ዓለም አቀፉ የእርቅ፣ የሰላም፣ የግልግልና የሽምግልና ረቡኒ (መምህር ) ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ “የሰላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች” በሚለው ማለፊያ መጽሐፋቸው የሰላም የእርቅ አድማሶች በማለት በመጀመሪያ ሰው ከራሱ ጋር ከዚያ ከጎረቤቱ ፤ ከማኅበረሰቡ ጋር በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ፤ ሰላም ማውረድ እንዳለበት ይተነትናሉ ። ትናንት የተከበረው የኢሬቻ በዓል ሰው በመጀመሪያ ከራሱ ጋር በመቀጠል ከጎረቤቱ ከዚያም ከተፈጥሮ ጋር የሚታረቅበት ማዕድ ነው ።
ኢሬቻ ሰላም ፣ ፍቅር ፣ ይቅርታና አንድነት የሚፈፀምበት በመሆኑ አብሮነትን ስለሚያበረታታ አሰባሳቢ ነው ። ጥልን ቂምን ጥላቻን እያራገፈ መልካም መልካሙን ማለትም ሰላምን ዕርቅን የሚያጠናክር ስለሆነ በውስጠ ታዋቂ ማካበትን ይዟል ። ኢሬቻም ሆነ ዐቢይ መገለጫው የሆነው እርቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ፣ ሲቀባበል ፣ ሲወራረስ የመጣ በሂደትም እያደገ እየጎለበተ ስለሆነ ማከማቸትን አካቷል ።
የኦሮሞ ባህልና ታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ ኦቦ ድርቢ ደምሴ ኢሬቻ ማለት ኦሮሞ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ፈጣሪን የሚያመስግንበት ክዋኔ ሲሆን በሐይቅ ፣ በወንዝ ፣ በምንጭ ወይም በውሃ ዳርና በተራራ ብቻ የተወሰነ ግን አይደለም ይላሉ ። ልጅ ሲወለድ ፣ አዲስ ቤት ሲሠራ ፣ ሙሽራ ሲወጣ ፣ በዘር ወቅትም ፣ ወዘተረፈ ኢሬቻ ይደረጋል በማለት ከማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ምን ያህል የተቆራኘ እንደሆነ ያስረዳሉ ። የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ኦቦ ሙሉጌታ ደበበ (ፒ ኤች ዲ) በሌላ በኩል ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንዱ አንጓ ነው ይላሉ ። በማሳያነት ከሚጠቀሱት ዓበይት ምክንያቶች ቀዳሚው የሥርዓቱ ክዋኔ በቃሉና በአባ መልካ አጋፋሪነት መመራቱ ነው በማለት በዋቢነት ይጠቅሳሉ።
ኢሬቻ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከወንና የመጀመሪያው በበልግ በተራራ ላይ አምላክን የሚያመሰግንበትና ዝናብ የሚለማመንበት ሲሆን ቱሉ ኢሬቻ ይሰኛል ። ኦቦ ድርቢ ቱሉ ኢሬቻ መሬት አፏን ከፍታ የበልግ ዝናብን የምትጠብቅበት ወቅት ስለሆነ ፈጣሪን ዝናብ የሚለማመኑበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ ። ባለፈው ሳምንት ለምለም ሳርና አበባ ተይዞ በሐይቅ ፣ በወንዝ ፣ በምንጭ ዳር የተከበረው የምስጋና በዓል ደግሞ መልካ ኢሬቻ በመባል እንደሚታወቅ ኦቦ ሙሉጌታ ያብራራሉ ።
ፈጣሪ ዝናብ ስለሰጠ ከክረምት ወደ ብራ ስለ አሸጋገረ የሚመሰገንበት እንዲሁም አዝመራው ደርሶ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እንዲገባ የሚለመንበት መሆኑን አክለው ይገልጻሉ ። በፕሮፌሰር የሰላም አድማስ እይታ መሠረት ኢሬቻ ሦስቱንም የሰላም አለባውያን በአንድነት የያዘ የእርቅ ፣ የሰላም ገበታ ነው ማለት ይቻላል። ሦስቱን የሰላም አድማሶች ከኢሬቻ እሴቶች አንጻር አንድ በአንድ እናመሳክር ፦
1ኛ. ከራስ ጋር ሰላም ፤
ዓለም አቀፍ አሸማጋይ እና የሰላም አባት ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ከፍ ብሎ በጠቀስሁት መጽሐፋቸው ገፅ – 102 ላይ”ውስጣዊና መንፈሳዊ ሰላም ከራስ ጋር ሰላም ማውረድ ፣ መታረቅ ነው ። ከፈጣሪ ጋር ሰላም ከማውረድ ጋር ትስስር አለው ። ውስጣዊ ሰላም ከሌሎች ጋር ለሚመሠረት ሰላም ወሳኝ ነው ። ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው ምን ያህል ከሌሎች ጋር በሰላም እንደሚኖር እና ሰላም እንደሚያካፍል ይታወቃል ። ውስጣዊ ሰላም ያላቸው ሰዎች አስታራቂና ሰላም ገንቢም ናቸው ። ሰላማቸው ወደሌሎች ይፈሳል ። ከራሱ ጋር የታረቀና ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው የሕይወትን መስተጋብር የተገነዘበ ስለሆነ ከማኅበረሰቡና ከተፈጥሮ ጋርም ሰላምና እርቅን ያወረደ ነው ። ከራስ ጋር የሚፈጠር ሰላም ለሰላም አድማሶች መነሻም ውጤትም ነው ። …”
ኢሬቻ ከመደረጉ በፊት ከራሱ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር የተቀያየመ የተጋጨ ካለ እንዲወጣ ሽማግሌዎች በኦሮሚኛ “እውነትን ከአምላክ ፆታን ከምድር መደበቅ አይቻልም ። በውሻም ሆነ በልጅ ምክንያት የተጋጨ ካለ ከፈጣሪ ጋር እንዳያቀያይመን ይውጣ” በማለት እንደሚያግባቡ ይህን ሳያደርጉ ቢቀሩ ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደሚያስወቅሳቸው ኦቦ ድርቢ ያስረዳሉ። የሀገር ሽማግሌዎች ቢያንስ በመጋቢትና በመስከረም በዓመት ሁለት ጊዜ እርቅ የማውረድ የመሸምገል አጋጣሚ እንዳላቸው ይገልጻሉ ። ሰሞኑን የተከበረው መልካ ኢሬቻም ሆነ በወርሐ መጋቢት የሚከበረው ቱሉ ኢሬቻ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከራስ ጋር መታረቅ ሰላም ማውረድ ማኅበራዊ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነና በዓሉ ቤትን ራስን በእርቅ የማፅዳት ፤ የጥል ግድግዳን የማፍረስና ፋይል ዘግቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሻገሪያ ድልድይ መሆኑን ኦቦ ሙሉጌታ አክለው ያብራራሉ።
2ኛ. ማኅበራዊ ሰላም፤
ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ስለ ሁለተኛው የሰላም አድማስ ገጽ – 103 ላይ”ማኅበራዊ ሰላም ከራስ ጋርና ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረግ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው ። ይህ ማለት ግን ማኅበራዊ ሰላም ከሌለ ውስጣዊ ሰላም አይኖርም ወደሚል መደምደሚያ አያደርስም ። ሆኖም ብጥብጥና ሁከት ባለበት ውስጣዊ ሰላምን ማስፈንንም ሆነ ማስቀጠልን ፈታኝ አያደርገውም ማለት አይደለም። ሌላው ማኅበራዊ ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረገው ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው መሆኑን መገንዘብ ነው ። ግጭትና ጦርነት በተደጋጋሚ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሚጎዳ ደኑም ስለሚጨፈጨፍ አካባቢው ይራቆታል። በዚህም ሥነ ምሕዳሩ ስለሚዛባ የከባቢ አየር ለውጥን ያስከትላል ። ለዚህ ነው የማኅበራዊ ሰላም መኖር ለፍጥረትና ለአካባቢ ጥበቃ ዋስትና ተደርጎ የሚወሰደው።”ፕሮፌሰር እንደሚሉት ከራስ ጋር የሚፈጠር ውስጣዊ ሰላም ከጎረቤትና ከማኅበረሰብ ጋር የሚደረግ እርቅ መሠረት ነው። በኢ-ሬቻ ለመታደም ከራስ ጋር መታረቅ ማኅበራዊ ቅድመ ሁኔታ ነው ። ከራሱ ጋር ሰላም ያለው ደግሞ ከጎረቤቱ ጋር የመጋጨት አጋጣሚው ዝቅተኛ ነው ።
ሆኖም ከጎረቤቱ ጋር ወይም ከሌላ ሰው ጋር ግጭት ቢፈጠር የሀገር ሽማግሌዎች በቱሉ ወይም በመልካ ኢሬቻ የማስታረቅ መልካም አጋጣሚም ኃላፊነትም ስላለባቸው ማህበራዊ ሰላምን ከመታወክ ይታደጉታል። ለዚህ ነው የሥነ ማኅበረሰብ አጥኚዎች መጀመሪያ ከራስ በመቀጠል ከጎረቤት ጋር የሚፈጠር ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረስ ሰላም መደላድል እንደሆነ የሚያስረዱት። ታላቁ መጽሐፍስ”እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።”አይደል የሚለው!?
3ኛ. የተፈጥሮ ሰላም፤
ፕሮፌሰር በገፅ – 104 ላይ”የተፈጥሮ ሰላም ከማኅበራዊ እና ከውስጣዊ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው ። ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ፣ እርቅ ማውረድ አካላችን ከታነፀበት ምድር ጋርም መታረቅ ነው ። ከተፈጥሮ ፣ ከዩኒቨርስ ሥርዓትና ኃይል ጋር መንሰላሰል የውስጣዊ ሰላም ምንጭ ነው። …የተፈጥሮ ፍቅርና እንክብካቤ ለማኅበራዊ ሰላም መስፈን የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። …” ኢሬቻ ከሁለቱ የሰላም አድማሶች ይልቅ ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረግ እርቅ ያደላል ቢባል ማጋነን አይሆንም። በቱሉ ኢሬቻ ፈጣሪውን ለበልግ እርሻ ፣ ለከብቶች ግጦሽና ለውሃ ዝናብ የሚለምንበት መሆኑ መልካ ኢሬቻው ደግሞ ፈጣሪው ዝናብ ስለሰጠው ፣ ከክረምት ወደ ብራ ስላሸጋገረው የሚያመሰግንበት በሌላ በኩል ያልተሰበሰበውን እህል በአደራ የሚሰጥበት የአምላክን ጥበቃ የሚለማመንበት መሆኑ በተለይ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ውሃ ዳር ፈጣሪ የሚመሰገንበት መሆኑ ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል ። ይሁንና ኢሬቻ ደረጃው ፣ ስፋቱ ፣ ጥልቀቱ በየሰላም አድማሱ የተለያየ ቢሆንም ሰው ከራሱ ፣ ከጎረቤቱ በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር በአንድ የእርቅ ፣ የሰላም፣ የመቀባበል ፣ ወዘተ . ማዕድ ቀርቦ የሚቋደስበት ስለመሆኑ አያጠያይቅም ።
ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ”…በተለያዩ ማኅበረሰቦች ሀገር ግንባታ Nation Building በመሀላቸው ያለውን ልዩነት አጥብቦ ግድግዳዎችን አፍርሶ የጋራ ማንነት መገንባት ነው ። …” ይላሉ። የሀገር በቀል እውቀቶችና የባህል ተመራማሪው አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ይሄን የፕሮፌሰር ሀሳብ ይጋራሉ። በዓሉ በአዲስ አበባ ሌሎችን የማኅበረሰብ ክፍሎች ባሳተፈ አግባብ መከበሩ ለሀገረ ግንባታ መሠረት ጥሏል ማለት ይቻላል ሲሉ ዘላቂ ፋይዳውን ያመላክታሉ ። የጋራ የሆኑ እሴቶችን ባህሎችን እያጎለበትን እያሳደገን በሄድን ቁጥር መተዋወቅ ፤ መከባበር ፤ መቀባበል ስለሚጨምር እኔነት በእኛነት እየተተካ ስለሚሄድ ለሀገርም ሆነ ለሀገር መንግሥት ግንባታ እርሾ እንደሚሆን ተመራማሪው ያስረዳሉ ።
ዛሬ ከምንገኝበት መንታ መንገድ ላይ የደረስነው ባህሎቻችንን እሴቶቻችንን ለሀገር መንግሥትም ሆነ ለሀገር ግንባታ ባለማዋላችን ነው ሲሉ አቶ አብዱልፈታህ ይሞግታሉ ። ኦቦ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደ ዓድዋ ያሉ የድል በዓሎቻችን ፣ ኢሬቻ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ፍቼ ጨምበላላ ፣ ጊፋታ ፣ ወዘተረፈ አንድ የሚያደርጉን ባህሎች በበዙ ቁጥር ኢትዮጵያዊነታችን ይጠናከራል። ከተገኘንበት ብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነታችን እየገዘፈ ይሄዳል። እየተዋሀድን ፣ እየተቀባበልን፣ እየተከባበርን በሄድን ቁጥር እየተዋደድን እንሄዳለን አንድነታችንም በዚያው ልክ ይጎለብታል ሲሉ ይጠቁማሉ ።
ለከርሞ…!?
ፈጣሪ የከርሞ “ሕዝብ” ካለን መስቀልንም ሆነ ኢ-ሬቻም ወይም ጊፋታ ፣ መስቀላዮም ሆነ ፍቼ ጨምበላላ አሸንዳ ሻደይም ሆነ ሶለል ፣ ወዘተረፈ ሲከበሩ በተቻለ መጠን ከፖለቲካዊ አንድምታ ጋር ላለማቆራኘት የተደረገው ጥረት ከርሞም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በሽግግር ፣ በመሠራት ላይ እንዳለ ሀገርና ሕዝብ በተወጠረች ፖለቲካዊ ገመድ በጥበብ በማስተዋል መጓዝ ግድ ይለናል። እሴቶቻችን ባህሎቻችን በራሳቸው ሙሉ፣ ጮኸው የሚናገሩ ፣ ከሩቅ እንደ ቀስተ ዳመና ደምቀው የሚታዩ ስለሆኑ ምንም ዓይነት ማጋጌጪያ አያሻቸውም ። ቱባ መሆናቸው በራሱ ሙሉኡ አድርጓቸዋልና። አቶ አብዱልፈታህ ኢሬቻ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይዞልን የሚመለሰው ምስጋናን፣ ይቅርታን ፣ ሰላምንና አንድነትን እንጂ ሌላ አጀንዳን ሊሆን አይገባም ይላሉ። ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ኢሬቻ ወደ ጋራ መድረክ ወደ አንድነት ሲመጣ እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ሊቀበለው ይገባል በማለት አበክረው አሳስበዋል ።
ሆኖም የክልል ሰንደቅ ዓላማ እና የፓርቲ ዓርማ በማንገብ ፖለቲካዊ ቡልኮ መደረቡ ተገቢ አለመሆኑ ከዓመት ዓመት ግንዛቤ ያገኘ ይመስላል ። ይህ ከኢሬቻም ሆነ ከሌሎች በዓላት እሴቶች ጋር የሚጣረስ ከመሆኑ ባሻገር አቃፊነቱ ላይ ጥያቄ ፣ ብዥታ ፣ ግርታ ሊያስነሳ ይችላል ። ከባህላዊ ፣ እሴታዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊ ቱማታው ላይ ጊዜያዊ ነጥብ ለማስመዝገብ የሚደረግ መሽሎክሎክ ዘንድሮ ደብዘዝ ማለቱ ይበል የሚያሰኝ ነው ። ከሀገራዊ ፣ ከቀጣናዊ ፣ ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂና ሕልማችን አንጻር አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ሀይማኖትንና በዓላትን ለአማኙና ለተከታዩ መተው ሊበረታታ ይገባል ። በነገራችን ላይ ሀይማኖትንና ባህልን ከፖለቲካ ጋር የማጣቀስ አባዜያችን ትናንት የተጀመረ አይደለም ። የዋለ ያደረ አባዜ እንጂ። ይህ ጥርሻ በዜጎች መካከል መጠራጠርን፣ ልዩነትን የሚያነብር ስለሆነ ሰከን ብሎ ማሰብ ይገባል። ለብሽሽቅ፣ ለእልህ ፖለቲካ በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል።ከሁሉም በላይ እንደኛ በሽግግር ላይ ላለ እና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ላልገነባች ሀገርና ሕዝብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት Political Correctness የልብ ትርታዋ ሊሆን በተገባ። ሆኖም በገዥው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍ ወለምታ፣ ግራ ቀኙን ካለማመዛዘን ፣ የመራጭን constituncy ቀልብ ለመግዛት ፣ “የአንቂን” Activist ቡራኬ ለማግኘት የሚፈፀሙ ፖለቲካዊ ስህተቶች ሀገርንም ሆነ ለውጡን ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍሉት ኑረዋል ። አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ለጭብጨባ ተሟጋች ነን ባዮች ለሰብስክራይብና ለላይክ ሲሉ በስሜት ከመጋለብ ዛሬም ሳይረፍድ ራሳቸውን በልጓም ፣ በልባብ ሊገቱ ይገባል ። ወደ መነጋገሪያው ቀርቦ አንደበትን ከመክፈት በፊት ሁለት ሦስቴ ማሰብና ከስሜታዊነት መታቀብ ያስፈልጋል ። ገና ብዙ ያልተሻገርናቸው ሸለቆዎች፣ ገደሎች አሉብንና በእንቅርት ላይ … እንዳይሆን አበክረን ልንጠነቀቅ ይገባል ። ከጊዜያዊ ድል ዘላቂውን የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ማስቀድም ትልቁን የተስፋ ስዕል አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል ።
ታዋቂው አሜሪካዊ የጥቁሮች መብት ተሟጋችና የሰላማዊ ትግል ሐዋርያ ማርቲን ሉተር ኪንግ “… እያንዳንዳችንን በቀጥታ የሚጎዳ ሁላችንንም በተዘዋዋሪ ይጎዳል። …”ሲል የተናገረው ሰሞነኛውን አውድ ይዋጃል ብዬ ስለአሰብሁ አጋርቼ ፤ በመጀመሪያ ኦቦ ድርቢ በመቀጠል ኦቦ ሙሉጌታ አምና ባስተላለፉት አባታዊና ወንድማዊ ዘመን ተሻጋሪ ምክር መጣጥፌን ልቋጭ ። “… ባለቤቱ የእኔ ነው በማለት ትልቅ ቦታ የሰጠውን በማጣጣል ጣትን መቀሰር አይገባም ።”
ከሁሉም በላይ ኢሬቻንም ሆነ መስቀልን በዓመት አንድ ጊዜ በአደባባይ ማክበር ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯችን እንተርጉማቸው ። እንኑራቸው ። በልካቸው እንገኝ ። ልካቸው ሰላም ፣ እርቅ ፣ ይቅርታ፣ መቀባበል ፣ መግባባት ፣ አብሮነት ፣ አንድነትና ሰው ሆኖ መገኘት ነውና ።
ፈጣሪ የከርሞ ሰው ይበለን !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም