናት የሚገባ አይደለም፤ በቂ የምርት ግብዓት ሊኖር ይገባል፤ የመሳሪያዎቹ አቅምም ወሳኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለዓመታት ወያኔን ከሚታገሉ ሰዎች አንዱ እንደመሆንዎ ፤ የዚያ ስርዓት መወገድ ምን ስሜት ፈጠረብዎት በጥቂቱ ያብራሩልን?
ኮር ዳዊት፡- የሚገርምሽ ይሄ ለውጥ ሲመጣ እኔ የመጀመሪያው ተቃዋሚ ነበርኩኝ። ምክንያቱም እኔ የታገልኩት ስርነቀል ለውጥ እንዲመጣ እንጂ ከዚያው ስርዓት ለሚወጣ ለውጥ አልነበረምና ነው። ስለዚህ ብዙ ሲደግፉ እኔ አልደገፍኩም ነበር። በወቅቱ ደግሞ ኮር ኢትዮጵያ የተባለ ትግል ነበረን። በነገራችን ላይ እኔ ኮር የተባልኩትም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው። የዚህ ትግል ዋነኛ ማጠንጠኛ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ስርነቀል ለውጥ ማምጣት ነው። በዚህ መሃል ነው ይህ ለውጥ የመጣው። በዚህ ትግል ውስጥ የነበሩ ጠንካራ ሰዎች ተበተኑ። ምክንያቱም በአብዛኛው የዚህ ለውጥ ደጋፊ በመሆናቸው ነው። ጥቂቶቻችን ደግሞ በአቋማችን ፀንተን ቆየኝ።
በሂደት ግን የለውጡ ደጋፊ ቁጥር እየጨመረ የእኛ እየተመናመነ ሄደና ኮር ኢትዮጵያ ፈረሰ። የቀረነው ሰዎች ተሰብሰብን ህዝቡ ሁሉ ተቀብሎት ሳለ እኛ እንዴት ተቃውሞችንን እንቀጥላለን? ብለን መከርን። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር እየደገፍን ለመቃወም፤ እየተቃወምን ለመደገፍ ተስማማን። ግን በዚህም ብዙ አልገፋንበትም፤ የምንደግፈው ነገር በዛ፤ በተለይ ዶክተር ዐቢይ በጭንቅላቱና በሚሰራቸው ስራዎች በለጠን። በመሆኑም ልንቃወመው የምንችለውን ነገር አሳጣን። ተከፍሎ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድ ሲያደርግልን፤ እስረኞችን ከየአገሩ አስፈትቶ ሲያስመጣን በአጠቃላይ የምናየው ነገር ሁሉ የግድ ሰውየውን እንድንደግፈው አደረገን። ከዚያ በኋላ ነው ሙሉ ለሙሉ መደገፍ የጀመርኩት።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ቡድን ስልጣን መልቀቁን ተከትሎ አገሪቱ በተደጋጋሚ ጦርነት ውስጥ ከቷታል፤ ይህ ከድርጅቱ ባህሪ አንፃር ምንን ያሳያል?
ኮር ዳዊት፡- ስለጦርነቱ ብዙ ሰዎች ግራ ይጋባሉ። ሕወሓት ካለጦርነት መኖር የማይችል ድርጅት ነው። ይህንን ባህሪያቸውን ደግሞ ራሳቸው ያውቁታል። ራሳቸውን ማዳን የሚችሉት በጦርነት ውስጥ ሲኖሩ ነው። በመሰረቱ መንግስት ለእነሱ የሰጠውን እድል ለማንም አልሰጠም። ንብረታቸውም ሆነ ሃብታቸው አልተወረሰም፤ ወህኒ አልገቡም፤ በሰላም እንዲኖሩ ነው መንግስት እድል የሰጣቸው። ግን እንደገና ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ያላቸው አማራጭ ውጊያ ነው። ውጊያውን ለመክፈት የሚያስችላቸውን ስራ ደግሞ አስቀድመው በደንብ ሰርተዋል። ያም ለ27 ዓመታት በጎሳ አገሪቱን መከፋፈላቸውን አብሮ ይኖር የነበረውን ህዝብ ልዩነቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረጋቸው ነው። ኦሮሞው ከአማራው እንዳይናበብ፤ የትግራይን ታላቅነት መንገር፤ በሃይማኖት ሳይቀር መቃቃር እንዲፈጠር አድርገው ነው የኖሩት።
በነገራችን ላይ ያ የመርዝ እንቁላል ነው አሁን ላይ ተፈልፍሎ አገር እያተራመሰ ያለው። ለምሳሌ አሁን የመከላከያን ሳያውቁት ቀርተው አይደለም እየተዋጉ ያሉት። ሊያሸንፉ እንደማይችሉ በደንብ ያውቃሉ። ግን ደግሞ የእነሱን ስልጣን ለማስቀጠል ሲሉ የትግራይ ህዝቡ በሙሉ ቢያልቅ ደንታ ስለሌላቸው ነው። ደግሞም በሕይወት የቆየ ህዝብ ካለ ‹‹ለምን?›› ብሎ ይጠይቀናል ብለው ስለሚሰጉም ህዝቡን በጦርነት እየማገዱ ያሉት። በመጀመሪያ ልጆቻቸውን ወስደው አስጨፈጨፉ፤ አሁን ደግሞ እናትና አባቶቻቸውን አዘመቱ። ይህንን የሚያደርጉት እንዳልኩሽ ‹‹ልጆቻንን የታሉ?›› ብለው እንዳይጠይቋቸው ማለቅ ስላለባቸው ነው።
ህዝብ በዚህ ደረጃ ካስጨፈጨፉ በኋላ እንደራደር ነው የሚሉት። ከዚህ ቀደም ሲሸነፉ ‹‹ስልታዊ ማፈግፈግ›› ነበር የሚሉት። አሁን ደግሞ ‹‹ለአማራው ሰላም ስንል ለቀን ወጣን›› ይላሉ። ስለዚህ ሕወሓት ያለ ጦርነት መኖር አይችልም፤ ያደጉበት ባህሪ ነው። በመሰረቱ እኔ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትንም ሆነ የመላው የፀጥታ ሃይል አቋምና አቅም ስለማውቅ ለዚህ ጦርነት ብዙም ስጋት የለኝም። ግን ደግሞ ህዝቡ ማለቁ ያሳዝነኛል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ቡድን ለመደራደር ፍላጎቱን አስታውቋል፤ በዚህ ላይ ያልዎት ምልከታ ምንድን ነው?
ኮር ዳዊት፡– ድርድር መልካም ቢሆንም ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር አገሪቱን ስጋት ውስጥ ይከታል ብዬ ነው የማምነው። ዋነኛ መደራደሪያ መሆን አለበት ብዬ የማምነው እነዚህ ሰዎች ወንጀለኞች ስለሆኑ ለህግ ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት ሲችሉ ነው። ምክንያቱም ይህንን ሁሉ ህዝብ አስጨፍጭፈው በሰላም ሊኖሩ የሚችሉበት ሁኔታ ባለመኖሩ ነው። ትግራይ ነፃ የምትወጣው እነዚህ ሰዎች ለፍትህ ሲቀርቡ ነው። ኢትዮጵያም ሰላሟ የሚጠበቀው ወንጀለኞቹ በህግ ጥላ ስር ሲሆኑ ነው። በመሰረቱ እነሱ ድርድር የሚሉት ልክ ሲወቀጡና የማጥቂያ እድሉን ሲያጡ ነው። አሁንም በድርድር ሀሳቡ የተስማሙ የመሰሉት ሴራቸውን ለመፈፀም፤ የውጭ ድጋፍ ለማግኘትና አየር ለመሳብ ነው። ይህንን ሲሉ ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆኑን ማጤን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ጦርነት የውክልና ጦርነት እንደሆነ ይታወቃል፤ በተለይ ምዕራብውያኑ ለአሸባሪው ቡድን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዴት ነው የሚያገልፁት?
ኮር ዳዊት፡– በመሰረቱ ይህንን አሸባሪ ቡድን የሚደግፉት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው። እነሱ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲኖር አይፈልጉም። የአንዳንደ አገራት ፍላጎት አባይ ጋር ብቻ የሚቀር አይደለም፤ እነሱንም የሚነካ ነው። ስለዚህ ሁሉም የየራሱ ጥቅም አለው። የህዳሴው ግድብ ሲያልቅ የእነዚህ አገራት ትንኮሳም ይቆማል። ምክንያቱም አባይ ራሱን ነው የሚጠብቀው። ኒዩክለር ታጥቋል፤ አሁን አባይን የመጠበቅ ግዴታ የኢትዮጵያ ሳይሆን የሱዳንና የግብፅ ነው ሊሆን የሚገባው። አለበለዚያ ሱዳንም ሆነ ግብፅ ይፈርሳሉ። አባይን እነካለሁ ቢሉ በቀጥታ የሱዳን ሁለት ግድቦች ጋር ነው የሚሄደው፤ የሱዳን ግድቦች ፈረሱ ማለት ደግሞ ሱዳንን አጥለቅልቆ አስዋን ግድብ ነው የሚደርሰው። አስዋን ግድብ አለቀለት ማለት ደግሞ የግብፅ ከተሞችና ህዝቡ በጠቅላላ ሜዲትሪያል ባህር ነው የሚገቡት። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ምንም የሚያሰጋት ነገር የለም። ግን እስከቻሉ ድረስ እኛን መቦርቦራቸው አይቀርም። አገሪቱ ካልታመሰች አያርፉም።
አዲስ ዘመን፡- የተባበሩት መንግስታ ድርጅት ሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን በቅርቡ ያወጣውን ሪፖርት እንዴት አዩት?
ኮር ዳዊት፡– በነገራችን ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች መንግስታት የሚሰሩት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር መሆኑን መዘንጋት አይገባንም። በተግባርም እንዳየነው ኢትዮጵያ ላይ የሚወስኑት ውሳኔ በሙሉ የራሳቸውን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ እንጂ ለፍትህ ወይም ስለሚሞተው ሰው አስበው አይደለም። እነዚህ ሰዎች ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ሲሉ በየሰዓቱ አጀንዳ ይሰጡናል። የእነሱን አጀንዳ እየሰማን የምንቀጥል ከሆነ አገራችንን እናፈርሳለን። አምነስቲም ሆነ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ለእኛ ራስ ምታት የሚሆን ነገር ነው የሚቆፍሩልን። መንግስታችን የእሱን ሃሰተኛ ሪፖርት የሚሰማበት ጆሮ የለውም፤ ይልቁንም አገሪቱን ለማሳደግ በስራ ላይ ነው ተጠም ዶ ያለው።
እንደእውነታው ከሆነ አሸባሪው ቡድን ንፁሃንን ሲደፍርና ሲገድል ብሎም የእነሱንም ንብረት ሲዘርፍ በተግባር አይተዋል። ሰው እንደችቦ ሲማግዱ፤ የህፃናት ምግብና መድሃኒት ሳይቀር ሰርቀው ሲጠቀሙ ታይተዋል። የዓለም የምግብ ድርጅት ለእርዳታ የተላኩትን ሁሉ በጁንታው ሲዘረፍ ዝም ካሉ ይህ ድርጅት የሚረዳው ማንን ነው የሚለው ነገር ራሱ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። ስለዚህ ይህንን እያወቅን እነሱ ስለሚያወጡት የሃሰት ሪፖርት ትኩረት መስጠት አለብን ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ሪፖርት ጀርባ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የታሰበ ነገር እንዳለ ግልፅ ነው። ይህ ጉዳይ እርስዎን አያሳስቦትም?
ኮር ዳዊት፡- አይ እኔ ስጋት የለብኝም። ከዚያ ይልቅ ድህነታችንን አሸንፈን እነሱን መመከት የሚችል አቅም መፍጠር ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን ብዬ ነው የማምነው። ከድህነት ከወጣን የሚያሰጋን ነገር የለም። ግፋ ቢል እርዳታ መከልከልና ማዕቀብ መጣል ነው። ጁንታዎቹም ቢሆኑ ጥረታቸው የተመድ ሰራዊት እንዲገባ ነው። ለዚህ ነው ከኤርትራ ጋር ግጭት የሚፈጥሩት፤ ይህንን የሚያደርጉትም ኤርትራውያውን እንዲወጓቸውና ግጭቱን ቀጠናዊ ይዘት ለማስያዝ ነበር። ግን ሰሚ ስላላገኙ ብቻቸውን ቀርተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሊገባበት የሚችልበት በር ተዘግቶበታል። እንጂ ወንጀሉን ሁሉ ያውቀዋል።
በአጠቃላይ እኛ ማድረግ ያለብን ራሳችንን መቻልና ከእነሱ እርዳታ መላቀቅ ነው። አሁን መንግስት በምግብ እህል ራስን ለመቻል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። በተለይ ስንዴ ልማቱ በጣም የሚያጓጓ ነው። አማራ ክልልም እንዲሁ ለሰሊጥ ልማት ዘርፍ እየሰራ ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው። ለሰሊጥ ምርት አንድ ሚሊዮን ሰራተኛ እፈልጋለሁ ብሏል። በሌሎችም ክልሎች እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ነው ያለበት፤ ሰሞኑን እንደተመረቀው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል አይነት ስራዎች ከሰፉ የማንም ጠባቂ ልንሆን አንችልም። እርግጥ ነው በቀላሉ ከምንፈልገው ደረጃ መድረስ አንችል ይሆናል። ግን እጅ ለእጅ ስንያያዝና ጎሰኝነትን ስናስወግድ እናድጋለን። ያን ጊዜ ዛሬ ሊያፈርሱን የሚያደቡት ሁሉ እኛን ፈላጊ መሆናቸው አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- በዚሁ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ፈፅሟል ተብሎ የተገለፁት ወንጀሎች በእርግጥ ያንን ሰራዊት የሚወክል ነው ብለው ያምናሉ?
ኮር ዳዊት፡- በፍፁም አይወክለውምም፤ አይመጥነውምም። በሰራዊት ቤት ውስጥ ትልቁ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ወታደራዊ ጨዋነት ነው። ትግራይ ውስጥ እኮ የአርሶ አደሩን ምርት ሲያጭድ፣ አንበጣ ሲከላከል፤ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት ሲገነባ ነበር። ይህ በስነ-ምግባሩ የተመሰከረለት ሰራዊት ነው። ያኔ ያላደረገው ዛሬ ጦር ሜዳ ስለሆነ እንዲህ አይነት ነገር አደረገ ቢባል ማንንም አያሳምንም። የትግራይ ህዝብ ከማንም በላይ የሚወደው የአገር መከላከያ ሰራዊትን ነው። ስም ለማጥፋት ሆን ተብሎ የተደረገ እንጂ ትላንት ያልነበረ ባህሪ በምን መልኩ አሁን ሊታይ አይችልም።
በነገራችን ላይ ስም ማጥፋትና አሉባልታ እውነት አስመስሎ ማቅረብ የጁንታው ሰዎች የኖረ ባህሪ ነው። የጁንታው ሰዎች ድሮም ቢሆን ቁጭ ብለው ማንን በምን የሃሰት አጀንዳ ጠልፈው እንደሚጥሉ ሲጎነጉኑ ነው ውለው የሚያድሩት። የእኛን ሰራዊት ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ሰራዊትንም ጭምር ሹካና ማንኪያ ሳይቀር ዘረፉን የሚል አስቂኝ ክስ ነው ያቀረቡት። በአጠቃላይ እነሱ ካላወሩ አይኖሩም። እኔ በተለይ ወታደር ስለሆንኩኝ እንዲህ አይነቱን ውሃ የማያነሳ ክስ ለመቀበል ይቸግረኛል።
አዲስ ዘመን፡- ኃያላን አገራትንም ሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በሚመጥን መልኩ እውነታውን የሚያሳይ የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል ብለው ያምናሉ?
ኮር ዳዊት፡– በእኔ እምነት አልተሰራም፤ ግን ሙከራ አልተደረገም ማለቴ አይደለም። መንግስትም ሆነ ዲያስፖራው የየራሱን ጥረት ማድረጉ የሚዘነጋ አይደለም። ታስታውሺ እንደሆነ እነ ጁሃር ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም ብለው ችግር በፈጠሩበት ወቅት የዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤቱ ይህንን አስተሳሰብ በይፋ ከመቋወም ጀምሮ ዲያስፖራውን በማስተባበር ረገድ ብዙ ሰርቷል። በዚያ ወቅት ዲያስፖራው ያደረገው እንቅስቃሴና የዓለም መንግስታት በማሳመን ረገድ የማይናቅ ሚና ተጫውቷል። እየቆየ ሲመጣ ደግሞ በየቦታው ሰዎች በማንነታቸው ሲገደሉ ዲያስፖራውን እያስኮረፈና እያስበረገገው እንደመጣ የሚካድ አይደለም። እንደዚያም ሆኖ ግን አቅማችንን በፈቀደ መጠን እየታገልን ነው ያለነው። ሆኖም መስራት በሚገባው ልክ ተሰርቷል ማለት አይቻልም። እንዳውም ከእኛ በላይ የጁንታው ተላላኪዎች የሰሩት ስራ ከእኛ በእጅጉ ይበልጣል። እነሱ አገር ለማጥፋት ያን ያህል ውጤት ካመጡ እኛ ለምን የአገራችንን ህልውና ለመታደግ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- የአሜሪካ ልዑካን በተደጋጋሚ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ነው፤ ይህ መመላለስ ምንን ያሳያል?
ኮር ዳዊት፡– በእኔ እምነት መንግስት የእነሱ አጀንዳ ቀድሞ ስላወቀና ስለቀደማቸው ነው። አሜሪካኖቹ አሁን እያደረጉ ያሉት ሬሳ ማከም ነው። ይህ መመላለስ የሞተውን ጁንታ ለማዳን ብዙ እየሞከሩ መሆኑ ማሳያ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው። በተለይ የእኛ መጠንከርና በአቋማችን መፅናት በርካታ የአፍሪካ አገራትንም ያነቃቃ በመሆኑ ይህ በራሱ ትልቅ ስጋት ሆኖባቸዋል። እነሱም በድፍረት በኢትዮጵያ ምክንያት እንዳሻቸው ይገዟቸው የነበረውን አገራት እንዳመፁባቸው ይናገራሉ። ስለዚህ በእኔ እምነት ትልቅ ስጋት ስላለባቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡-ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኮር ዳዊት፤ እኔም አክብራችሁ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015 ዓ.ም