ርእሳችን ገራገር ቢጤ መሆኑ ያስታውቅበታል። በአንባቢያን ዘንድ ”ድሮስ ሀበሻና እስልምና ምን አለያያቸውና ነው እንደ አዲስ …” የሚል ስሜትን ሊያጭር ይችልም ይሆናል። ግን አይደለም። ሀበሻና እስልምናን በተመለከተ ከምናውቃቸው የማናውቃቸው፤ ካየናቸው ያላየናቸው፤ ከሰማናቸው ያልሰማናቸው …. የሚበልጡ እንደ መሆናቸው መጠን፣ ርእሳችን ገራገርነቱን እንደ ያዘ ሆኖ አሳዋቂነቱንም ያካተተ ነው ተብሎ (በጸሐፊው) ይታሰባል።
የዚህ ጽሑፍ መነሻ ዐቢይ ምክንያት ነገ የሚከበረው የመውሊድ በዓል ሲሆን፤ በእሱም አማካይነት የሐበሻን እና የእስልምናን የጊዜ ፈተናን ያለፈ፣ የማይፈታ ቁርኝት፤ እንዲሁም ለአጠቃላይ እስልምና ኃይማኖት እዚህ ደረጃ መድረስ የሐበሻን እና ሐበሾችን ሚናና ድርሻ በጨረፍታም ቢሆን (አንባቢያን ገፍተው ይሄዱበታል ከሚል ታሳቢ) ለመቃኘት መሞከር ነው።
ይህንን ስናደርግ፣ ከፈረሱ አፍ እንደሚገባው፣ ምንጮችን ተጠቅመን ሲሆን፣ ምንጮቻችንም በእኛው፣ ከእኛው ለእኛው የተበረከቱና አንቱታን ያተረፉ ናቸው በሚል መተማመን ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ምናልባት ጽሑፋችን ለርእሱ ከመገዛት ባለፈ ስለ በአሉ ዝግጅትና አከባበር ብዙ የሚለው ላይኖር ቢችል አንባቢያንንም ሆነ ምእመናንን ይቅርታ እየጠየቅን፣ በአሉን በተመለከተ ጋዜጣችን በተለያዩ አምዶቹ ሽፋን እየሰጠና የሚሰጥም መሆኑን በመጠቆም ነው።
ይህ ጸሐፊ እስከሚያውቀው ድረስ በራቸውን ለሚዲያ ክፍት አድርገው ያላቸውን ከሚወረውሩ ሰዎች አንዱ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፋሪስ ናቸው። ሁሌም በራቸው ክፍት ነው፤ ሁሌም ኢትዮጵያንና እስልምናን አስተሳስረው እንደ ገለፁ ነው፤ ሁሌም በእስልምና ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን (ሐበሻ)ንና ሐበሾችን ያህል ከፍ ብሎ የሚታይ አለመኖሩን እንደ ተናገሩ ነው፤ ሁሌም ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ይህንን የኢትዮጵያን እውነታ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲናገሩና እንዲያስተምሩ እንደ መከሩና አሳሰቡ ናቸው፤ እንዲመኩበትም ጭምር እየመከሩ ይገኛሉ።
በአባይ ጉዳይ ላይ ብቻ ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ የጥናትና ምርምር ልምድና መረጃ ያላቸው፤ የአረቡን ዓለም ስነልቦና ጭምር ጥንቅቅ አድርገው የሚያውቁት እኝህ ምሁር ከአንባቢና አድማጭ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የእሳቸውን ስራ ለዛሬ ይዘን ቀርበናል። በዚሁ አማካኝነትም፣ በብዙዎቻችን ብዙም ያልታወቁ የሐበሻና ሐበሾችን፤ በአጠቃላይም የአፍሪካና አፍሪካዊያንን ሚና፣ ተግባርና ለእስልምና ኃይማኖት መሰረት መጣል ያደረጉትን አስተዋፅኦ፤ የከፈሉትን መስዋእትነት … እንመለከታለን።
ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፋሪስ ከደራሲነታቸው ባለፈ በተመራማሪነትና ሀሳብ አፍላቂነታቸውም ይታወቃሉ። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ፣ ”ሐበሾች በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዙሪያ፣ ቁጥር 2፣ መጽሐፍ አንድ”፤ እንዲሁም፣ ”የሀበሾች አሻራ በእስልምና፣ ቁጥር 3፣ መጽሐፍ ሁለት” በሚል ርእስ የተዘጋጀ (ሁለቱም በአንድ ጥራእዝ)፣ የተለያዩ ክፍሎች ያሉትና በ2008 ዓ.ም ለንባብ የበቃ መጽሐፍ አላቸው።
በእውነቱ፣ መጽሐፉ፣ በተለይ ለIslamic Literature ኮርስ ተገቢ ማስተማሪያ ለመሆን ሙሉ አቅም ያለው ስራ ነው። ከአጋዥነትም ባለፈ ማስተማሪያነትን የሚመጥን ቁንጮ ስራ ነው እያልን ነውና የዚህች ቅንጫቢ ጽሑፍ ምንጭም ሆነ መሰረት ይኸው መጽሐፍ መሆኑን በመግለፅ እንቀጥል።
ደራሲ አደም ካሚል ፋሪስ መጽሐፉን ሲያዘጋጁ ደም ከመስጠት ያልተናነሰ ጥንቃቄ እንዳደረጉ ከስራው መረዳት ይቻላል። እውነቱን ለማስረዳት ረጅም ርቀት እንደ ሄዱም ድካማቸው ይናገራል። ርእሰ ጉዳዩንም በጥልቀት መዳሰሳቸው የመረጃ ቁፋሯቸውና አቆፋፈራቸው ያመለክታል። ወሰናቸው ከዚህ መለስ አለመሆኑም የልፋታቸው፣ የፍላጎታቸው፣ የመረዳታቸው ልክ፣ የእምነታቸው ከፍታ፣ የሰብአዊነታቸው ስሱነት፣ የቋንቋ ክሂላቸው … ማሳያ ነው። በግጭት አፈታትና አገራዊ መግባባት ላይም በብዙ ያሰቡበት ስለመሆኑ መጠራጠርም ሆነ መከራከር አይቻልም። ማንነትን ማሳወቅ ላይ ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውም ሌላው በመጽሐፉ ውስጥ በግልፅ የሚንፀባረቅ የደራሲው የደራሲነት አላማ ነው።
ገና ከመነሻው ሁለቱን (ክርስትናን እና እስልምና) ኃይማኖቶች በማስተሳሰር (ዮሀንስ ወንጌል ም.15፣ ቁ.26ን በመጥቀስ) የሚጀምሩት (ገፅ 18ን ይመልከቱ) አደም ካሚል ”ለመሆኑ ይህንን ያህል ያወራንለት ስራ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል?” የሚል ጥያቄ ብናነሳ ትክክል ነን።
እርግጥ ነው፣ ደራሲው የዮሀንስ ወንጌል ም.15፣ ቁ.26ን በመጥቀስ ብዙዎቻችን ያልተገነዘብነውን፣ እስከዛሬም እስከ መኖሩ እንኳን ልብ ያላልነውን፣ ያልተረዳነውን … እውነት ያሳዩናል፣ ያስረዱናል። አንዱ በአንዱ ውስጥ ህያው መሆኑንም ያስገነዝቡናል። ይህ አንዱ ፍሬ ነገራቸው ብቻ እንጂ ሁሉንም አይደለምና ወደ ሌሎቹ እንሂድ።
ደራሲ አደም ከላይ በጠቀስናቸው ርእሶቻቸው ዙሪያ ያላሉት፤ ያልጠቀሱትና ያላብራሩት ርእሰ ጉዳይ የለም፤ በስራዎቻቸው ውስጥ የሐበሻ (ኢትዮጵያ)፣ ሐበሾች እና እንደ አህጉር አፍሪካ … ሚናና አስተዋፅኦ (ለምሳሌ ከገጽ 52 እስከ 60 ያለውንና ”ሐበሾች በነብዩ ዙሪያ” በሚል ርእስ የሰፈረውን) መመልከት ይቻላል) ተዘርዝሯል፤ የሐበሾች ማንነት ከተግባርና ሥነምግባራቸው ጭምር በግልፅና በማያሻማ ቋንቋ ሰፍሯል። ቀደምትነታቸው፣ ሶስቱን (አይሁድ፣ ክርስትና እና እስልምና) ትላልቅ ኃይማኖቶች ከማንም በፊት አስቀድመው ማቀበላቸው፤ ይህም ለእስልምና ኃይማኖት ምቹ ሁኔታን እንደ ፈጠረ … ምንም ሳይቀር፣ ከቁርአን በተወሰዱ ጥቅሶች ተደግፎ ሰፍሯል።
በመጽሐፉ መሰረት ነብዩንና እስልምናን ለማጥፋት የተነሱ ጠላቶችን በመከላከል እስከ መስዋእትነት የከፈሉና የጂሀድን (ገፅ 61) የኻዳሚነትን ክብር (ገፅ 63) ያገኙ ሐበሾች ናቸው። ነብዩ ከተቃራኒ ወገኖቻቸው ጋር በገጠሙት ከባድ ጦርነት ቀዳሚ መስዋእትነትን የከፈሉት ሐበሾች ሲሆኑ፣ ዝርዝራቸውና በነብዩና ቁርአን የተሰጣቸውም ልዩ ክብር በግልፅ ሰፍሯል (ከገፅ 74 እስከ 101፣ 121 እና ሌሎችንም ይመልከቱ)።
በእስልምና እምነትና ኃይማኖተኞች ዘንድም ያላቸው የክብር ቦታ በስምና በመረጃ ተደግፎ ቀርቧል። ከሁሉም በላይ አላህ (ሱወ) ለሐበሾች የለገሳቸው ክብርም 1፣ 2 … ተብሎ የተዘረዘረ ሲሆን፤ እስከ 27ኛ ድረስ የዘለቀ ማስረጃ ቀርቧል (ከገፅ 121 እስከ 124 ተመልከት)፤ በ”ሐበሾችን በማሞገስ የወረዱ የቁርአን አንቀፆች”፣ በ”ስለ ኃበሾች በነብዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) የተነገሩ ሀዲሶች”ና ተከታዮቹ ርእሶች ስርም የሰፈረውን አንብብ)።
ሐበሾች የነብዩ (ሰዐወ)ን ዓለም አቀፋዊ (ለሰው ልጅ ሁሉ) የተላለፈን ጥሪ በመቀበልና ከጎናቸው በመሆን ቀዳሚዎቹ ሐበሾች ሲሆኑ ይህም በገጽ 68 እና 69 ላይ በመረጃና ማስረጃ ተደግፎ ቀርቧል።
ገና ከህፃንነታቸው ጀምሮ ነብዩን በማዕቀፍ፣ በማዘል፣ በማጥባት እና በመንከባከብ ለቁም ነገር ያበቃቸው፤ የእናትነት ኃላፊነትን የተወጣችው … ሐበሻዊቷ ኡሙ አይመን (ረዐ) ታሪክም ”ኡሙ አይመን (በረካ አል ሐበሺያ) (ረዐ)” በሚል ርእስ ስር ከነምስጢራቱ ለንባብ በቅቷል (ገጽ 106 እና ሌሎችንም ይመለከቷል)።
እስልምናን ለማዳን፣ ለመጠበቅና ለማስፋፋት ሐበሾች የከፈሉት መስዋእትነት ቀላል አይደለም። ከማንም በፊት ተገኝተው ከሁሉም በፊት መስዋእት ሆነው ለዛሬው እስልምና እዚህ መድረስ ዋጋ ከፍለዋል፤ ይህንንም በመጽሐፉ ገፆች (ለምሳሌ ከ145 እስከ 152 – ዋቢ መዘርዝሮችን ሳይጨምር ”ቁጥር 2፣ መጽሐፍ አንድ”ም የሚያልቀው በዚሁ ነው።) ላይ መመልከት ይቻላል።
የእስልምና ሰራዊት አድማሱን ለማስፋት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ለሰራዊቱም ሆነ ለሚገቡት አማኞች እስልምና ኃይማኖትን በስፋት የሚያስተምሩ ኡለማዎች ከሰራዊቱ ጋር አብረው ይዘምቱ ነበር። በየጊዜውም የነበሩት የሙስሊሙ ህብረተሰብ መሪዎች ለማስታወቂያና የቅስቀሳ ስራ በዘመናችን እንዳሉት የሚዲያ ባለሙያዎች አይነት ያስፈልጓቸው ነበር። በተለይ ቁርአንና ሀዲስን መዘገብ፣ መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ የአመጣጡንና አወራረዱን ታሪክ ማስተማር ያስፈልግ ነበር። ይህንን ሁኔታ በቅርቡ ሆኖ መከታተል የሚገባው አካል የሚያስፈልግበት ጊዜም ነበር። … በመሆኑም በነብዩ ዙሪያ የነበሩት ሐበሾች ለእነዚህ አቢይ ጉዳዮች በጊዜው አስፈላጊና ብቁ ሆነው (ቁጥር 3፣ መጽሐፍ ሁለት፣ ገፅ 5 እስከ 6) በመገኘት ለእስልምና ኃይማኖት መስፋፋት በከፍተኛ ደረጃ ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል። አዲሱ ትውልድ በእስልምና እውቀት እንዲበለፅግና ከጥርጣሬ ነፃ እንዲሆን ሳይታክቱ ሰርተዋል። ተሳክቶላቸዋልም።
”የሀዲስ ሕግና ደንብ በአግባቡ በምእመናን ይታወቅ፣ መሰረቱን ይጥልና ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ሐበሻ እንደ ሀገር፣ ንጉሥስ አስሃማ (ነጃሺ) እንደ ንጉሥና ሐበሾች እንደ ዜጋ ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል።” (ተመሳሳይ፣ ገጽ 8)
የሙስሊሙ አድማስ በመስፋቱ በተገኘው ከፍተኛ ገቢ መሪዎቹና ተከታዮቻቸው መንፈሳዊውን ፈር በመልቀቅ አለማዊ ምቾትና ድሎትን ማዘውተር በመጀመራቸው በሙስሊም መሪዎች መካከል አለማዊ የስልጣን ሽኩቻ ተከስቶ ነበር። ይህ ሁኔታ ነብዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) እና የቅርብ ተከታዮቻቸው ሲከተሉት ከነበረው አካሄድ የወጣ በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል ሱፍያ የሚባለውን መሰረተ ሀሳብ በማፍለቅ ማስተማር የጀመሩት የዘር ሀረጋቸው ከሐበሻ የሆኑ የኢስላም ምሁራን ይገኙበታል (ቁጥር 3፣ መጽሐፍ ሁለት፣ ገጽ 39) ተብሎ ከመገለፁም በላይ ከተወላጆቹም መካከል ለማሳያ ያህል የተወሰኑት ስማቸው ተዘርዝሯል።
ነብዩንና እስልምናን ለማጥፋት የተነሱ ምእራባውያንን በመከላከል በኩል የሐበሻች ሚና (ከገጽ 61 ጀምሮ)፤ የነብዩ ሙሀመድ የቅርብ አገልጋይ በመሆን የተወጡትን ሀላፊነት (ከገጽ 63 ጀምሮ) … ወዘተርፈ በመጽሐፉ (በተለይም፣ በቁጥር 2 ላይ) በሚገባ ቀርቧል። በተለይ በ13ኛውና በ14ኛው ክፍለ ዘመን የምእራቡ አለም በነብዩ እና እስልምና ኃይማኖት ላይ ያነጣጠረውን ጦርነት በመቀልበስ በኩል፤ በነብዩ ላይ የተከፈተውን ከፍተኛ ዘመቻ በማክሸፍ፤ የሙስሊሙን አንድነትና ክልል ለማፈራረስ ያደረጉትን ሙከራ በማኮላሸት … በኩል ሐበሾች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እደነበር (ቁጥር 3፣ መጽሐፍ ሁለት፣ ገጽ 8 ላይ) በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ ሲሆን፤ የምእራቡ አለም ምሁራንም በእስልምና ኃይማኖት ጉዳይ ለሁለት መከፈላቸውን፤ ምሁራኑ ከነበሯቸውና ሲያራምዷቸው ከነበሩት አስተሳሰቦች መካከል የተናገሩትንም ማሳያ ይሆን ዘንድ በስፋት (እስከ ገጽ 18 ድረስ) ቀርቧል።
በዚሁ መጽሐፍ ከአረቡ አለም ጋር ለነበረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሐበሻ (ኢትዮጵያ) ስልጣኔና የንግድ ስርአት፤ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቷና (ለምሳሌ የውሃ ሀብቷ)፣ ነባርና ቀዳሚ ታሪኳ … በአጠቃላይ፣ የሐበሾች አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልነበረ የተገለፀ ሲሆን፤ የሐበሾችንና የአረቦችን ፍልሰት (አንዱ ወደ አንዱ) በተመለከተም ተገቢው ስፈራ ተሰጥቶት ይገኛል።
ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ በብዙዎቻችን ስለሚታወቀው፣ ነገር ግን በጥልቀት ስለማናውቀው ቢላል በቁጥር 3፣ መጽሐፍ ሁለት፣ ገጽ 51 ”ቢላል ቢን ረባሕ አልሐበሽ (ረዓ)” በሚል ርእስና ሌሎችም በቀረበ ጽሑፍ ከምንጠብቀው በላይ በማብራራት የሐበሻና ሐበሾች አስተዋፅኦ ተዘክሯል። በ”ቢላልና አዛን” (ገጽ 66) ስርም እንዲሁ። በምስራቅ ወሎ፣ እርጎያ አካባቢ የተወለዱት ሼህ ሙሀመድ ራፊዕ አልቡሰይሪ ማንነትና ምሁራዊ አስተዋፅኦም ተገቢውን ስፍራ ይዞ እንመለከታለን (ከገጽ 99 ጀምሮ ይመልከቱ)።
ይህ ጽሑፍ የሐበሻና ሐበሾችን ሚና፣ ድርሻና አስተዋፅኦ በተመለከተ በዚህች የጋዜጣ ገጽ ላይ ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም ዋና ዋናዎቹን መነካካት ያስፈልጋል በሚል የተደረገ ሙከራ መሆኑን አስቀድመን ጠቆም አድርገናል። ከዋና ዋናዎቹ መካከል ደግሞ በቁጥር 3፣ መጽሐፍ ሁለት፣ ገጽ 76 ላይ በ7ኛነት ደረጃ ”በኢስላማዊ ስርጭቱ ላይ በተከሰተው አደጋ የሐበሾች ድርሻ” በሚለው ንኡስ ርእስ ስር የሰፈረው ሲሆን በቅኔው፣ በሥነፅሁፉ …፤ የተካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች (በተለይ ገጽ 79)ና የሐበሻና ዜጎቿ ተሳትፎና ድርሻ ቀርቧል። የሐበሻ ዝርያ (የዘር ግንድ) ያላቸው ባለቅኔዎች ከነ አበረከቷቸው ስራዎቻቸው በስፋትና አስደማሚ በሆነ መልኩ ተዘርዝሯል። (የአገራችን የሥነጽሑፍ ሰዎች እዚህ ጋ ይባንናሉ ተብሎ ይታሰባል – ጉዳዩን ለመመርመር።)
”ቢላል ቢን ረባህ ማን ነው?” (ገጽ 52) ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ መልስ የሚሰጠው ይኸው የመጽሐፉ ክፍል ከቢላል መልክና ቁመና ጀምሮ የቢላልን ሁለንተናዊ ይዞታ የሚገልጽ ሲሆን፤ ከአዛን ጥሪ ጋር በተያያዘ የቢላልን አስተዋፅኦ ያስረዳል። በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 132 ላይ ”ስለሐበሾች ክብር በነብዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) የተነገሩ ሀዲሶች” በሚለው ርእስ ስር ”ነብዩ ሙሐመድ ንግሥናን ለቁረይሽ፣ ዳኝነትን ለመዲና አንሷሮች፣ የአዛን ጥሪን ለሀበሻ ብለውም በተናገሩት መሰረት በእነኚህ ሶስቱ መሰረታዊ ሀሳቦች እስልምና ኃይማኖት መሰረቱን ጣለ።” የሚልም ሰፍሮ እናገኛለን።
በስራዎቻቸው የሐበሾችን ጀግንነት፣ ታማኝነት፣ አስተዋይነት፣ ቅንነት፣ መልከ መልካምነት … በተለያዩ ቦታዎች የሚገልፁት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፋሪስ በቁጥር 3፣ ገጽ 68 ላይ የሚነግሩን በርካታ ቁም ነገሮች ያሏቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ለአንባቢ ትተን የሚከተሉትን ብቻ እንጠቅሳለን፤
የመጀመሪያዋ የእውነት ምድር በመባል ሐበሻ ከመካ በፊት 16 አመት ትቀድማለች፤ ከእስልምና መመሪያዎች በተለይ ፆምና ዘካን ተግባራዊ በማድረግ ሐበሻ ከመካ በፊት በ6 አመት ትቀድማለች፤ ጥሪውን በመቀበል ከአለም ነገስታት የሐበሻ ንጉሥ ነጃሺ የመጀመሪያው ነው፤ የእስልምና ስደትን በማስተናገድ ሐበሻ የመጀመሪያ አገር ነች፤ ቁርአንን በግእዝ በማንበብ ሐበሻ የመጀመሪያዋ ነች፤ ሙሀመድ የሚለው ስያሜ ከነብዩ (ሰዐወ) ቀጥሎ ሐበሻ ለተወለዱ ህፃናት ነው መጀመሪያ የተሰጠው፤ በእስልምና ደንብ መሰረት የሟች ንብረት ውርስ ሥነስርአት በሐበሻ ነው የተጀመረው።
እንደ ፕሮፌሰሩ ግኝት እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎችም ተዳምረው ”ከሌላው [ዓለም] ዜጋ በበለጠ፣ በተለየ ሁኔታ ክብር የተጎናፀፍንባቸው ሲሆኑ በዚህም አላህ (ሱወ) በተለያዩ የቁርአን አንቀፆች ጠቅሷቸዋል።” እኛም ፕሮፌሰርን ለትጋታቸው እያደነቅን፤ ለልግስናቸው እያመሰገንን … ወደ ማጠቃለያችን እንሄዳለን።
የመጀመሪያዎቹ (እኤአ በ616) ወደ ሐበሻ የተሰደዱ 14 ሶሐባዎች ሲናገሩ “ሐበሻ ገባን፣ መልካም ጎረቤቶችም አገኘን፣ በሐይማኖታችን ምክንያት የሚደረግብን አንድም ተጽኖ አልነበረም። አንድም ችግርና መከራ አላጋጠመንም። የምንጠላው ነገርም አልሰማንም” ማለታቸው፤ ይህ አስተያየታቸውም በታሪክ መመዝገቡ ከማንም የተሰወረ አይደለም። በመሆኑም፣ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ሐበሻና እስልምና አንድና ያው እንጂ እንደሚደለቀው ድቤ አለመሆኑን እስላሙም ያውቃል፤ ክርስቲያኑም ያውቃል፤ ድፍን አለሙም ያውቃል፤ ሁሉም ያውቃል። ይህ ደግሞ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ የበለጠም ስሩን እየሰደደ ይኖራል እንጂ የትም ሆነ የት ያሉት አዛኝ ቅቤ አንጓቾቻችን እንደሚመኙልን በወሬ ወለደ ተሰናክሎ እዝችው የሚቀር አይደለም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015