በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1944 በአዲስ ዓመት ማግስት የታተሙ ጋዜጦችን ቃኝተናል። ከተመለከትናቸውና ቀልባችንን ከሳቡ የጋዜጣው ዘገባዎች መካከል የእንግሊዙ ንጉሥ ጆርጅ እረፍትና እሳቸውን ተክተው ወደ ንግስናው የመጡት ንግስት ኤልሳቤጥ ጉዳይ አንዱ ነው። በቅርቡ ያረፉት ንግሥት ኤልሳቤጥ በወቅቱ ወደ ንግስና ሲመጡ በጋዜጣው የፊት ሙሉ ገፅ ሽፋን አግኝቶ ነበር። ከጋዜጣው ዘገባ መካከል የንጉሡን ዕረፍት የተመለከተውን የመጀመሪያ ዜና ለዛሬ መርጠን የምናስታውሳችሁ ሲሆን፣ የውጭ አገር ሰዎች በጅማ ቡና ገበያና በጫካው ቡና መደነቃቸውን በዚህም የንግድ ቤት ለመክፈት እንደወሰኑ የሚነግረንን ዘገባም መርጠናል። በተጨማሪም በያኔው ዘመን ምርትና ወንጀል ነክ እንዲሁም አደጋ ተኮር ዘገባዎችንም እንደሚከተለው አካተን ቀርበናል።
ስለ ግርማዊ የእንግሊዝ ንጉሥ ጆርጅ ዕረፍት
ጥር ፳፰ ቀን ከሬውተር
ሎንዶን
ግርማዊ ንጉሥ ጆርጅ ዛሬ ጥር ፳፰ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ.ም ጠዋት በመኝታቸው ላይ ሳሉ በማረፋቸው የበከር ልጃቸው ልዕልት ኤልሳቤጥ ወዲያውኑ የእንግሊዝ ንግሥት ሆነዋል።
የንጉሥ ጆርጅ ዕድሜያቸው ፶፮ ዓመት ነው። ታላቅ ወንድማቸው ኤድዋድ ስምንተኛ በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም አልጋውን በለቀቁ ጊዜ ግርማዊ ንጉሥ ጆርጅ ፮ኛ በእንግሊዝ መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀመጡ።
ዕድሜያቸውን ሙሉ እንደ አንድ ተራ ሰው ለመሆን ይሞክሩ በነበሩት ንጉሥ ዕረፍት የእንግሊዝ ሕዝብ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል። ሕዝቡ ንጉሡ ብዙ ጊዜ ታመው ከባድ የሆነ ኤፕራሲዮን ከተደረገላቸው በኋላ ጤናቸው ይመለስላቸዋል በማለት ተስፋ ያደርግ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚስተር ቸርችል የንጉሡን ዕረፍት እንደ ሰሙ ወዲያውኑ ምክር ቤቱ እንዲሰበሰብ አድርገው ፤ ምክር ቤቱ ስለ ሕዝቡ ሐዘን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርጉት መግለጫ ለመስማት ከሰዓት በኋላ ስብሰባ አድርጎ ነበረ።
ልዕልት ኤልሳቤጥ የኮመንዌልዝ አገሮችን ለመጎብኘት ከባለቤታቸው ከፕሪንስ ፊሊፕ (የኤዲንበራካዱ) ጋር በመንገዳቸው ላይ ሳሉ ለጊዜው በሚገኙበት ኬንያ ውስጥ ናሪያ በምትባል ስፍራ የንጉሡ መሞት ወሬ ደረሳቸው። ዕድሜያቸው ፳፯ ዓመት የሆናቸው ልዕልት ከአምሳ ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግሥት ሆኑ። ንግሥት ቪክቶሪያ ያረፉት በ፲፰፻፺፫ ዓ.ም ነው።
(የካቲት ፩ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን )
የእሳት አደጋ ጠባቂዎች ትጋት
መስከረም ፩ ከጠዋቱ ፫ ሰዓት ተኩል ሲሆን በአቡነ ጴጥሮስ መንገድ በቤንዚን ማደያው አጠገብ ከፍ ያለ የእሳት አደጋ ተነስቶ የ፩ኛና የ፪ኛ እሳት አደጋ ተጠባባቂዎች በፍጥነት ደርሰው በኃይል ተከላክለው ቃጠሎውን አጥፍተውታል። አደጋው የተነሳው ከቤንዚን ማደያው አቅራቢያ ከሰል ነጋዴዎች በመኖራቸውና እሳትም ከዚያ ውስጥ በማንደዳቸው ሲሆን፤ እንዲሁም ቤንዚን ቀጂዎች በቆርቆሮ እየቀዱ ከዚያው ቤት በማስቀመጣቸው ነው።
ቤንዚን ይዞ ወደ ከሰሉ እሳት ቀርቦ ለቃጠሎው መነሻ የሆነው ሰው በጣም ቆስሎ ከራስ ደስታ ሆስፒታል ሲገባ የእሱው አባሪ የሆኑ ሦስት ልጆች ጥቂት ቆስለው ነበርና የእሳት አደጋ ተጠባባቂዎች በመድኃኒት ወዲያውኑ አክመዋቸዋል። ቁስሉም ለጉዳት አይሰጣቸውም።
የእሳት አደጋ ተጠባባቂዎች በፍጥነት ባይደርሱ ኖሮ ይህ አደጋ በቤንዚን ማደያ አጠገብ በመሆኑ አስጊ ሳይሆን አይቀርም ነበር። ይልቁንም በማዘጋጃ ቤት አማካይነት አሁን በቅርብ ጊዜ የመጡት የእሳት አደጋ መጠባበቂያ መኪናዎች በዚሁ አደጋ ላይ አገልግሎታቸውን በማሳየታቸው በሕዝቡ ዘንድ ተመስግነዋል።
ስለዚህ ይህን የመሰለ ከፍ ያለ አደጋ በከተማው እንዳይደርስ ከሰል ነጋዴዎች ከቤንዚን ማደያ አቅራቢያ እንዳይገኙ ማድረግ የሚገባ ነው።
(መስከረም 18 ቀን 1944 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን )
በጥፋታቸው ስለተቀጡ ወንጀለኞች፤
ከወንጀል ምርመራ ክፍል
የተገኘ ሁኔታ
፩ኛ ጥላሁን ከበደ፤ ፪ኛ ቶሎሣ ገብረማርያም፤ ፫ኛ ተክሌ ወልደማርያም፤ ፬ኛ ዘውዴ ንጉሤ፤ ፭ኛ ገበየሁ ካሣ፤ ፮ኛ መንግሥቱ ደስታ፤ ፯ኛ ከበደ ኃይሉ፤ ፰ኛ ደስታ በላይ፤ ፱ኛ አረሩ ገብረ ወልድ ከ፩ኛ እስከ ፱ኛ ተራ ቁጥር የተከሰሱት ወንጀለኞች ከነሐሴ ወር ፵፪ ዓ.ም ጀምረው በየጊዜው በከተማው ውስጥ እየተዘዋወሩ ቤት እየሰበሩና ግድግዳ እየማሱ በመስረቅ ከቆዩ በኋላ ነሐሴ ፳፪ ቀን ፵፫ ዓ.ም በወንጀለኛ ምርመራ ፖሊሶች ትጋት ተይዘው በምርመራ የሰረቁባቸውን ሰባ አራት ቤቶች መርተው ተቀባዮቻቸውን አስያዙ።
ከዚህ በኋላ ጥቅምት ፲፭ ቀን ፵፬ ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነትና የክህደት ቃላቸውን ተጠይቀው ጉዳዩ እንደገና ለጥቅምት ፳ ቀን ፵፬ ዓ.ም ተቀጠረ።
በዚህ ቀን በ፮ኛው ቁጥር የተጠቀሰው ብቻ ታሞ ሲቀር ፰ቱ ወንጀለኞች እያንዳንዳቸው ፪ ሁለት ዓመት እሥራትና አርባ ፵ ጅራፍ ግርፋት ተፈርዶባቸዋል። የነዚሁ ወንጀለኞች ተቀባይ ሆነው የተገኙ ሰላሣ አንድ ሰዎች በተለይ ፋይል ተከፍቶ በፍርድ ላይ ናቸው።
(ኅዳር 14 ቀን 1944 ከወጣው አዲስ ዘመን )
የቡና አዝመራ
በከፋ ጠቅላይ ግዛት ቡና የሚለቀምበትና የሚሸጥበት ወራት አሁን በመሆኑ በያሉበት ገበያዎች ተሟሙቀው ካሚዮኖቹም ሲመላለሱ ይታያሉ። በተለይ ጅማና አጋሮ ሐሙስና ማክሰኞ ከየአገሩ ገበያተኞችና ነጋዴዎች የሚጎርፉበት ቀን ስለሆነ በዚህ ገበያ ቀን በመኪናና በሰው ብዛት የተነሣ መተላለፊያ አይገኝም።
ብዙ የውጭ አገር ሰዎች የዕረፍታቸውን ጊዜ ለማሳለፍ ጅማ ከተማ በትልቁ ሆቴል አርፈው በአገሩ ውስጥ እየተዘዋወሩ በቡናው ጫካና በአገሪቱም ሀብታምነት፤ በእርሻውና በየኮረብታዎቹ ውበት መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ብዙ ነጋዴዎች ከአዲስ አበባ፤ ከሌላውም አገር ቤት እየመጡ የንግድ ቤት ለመክፈት ፈቃድ ጠይቀዋል። በአዲስ አበባ የሚገኙ ትልልቅ ንግድ ቤቶች ቅርንጫፋቸውን ለማቋቋም ሰዎችን ልከዋል። በዚህ አኳኋን የጅማ ከተማና ንግዱ እየተስፋፋ የሚሔድ መስሎ ይታያል።
የጅማ ተላላኪያችን ።
(ጥር 17 1944 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2015