ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? በደንብ እያነበባችሁ ነው አይደል? ከመጀመሪያው ጀምሮ ማንበብን ልምምድ ካላደረጋችሁ ውጤታማ አትሆኑም። ስለዚህም ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ከፈለጋችሁ ዛሬ የተማራችሁትን ዛሬውኑ በማንበብና ተጨማሪ ነገሮችን በማከል አቅማችሁን ማጎልበት አለባችሁ። ልጆች ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት ከእስከዛሬው ለየት ያለ ጉዳይ ነው። ምን መሰላችሁ ስለ ኦቲዝም ተጠቂ ልጆችና ሥራዎቻቸው ነው። ስለዚህም ኦቲዝምና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ስላሉባቸው ሕፃናት እንነጋገራለን።
ልጆች በደንብ እንድታውቁ እነግራችኋለሁ። መጀመሪያ ግን ስለ በሽታው ምንነት እንነጋገር። ኦቲዝም ምንድን ነው? ከሚል ብንነሳ ኦቲዝም የአዕምሮን እድገት ውስንነት እንደሆነ ምሑራን ያስረዳሉ። ከአዕምሮ እድገት ጋር በተያያዘ ነገሮችን ቶሎ መረዳት አለመቻል በስፋት በተጠቂዎቹ ዘንድ ይታያል። ይህ ደግሞ አካላዊ ጤናን ጭምር ሊያቃውስ ይችላል።
ሁሉም ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ይነስም ይብዛም ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገሮች አሉ። ለአብነት ከሚታዩ ችግሮች መካከል፡- ውስን የሆነ ስሜታዊነት አንዱ ነው። ማለትም የራሳቸውን ማንነት መግለጽም ይሁን ሌሎችን መረዳት ይከብዳቸዋል። በማንኛውም አፍ መፍቻ ቋንቋ መግባባት ይቸግራቸዋል። ማኅበራዊ ግንኙነት ላይም ይቸገራሉ። ማለትም የራሳቸውን እንጂ የሌሎችን ሰዎች ስሜት መረዳት ቀላል አይሆንላቸውም።
ሌላው የሚደጋገም ባህሪያት/የተለመዱ ነገሮችንን መውደድ፤ ለነገሮች ባልተለመደ መልኩ ስሜታዊ መሆን ይታይባቸዋል። አንድ ነገር ላይ ከመጠን በላይ ማተኮር ይፈልጋሉ። ተደጋጋሚ የሆነ ትርጉም የማይሰጥም ሆነ የማይገባ ቃላት ወይም ድምጽ ወይም እንቅስቃሴ ሊያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህም ለእነዚህ ልጆች ጥብቅ ክትትል ማድረግ ይገባችኋል።
ኦቲዝም በማኅበራዊ ግንኙነት ላይ፣ በተግባቦት ላይ ከሚያደርሰው ተፅዕኖ አንፃር ሦስት አይነት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው መጠነኛ የሆነ የሌላ ሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ ከሰዎች ጋር ለመግባባት፣ ራሳቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ የሆነ የሌላ ሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ፤ በሦስተኛ ደረጃ የምናነሳው ደግሞ መጠነኛ የሆኑ ነገሮች ለማድረግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የሌላ ሰው ድጋፍ የሚጠይቁት ናቸው። ስለሆነም እነዚህን ማገዝ ከእድሜ እኩዮቻቸው የሚጀምር ነውና እናንተ በድጋፍ ማገዝ ይኖርባችኋል። ምን እናድርግ ካላችሁ የሚከተሉትን ብታደርጉላቸው በቂ ነው።
ለኦቲዝም ተጠቂዎች የሚሰጠው ሕክምና ዓላማው የኦቲዚም ምልክቶችን በመቀነስ ያላቸውን ችሎታ በመደግፍ ልጆች ቢያንስ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ነውና ለቤተሰብ በመንገር እንዲመረመሩና ክትትል እንዲደረግላቸው ማድረግ ነው። እናንተም ብትሆኑ ልጆቹ በማኅበራዊ ግንኙነታቸዉ የተለዩ እንዲሆኑ ቀርባችሁ የሚፈልጉትን ማድረግ አንዱ እገዛ ነው።
በሌላ በኩል ማድረግ ያለባችሁ ነገር በሁኔታዎች ወይም በአካባቢያቸው በሚፈጠሩ ተግባራት እንዳይደናገጡ ማገዝ ነው። ለዚህ ደግሞ ተደጋጋሚ መልካም ልምምዶችን እንዲያደርጉ መደገፍ አለባችሁ። በአስጨናቂ እና በማያውቋቸው ሁኔታዎች እና አካባቢዎች ተጨማሪ ድጋፎችን ይፈልጋሉና ይህንንም ልታደርጉላቸው ይገባል።
ሌላው ማድረግ ያለባችሁ ቃላቶችን ማውጣት ባይችሉም ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም መግባባትንና መማር ይችላሉና ይህንን እያያችሁ ማበረታታት ነው። እነርሱን ለመደገፍ ካሰባችሁ ነገሮችን በተደጋጋሚ እንዲሞክሯቸው እድሎችን መስጠትም አለባችሁ።
ልጆች ለመሆኑ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች የተወሰነ የሥራ ዘርፍ ላይ የአዕምሮ አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ለምሳሌ፡- በሙዚቃ፣ በሒሳብ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በስነ-ጥበብ እና በምሕንድስና መስኮች ውስጥ አብዛኞቹ የተዋጣላቸው ሥራ ይሠራሉ። ከማኅበረሰቡም ሐቀኞች ናቸው፣ ማጭበርበር፣ ማስመሰል ወይም መዋሸት አይፈልጉም፣ ምን ያመጣብኛል የሚለውን አይጨነቁበትም። ለማንኛው ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ልንገራችሁ። ሀገር አቀፍ የልዩ ፍላጎት (አካቶ ትምህርት) ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ሥራቸውን ለታዳሚዎች ያቀረቡ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ነበሩ።
ልጆቹ በሁሉም ቋንቋ የመጨፈር ብቃታቸው እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ዘፈኑን ጭምር ሸምድደውታል። እንቅስቃሴያቸው ደግሞ በእኩል ደረጃ የሚከወን ነበር። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ተደጋጋሚ ልምምድ ካደረጉ ብቃታቸውን ማስመስከር እንደሚችሉ ነው።
ልጆች ከላይ እንዳልኳችሁ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች በእጅ ሥራውም የተለየ ክህሎት ያላቸው ናቸው። ለዚህ ምስክር የሚሆነንም እነዚሁ ልጆች ያቀረቧቸው ነገሮች ናቸው። የአልጋ መውረጃ ምንጣፍ፣ ዳንቴል፣ የስኒ ልብስና የመሳሰሉትን ሠርተው ለታዳሚው ሲያሳዩ ነበር። ይህ ደግሞ የሚያሳየን ድጋፍና ክትትል ከተደረገላቸው የራሳቸውን ገቢ በራሳቸው መፍጠር እንደሚችሉ ነው። ስለሆነም እናንተ በአቅራቢያችሁ አሉና በሁሉም ነገር ማገዝ ይኖርባችኋል። በተለይም ከላይ የጠቀስኩላችሁን ነገር ካደረጋችሁላቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ትረዷቸዋላችሁ። ስለዚህ ልጆች የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑትን ወንድምና እህቶቻችሁን አግዟቸው እሺ። ጎበዞች። ለዛሬ ሀሳባችንን በዚህ እንቋጭ። በቀጣይ በሌላ ጉዳይ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2015