ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተሰማ መንግሥቴ፣ ገብረየስ ገብረአምላክና ዘውዴ መታፈሪያ በተደጋጋሚ እየተገናኙ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መነታረክን እንደ መደበኛ ሥራ ወስደውታል። በግሮሰሪው የሚያስተናግዳቸው ይርጋለም አንዳንዴ በክርክራቸው ተመስጦ ሥራውን ይዘነጋል። በመሃል ሲያዙት እያቀረበ እርሱም ለውይይታቸው ማድመቂያ ሃሳብ ወርወር በማድረግ ተንፈስ ይላል። ንግግሩ ልክ ትልቅ የፖለቲካ የሕይወት ልምድ እንዳለው ሰው ይመስላል። አንዳንዴም የውስጥ አዋቂ አንዳንዴም ተንታኝ ይመስላል ብቻ ቅለ ባዶ እንደሚባለው አይደለም መሀል ሆኖም አስታራቂ ሃሳቦችን ይሰነዝራል።
ዛሬም ሶስት አረፋ የሞላው የድራፍት ብርጭቆውን ጨብጦ ወደ ጠረጴዛው እየተጠጋ የመነጋገሪያ አጀንዳ ጣል አደረገ። ‹‹የጥቂቶች ዕብሪትና ጥጋብ የሚፈጥረው ቀውስ አገሪቱን እንዳመሳት ቀጠለ አይደል!›› ሲል። ይርጋለም ቀና ብሎ በፈገግታ ዘውዴን እያየ ‹‹አይ አንተ፤ አንተ እኮ ከነቃላቶችህ እንኳን የግሮሰሪ አስተናጋጅነት የወረዳ ሊቀመንበርነትም ሲያንስህ ነበር ¡ ምን ያደርጋል? ዕድል ይሁን ጊዜ ብቻ ከሁለት አንዱ ይኸው የንግግር ብቃትህ ከዚህ ግሮሰሪ እንዳያልፍ ገደበው።›› ብሎ ዘውዴ ሲስቅ ገብረየስ እና ተሰማ ተከትለውት ፈገግ አሉ።
ዘውዴ ቀጠል አድርጎ ተሰማ እና ገብረየስን እያየ ‹‹ እውነቱን ነው፤ በጥቂቶች የሥልጣን ጥማት ምክንያት የደረሰው መከራ አላባራ ማለቱ ክፉ ቁጭት ውስጥ ይከታል። ይሔ ጉዳይ እኛን ብቻ ሳይሆን መላው ሕዝብን እያበሳጨ ነው ›› አለ። ተሰማ ግን ዘውዴን መቃውም በሚመስል ድምፀት ‹‹እንግዲህ መማረር ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም። ቁጭትም መጥፎ ነው። በቁጭት መብገን እና እያቀጣጠሉ መናደድ ስህተት ላይ ሊጥል ስለሚችል መጠንቀቅና ነገሮችን በትዕግስት ማየት አስፈላጊ ነው። ሰዎች የግድ ይህንን ጊዜ በትዕግስት ማለፍ አለባቸው።
በመንግሥት በኩል ከጦርነት ይልቅ ሰላም እንደተመረጠ በተደጋጋሚ ሰምተናል። ደግሞም አይተናል። ሆኖም ምን ያደርጋል? ለማየት የፈለገ አይንኑ ይገልጣል። ፍላጎት ካለ የፈለጉትን ማከናወን ይቻላል። ነገር ግን ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚመጣ ነገር አይደለም ። በወዲያ በኩል ያሉት ሰዎች ፈፅሞ የሰላም ፍላጎት የላቸውም። ምን ይደረግ? ›› አለ ተሰማ በጥያቄ አዘል አስተያየቱ።
ዘውዴ በተሰማ ንግግር የተናደደ ይመስላል። ‹‹በትዕግስት ማለፍ ብቻ ነው ትላለህ እንዴ?›› ሲል አፈጠጠ። አላቋረጠም በድጋሚ ቀጠለ ‹‹በኢትዮጵያ ሕዝብ መሀል ይህ ነው የሚባል ለግጭት የሚዳርግ ቅራኔ የለም። ታዲያ እንዲህ መጫረሳችን ሊያስቆጭ እና ሊያበሳጨን አይገባም ?›› ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ። ዘውዴ አምርሯል። ‹‹እነኚህ ሰዎች እኮ እየለያዩን ነው። ‹ለሰው ሰው ነው ልብሱ› ሰው የሚኖረው ከሰው ጋር ነው። የሰው ጉልበቱ፣ ድምቀቱና ህልውናው በሌሎች ሰዎች በጎ አመለካከትና ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ነው። አሁን ግን በምንም መልኩ አንዱ ለሌላው የማይሆንበት፤ አንዱ ለሌላው የማይኖርበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ።… ቀጠለ ንግግሩን።
የሕወሓት ጉዳይ ከአምናው ቢሻላት ቁንጣን ገደላት እንደሚባለው ሆኗል። ተሻለ ሲባል መልሶ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። ሁሉም ሥነሥርዓት መያዝ አለበት። ሥነሥርዓት ማስያዝ ይገባል፤ አለሁኝ ብሎ ያለቅጥ አግድም ተንሻፎ መሔድ ተገቢ አይደለም። ሁሉም ያልፋል፤ ለትውልድ የተበላሸ ታሪክ ማስቀመጥ እና አገርን መቀመቅ የሚከት ትውልድ አካል መሆን ግን ያሳምማል። ከዚህ በኋላ ለኢትዮጵያውያን ጦርነት አይገባቸውም። ለሁላችንም ጦርነት አይገባንም። በቃ…በቃ… ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ወተት ነው የማይጎረብጥ፣ ደግና ተስማሚ ነው። ነገር ግን ሥልጣን ወዳዶች የመከራውን ጊዜ እያረዘሙበት ነው። ተስፋ እያሳጡት ነው። ሁሉ ነገር በአጭሩ መቋጨት ሲኖርበት ተመዞ እንደማያልቅ ክር እየረዘመ ከማሰልቸቱም በላይ መናቆሩ፣ መተጋተጉ እየበረታና እየተባባሰ ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም ብሎ ታግሶ መቀጠል ይከብዳል። መበሳጨት የሰውነት ተፈጥሮ ነው። ማንም አልበሳጭም ቢል እንኳን እንዲህ የከፋ ነገር ሲያጋጥም መበሳጨት የግድ ነው።›› ሲል በዘውዴ ንግግር ተመስጦ ደንዝዞ የነበረው ይርጋለም ሌሎች እንግዶችን የማስተናገድ ስራውን ዘንግቶ ከደንበኞች በቀሰቀሰው ጭብጨባ ተደናግጦ ሮጠ ።
ገብረየስ የተቀዳውን ድራፍት ከተጎነጨ በኋላ በረዥሙ ተነፈሰ ‹‹እንግዲህ የአገሬ ሰው ውሃ ለሚወስደው በትርህን እንጂ እጅህን አትስጠው›› የሚባለውን አባባል ፈፅሞ የሚያውቀው አልመሰለኝም። ሕወሓትን ረድቶ ለማያድነው ራሱን ለአደጋ በማጋለጥ ሕይወቱን እስከ አሁን እየሰዋ መኖሩ ያሳዝናል። አሁን እንኳን በአጉል ተስፋ በመታለል እየከፈለ ያለውን ዋጋ ማቆም ቢችል ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር።›› ብሎ ገብረየስ አቀረቀረ።
የዛሬው ተረት አቅራቢ ተሰማ ነው። እንዲህ ሲል ቀጠለ ። ‹‹ አንዲት እማወራ ለባሏ ምግብ ስታቀርብ ብዙ ጊዜ የሚጠጣ ውሃ አብራ አታቀርብም። ባል በተደጋጋሚ ቢነግራትም ሚስት ዝንጉ በመሆኗ መልሳ ትረሳለች። የምታየው ከትሪው ላይ እንጀራ እና ወጥ መኖሩን አለመኖሩን ባሏ መጥገቡንና ‹በቃኝ ትሪ ከፍ አድርጉ› ማለቱን ብቻ ነው።
አንድ ቀን ምሳውን አቅርባ እንደልማዷ እህሉን የሚያወራርድበትን ውሃ አላመጣችለትም። ከትሪው ላይ የመጨረሻውን ጉርሻ ጠቅልሎ ሲጎርስ እንጀራ ለመጨመር ጓዳ ገባች። ባል ውሃ ልታመጣለት የገባች መስሎት ነበር። ነገር ግን ይዛ የመጣችው እንጀራ ነበር። ሲያንቀው የሚጠጣውን አጣ። አንገቱን በእጁ ይዞ አይኑን አፈጠጠ። ሚስት ግራ ተጋባች። መናገር አቃተውና አንገቱ ላይ የነበረውን እጁን አንስቶ ጆሮ ግንዷን በጥፊ አላሳት። ጩኸቷን አቀለጠችው።
ተንደርድሮ ማጀት ገባ። ሚስት ሊደበድባት መስሏት ወደ ደጅ ሮጠች። ባል ከእንስራ ውሃ ቀድቶ ጠጣና ተነፈሰ። ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ምን ሆነሽ ነው? ተብላ ተጠየቀች። እያበላሁት ደበደበኝ አለች። ባል ‹ደግ አደረግኩልሽ፤ ሁልጊዜ ያነሰኝን ትተሸ ያነቀኝን› ብልሽም አልሰማ ብለሻል። ስለዚህ ታንቄ ከመሞቴ በፊት በቃል ያልሰማሽኝን በዱላ ከሰማሽኝ ብዬ ነው›› አለ። ማንም ባል ላይ አልፈረደም። ጥፋትሽ ነው ብሏት ሁሉም ሔደ። የትግራይ ሕዝብ ጉዳይም ተመሳሳይ ነው›› አለ።
ተሰማ ስለተረቱ ብዙ ማብራሪያ ለመስጠት አላሰበም። ‹‹ነገር ግን ቅድሚያ መሰጠት ላለበት ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት እንጂ የማይሆን ድጋፍ እየሰጡ መሰዋት አይገባም። ሃላፊነትን ሳይወጡ ሁሉንም ከሌላው መጠበቅ አይቻልም። መንግሥት የትግራይን ሕዝብ መርዳት የሚችለው ሕዝቡም እርሱን ሲረዳው ነው። ሕዝቡ ሕወሓትን ከመጠበቅ ይልቅ የሚጠፋበትን ሁኔታ መፍጠር ሲችል ነው›› አለ። ለእዚህ ሃሳብ ገብረየስ ምላሽ መስጠት ከበደው።
ገብረየስ የነበረው አማራጭ ተሰማን ደግፎ መቆም ብቻ ነበር። ‹‹ጉዳዩማ ‹ያባበለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ ነበር። ምን ዋጋ አለው? ሕዝቡ አልገባውም። የሚያዋጣው ከሕወሓት ጋር መሰለፍ አይደለም። ሕወሓት ሲመቸው ጉልበት ለማሳየት ይንጠራራል፤ ሲያቅተው ድርድር በማለት ሕዝቡ ላይ ድራማ ይተውናል። ሕዝቡን የእድሜ ማራዘሚያ የቁማር መጫወቻ ካርድ አድርጎታል። ቁማሩን እበላለሁ ወይም እበላለሁ ብሎ የወጣቱን ሕይወት የጦርነት ግብር አድርጎታል። ይህ ግን እስከመቼ ይቀጥላል? ።
የስሥልጣን ነገር እንደሆነ ካልቀመሰ የደገመ ባሰ ነው። ሥልጣንን ያልቀመሰ ደጋግሞ ሥልጣን ከያዘው ሰው ሃሳቡ የተለየ ነው። ምክንያቱም ሥልጣንን የደጋገመ ራሱን ብቻ የሚያስቀድም ሌላውን የማያስብ ነው። ሥልጣኑን ከሚያጣ እንኳን ጥቂት ሰው ሰማይን ተቆጣጥሮ ያቆመ ምመሰሶ ወድቆ ሰማይ ምድሩ ቢገለባበጥ ይመርጣል። ሥልጣኑን ላለማጣት የሰዎችን ብቻ አይደለም የራሱንም ሕይወት ይሰዋል። ይህንን ሕወሓቶች ቢያደርጉትም ሊገርመን አይገባም። ደግሞም ወደ ፊትም በፍፁም የሚያቆሙ አይመስሉም። ችግሩ ሕዝቡ በቃን የሚለው መቼ እንደሆነ አለመታወቁ ነው።›› አለ።
ዘውዴ ለገብረየስ‹‹ እኔ የአንተን ሃሳብ ብጋራም ከአንተ የተለየ የምለው አለኝ። ኢትዮጵያ ለዘመናት ምንም ሳታጣ በድህነት ውስጥ ተዘፍቃ የኖረችበት ዋነኛው ምክንያት ሥልጣን የመውደድ እና ለዘላለም ለሥልጣን ሲባል ጦርነት ውስጥ በመግባት ብቻ ነው የሚል እምነት የለኝም። ሥልጣን ወዳድነት ያስከፈለው ዋጋ እንዳለ ቢሆንም ጉዳዩ የውስጥ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት በእውነተኛ ስሜት አገር እና ሕዝብን ማስቀደም ያለመቻል ችግር ይመስለኛል። በእውነተኛ ስሜት መነጋገር ቢቻል ሥልጣንንም መመጠን ይቻላል። ሥልጣንም ሆነ ምንም የተመጠነ ነገር አያስቸግርም። ጉሮሮ የሚውጠውን እጅ ይመጥነዋል፤ እኛ ግን መመጠን የቻልን አይመስለኝም።
ከጥንት ጀምሮ ስንነሳ ተፈፃሚነት ያለው ነገርን ስንገምት ትክክል የምንሆንበት ሁኔታ አነስተኛ ነበር። ሥልጣን ስንሰጥ ገደብ የለንም። ማንም ቢሆን ከሕግ በታች መሆኑን አስረግጠን አናስቀምጥም። ንጉሡን እንደፈጣሪ ሰግደንላቸዋል። ደርግንም ሆነ ሕወሓትን ከሕግ በላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርገን አግዝፈናቸዋል። ሕወሓት ከሶስት አስርት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የሰጠነው የሥልጣን ቦታ ከሕግ በላይ ነበር። ስለዚህ ሥልጣን መልቀቅ ተሳነው። ችግሩ ሥልጣኑን በልክ መጥነን ስለማናጎርስ ነው።
ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖርበት ሥርዓት ከማቆም ይልቅ ሁሉም ለራሱ ቤተሰብ፣ ለራሱ ጎሳ ወይም ዘር እንዲያደላ የሠራው ሕወሓት ብቻውን አይደለም። በጊዜው የተማረ እና በስራ ላይ የነበረ ሁሉ አነሰም በዛ ሚና ነበረው። እኛም የችግሩ አካል ነን። የቅርብ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የቆየ ታሪካችንም እንደሚያሳየው ጥያቄ ሲቀርብ በመነጋገር ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ጦር መነቅነቅ፤ አንዱን አሳንሶና አንኳሶ ሌላውን አሞግሶ እና አንግሶ የማቅረብ ልማድ አለን። ይህን ተከትሎ ጥያቄ ሲቀርብ ልዩነቶች ተከብረው በሥርዓት መነጋገር ሲቻል፤ እንዲህ እንደአሁኑ ጉልበተኛው ይነሳና ጦርነት ያውጃል። ተከታይ አይጠፋም፤ ከዛም ሕዝብ ያልቃል።
በኢትዮጵያ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተካሔደው ጦርነት ከተዋጊዎቹ በተጨማሪ ንፁኃን ወገኖች ለዕልቂትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል። በተከናወኑ ሁለት ዙር ጦርነቶች መቶ ሺዎች አልቀው፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከመፈናቀላቸው በተጨማሪ፣ መጠኑን ለመግለጽ የሚያዳግት የዚህች ድሃ አገር ሀብት ወድሟል። እኔ የምስማማበት አሁን ላይ የአገር ህልውና ጉዳይ የሚያሳስበን ከሆነ ማንሳት ያለብን ጥያቄ የሚካሄደው ጦርነት ማብቂያው መቼ ነው? የሚለው ነው። በኢትዮጵያ ምድር የጦረኝነት አባዜ ቆሞ ለውይይት ዕድሎች እንዲመቻቹና የጠላትነት ስሜት እንዲወገድ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መተባበር የምንችለው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ ወደፊት ማምጣት አለብን። ›› አለ።
ተሰማ በዘውዴ ሃሳብ በመስማማት ‹‹ችግሮች ሲያጋጥሙ ተቀምጦ ለመነጋገር የሚያስችል ባህል ማዳበር ያስፈልጋል። ይሔ በትክክልም ተገቢ ነው። ነገር ግን ማቆሚያው መቼ እንደሆነ የማይታወቅ የተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ለመቆየት ማሰብ በእርግጥም ጤነኝነት አይደለም። ታዲያ ምን ይሻላል?›› ሲል እርሱም ደገመና ጠየቀ።
ገብረየስ በበኩሉ ‹‹በኢትዮጵያ ከሚታወቁ በርካታ አኩሪ እሴቶች መካከል አንደኛው ግጭቶችን በሽምግልና መፍታት ነው። ይህንን የመሰለ ዘመን ተሻጋሪ የሚያኮራ እሴት ባለበት የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ቅን አሳቢ ዜጎች እያሉና በእጃቸው ላይም አገር በቀል መፍትሔ እያለ ወደ ሰላማዊ የውይይት ሜዳ ከመምጣት ይልቅ በጥቂቶች የፖለቲካ ፍላጎት በተቃኘ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኖ ጦርነቱ ባለበት ግለት እንዲቀጥል እና እውነተኛ ሰላም ሰፍኖ አገር ከገባችበት ቀውስ እንዳትወጣ መትጋት በታሪክና በመጪው ትውልድ ጭምር የሚያስጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በእኔ በኩል መፍትሔው መነጋገር ብቻ ነው።አሁንም መነጋገር፣ ወደፊትም መነጋገር… …መነጋገር ብቻ ነው መፍትሄው ›› ብሎ የሃሳብ ማወራረጃውን ከድራፍት ተጎነጨ።
ዘውዴ በገብረየስ ሃሳብ በመስማማት ‹‹ለመነጋገር ደግሞ ግፊት ማድረግ ያለበት መላው ኢትዮጵያዊ ነው። አገሪቱ ምንም ሳታጣ የነጣች ደሃ የሆነችው በሥልጣን ወዳዶች ምክንያት ነው ወይስ ምክንያቱ ሌላ ነው የሚለው ብዙ ምርምርን የሚጠይቅ ነው። ነገር ግን የየዘመኑ ፖለቲከኞች ችግሮቻቸውን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ቢችሉ ኖሮ፣ ዜጎች በቀን ሦስቴ መመገብ የሰማይ ያህል አይርቃቸውም ነበር።
አገራችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም የግብርናም ሆነ ሌላ ምርት ላኪ መሆን አያቅታትም ነበር። ነገር ግን ልዩነቶቻቸውን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ባቃታቸው ፖለቲከኞች ምክንያት እንኳንስ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ቀርቶ በቀን አንዴ በልቶ ማደር ብርቅ እየሆነ ነው። በአፍሪካ በእንስሳት ሀብት አንደኛ ነች እየተባለ የሚወራላት ኢትዮጵያ እነ ሥጋ፣ ቅቤ፣ ዶሮ፣ እንቁላል… ሰርግ ጥሪ ላይ ሲገኙ የሚበሉ ምግብ እየሆኑ ነው።
ይህ ትውልድ ከዚህ አሳዛኝ ታሪክ በመማር የራሱን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ በበጎም ሆነ በክፉ የሚታወሱ ታሪኮች አሉ። እነሱ ለአዲሱ ትውልድ የመነታረኪያ አጀንዳ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በሥልጣኔ ወደፊት የገፉ አገሮች ግስጋሴያቸውን ያሳመሩት ከበፊቱ መልካሙን በመውሰድ፣ አስከፊውን ደግሞ ለታሪክ በመተው ነው። የራስን ግዳጅ ሳይወጡ የቆየ የሆነም ያልሆነም ትርክት መፍጠር የደካማ ፖለቲከኞች ተግባር መሆኑን በመገንዘብ፣ አዲሱ ትውልድ የራሱን ደማቅ ታሪክ የሚያጽፈው የአገር ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ጦርነት ሳይሆን መስማማት እና መግባባት፤ ርሃብ ሳይሆን ጥጋብ እና ዕድገት የሚታይባት አገር መሆን አለባት። ለዚህም ዋነኛው መፍትሔ ጦርነት ሳይሆን ውይይት ነው።›› ብሎ ዘውዴ ንግግሩን ሳይጨርስ ሁሉም ብርጭቋቸውን አንስተው አጋጩ ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015