ባህላችን ፈጣን የሆነ ለውጥ እያስተናገደ ነው። ግሎባላይዜሽን(ሉላዊነት) ቀስ በቀስ ተጽእኖውን እያሳረፈብን እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ አኳኋናችን በሙሉ ተቀይሯል፡፡ የአለባበስ ባህላችን በጣም ተቀይሯል፡፡ አነጋገራችንም እንደዚያው፤ አመጋገባችንም እንደዚያው ሌላውም ሌላውም…፡፡ በየፈርጁ በጣም ብዙ ለውጦች እየተከሰቱ ነው፡፡ እነዚህ ለውጦች የት እንደሚያደርሱን አይታወቅም፡፡ ምን እንደሚያስከትሉብንም ለመረዳት ከመሀል ነጠል ብሎ ወጥቶ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው ግን ለውጦቹ በጣም ግዙፍ እና ፈጣን ስለሆኑ ቆም ብሎ ማሰቢያ እድል አልተገኘም፡፡
የሆነ ሆኖ የዛሬው ጉዳያችን ስለ ለውጥ ለማውራት ሳይሆን ለውጥ ካጠቃቸው ባህሎቻቸችን አንዱ የሆነውን የለቅሶ ባህላችንን ለመቃኘት ነው፡፡ የለቅሶ ባህላችን ሳይታሰብ ዲጂታል እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ኦንላይን እየሆነ ነው፡፡ ሲለቀስ ፤ ሲቀበር ፤ የማጽናኛ ስብከት ሲሰጥ ወዘተ…ሁሉም ነገር በቀጥታ ስርጭት በማህበራዊ ሚዲያ የሚታይ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ አሁን ላይ ብዙ ሰዎች የሚያውቋቸው ወይም የሚወዷቸው ሰዎች መሞታቸውን የሚረዱት በፌስቡክ ነው፡፡ ለቅሶ የሚደረሰውም እዚያው ፌስቡክ ላይ ነው፡፡ እርም የሚወጣውም እንደዚያው፡፡
እርግጥ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ቴክኖሎጂን መጠቀም ምንም ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን ሀዘን ደግሞ ግላዊ እና አካላዊ ስሜት ነው፡፡ ማልቀስ ፤ መታመም ፤ መጨነቅ ፤ መደንገጥ ፤ የአካል አለመታዘዝ እና መሰል ስሜቶች ይኖሩታል፡፡ ሰዎች በሀዘን ወቅት ደግሞ እነዚህን የስሜት ውጣ ውረዶች እንዲያልፉ እድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን ስልክ እና ካሜራ አጠገባቸው ተደቅኖ እንዴት ብለው ይህን ነገር ይወጡት፡፡ የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ቀብር ቀን ያየነው ይሄንን ነበር፡፡ ካሜራ ይዘው ከሚራወጡት ብዙ ሰዎች በተጨማሪ ሁሉም ስማርት ስልክ የያዘ ሰው በሙሉ የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ እና ተንቀሳቃሽ ምስል ቀራጭ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው ሞቶ ቀብር ላይ ያለን ሳይሆን አንድ የሽልማት ፕሮግራም ላይ የታደምን ነበር የሚመስለው፡፡ አንዳንዶቹም እዚያው ሀዘንተኞች አጠገብ ቆመው በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፉ ላይክ እና ሰብስከራይብ አድርጉን ሲሉ ሁሉ ይሰማ ነበር፡፡ ያሳፍራል፡፡ ሰዎች ሀዘናቸውን እንዲወጡ የተወሰነ ክፍተት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ፈረንጆቹ በዚህ ብዙ ስለተማረሩ እና ልምድም ስለቀሰሙ ለቅሶ ሲኖርባቸው አንዳንድ የለቅሶውን ጉዳዮች ከየትኛውም አይነት ሚዲያ እይታ የተከለከለ እንደሆነ ያሳውቃሉ። እኛም ጋር እንዲህ አይነት ነገር ሊለመድ ይገባል። አልቅሰህ እንኳ በማይወጣልህ ሀዘን ውስጥ ሆነህ ጭራሽ እንዳታለቅስ እየተከታተሉ የሚያውኩህን ባለ ካሜራዎች አትምጡብኝ ማለት አግባብ ነው፡፡
ሌላኛው በጣም አሳፋሪ ነገር ደግሞ ለቅሶ ላይ ሄዶ ከለቅሶው አላማ ውጭ የግል ጉዳይን መፈጸም ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ያህል ለቅሶ ላይ ሄደው የሚያደንቁትን ሰው ሲያገኙ ለቅሶውን ትተው አድናቆታቸውን ለመግለጽ እና ፎቶ ለመነሳት አጋጣሚውን የሚጠቀሙበት ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሽ የሚያደንቁትን ሰው ለማግኘት ብቻ ብለው ቀብር እንደሚመጡ በሚያስታውቅ ሁኔታ ተደናቂውን ሰው ሲከታተሉ ነው የሚውሉት፡፡ እንዲህ አይነቱ ነውረኝነት ሟችንም መናቅ ተደናቂውንም ሰው ሀዘኑን እንዳይገልጽ ማወክ ነው፡፡ ይሄ ዘመን ያመጣው አሳፋሪ ባህል ነው፡፡
ሌላኛው ደግሞ ለቅሶን የግል ትርኢት ለመስራት የሚጠቀሙት ጉደኞች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የሚያለቅሱት ሁሉ ካሜራውን እየተከተሉ ነው፡፡ ሌሎቹ ካሜራ አይን ውስጥ ለመግባት ለየት ብለው ይቀመጣሉ ፤ ወይም ለየት ያለ አለባበስ ይለብሳሉ ወይም የሆነ ወጣ ያለ ነገር ያደርጋሉ፡፡ የግል የገጽታ ግንባታቸውን ለማካሄድ ለዚያ ቀን ብቻ ልብስ የሚገዙ ወይም መኪና የሚይዙ ወይም ከእነሱ የበለጠ ታዋቂ ሰው ስር ልጥፍ የሚሉም አሉ። ድሮ ሀዘን ሲኬድ ሀዘንን በሚገልጽ እና የሀዘንተኛን ስሜት ለመጋራት በሚያስችል አለባበስ ነበር፣ አሁን ላይ ሀዘን ሲኬድ ተዘንጦ ራስን ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ግሩም ነው መቼም፡፡
ለሀሜት የሚመጡም አሉ፡፡ እገሌ ለምንድን ነው በደንብ የማያለቅሰው ፤ እገሌ ሲያለቅስ ያሳዝናል፤ እገሊት አግብታለች እንዴ ምነው ወፈረች ፤ እገሌ እና እገሌ የሆነ ነገር ጀምረዋል አሉ ….በቃ ሀሜት እንደጉድ ይፈልቃል፡፡ አንዳንዴ ሀሜቱ ሟችንም ያካትታል፡፡ እንዲህ ሆኖ ነው የሞተው ፤ እንትን ብሎ ነበር ፤ ምንትስ አድርጎ ነበር ፤ ወፍሮ ነበር ፤ ከስቶ ነበር ፤ ጠቁሮ ነበር ፤ ከእገሊት ጋ እንዲህ ነበረው ፤ ከእገሌ ጋር ተጣልቶ ነበር ወዘተ…ይሄ ሁሉ የሚወራው እዚያው ሟችን ሊቀብሩ በቆሙበት ወይም ሀዘንተኞቹ ቤት ቁጭ ተብሎ ነው። አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ የበለጠ አሳፋሪው ነገር ሟች ታዋቂ ከሆነ የሟች ቤተሰቦች ይህን ሀሜት ትንሽ ቆይቶ በዩቲዩብ ይሰሙታል፡፡ ምን ያህል ስሜትን የሚጎዳ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው፡፡
ሰው ሲሞት ሀይማኖቱን እና ብሄሩን የሚጠይቁ ጉደኞችም አሉ፡፡ ገና ሟች አፈር ሳይቀምስ ሀይማኖቱን ያጣሩና ከእነሱ ሀይማኖት ውጭ ከሆነ መጨረሻው ሲኦል መሆኑን ደምድመው የሚናገሩ ግብዞች ብዙ አሉ። ይህ በተለይ ለሟች ቤተሰብ በቁስላቸው ላይ እንጨት የመስደድ ያህል ነው፡፡ ነውርም ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ባህላችን መሰረት ሰው ሲሞት ማንም ይሁን ማን የመጀመሪያው ስራ ማዘን ነው፡፡ እናት አባቶቻችን እንኳን ለሚያውቁት ለማያውቁት ሰው ሁሉ ያለቅሱ ነበር፡፡ ለቅሷቸውም አንድም ስለሟች ነው አንድም ነግ በኔ በሚል ስሜት ነው እንጂ ራሳቸውን በማጽደቅ አይደለም፡፡ ከአንደበታቸው የሚወጣቸው ብቸኛ ቃልም ነፍስ ይማር የሚል ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግን ሰው ሲሞት ጥቅስ አንጠልጥሎ ለአተካሮ በየሶሻል ሚዲያው መሮጥ ፋሽን ሆኗል፡፡ ሌሎች ደግሞ ሟቹን ከአንድ ብሄር ወይም የፖለቲካ ቡድን ጋር በማያያዝ እነሱ ብቻ የማዘን መብት እንዳላቸው እና ሌሎችን ለሟች የማዘን መብት እንደሌለው ያሳስባሉ፡፡ ነውር ነው፡፡ ማን ለማን ማዘን እንዳለበት መወሰን አግባብም አይደለም፡፡ እገሌ ሲሞት ሳታለቅሱ ለእገሌ ለምን አለቀሳችሁ የሚሉ የለቅሶ ኦዲተሮችም እንዲሁ አሉ፡፡ እንዲያው ብቻ ብዙ አይነት አሳፋሪ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡
እነዚህ ልምምዶች መስተካከል አለባቸው፡፡ ለቅሶ ላይ ካሜራ መደቀን ፤ ተኳኩሎ የግል ትርኢት መስራት ፤ ለቅሶን ለሀሜት ማራገቢያ መጠቀም ፤ በሟች ሞት ላይ የግል ሀይማኖት እና የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈጸም መጠቀም ያልነበረ አሁን የመጣ አዲስ ባህል ነው፡፡ ሊታረም ይገባል፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2015