የምናብ ታሪካችን ወደ አንድ ለበዓል ትልቅ ቦታ ወደ ሚሰጥ ቤተሰብ ይወስደናል። የቤተሰቡ አባላት በአመት ውስጥ ካሉት በዓላት መካከል በአንዱ በዓል ላይ ከያሉበት ተሰባስበው ቤተሰባዊ ጊዜ የማሳለፍ ልማድ አላቸው። የዘንድሮ በዓል ላይ ለመገኘትም ከየአቅጣጫው ጉዞ አድርገው ከአባትና እናታቸው ቤት ደርሰዋል። አንዱ ወንድማቸው ግን በሚጠበቅበት ጊዜ አልደረሰም። የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ የተሰማራው ወንድማቸው በሚጠበቀው ሰዓት ሊደርስ እንደማይችል ይጠብቁትም ነበር።
ይህ የቤተሰብ አባል ዘወትር ስራን ምክንያት በማድረግ እንደ ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት በትኩረት አለመገኘቱም ሁሉም ቅይማት እንዲሰማቸው ያደረገ ነው፤ ለቤተሰብ ቦታ የለውም በማለት። በተመሳሳይ ስራ ላይ የተሰማሩ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ግን መኪናቸውን አቁመው ለቤተሰብ ቦታ በመስጠት ከበዓሉ ሲገኙ የወጣት ወንድማቸው ጉዳይ ግን ሁሌም ይከነክናቸዋል። ዘወትር የሚያቀርቡበት ክስ ለቤተሰብ ቦታ አይሰጥም ከቤተሰብ በላይ ገንዘብ ይበልጥበታል የሚል ነው።
ዘግይቶም ቢሆን ማምሻው ላይ የቤተሰቡ አባል ከስፍራው ደረሰ። ዛሬ የገጠመው ግን የተለየ ሆነ፤ ታላቅ ወንድሙ የእርሱን መግባት አይቶ ተነስቶ ወጣ። ምክንያቱ “ብሞት በቀብሬ ላይ ከማይገኝ ጋር አብሬ በዓል አላሳልፍም፤ እርሱ ወንድሜም አይደለም” የሚል ነው። ሌላው የቤተሰብ አባል በመቀጠል፤ “እርሱ በእዚህ ሰዓት የሚመጣው ለቤተሰቡ ንቀት ስላለው ነው፤ ከቤተሰብ በላይ ገንዘብን ስላስቀደመ ነው”በማለት ተነስቶ ወጣ። እናት እና አባት ግን በሁኔታው አዘኑ። ልጃቸው ዘግይቶ የመጣ መሆኑ ደስ ባያሰኛቸውም በልጆቻቸው መካከል አታካሮ በመፈጠሩ አዘኑ። ሁለቱም ልጆች ወጥተው ሄዱ፤ ለደስታ የታሰበው በዓል ለሃዘን ሆነ።
በማግስቱ ማለዳ እናት መኪና አስነስቶ የሄደውን ልጃቸውን ፍለጋ በበዓል ቀን አርባ ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የሚገኘው የልጃቸው ቤት ሄዱ። የእናትነት አንጀታቸው አላስችል ብሏቸው ለልጃቸው ቁርስ ቋጥረው አደረሱ። የእናት ልብ፤ የአባት ቀልብ።የተቀሩት የቤተሰብ አባላትም በማዘን ድባብ ውስጥ ሆነው በዓሉን አሳለፉት።
ለወትሮውም አልኮል መጠጥ መውሰድ ልማዳቸው የሆኑት የቤቱ አባወራ በእለቱ አብዝተው ከወደ ውሃው ወሰዱ። አብዝተው መውሰዳቸውም በልባቸው ስለሌላው የቤተሰብ አባላት የቋጠሩትን አውጥተው እንዲናገሩ ስላደረጋቸው የቤተሰቡ በዓል እንደወትሮው ሳይሆን ይበልጥ መበጥበጡን ቀጠለ። አታካሮ እንዲሁም እምባን የቋጠሩ አይኖች ታዩ፤ ቤተሰቡ ውስጥ በይሉኝታ ተሸፍኖ ተደብቆ የነበረው ሁሉ በመጠጥ ሃይል ወጣ። ቤተሰቡ በሃዘንም ሆነ በደስታ አብሮ ሲቆም በውስጡ ያለ ሽንፍልና ሳያጠራ በመሆኑ በንግግር እርስበእርስ መጎዳዳት ሆነ። በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባው ቤተሰብ የተሰኘው ተቋም በግጭት ውስጥ ታመሰ።
ሁኔታውን በእርጋታ የሚመለከቱ የነገ የቤተሰብ መሪዎች ህጻናትና ታዳጊዎች በስፍራው አሉ። ከልጆቹ መካከል የስምንት ዓመት ልጅ በስተመጨረሻ በውስጡ የያዘውን በልጅ አንደበቱ ይናገር ጀመር እንዲህ በማለት “እማማ፤ አባባ፤ እህትዓለም፤ ወንድምዓለም ለካስ ሁለት አይነት ሰዎች ናችሁ። ስትናደዱ ሌላ፤ ሳትናደዱ ሌላ። እውነተኛው ግን የትኛው ነው? ስትናደዱ የምትሆኑት ወይንስ ሳትናደዱ?” ብሎ ጠየቃቸው። የህጻኑ ጥያቄ እውነትነት ያለው በመሆኑ ሊመልስለት የሚችል አልነበረም። ሁሉም አንገቱን አቀርቅሮ የምን ውርጅብኝ ወረደብን እያለ ያብሰለስላል። በበዓል ስም የተሰባሰበው ትልቅ ቤተሰብ ቀላል በሚመስለ ጸብ እያዩት በውስጡ ያለው ችግር እንደ ዳንቴል እየተተረተረ ሄደ።
ትልቅ የሚባል ቤተሰብ አነስተኛ በምትባል ግጭት ምክንያት ብጥብጥ ውስጥ ገብቶ ቅጽበት በሚባል ደረጃ ቤተሰብ ተጎድቶ ሊበታተን እንደሚችል የሚያሳይ። እንዲህ ባለ ገጠመኝ ውስጥ እስከወዲያኛው የሚሆን ስንጣቅ የመፈጠሩን ያህል ህይወትን የሚያሳጣ ክስተት ሊከሰት እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። እርቅ የሚባለው የባህላችን ጠንካራ ክፍል ባይኖር ኖሮ በትንሽ በትልቁ ቤተሰብ ሊበተንም ይችል ነበር። ለእርቅ ቦታ መስጠት በቻሉ በርካታ ቤተሰቦች ውስጥ ችግሮች በእርቅ እየተፈቱ፤ እየተጠገኑ፤ እየተስተካከሉ ሲሄዱ፤ በተቃራኒው መንገድ ላይ የተገኙ ቤተሰቦች ግን እየኖሩ ግን ተለያይተው ሲኖሩ እንመለከታለን።
ጉዳዩን የሰሙ በአካባቢው የተከበሩ አባት ከቤታቸው ከበዓል ፕሮግራም ተነስተው ወደ ጎረቤታቸው መጥተው ነገሩን በውል ከተረዱ በኍላ በስልክ እርቀው ያሉትንም አናግረው ሰላም ለማውረድ ሞከሩ። ሙከራው በእለቱ ባይሳካም ሁሉም ከበዓል ድባብ ወጥቶ በእርጋታ ነገሩን ወደፊት ሊያየው ሃሳብ ቀርቦ ተስማሙ። ብዙ ብር ወጥቶ ከሌሎች ፍላጎቶች ተቀንሶ የተደገሰው ድግስ፤ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰበው ቤተሰብ፤ ለነገሮች ባለ የእይታ ልዩነት ምክንያት የናፈቀውን በዓል በአግባቡ ሳያጣጥም ወደየቤቱ ተበተነ። በእርቅ ወቅት ነገሮች መስመር እንደሚይዙ ተስፋ ያደረጉት ሽማግሌም መካከለኛ ሆነው ተገኙ። ለዚህ ቤተሰብ መልካም እንዲሆን እየተመኘኝ‘ቤተሰብና በዓል’ ብለን እንቀጥል።
ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር
የምናብ ታሪካችን ቤተሰብ ውስጥ የተከሰተውን ነገር ስናይ ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባ ነገር እናነሳለን። ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር አጠገባችን ካሉ ሰዎች አድናቆትም ሆነ ትችት እንድናስተናግድ ሊያደርገን ይችላል። ቅድሚያ በምንሰጠው ነገር የሚገጥመንን ተግዳሮት እንዴት ማለፍ እንዳለብን ማሰብ አስፈላጊነቱ የሚገባን እንደ ወጣቱ የቤተሰብ አባል የከፋ ተቃውሞ ሲገጥመን ሊሆን ይችላል። አስቀድሞ ያንን መግራት የቻሉ ግን እነርሱ ጥበበኞች ናቸው።
በመርህ ደረጃ ቅድሚያ ልንሰጠው ስለሚገባ ነገር ቅድሚያ መስጠት ችግር ሳይሆን ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ነገርግን ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር አደጋ ይዞብን እንዳይመጣ ማሰብ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ቅድሚያ የሰጠነው ነገር ሌላ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባን ነገር እየደፈጠጠ መሆን አለመሆኑንም መረዳት አለብን ። ቅድሚያ የምንሰጠውን ለይቶ ማወቅ አንድ ነገር ሆኖ ቀጣዩ ነገርግን ቅድሚያ በምንሰጠው ነገር ሊከተል የሚችለውን ተግዳሮት ለይቶ በተግዳሮቱ ላይ መስራት ነው። የትራንስፖርት ባለሙያው ዘወትር ለስራው ትኩረት እየሰጠ ከቤተሰብ የጋራ መገናኛ በዓል ሲጎድል ቅድሚያ ሊሰጥ ለፈለገው ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢ ቢሆንም ቤተሰቡ እንዲረዱት ማድረግ ግን ነበረበት፤ ነገርግን አልሆነም። ባለመሆኑም ግጭት ተፈጠረ፤ ግጭቱም ሌሎች ግጭቶችን እየፈጠረ ሄደ።
በህጻንነት እድሜ ላይ ያሉ ልጆች ፊትለፊታቸው ላለው ነገር ቅድሚያ ይሰጣሉ። ፊትለፊታቸው ያለውን ነገር ተመልክተው መጨበጥ የፈለጉትን ለመጨበጥ ማድረግ የሚገባቸውን ያደርጋሉ። ማድረግ የሚገባቸው ማልቀስ ከሆነ በሚችሉት አቅም ያለቅሳሉ። ለመጨበጥ የሚሞክሩት ነገር የሚጎዳቻው ይሁን አይሁን የሚያውቁበት መንገድ የለም። ጎጂም ቢሆን ያደርጉታል። በጊዜ ሂደት ግን ጎጂውን ከመልካሙ እየለዩም ይመጣሉ፤ መቅደም ያለበትን ከሌላው ይለያሉ። በእድሜ ውስጥ በማደግ ሊታዩ ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባውን ነገር ማወቅ መቻል ነው።
ከቤተሰብ ጋር ጊዜን መስጠት ቅድሚያው ያደረገና ጊዜውን በስራ በማሳለፍ ተጨማሪ ገቢ ማግኘትን ቅድሚያው ያደረገ ሁሉም ቅድሚያ የሰጡት ነገር አለ፤ በውስጣቸው በከበደው ነገር ልክ። ሁለቱም በራሳቸው ሚዛን ትክክል ናቸው። በዓልን ለመደገስ ተበድሮም ቢሆን የሚያደርገው ሰውና በአቅሙ ልክ ብቻ የሚደግስ ወይንም ከአቅሙ በታችም የሚደግስ ሁሉም ቅድሚያ የሰጡት ጉዳይ አለ። አሁንም ሁሉም በሚዛናቸው ትክክል ናቸው። ጥያቄው ቅድሚያ የሰጡት ነገር ምን አስከትሎ እንደሚመጣ ይረዳሉ የሚል ነው።
ከድርጊቱ ቀጥሎ የሚመጣውን አውቆና ተዘጋጅቶ መስራት አስፈላጊ ነገር ነው። የጥበብም መንገድ ያለው እዚያ ውስጥ ነው። ቅድሚያ የሰጠነው ነገር ሌሎችን በምን ደረጃ እንደሚነካም መገንዘብ እንዲሁ የተገባ ነው። የበዓል ሰሞን ያለውን ነገር ሁሉ አድፋፍቶ እለቱን ብቻ በደስታ ለመዋል የሚደረግ ጥረትን በምንም መመዘኛ ትክክል ነው ተብሎ ሊጠቀስ አይችልም። በእለቱ ያለው ገንዘብ ሁሉ መበተን አለበት የሚል ስሌትም በሰፊው የሚስተዋል ይመስላል። የበዓሉ ድባብ ሲያልፍ እያንዳንዱ ሰው የሚጋፈጠው እውነታው ግን ግልጽ ነው። በመሆኑም የጥበብ መንገዳችን ቅድሚያ የሚሰጠውን ለይቶ በማውጣት ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀስ መቻል ነው፤ አትራፊነት እንጂ ኪሳራ የሌለው መንገድ። ከህጻንነት ጀምሮ ያለው የእድገት መንገድ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባውን መለየት እንድንችል ካላደረግ እድሜ ቁጥር ብቻ ይሆናል።
እንደ ማህበረሰብ አኩሪ የሆኑ በርካታ እሴቶች አሉን። እንደ ማህበረሰብ ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባ ቅድሚ የመስጠት እድገታችን ግን እንዳስቆጠርነው አመት አይመስልም። የበዓል ሰሞን ዳንኪራ የሚያሳየን ይህንን ነው። ነገሮችን በልክ ማድረግ አለመቻል እስከ ህይወት መጥፋት ድረስ ሲያደርስ ይስተዋላል። ዳንኪራ ያው ዳንኪራ ነው፤ ስካርም ያው ስካር ነው፤ ከሰዓታት በኋላ ስሜቱ በኖ የሚጠፋ ከትላንቱ ዳንኪራ ሆነ ስካር ጋር ተዳምሮ ነገ ላይ ጎጆ መስራት የማያስችል።
የቤተሰብ ቦታ
ከዴዝሞንድ ቱቱ አባባሎች መካከል አንዱ “ቤተሰብህን አልመረጥክም፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፤ አንተም እንደሆንከው” የሚል ነው። ለቤተሰብ ትልቅ ቦታ ለመስጠት መነሻ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል ቤተሰብን መርጠን አለመወለዳችን እና አጋጣሚ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ የፈጣሪ ጣልቃገብነት ያለው በመሆኑ ነው። ትምህርትን መርጠን እንማራለን፤ የመኖሪያ አካባቢን እንዲሁ መርጠን ልንቀይር እንችላለን፤ ነገርግን ከእከሌ ቤተሰብ ልወለድ ብለን ፈጽሞውኑ ምርጫ አላደረግንም።
ቤተሰብ በህይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖረው የተገባ ነው። አንድ ግለሰብ ከራሱ ቀጥሎ የሚያገኘው ቤተሰቡን ነው። ለቤተሰብ ተገቢውን ቦታ በሚሰጡ ሀገራት ላይ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር የቤተሰብ ጠንካራ መሆኑ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ነው። ቤተሰብ ቦታ በተሰጠው መጠን ማደግ ይችላል። እድገቱም ሁሉን አቀፍ ይሆናል፤ ከትውልድ ትውልድም ተጽእኖው ይቀጥላል።
ግለሰባዊ ደስታም ጋር እንዲሁ የቤተሰብ ህይወት ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው። ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ቤተሰብ ብንሄድ ተመሳሳይ ነገር የማግኘታችን እድል ሰፊ ነው። ቤተሰብ ውስጥ የሌለ ደስታ በግለሰብ ህይወት ውስጥ ላይታይ ይችላል። ጆን ማእከስዌል የተባሉ ሰው “ቤተሰብና ወዳጅነት ሁለቱ የደስተኝነት ማቀጣጠያ ናቸው” ማለታቸውም ከእዚህ አንጻር ነው።
ቤተሰብ ባለንበት ዘመን ከየአቅጣጫው ፈተና እየበዛበት ያለ ይመስላል። ግለኝነት እየነገሰ በመጣበት ሁኔታ የቤተሰብ እድገት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው። በሁለት ጥንዶች ጋብቻ ውስጥ የሚወለዱ ልጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆሉ ልጆች ለሰፊ ማህበረሰባዊ ቀውስ ተጋላጭ እየሆኑ እንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፤ ቤተሰብም እንደ ተቋም ጉዳትን እያስተናገደ እናገኛለን። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960ዎቹ ውስጥ 95% የሚሆኑት አሜሪካውያን በሁለት ጥንዶች ትዳር ውስጥ እንደሚወለዱ የሚያሳይ ጥናት አሁን ባለንበት ዘመን 40% የሚሆኑ ልጆች በነጠላ ወላጅ ወይንም በጋብቻ ውስጥ ባልሆነ ሁኔታ እንደሚወለዱ ያነሳል https://gillespieshields.com/40-facts-two-parent-families/
ቤተሰብ ትልቅ ተቋም መሆኑን እና ተገቢው ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ማመን አስፈላጊ ነው። ለቤተሰብ ቦታ መስጠት መገለጫዎቻችን ግን ሊለያዩ ይችላሉ፤ አንዳንዱ ለቤተሰብ ቦታ መስጠትን የሚያየው በገንዘብ በመርዳት ነው። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ለቤተሰባቸው በአካል ከሚሰጡት ጊዜ በላይ ገንዘብ ለመስራት ተሯሩጠው ገንዘብ ቢሰጡ ይመርጣሉ። የብዙ ነጋዴዎች ችግርም ይህ እንደሆነ ይነገራል። ከሀገር ሀገር ተንቀሳቅሰው ገንዘብ ከእጃቸው አድርገው ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ማሟላት ዋናው ነገር እንደሆነ ያስባሉ። በገንዘብ ቤተሰብን መርዳት የሚገባ ነገር ቢሆንም ብቸኛው ግን አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በቤተሰብ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮች ከገንዘብ ጋር ብቻ የተገናኙ አይደሉምና።
ሌላው ለቤተሰብ ጊዜ መስጠትን ዋና ጉዳይ ያደርጋል። በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ እየኖሩ ነገርግን ከቤተሰብ ጋር ተጠባቆ መገኘትን የትክክለኛነት ማሳያ አድርጎም ይቀርባል። ቤተሰብ በችግር ውስጥ መሆኑን እያወቁ እግዛ ማድግ አለመቻል ተገቢነት የለውም። ቤተሰበን በገንዘብ፤ በምክር፤ እንዲሁም በመረጃ መርዳት አስፈላጊነት አለው። ጊዜን ብቻ በመስጠት ውስጥ ውጤታማ የቤተሰብ ህይወትን መገንባት አይቻልም። ሁልጊዜ የቤተሰብን ቦታ ለማየት በሚዛን መሆኑን ማሰብ አስፋላጊ ነው።
ሚዛን ነገሮች በልካቸው መሆናቸውን የምናረጋግጠበት ነው። በቤተሰብ ህይወት እንዲሁም በአጠቃላይ በስጋ ዝምድና ውስጥ ጊዜ፤ ገንዘብ እና ምክር ትልቅ ቦታ ይይዛሉ። ጊዜ ለመጨዋወት፤ ለመቀለድ፤ እግር ለመተጣጠብ፤ ያለፈን ትዝታ አንስቶ አብሮ ትዝታን ለመጋራት ወዘተ አስፈላጊ ነው። ገንዘብ ደግሞ በቁሳቁስ፤ እንዲሁም በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ባላቸው ነገሮች ከጎን መሆን መረዳዳት አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጠንካራ የቤተሰብ ህይወት አንጻር በቤተሰብ ውስጥ ያለውን መካፈል ትልቅ ፋይዳ አለው። ያለችውን ትንሿን ቦታ ተካፍሎ አብሮ ከመኖር አንስቶ መሶብ እስከመጋራት ድረስ እጅግ የገዘፈን የችግር ወራት አብሮ ማለፍ ይቻላል። ስንቱ ቤተሰብ በአንድ ክፍል ውስጥ እንደሚኖር ስንመለከት ትርጉሙ ትልቅ መሆኑ ይገባናል። በአንዱ ክፍል ውስጥ ባልና ሚስት፤ ልጆች እንዲሁም አብሮ የሚኖር እህት ወይንም ወንድም ሲጨመርበት እናስተውላለን። በዚህ መንገድ ለቤተሰብ የሚሰጠው ቦታ ትልቅ መሆኑኑን እናስባለን። ምክር ደግሞ ሌላው ነገር ነው። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚያልፍበት የህይወት መንገድ አለ። ይህን የሚያልፍበትን መንገድ ተረድቶ አንዱ ለአንዱ በምክር ለመቆም የሚያስፈልገው ከገንዘብም እንዲሁም አብሮ ጊዜን ከማሳለፍም ከፍ ያለውን ትኩረት ነው። በምክክር የሚፈቱ ብዙ ችግሮች ይኖራሉና።
የበዓል ድግስ በበዛበት ወር ውስጥ ስንሆን በአንድም በሌላም ከቤተሰብ ጋር መገናኘትን መነሻ በማድረግ ቤተሰብን በአግባቡ እናስብ ዘንድ የተጻፈ። ቤተሰብ ግን ከበዓል በላይ ነው።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም