በህይወት ፋራፋንጎ ላይ ከፍና ዝቅ እላለው..ሀሳቤን ማሸነፍ አቅቶኝ፣ እውነቴን መርታት ተስኖኝ። ፋራፋንጎውን የሳተው ጋላቢው ልቤ ከዚህ እዛ እየወሰደ በማላውቀው መሬት ላይ፣ በማላውቀው ዓለም ላይ ይፈጠፍጠኛል። በተስፋ ማጣት ነፍሴ ተመጦ እንደ ተጣለ ሎሚ..ታኝኮ እንደተተፋ ማስቲካ ከአፈር ትውላለች። ያኔ እኔን መሆን ያቅተኛል..ሩቅ ህልሜ..አጽናኝ ምኞቴ ምናምንቴ ይለብሳል። ከምንምነት ለመውጣት፣ ራሴን ባለማዕረግ አድርጌ ለመስራት ባደነቃቀፉኝ ጎዳናዎቼ ላይ ቀጥ ብዬ ለመራመድ ሞክሬ ነበር። እያደናቀፉ ወደ ፊት ያስፈነጠሩኝን እንቅፋቶቼን እየዘለልኩ ማንም ካልደረሰው የህይወት ከፍታ ላይ ስሜን ልጽፍ መሻት ነበረኝ። ኋላዬን ትቼ ወደ ፊት ለመሄድ፣ የረገጥኩትን የታሪክ ዳና ላለመድገም ብዙ ለፋሁ። ብኩን ባደረጉኝን ሀሳቦቼ ተጠልፌ አርቄ ካየሁት የመጽናኛ ደብሬ አልደረስኩም። ለምን ብዬ ስጠይቅ ለምንን የፈጠረው አእምሮዬ መልስ አይሰጠኝም። ከራሴ ጋር ከፍና ዝቅ እያልኩ የፈንጠዝያ ምኩራቤን ከለልኩት።
ወደፊት ያላራመዱኝ ረኸጥ ሀሳቦቼ የነፍሴን አጥቢያ በነውር ገርግረው ማንም የማይሳለመው..ማንም የማይፈወስበት ገረገራ አድርገውኛል። ክብር ያላለበሱኝ እንቶ ፈንቶ ሀሳቦቼ የሩቅ ህልሜን ፍኖት በጋሬጣ ዘግተው የማሻቅብበትን የድህነት ሰርጥ የማርያም መንገድ ነፍገውኛል። ወዴት እንደምሄድ የማውቅ ሴት ነበርኩ..እንዴትና ለምን መራመድ እንዳለብኝ የገባኝ ነበርኩ። አሁን ግን እነዚያ ሁሉ ማስተዋሎቼ አብረውኝ የሉም። ወዴት እንጂ እንዴት መራመድ እንዳለብኝ አላውቅም። እነዚያ ሁሉ የክብር ማማዎቼ በከፍና ዝቅ የህይወት ዥዋዥዌ ውስጥ ናቸው።
ሀሳብ ከልብ ነው የሚጸነሰው..ልብ የሀሳብ ካዝና ነው። ከአእምሮ የራቁ፣ ከራስ በላይ የገነኑ ወርቃማ እውነቶች፣ ወርቃማ ስሜቶች፣ ወርቃማ ሀሳቦች ስፍራቸው ልብ ነው። የኔም የሀሳቦቼ መጸነሻ ማህጸን ልቤ ነው። ልቤ ከአእምሮዬ እንዲልቅ ያላደረኩት ጥረት አልነበረም። ልቤ ከአእምሮዬ እንዲበረታ ያልመገብኩት የምኞት ምግብ አልነበረም። ግን ሰመረልኝ..ሲሰምርልኝ ግን የምፈልጋትን እኔን ልቤ አልሰጠኝም። ከአእምሮዬ የባስኩ ሆኜ ነበር ራሴን ያገኘሁት። ከአእምሮዬ እንዲልቅ የተመኘሁት ልቤ የምፈልጋትን እኔን ሳይሰጠኝ ቀረ። እንደ አእምሮዬ አይነት ሴት ነኝ። መሄድ እየፈለኩ መንገድ የጠፋኝ..መራመድ እየፈለኩ ድጋፍ ያጣሁ ሴት። ልቤ የብኩን ሀሳቦቼ ማህጸን ሆኖ፣ ሀሳቦቼም የብኩን ልቤ ርዝራዥ ሆነው ከኋላ አቁመውኛል። ሰው መቼ ነው በራሱ ውስጥ የሚነግሰው? ስል ያልበቃ ራሴን እጠይቃለው።
አይ እኔ..እስካሁን አምጨ የወለድኩት በብኩርና የሚጠራ ፊተኛ አብራክ የለኝም። በአእምሮዬ ተጠቅቶ ልቤ ብዙ ብኩን ሀሳቦችን ጸንሶ ያውቃል። በአእምሮዬ ዘር በልቤ ተጸንሶ ነፍስ የዘራ የሀሳብ ጽንስ የለኝም..መሀን ነኝ። ሰው በራሱ ውስጥ ራሱን ሲመክን..ራሱን ሲጨነግፍ፣ ራሱን ሲያስወርድ እኔን ይመስላል። እኔ በሀሳቦቼ ውስጥ ከአሁን የተሻገረ..አምናን የተወ አጽናኝ ህልም የለኝም። ህልሞቼ ሁሉ እንዳልተገራ ሰጋር ፈረስ በሀሳቦቼ ጀርባ ጠፍረው ወደማላውቀው ስፍራ ወስደውኝ የሚመልሱኝ ከርታታ እፉዬ ገላን ነኝ። መሆን የምፈልገው እኔ ግን የተገራ..ባልደራስ ያለው..የት ሄዶ እንደሚመለስ የሚያውቀውን እኔን ነበር። ይሄ እኔ ጠፋብኝ። በህይወት ከፍና ዝቅ ውስጥ ራሴን ፍለጋ ላይ ነኝ።
ዛሬም መሀን ነኝ..ወደፊት የሚያራምዱኝን የሀሳብ ምርኩዝ አላገኘሁም። አበባቸውን አርግፈው ፍሬ ያላፈሩ ብዙ ሀሳቦች በሴትነቴ ውስጥ አሉ። በነፍሰ ጡር ልቤ ውስጥ ሁሌም የእንግዴ ልጅ እንዳረገዝኩ ነው።
ራሴን መች ይሆን የምወልደው እያልኩ አስባለው። በጀምበር መውጫና መጥለቂያ አድማስ ላይ አይኖቼን ሰቅዬ የራቀኝን ተስፋ እፈልገዋለው። ልክ እንደ ጀምበሯ፣ ልክ እንደ ሰማዩ፣ ልክ እንደ ደመናው ተስፋዎቼም ሩቅ ናቸው..በጣም ሩቅ።
አይኔን በአይኔ ሳላይ አረጀሁ..። ነፍሴ በአለም ላይ ተራቆተች። በራሴ ውስጥ ራሴን ስላጣሁት መኖር ሬት ሬት አለኝ። ሳራን መሆን አማረኝ። በአምላኳ ተማምና በዘጠና አመቷ እናት እንደሆነችው ሳራ በሽምግልና ወልጄ ባለታሪክ መባል አማረኝ። ግን ልቤን ከሽምግልና የሚያሳርፋት አብረሀማዊ ሀሳብ የለኝም። በልቤ ውስጥ ያሉት ሀሳቦቼ ይስሀቅን ለመጸነስ የማይበቁ ናቸው። በመካኗ ነፍሴ ውስጥ ክበዷ ሳራ ናፈቀችኝ። አምላኳን ተደግፋ መከራዋን የረሳችው ሳራ፣ አምላኳን ተማምና ነውሯን የገደለችው ሳራ..እሷን መሆን አማረኝ።
ከሁሉም በኋላ ነፍስ ብዙ መጎሳቆያ እንዳላት ተረዳሁ። ሰው በእድሜ ብቻ፣ በጊዜ ብቻ እንደማያረጅና እንደማይሸመግል ደረስኩበት። ሰው ተስፋ ሲርቀው..ነፍስ እውነት ስታጣ እንደሚያረጅ..እንደሚጎሳቆል ከራሴ ተማርኩ። ሀሳቤ አስረጀኝ..ሀሳቤ መኖር እንድጠላ አደረገኝ። በልቤ ውስጥ ባለብዙዋን ፍሬ ሳራን መፍጠር አቃተኝ።
ሙት ወላድ ነኝ..ማቀፍ ባማራቸው ክንዶቼ፣ መሳም ባማረው አፌ ራሴን ወልጄ ማቀፍ፣ ራሴን ወልጄ መሳም አልቻልኩም። እስከመች ልባክን? መች ይሆን ሳራን መሆኛዬ? መች ይሆን ልቤ ህያው ጽንስ የሚያረግዘው? እያልኩ እባዝናለው። አይሆኑ እሆናለው።
ሀሳቦቼ ምኞቴን መሸከም አልቻሉም። ልቤ ህልሜን ወልዶ ማሳደግ አልቻለም። በሀሳቤ ቅርንጫፍ ላይ ያለ ስር ዛፍ፣ ያለ ፍሬ አበባ ሆኜ ሰነበትኩ። ዛፍ ስር ከሌለው..አበባ ፍሬ ካልሰጠ ምን ውበት አለው? ጋለሞታ ልቤ ልጃገረድ ሀሳቤን መድፈር አቅቶት እቃትታለው..። በራሴ ውስጥ ራሴን እንዳረገዝኩ ዘላለማት ጠቡ። ለኔ ሀሳብ ዘላለማት ስንት ናቸው? ካለ ስር በዛፍነት፣ ካለ ፍሬ በአበባነት ዘመን መቁጠር ምን የሚሉት ሴትነት ነው? እበት ትልን ሲወልድ እኔ ዘር አጣሁኝ።
መሆን የምፈልጋት ሴት አሁን እኔ የሆንኳትን አልነበረም። መሆን የምፈልገው እኔ ይሄኛውን አልነበረም። መሆን የምፈልጋት ሴት ልቤ ውስጥ ናት..እስካሁን አልተፈጠረችም። እስካሁን አልተጸነሰችም። ልወልዳት ብዙ ዘመን፣ ብዙ ንጋት አምጫለው..ግን አልወለድኳትም። ያቺን ሴት ዛሬም ድረስ ነፍሰ ጡር ነኝ። የህልሜን እንቦቃቅላ ታቅፌ እናት መሆን..ሴት መሆን ያምረኛል። አራስ መሆን ይናፍቀኛል። ልቤ ውስጥ እኔን መፍጠር እንዴት አቃተኝ? ሀሳቤ እኔን መውለድ እንዴት ተሳነው? እያልኩና እየተደነኩ ለዘላለማት በቀረበ እድሜ በጸሀይ መውጫና መጥለቂያ አውድ ስር በባይተዋርነት አለው።
ሰው በልቡ ውስጥ ሀሳቡን፣ በሀሳቡ ውስጥ ህልሙን፣ በህልሙ ውስጥ ራሱን መፍጠር ካልቻለ እንደ እኔ ነው። ሁሌም ነፍሰ ጡር..ሁሌም እርጉዝ። ሰው በዘመን ውስጥ በእምነትና በእውነቱ ካልጀገነና ካልበረታ እንደ እኔ ነው..አብራሀማዊቷን ሳራን ናፋቂ..። ሰው በተፈጥሮ ውስጥ የሚፈልገውን ራሱን ጸንሶ መውለድ ካልቻለ እንደ እኔ ነው..የታሪክ መሀን..የምንም ነገር መሀን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015