ኢሬቻ አንድ ሰው በመጀመሪያ ከራሱ ጋር ከዚያ በቅርቡ ካለው ከጎረቤቱ ጋር ከዚያም ከማኅበረሰቡ ጋር በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር እርቅ የሚያወርድበት በዓል መሆኑ ይነገራል። ሰዎችን በማሰባሰብ አንድነትን የሚሰብክ የሰላም ተምሳሌት መሆኑም ይጠቀሳል ። የሰላም ተምሳሌት የሆኑት ሴቶች “መሬሆ”“ መሬሆ ” በማለት ትክሻ ለትከሻ ተቃቅፈው ለፈጣሪያቸው ውዳሴ ያቀርቡበታል።
ውዳሴውን የሚያቀርቡት በተለያዩ አካባቢ ባሉ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ተውበውና አሸብርቀው ነው ። ከቱባው ባህል መገኛ አንዱ በሆነው አርሲ የመጣችውና ኢሬቻን በአዲስ አበባ ስታከብር ያገኘናት ወጣት ፌቨን የኋላሸት ኢሬቻ የሰላም፤ የፍቅርና አብሮነት በዓል መሆኑን ትናገራለች።
ወጣት ፌቨን ኢሬቻን ሴቶች እርስ በእርሳቸው ትክሻ ለትክሻ ተቃቅፈው ለምለም ሳርና አደይ አበባ በመያዝ “መሬሆ” “መሬሆ” እያሉ በሐይቅ፤ በወንዝ፤ በምንጭና በውሃ ዳርቻ እንዲሁ እንደ አዲስ አበባው በደመቀ የሚያከብሩበት ስርዓት ላይ የመሳተፍ ዕድል ማግኘቷንም ታወሳለች።
‹ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከገዳ ሥርዓት ከወረሳቸው ትሩፋቶች አንዱ ነው። የክረምቱን ድቅድቅ ጨለማ አልፎ የፀደይ ብርሃን ወቅት ሲገባ ክረምቱን ያሳለፈ፣ ሰብልን ያበቀለ፣ ማሳውን ያለመለመ ፈጣሪውን ማመስገኛ ስነስርዓት ይካሄድበታል። እርቅ፤ አንድነት፤ ሰላምና መተሳሰብ በስፋት ይሰበክበታል ። መጀመሪያውኑ ሰው ከራሱ ጀምሮ በየደረጃው እርቅ ሳያወርድ ኢሬቻ አይከበርም›› የምትለው ወጣቷ በኦሮሞ ባህል ዘንድ ከፍተኛ ሚና ያለውና ሴቶች መሪ ተዋናይ የሆኑበት ስንቄ ወይም ሲቆ የተሰኘው ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት የሚተገበርበትም እንደሆነ ታነሳለች።
ሲንቄ ሆሮሬሳ ከሚባልና ከሌሎች ከማይነቅዙ ከተመረጡ የዛፍ ዓይነቶች ተቆርጣ የምትዘጋጅ ቀጥ ያለችና ያልተጣመመች ዘንግ በትር ስትሆን የጋብቻ ዕለተ እናት ለምትድራት ልጇ የምትሰጣትና ልጅቱም እስከ ዕለተ ሞቷ የማትለያት የክብር መገለጫ ስጦታዋ ናት ትላለችም።
በመሆኑም ኢሬቻ ሴቶች ከዚሁ ጋር በተያያዘ በልዩ ሁኔታ ክብራቸውን የሚያስጠብቁበት፤ ሰላምን የሚያወሩድበት፤ የሚሰብኩበት፤ ፈጣሪን የሚለምኑበት በርካታ ተግባራትን የሚከውኑበት ባህላዊ ስርአት ነው ማለት ይቻላል። በተለይ ከዚሁ ሴቶች መሪ ተዋናይ በሆኑበትና ሚናቸውን በሚያጎላው ሲንቄ የተሰኘ ስያሜ በኦሮሞ ሕዝብ ሃደ ሲንቄ ተብለው ልዩ ክብርና ቦታ የሚሰጣቸው እናቶች በኢሬቻ በዓል ፈጣሪን ከማመስገን አልፈው ሕዝቡንና አገርን ይመርቁበታል። በበዓሉ ላይም ሕዝቡ ጥላቻን እንዲያርቅ እርስ በእርስ መተሳሰብን፤ አንድነትን፤ ሕብረትን እንዲያጠናክርና በጋራ በመቆም አገሩንና ወገኑን እንዲጠብቅ የየራሳቸውን መልዕክት ያስተላልፋሉ። ምስጋናንና ሰላምን የሚሰብኩና የሚያመለክቱ ሲንቄን ጨምሮ ትኩስ ወተት፤ ጭኮ፤ ለምለም ቄጤማና አበባ ይዘው ይመጣሉ። በዓሉ ለበርካታ ሺህ ዘመናት በዚህ መልኩ ሲከበር እንደቆየ ለቀጣዩ ትውልድም በዚህ መልኩ ማስተላለፍ እንደሚገባ በማሳሰብ ያከብሩታል።
ወጣቷ እንደምትለው ከዚህ አንፃር እሷና ሌሎች ወጣት ሴቶች በዓሉን ለማስቀጠልና ባህሉን ሳይለቅ እንዲከበር ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል ።
ስለ ኢሬቻ በዓል ብዙ ነገሮች ሲወሩ መኖራቸውን ያስታወሰችው ወጣቷ አንዱ በዓሉን ከባእድ እምልኮና ከተለያዩ ነገሮች ጋር ተያይዞ ሲነዛ የነበረው ወሬ መሆኑን እንደማሳያ ታነሳለች። አንዳንድ ሴቶች በተለይም በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ እንዲሁም የቀለም ትምህርት ያልቀሰሙና ስለ በዓሉ ብዙም ግንዛቤ የሌላቸው እናቶች ዛፍ ቅቤ ሊቀቡ፤ በሥሩም ቡና ሊያፈሉ፤ በስለታቸው መሰረትም ሐይቅ ውስጥ ሽቶ ወይም አረቄ ይረጫሉ ሲባል መስማቷንም ታወሳለች። ይሄ እየተጋነነ ወሬ ነው ባይ ነች ።
በተለይ በቢሾፍቱ አርሰዲ ሐይቅ የሚከበርበት ሁኔታ ቆሪጥ ከሚባል ያልተጨበጠ መንፈስን እንደማምለክ ተደርጎ በመውሰድ በዓሉ በሀሜት የሚብጠለጠልበት ሁኔታም አለም ትላለች ። እንደ ፌቨን እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከሌሎች ሰዎች ብቻ ሳይሆን የሚንፀባረቀው ከራሱ ከአንዳንድ የኦሮሞ ተወላጅ ጭምር ነው። አሷም ይሄንን እየሰማች እንደ ማደጓ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ነበራት። ይሄ ኢሬቻ በስፋት እንዳይከበር፤ እንዳይተዋወቅ፤ የራሱ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል ብላ ታስባለች። በቱሪስት መስህብነቱ ለኦሮሚያ ክልልም ሆነ ለአገር ሊያስገኝ የሚችለውንም ከፍተኛ ገቢ ሳያስገኝ ቀርቷልም ስትል ተፅዕኖውን ትገልፀዋለች ።
እንዲህ ዓይነቱ ከበዓድ አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ሀሜት በዓሉ ምንነቱ ጎልቶ እንዳይንፀባረቅም ተፅዕኖ አድርጓል። ‹ይቅርታ አድርጉልኝና የበዓሉ ባለቤት በነፃነት እንዳያከብረው ወይም እንዲሸማቀቅ ሳያደርገውም የቀረ አይመስለኝም › ትላለች ወጣቷ ። አሁን ላይ በተለይም በአዲስ አበባ መከበር ከጀመረ ወዲህ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እየተቀየረ መጥቷል። እሷን ጨምሮ ብዙዎች በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ጥሩ ግንዛቤ እያገኙ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ ሲከበር ኢሬቻ ከእንዲህ ዓይነቱ ባአድ አምልኮ ጋር በፍፁም የማይገናኝ ባህል መሆኑ ታውቆና ተረጋግጧል ማለት ይቻላል ስትል ትናገራለች።
ባህል የሆነው ኢሬቻ እሷንና ሌሎች ወጣቶችን ጨምሮ በበርካታ ማህበረሰብ ዘንድ ተገቢ ግንዛቤ ተይዞበታል ። እነሱም በበዓሉ ዙርያ አንዱ ተልኳቸው በሕዝቡ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ትክክለኛ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲፈጠር ማስቻል ነው። በዘንድሮ በዓልም በተለይ በአዲስ አበባ ለአራተኛ ጊዜ በተከበረው ወጣቶች ይሄን ግንዛቤ ፈጥረናል ብላ ታስባለች። በመሆኑም እንደማንኛውም በዓላት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ ወጥተው ሊያከብሩት መቻላቸውን ለመመልከት በቅተናልም ብላለች።
ሥራውን ሲያከናውኑ የቆዩት በዋነኝነት በሴቶች አማካኝነት ለበዓሉ ከሚደረግ የባህላዊ ምግብና መጠጥ ዝግጅት ጎን ለጎን መሆኑንም ገልፃልናለች። ለበዓሉ በሴቶች በርካታ ባህላዊ መጠጦችና ምግቦች እንደሚዘጋጁና ሴቶች በዚህ ወቅት ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ በሥራ እንደሚጠመዱም አውግታናለች። በወቅቱ ከሚዘጋጀው ምግብ በማር ብቻ የሚጣል ጠጅ ዋናው እንደሆነም አውግታናለች። ጠጁን የሚጥሉት በአካባቢው በጠጅ ሙያ አንቱ የተባሉ እናቶች እንደሆኑና ጠጅ የመጣል ዝግጅቱም በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብሎ እንደሚጀመርም አጫውታናለች።
በአብዛኛው ይሄ ደረቅ ጠጅ እንደ አባ ገዳ ላሉ ለተከበሩና በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ለሚሰጣቸውና አንቱ ለተሰኙ ሰዎች እንዲሁ በአዋቂ ዕድሜ ደረጃ ላሉ የሚዘጋጅ መሆኑንም ነግራናለች። በበዓሉ በተለይ ለወጣትና ታዳጊ ልጆች እንዲሁም የማር ብርዝ እንደሚዘጋጅ ታነሳለች። ለኢሬቻ በዓል ከሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች መካከል ቡነቀላ፤ የአንጮቴ ገንፎ ፤ ቂንጬ እንደሚያዘጋጁና ሁሉም የሚዘጋጁት በቅቤ እንደሆነም አጫውተናለች። ቡነቀላ ምግብ ከጠጅ ጋር አብሮ እንደሚቀርብም ታስረዳለች። የከብት እርድ ስርዓት እንደሚከናወንም ነግራናለች።
ኢሬቻ ከኢትዮጵያውያን ውጪ ሌሎች የዓለም አገራት የሌላቸው ባህል እንደመሆኑ በአንድነት ማክበርና ለሌሎች ዓለማት ማስተዋወቅ ይገባል። ባህላዊ ቅርፁን ሳይለቅ በቱሪስት መስብዕነቱ እንዲቀጥልና የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆንም በአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ኢንዲወጣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም መልዕክት ታስተላልፋለች።‹‹ አያቶቻችን በዓሉን በዚህ በባህላዊ መልኩ ነበር የሚያከብሩት እኛም ዘንድሮ በዚሁ መልክ ነው ያከበርነው ። ይሄ በጎ የምስጋና ስርዓትም ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ይቀጥላል›› ስትልም አስተያየቷን ትቋጫለች ወጣቷ የአርሲ ተወላጅ ፌቨን ።
‹‹ተተኪ ወጣት ሴቶች የባህላዊ ምግብ ዝግጅቶቹን ከእኛ ከእናቶችና ከአያቶቻችን መማር አለባቸው። ምክንያቱም አሁን በዓሉ ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ እንደ አገር ብሎም የዓለም ኃብት ሆኗል ››ያሉን ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሀናን ታዬ ናቸው ።
እንደ ወይዘሮዋ ሴቶች ከእናቶቻቸውና አያቶቻቸው የወረሱትን የኢሬቻን በዓል ባህላዊ ምግብ ዝግጅት ለተተኪ ወጣት ሴቶች ያሳዩበት ሁኔታ አለ። ይሄ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች በ121 ወረዳዎች ወርዶ በመተግበሩ ኢሬቻ በዓል ባህሉን ጠብቆ ለዓለም ቅርስነት በሚመጥን መልኩ መከበር አስችሏል። በዚህ መልኩ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ባህላዊ ምግብና መጠጥ በውጪ ቱሪስቶች መስህብ ሆኖ መደነቅም ችሏል። በተለያየ የኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ባህላዊ አለባበሶችም የበዓሉ አንዱ አካል ነበሩ። ወንዶችና ሴቶች፤ ወጣቶችና ህፃናት በተለይም አረጋውያን በዚህ ዓይነቱ በዓመት አንዴ አንዳንዴም ሁለቴ በሚለበስ የባህል ልብስ እንዲያሸበርቁና አደባባይ ወጥተው በዓሉን እንዲያከብሩት ተሰርቷል። ምክንያቱም አሁን በዓሉ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያና የዓለም ሆኗልና ነው። ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ የተለያየ ብሄር ቅልቅል ባለው ሕዝብ በዓሉ የሁላችንም ነው በሚል ስሜት መከበሩንም አስተውለዋል።
ክትፎ፤ ጭኮ ፤ አነባበሮ፤ በቅቤና በርበሬ የተለወሰ ቆሎና በሌሎች የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች ዝግጅት በዓሉ መከበሩን ያወሱት ሌላኛዋ እንግዳ ወይዘሮ ኩሪ ኃይሉ እንደተናገሩት በዕለቱ እያከበሩት ያለው የኢሬቻ በዓል የመጀመሪያቸው አይደለም። ኢሬቻን ለረጅም ጊዜ ሲያከብሩ ቆይተዋል። በዓሉ በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ መከበር ከጀመረ አራተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን እሳቸው አራቱንም ዓመት ተገኝተው አክብረውታል። በዓሉ የሚከበረው የኦሮሞ ቤሄረሰብ ባህል ብቻ በመሆኑ ሳይሆን የኢትዮጵያውያኖች ባህል ጭምር ሆኗል ብለዋል።
ወይዘሮ ኩሪ ኃይሉ እንደ ብሄረሰቡ አባልነታቸው ይሄ ግንዛቤ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዲሰርጽና በዓሉን በነቂስ ወጥቶ እንዲያከብር መሰራት አለበት ይላሉ። ኢሬቻ ማለት ሰላም፤ ፍቅር፤ አንድነትና ወንድማማችነት እህትማማችነት ማለት ነው። የኦሮሞ ቤሄረሰብም ከጨለማው ዘመን ወደ ብርሃናማው ዘመን በሰላም ስላሸጋገረው አምላኩን የሚያመሰግንበት፤ እርጥብ ቄጤማ ይዞና ሐይቅ ዳርቻ ሆኖ ለአምላኩም ምስጋናውን የሚያቀርብበት ነው። መጪውና ቀሪው ዘመኑ የተባረከና የተቀደሰ እንዲሆን ፈጣሪውን የሚለምንበትም በዓል ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ኩሪ እንደነገሩን ለዚህ በዓል ሴቶች በልዩ ሁኔታ ዝግጅት አድርገናል። በአዲስ አበባ ዙሪያ በአራቱም በሮች በመግባት ወደ መስቀል አደባባይ የሚጓዙትን እንግዶችን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅቶች በመደረጋቸው የመጡት እግዶች ተደስተው ተመልሰዋል። እኛም እንዳስተዋልነው በዓሉን ለማክበር ወደ መስቀል አደባባይ የሚጎርፈውም ሆነ ከመስቀል አደባባይ በዓሉን እያከበረ የሚመለሰው የተዘጋጀውን ማዕድ በጋራ እንዲመገብ ተደርጓል። በአንዳንድ የሰው ንክኪ በሚበዛባቸውና ለኮረና መተላለፍ መነሻ ይሆናሉ በተባሉ ቦታዎች ደግሞ ዳቦ፤ ዳቦ ቆሎ፤ ቆሎ፤ ውሃና ሌሎች ደረቅ ምግቦችን የሚመገቡበት ሁኔታ እንዳለ መታዘብ ችለናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2015