በአንጀት ካንሰር የሞተችው የአርባ ዓመቷ ጎልማሳ ዴሚ ዴብራ ጄምስ በሽታውን ቀድሞ ለማወቅ ሁሉም ሰው ሰገራው ላይ ያሉ ለውጦችን ትኩረት እንዲሰጥ ስትመክር ቆይታለች።
ታዲያ እንዴት የአንጀት ካንሰርን ልንለይ እንችላለን?
ከዚህ የጤና ችግር ጋር በተያያዘ ሦስት ነገሮችን ልብ ማለት ይኖርብናል።
- በሰገራ ላይ ደማቅ ቀይ ወይም ጠቆር ያለ ቀይ ደም መታየት
- በሰገራ ላይ ለውጥ መታየት – በተደጋጋሚ መፀዳጃ ቤት መጠቀም ወይም ተቅማጥ ወይም የሰገራ መድረቅ
- ከምግብ በኋላ ሆድ የሞላ ሲመስል በታችኛው የሆድ ክፍል ላይ ሕመም ወይም እብጠት መኖር
እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በአንጀት ካንሰር የተያዘ ሰው የሚከተሉት አይነት ሌሎች ምልክቶችም ሊኖሩት ይችላሉ።
የክብደት መቀነስ፣ መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ በደንብ ያልተፀዳዱ ያህል መሰማት፣ ከተለመደው በተለየ የሰውነት መድከምና የመዛል ስሜት ያጋጥማል።
እነዚህ ምልክቶች ታዩ ማለት ግን የአንጀት ካንሰር አለ ማለት ላይሆን ይችላል።
ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች ለሦስት ሳምንታትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ከታዩ እንዲሁም የሚሰማን ነገር ትክክል ካልሆነ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።
በዚህም ተገቢው ምርመራ በፍጥነት ተደርጎ ካንሰር ከሆነ እና በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ከተደረሰበት ለማከም ቀላል ይሆናል።
አንዳንድ ጊዜ የአንጀት ካንሰር ሰገራ በተገቢው መስመር እንዳይወገድ በማድረግ መዘጋትን ሊፈጥርና ይህም ከባድ የሆድ ቁርጠት፣ ድርቀት እና ህመምን ሊያስከትል ይችላል።
እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም ችላ ሳይሉ ወደ ሐኪም ዘንድ በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው።
የበሽታውን ምልክቶች እንዴት መለየት ይቻላል?
መፀዳጃ ቤት በሚጠቀሙ ጊዜ የሚወጣውን ሰገራ ይመልከቱ፣ የተለየ ነገር ሲያጋጥምዎት የሕክምና ባለሙያ ለማማከር ወደ ኋላ አይበሉ።
በተለይ ሰገራ ላይ የደም ምልክትና መፀዳጃ ቤት ሲጠቀሙ የመድማት ሁኔታ ካጋጠመ በቀላሉ መታለፍ የለበትም።
አንዳንድ ጊዜ በሰገራ መተላለፊያ አካል ላይ ባሉ የደም ስሮች እብጠት ሳቢያ ቀይ ደም ሊወጣ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ በአንጀት ካንሰር ሳቢያ የተከሰተ ሊሆን ይችላል።
ጠቆር ያለ ደም ወይም ጥቁር ደም ሰገራ ላይ ከታየ ይህ የተከሰተው በአንጀት ወይም በጨጓራ ላይ ባጋጠመ የጤና ችግር ስለሚሆን አሳሳቢ ሊሆንም ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ቀጠን ያለ ሰገራ መኖር ወይም ከወትሮው በተለየ ቶሎ ቶሎ መፀዳዳት ሊኖር ይችላል።
ወይም ደግሞ አንጀት ውስጥ የተከማቸው ሰገራ ያልወጣ መስሎ መሰማት አሊያም በበቂ ሁኔታ አለመፀዳዳት ያጋጥማል።
በዩናይትድ ኪንግደም ስለ አንጀት ካንሰር መረጃ የሚሰጠው ድረ ገጽ ወደ ሐኪም ዘንድ ከመሄድ በፊት በየዕለቱ የሚታዩ ምልክቶችን በመከታተል መመዝገብ እንደሚገባ ይመክራል። ይህንንም ለሐኪምዎ መናገር ያለብዎትን ሳይዘነጉ አንድ ባንድ መናገር እንዲችሉ ይረዳል።
ሐኪሞች በተለያዩ የአንጀት ጤና እክሎች ያሉባቸው በርካታ ሰዎችን ስለሚመለከቱ በእራሳችሁ ላይ ያያችሁትን ለውጥ ወይም መድማት ካለ መናገራችሁ የበሽታውን መንስዔ ማወቅ እንዲችሉ ያግዛል።
የአንጀት ካንስር በዘር ይተላለፋል?
በአብዛኛው የአንጀት ካንሰር በዘር አይተላለፍም። ይሁን እንጂ የቅርብ የቤተሰብ አባል ከሃምሳ ዓመት ዕድሜ በፊት በበሽታው ተይዘው ሕክምና አድርገው የሚያውቁ ከሆነ፣ ይህንን ለሐኪም መናገር አስፈላጊ ነው።
እንደ ሊንቺ ሲንድረም ያሉ አንዳንድ በዘር የሚተላለፉ ካንሰሮች ለአንጀት ካንሰር የመጋለጥ እድል እንዲሰፋ ያደርጋል። ስለዚህ ሁኔታ ሐኪም ማወቅ ከቻለ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል ያስችላል።
የመጋለጥ ዕድልን እንዴት መቀነስ ይቻላል?
የሚከሰቱት የአንጀት ካንሰሮች ግማሽ ያህሉ ጤናማ የሕይወት ዘይቤን በመከተል ቀድመን ልንከላከላቸው የምንችላቸው እንደሆኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በብዛት አሰር ያላቸውን ምግቦችን በመመገብ እና ስብን በመቀነስ እንዲሁም በቀን ውስጥ ከስድስት እስከ ስምንት ብርጭቆ ውሃ በመጠጣት የአንጀት ካንሰርን ቀድሞ መከላከል ይቻላል።
ነገር ግን የሚያሳስብ ምልክት ከተከሰተ የጤና ባለሙያን ማማከር እና የካንሰር ምርመራ ማድረግ ይመከራል።
የአንጀት ካንሰር በትልቁ አንጀት ወይም በፊንጢጣ አካባቢ የሚከሰት ነው
የአንጀት ካንሰርን እንዴት መለየት ይቻላል?
የአንጀት ካንሰር ምልክቶች ከታዩ ፈጠን ብሎ ሐኪም ማማከር በሽታውን ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው።
ምርመራውም ቱቦ በመጠቀም ሁሉንም የአንጀት ክፍሎች በካሜራ በሚያሳይ መሣሪያ (ኮሎኖስኮፒ) ይደረጋል።
ወይም ደግሞ የተወሰነውን ክፍል ለማየት በሚያስችል መሣሪያ (ሲግሞዶስኮፒ) በተባለ ተጣጣፊ መሣሪያ ምርመራው ይካሄዳል።
በመጀመሪያው የአንጀት ካንሰር ደረጃ ላይ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች በሽታውን በቶሎ በመለየት አስፈላጊውን ሕክምና በወቅቱ ማግኘት ስለሚችሉ የሚከሰተውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል።
የካንሰር በሽታ በብዛት የሚከሰተውና ገዳይ የሚሆነው እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ በመሆኑ ልክ እንደ ሌሎች የካንሰር በሽታዎች ሁሉ በአንጀት ካንሰር የተያዙ ከ15 እስከ 40 ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በሕይወት የመቆየታቸው ዕድል ሰፊ ነው።
ሆኖም አጠቃላይ በሕይወት የመቆየት እድል ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር ሲነጻጸር በዩኬ ያለው ጥሩ የሚባል አይደለም።
የአንጀት ካንሰር ሕክምና ምንድን ነው?
የአንጀት ካንሰር በተለይ ቀድሞ ሕክምና ማድረግ ከተቻለ የሚድን በሽታ ነው።
በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል ያለው ሕክምና በአብዛኛው በግል የሚከናወን ሲሆን፣ የዘረመል ምርመራ ቀድሞ ማድረግ የተከሰተውን ካንሰር ለማከም ያስችላል። ይህ ዘዴ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተጨማሪ ዓመታትን በሕይወት እንዲቆዩ ይረዳል።
በየትኛውም የዕድሜ ክልል በበሽታው ለተያዘ ሰው ሕክምናው ይሰጣል።
ሕክምናው ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ ራዲዮቴራፒ ወይም ደግሞ እንደየግለሰቡ የካንሰር ሁኔታ ሌሎች ሕክምናዎች ሊሰጡ ይችላሉ።
የካንሰር ደረጃዎች የትኞቹ ናቸው?
- ደረጃ አንድ ካንሰር፡ በመጠን ትንሽ እና ወደ ሌሎች የአካል ክፍል ያልተሰራጨ
- ደረጃ ሁለት ካንሰር ፡ በመጠን ትልቅ ግን ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች ያልተሰራጨ
- ደረጃ ሦስት ካንሰር፡ በአካባቢው ወዳሉ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች (ሊይምፍ ኖድስ ) የተሰራጨ
- ደረጃ አራት ካንሰር፡ ካንሰሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመሰራጨት ሁለተኛ ዕጢ ይፈጥራል።
ምንጭ፡- ቢቢሲ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም