የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየጊዜው በሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ባለድርሻ አካላትን በሚመለከቱ መመሪያዎች ላይ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ምክክር ያደርጋል። ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያም በጠቅላላ ጉባኤው አማካኝነት የጸደቁ መመሪያዎችን ወደ ስራ ማስገባትና ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓትን ለመፍጠር አላማው ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
በዚህም መሰረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አሰጣጥ፣ የአሰልጣኞች ደረጃ መስጫ መስፈርት(ስታንዳርድ)፣ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች ምልመላና የአሰልጣኞች ምርጫ፣ የአትሌቶች የግል የውጭ ውድድሮች ጉዞና የአትሌት ተወካዮች ፈቃድ እድሳት እንዲሁም የአትሌቲክስ ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት ስነምግባር መመሪያዎችን በሚመለከት ውይይት አድርጓል። በመድረኩ በቀረቡት መመሪያዎችም ላይ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ አድርገዋል።
የክልል ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች፣ የአትሌቲክስ ማህበራት እንዲሁም በስፖርቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላትና የስፖርቱም የጀርባ አጥንት መሆናቸው ተጠቁሟል። ይህንንም በተግባር እየተወጡት መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጄኔራል ደራርቱ ቱሉ ገልጻለች፡፡ ነገር ግን በ2014 ዓ.ም ፌዴሬሽኑ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ካጸደቃቸው በርካታ መመሪያዎች መካከል ከፊሉን እየሰራበት እንደሚገኝና በከፊል ደግሞ ተግባራዊ እንዳልሆነ ተናግራለች። ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል
የተወሰኑት ባለድርሻ አካላትን የሚመለከቱ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለም ጠቁማለች። በመሆኑም መመሪያዎቹ ወደ ተግባር እንዲገቡና በተሳለጠ መልኩ እንዲሰራባቸው ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሆኑበትን የምክክር መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ተግባር ላይ ካልዋሉ መመሪያዎች መካከል አንዱ የአሰልጣኞች ደረጃ መስጫ ስታንዳርድ ሲሆን፤ ይህም ያለፈው ዓመት በርካታ ውድድሮች የነበረበት ዓመት በመሆኑ እንዲሁም ፌዴሬሽኑም ለአሰልጣኞች አስፈላጊውን ስልጠና ባለመስጠቱ ምክንያት ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ ተጠቁሟል። ይህን ክፍተት ለመሸፈን ፌዴሬሽኑ በቅርቡ በሁለት ዙሮች ዓለም አቀፍ የአሰልጣኞች ስልጠና የሰጠው አሰልጣኞች ራሳቸውን አብቅተው መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችሉ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጻለች፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ፌዴሬሽኑ ያወጣቸውን አሰራሮችና መመሪያዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየቱ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ወቅት ወደፊት ለሚኖሩት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች አትሌቶችን ለማዘጋጀት እንዲሁም የኢትዮጵያን ውጤታማነት ለማስቀጠል ወሳኝ የሆኑ አሰራሮች የሚዘረጉበት እንደሆነም ተናግረዋል። በዚህም ላይ መወያየት አስፈላጊ ሲሆን፤ በብሄራዊ ቡድን ምርጫና ዝግጅት፣ በምልመላ፣ በአሰልጣኞች፣ በማናጀሮች እና ሌሎች በውድድር ወቅት የሚገጥሙ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉትም በዚህ መልክ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከታወቀችባቸው ነገሮች መካከል አንዱ አትሌቲክስ እንደመሆኑ ስፖርቱን ውጤታማ የሚያደርጉ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ባጠናቀቀችበት 18ኛው የኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በነበረው የተቀናጀ አሰራርና በተገኘው ውጤት ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጀነራል ደራርቱ ቱሉ ሽልማት ተበርክቷል፡፡ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳም 40 ግራም የአንገት ሃብል ወርቅ ለፕሬዚዳንቷ አጥልቀዋል። በመቀጠልም መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገውና በትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚካሄደው ግራንድ አፍሪካን ራዘን ለኢትዮጵያ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር የ120ሺ ብር ድጋፍ አደርጓል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015