ሀዲያ ከጥንት ጀምሮ የበርካታ እሴቶች ባለቤት ሲሆን፤ በረጅም ታሪካዊ ሂደቱ ይዞ ካቆያቸው ባህላዊ ዕሴቶቹ አንዱ የ‘’ያሆዴ’’ በዓል ነው። ‘’ያሆዴ’’ በሀዲያ ብሔር ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት መካከል በክዋኔዎቹ ስፋት፣ በዘመን ተሻጋሪነት፣ በውስጡ በያዛቸው ባህላዊ እሴቶችና ማኅበራዊ ፋይዳው ቀዳሚነቱን የሚይዝ ትልቅ ክብረ በዓል ከመሆኑም ባሻገር በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ያለ ሃይማኖት ልዩነት በልዩ ድምቀት እና በአንድነት ከሚከበሩ ቱባ በዓላት አንዱና ቀዳሚው ነው።
‘’ያሆዴ’’ የሚለው ቃል በያሆዴ በፕሮግራም ከሚቀነቀነው ዘፈን ሁለት ቃላት የተመሠረተ ነው፤ ቃሎቹም ‹‹ያሆሆሆ_ያሆሆ ያሆዴ- ያሆሆ›› ሲባል ያሆሆ የሚለው ድምጽ የዘፋን የድምፅ ቅላጼ ሲያመላክት ኤዴ የሚለው ደግሞ ማገናኘትን፣ ማጣመርን፣ ማያያዝን ያመለክታል።
‘’ያሆዴ’’ ከአዲስ የልምላሜ፣ የብርሃን፣ የፍካት፣ ብሩህ ተስፋ፣ ሰላም እና ደስታ ካለበት ዘመን ጋር ማገናኘቱን / ማጣመሩን/ የሚያመለክት ቃል መሆኑን የሀዲያ ብሔር ባህልና ቋንቋ ተመራማሪ እና የሀዲይሳ መጽሐፍት ጸሐፊ አቶ ግርማ ሱልዶሎ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ፡ የጥንቱ የሀዲያ አባቶች ዝናብ፣ ጤዛ፣ ውርጭ፣ ቅዝቃዜ ሳይበግራቸው የሚያርሱ፤ በሄክታሮች የተዘራውን በቆሎና ማሽላ በግልና በሕብረት /Geja/ የሚኮተኩቱ፤ ቀኑን ሙሉ ተቀምጠው እንዳጎነበሱ ጤፍ የሚያርሙ፣ በክረምቱ ጭቃ፣ ጤዛ፣ ዝናብ ከብቶቻቸውን በመከራ እንደሚያግዱ እረኞች መንፈሰ ጠንካሮች ነበሩ። ከወንዝ ሙላት የተነሳ ገበያ፣ ለቅሶ፣ ዘመድ ጥየቃ ለመሄድ የዋና ስልቻን ጭምር ፈጥሮ ለመጠቀም ቢሞከርም ያስከፍል የነበረው ዋጋ እጅግ ከባድ ነበር።
ከብቶቻቸው ሜዳ ላይ ሲሰማሩ ተናዳፊ ዝንብ ሻኛቸውንና ጀርባቸውን እያቆሰላቸው መቆሚያ የሚያሳጣ ቸሬኤ የተሰኘው ወፍ በነፍስም ጭምር ዋጋ የሚያስከፍል የሦስት ወራት እልህ አስጨራሽ ትግል አብቅቶ፤ በፀደይ ወቅት መነሻ በመስከረም (ሞሶሮኦ) ወር የሚታየውን የአበባ ፍካት፣ የሳር ቅጠሉ ልምላሜ፣ የአዝመራው ልምላሜ አንዳንዱም ማሸት የጀመረበት፣ ንቦች በዜማ በአበቦች ላይ እየተመሙ የሚቀስሙበት ዘመን መነሻ መሆኑን ያነሳሉ::
ወሩ ከፊት ለፊት ያለውን ብሩህ ተስፋ፣ በመሰነቅ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የመሻገር ጊዜ ማሳያ በመሆኑ የጥንቱ ሀዲያ መስከረምን ለዘመን መለወጫነት እና ለቀን መቁጠሪያ መነሻነት ሲጠቀም ክብረ በዓሉን ደግሞ እጅግ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ሲያከብር ቆይቷል።
የያሆዴ በዓል ሙሉ ይዘት ይዞ መከበር የጀመረበት ትክክለኛ ቀን፣ ዓመት፣ ወቅት በወል እንደማይታወቅ በዘንድሮው ያሆዴ በዓል ዋዜማ በሲምፖዚየም ላይ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል። ያሆዴ በዓል የመጀመሪያ ፈጣሪ ሰው የማይታወቅ ሲሆን ፣ጥንታዊ የሆነው ሀዲያ በዕድገት ሂደቱ ክህሎቱን ተጠቅሞ የፈጠረና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ጥንታዊ በዓል መሆኑን አቶ ግርማ ሱልዶሎ ይናገራሉ።
የያሆዴ በዓል በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉት የሚያነሱት አቶ ግርማ፤ ያሆዴ የአዲስ ዘመን ማወጂያ፣ የዘመን መለወጫ እና የቀናት መቁጠሪያ መነሻ ማብሰሪያ ነው ይላሉ። በሀዲያ ሕዝብ ዘንድ ሰዎች ቀን መቁጠር የሚጀምሩት ያሆዴ ከወጣበት ቀን አንስቶ ነው።
ያሆዴ የዘመን መለወጫ እና የቀናት መቁጠሪያ መነሻ ከመሆኑም ባሻገር የምስጋናና የተስፋ በዓል ነው። በሕይወት፣ በጤና፣ በሰላም፣ በዝናብ፣ በፀሐይ፣ በሀብት፣ በልጅ፣ በከብት፣ በእህል፣ የባረከውንና አዕምሮና ምሪት የሰጠውን አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።
በክረምቱ ወንዝ ሙላትና ጭቃ ለመገናኘት የተቆራረጡ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ገበሬው እና ቤተሰቦቹ በክረምቱ ዝናብ፣ ውርጭ፣ ደመና፣ ጤዛና ብርድ በብዙ ድካም እና ልፋት ከሚያርሱበት፣ ከሚያርሙበትና ከሚኮተኩቱበት ዕረፍት ማግኘታቸውን የሚያበስሩበት በዓል ነው። እንዲሁም እንስሳት በክረምቱ ዝናብና ጤዛ ኮቴያቸው ከሚነቀልበት፣ በተናዳፊው ዝንብ እና ወፍ አደጋ ነፃ የመውጣት ተስፋ የሚታይበት፣ ጽልመት መወገዱን ማብሰሪያና የብሩህ ተስፋ ምልክት ነው ይላሉ።
ተስፋ በጨለማ አሻግሮ ብርሃንን ማየት በመሆኑ ነጋችን ብሩህ እንዲሆን እንደ ቁስል ከሚመረቅዝ ምሬት፣ ከቂም በቀል፣ ከጥላቻ ወጥተን ይቅርታ ውስጥ ሆነን በንጹሕ ልብ የምንታረቅበት፣ ከስህተት የምንታረምበት፣ አንዱ ሌላኛውን የሚባርክበት፣ ክፉ በጋራ የሚረገምበት፣ ከዕምነት በሚመነጭ ተስፋ መሰናክሎችንና የሚያማርሩ ነገሮችን አልፈን ነፍሳችን የሚለመልምበት፣ የምንስተካከልበት፣ ጎዶሎ የሚሞላበት፣ ከትላንቱ ብቃት የተሻለ ዕውቀትና ብቃት በመፍጠር ለሥራ የሚነሳሳበት፣ የምንመራረቅበት፣ ሴቶችን፣ አረጋውያን፣ ወላጅ አጥ- ችግረኞችና አቅመ ደካሞች በክብር የሚደጋገፉበት የመተሳሰብ በዓል ነው።
አንዳንድ ሰዎች ያሆዴን ከመስቀል በዓል ለማያያዝ እንደሚሞክሩ የሚያነሱት አቶ ግርማ፣ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ተዓማኒነት ያለው ማስረጃ ሊቀርብ የማይችልበት ሐሳብ ነው ይላሉ። ለዚህም በማረጋገጫነት የሚቀርበው ለያሆዴ በዓል ዝግጅት በሴቶች እንሰት፣ ቅቤ፣ ቆጮ፣ ምግብ ወዘተ ዝግጅት፤ በወንዶች የሰንጋ አደላለብ እና የዱቤ ግዥና ሽያጭ፣ የሳር ማከለል፤ በወጣቶች የሚካሄድ የእንጨት ዝግጅት፣ የወሮዬ ጨዋታ፣ ፊነጃ፣ ጋሚሻና ስንደዶ ለቀማ፤ በልጃገረዶች የሚከወኑ የቤት ውበት፣የቆጮ ዝግጅት፤ በልጆች የሚዘጋጅ ጦምቦራ፣ ኮንዳ ሥራዎች፣ የዋሽንት ጨዋታ፤ የመቻዕል ሜራ ግብይት ሥርዓት እንዲሁም ለምርቃት የሚዘጋጀው ጠሊላ፣ ማር፣ ወተት፣ ሰዳ፣ ቅቤ እና የምርቃት ሥርዓት አፈጻጸም፤ የይቅርታና የዕርቅ ሥርዓት፤ ያለው ለሌለው አካፍሎ ማክበር፣ ዘራሮ፣ ሳቴ፣የአተከና፣ የክትፎና ሌሎች የአመጋገብ ሥርዓት እና የያሆዴ የጨዋታዎች ሥርዓት፣ በአጠቃላይ በቅድመ ያሆዴ፣ በያሆዴ ዐውድ በድሕረ ያሆዴ የሚከወኑ ክዋኔዎች በመስቀል በዓል ወቅት በኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ከሚከናወኑ ክዋኔዎች ጋር ፈጽሞ የማይገናኙ፣ በሀዲያ ባህላዊ ዕሴቶች ብቻ ተውቦ የቀረበ ባህላዊ በዓል ስለመሆኑ ማሳያዎች በመጥቀስ ያብራራሉ።
የዘንድሮ የያሆዴ በዓል በዞኑ ዋና ከተማ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ በሚገኘው ያሆዴ ማክበሪያ ‘’ሀዲይ ነፋራ’’ ከፌዴራል እና ከክልል እንዲሁም ከአጎራባች ዞኖች በርካታ እንግዶች በተገኙበት ከወትሮው እጅግ በደመቀ መልኩ ተከብሯል። በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።
በያሆዴ በዓል ሁሉም ሰው የየራሱ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙት የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዋ ወይዘሮ አለሚቱ ጋቦሬ እንደተናገሩት፤ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞም ሁሉም ሰው የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፤ ከዚያ በኋላ ሁሉም በጋራ በደስታ በዓሉን ያከብራል፤ ፈጣሪውን ያመሰግናል ይላሉ።
ይህ የ”ያሆዴ” በዓል ሲነሳ ሁሌም አብሮ የሚነሳው ወጣት ወንዶች በአካባቢያቸው ተሰብስበው በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምሽቱን ሙሉ የሚጨፍሩት የያ ሆዴ ጭፈራ (ጨዋታ) ባሕላዊ ጨዋታ ነው። በዚህ ዕለት ማታ ፉሊታ ( ያሆዴ) የሚጨፈርበትና ጨፋሪዎች ደግሞ “ከዚህ ቤት ችጋር ይውጣ፣ በሽታ ይውጣ!” ብለው ችቦ እያቀጣጠሉ ይጨፍራሉ። ጨፋሪዎች መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባወራና እማወራ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁና ይሸኟቸዋል።
ወይዘሮ አለሚቱ ጋቦሬ እንደሚሉት፤ የያሆዴ እለት ሁሉም የሀዲያ ሕዝብ የሚመራረቅበት ነው። ያሆዴ ጭፈራን ከሌሎች ጭፈራዎች የተለየ የሚያደርገው ልጆች ወላጆቻቸውን የሚመርቁበት በመሆኑ ነው። በየገቡበት ቤት ሁሉ አተካና እና ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግቦችን እየበሉ የቤቱን አባወራና እማወራ ይመርቃሉ።
ለዚህ በዓል ሴቶችም ከአለባበስ እስከ ፀጉር አሠራር ድረስ በተስተካከለ ሁኔታ ይዘጋጃሉ። የሀገር ሽማግሌዎች ተሰልፈው ሥርዓቱን ያስጀምራሉ፤ ይከታተላሉ፤ ይመርቃሉ። የሀዲያ ብሔር እሴት የሆነው ያሆዴ ከነሐሴ ወር ጀምሮ በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነው። በዚህ በዓል ሴቶች ቀደም ብለው ሥራቸውን ይጀምራሉ። ቤታቸውን ያዘጋጃሉ። በኅብረት ይሠራሉ። ወንዶች ደግሞ እንጨት ያዘጋጃሉ። ሰንጋ ይገዛሉ። ሕፃናት ጦምቦራ (ችቦ) ቀድመው ይሠራሉ።
በሀዲይ ነፈራ በተካሄደው የያሆዴ የአከባበር ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ አብርሃም መጫ እንደተናገሩት፤ በያሆዴ ሰው ብቻ ሳይሆን ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት በመሆኑ ከአምስት ወር ጀምሮ ጥብቅ ወይም ክልክል ሳር ይፈቀድላቸዋል።
ያሆዴ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ለዛሬ የደረሰ ባህላዊ እሴት መሆኑን ጠቅሰው፣ የዘንድሮውን የያሆዴ በዓል ከወትሮው የሚለየው ኢትዮጵያ የበርካታ ድሎች ባለቤት በሆነችበት ወቅት መከበሩ መሆኑ ነው ይላሉ:: በተለይም ባለፉት ዓመታት በዓሉ በድምቀት እንዳይከበር እንቅፋት ሆኖ የነበረው ኮቪድ 19 ስጋት በቀነሰበት እና ሌሎች ሀገራዊ ድሎች በተመዘገቡበት ማግስት መከበሩ ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
ያሆዴ የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተቸገሩ ወገኖች የሚደገፉበትና በአንድነት የሚከበር ታላቅ ሕዝባዊ በዓል ነው ያሉት አቶ አብርሃም፤ በዓሉን በዓለም ቅርስነት በዩኒስኮ ለማስመዝገብና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም አቶ አብርሃም ገልፀዋል::
ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ እና ከትውልድ እስከ ትውልድ ተሻጋሪ እሴቶች አንዱ ያሆዴ በዓል ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሲርሞሎ ናቸው:: ያሆዴ የተጣላ ታርቆ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ፣ በመተሳሰብ እና በፍቅር መጪውን አዲስ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት ልዩ የሀዲያ ሕዝብ መገለጫ መሆኑን አስታውቀዋል።
አስታራቂዎችም ቂም ይዞ አዲስ ዓመትን መቀበል አይቻልም በማለት የተጣሉ ሰዎችን የሚያስታርቁበት መሆኑን በማንሳት የሰላምና የእርቅ ጉዳይ ሲነሳ ያሆዴን አለማንሳት አይቻልም ሲሉ ዋና አፈ-ጉባኤዋ ተናግረዋል። እነዚህን መልካም እሴቶችን አቅፎ የያዘው የያሆዴ በዓል ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል:: የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ የሆነውን ያሆዴ በዓልን በጥናትና ምርምር ሥራዎች በማስደገፍ የመጠበቅና የማልማት ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ወ/ሮ ፋጤ ሲርሞሎ አሳስበዋል::
በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው፤ የሀዲያ ሕዝብ እንደ አንድ ማኅበረሰብ መኖር የጀመረው ከሺህ ዓመታት አንስቶ መሆኑን እና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የሀዲያ መንግሥት እና ማኅበረሰብ ጠንካራ አደረጃጀት እንደነበረውም ታሪክ ይነግረናል ብለዋል።
የሀዲያ ሕዝብ በፖለቲካ ማኅበር ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ራሱን የቻለ ጠንካራ እና ታላቅ ሕዝብ እንደሆነ ያወሱት ሚኒስትሩ፤ የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው (ያሆዴ) የሀዲያ ሕዝብ የጥንታዊ ሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን አስታውቀዋል።
አንዳንዶች የያሆዴ በዓልን ከመስቀል ጋር ያያይዙታል ያሉት አቶ ቀጄላ፣ ነገር ግን በዓሉ ሃይማኖታዊ እንዳልሆነ እና የሀዲያ ሕዝብ የፈጠረው ታሪካዊ ቅርስ እና ጥንታዊ የሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደዚህ ዓይነት በዓላት መቀጠል እና ለትውልድ መተላለፍ ያለባቸው መሆኑንም በመልዕክታቸው ያነሱት ሚኒስትሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በዚህ ረገድ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2015