በአሁኑ ወቅት የየትኛውም የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነ ሀገር የኢኮኖሚው አስተማማኝነት የሚረጋገጠው ባለው የቴክኖሎጂ አቅም እንደሆነ ሁሉንም የሚያስማማ እውነታ ሆኗል። ይሄ የቴክኖሎጂ አቅም የሚለካው ሀገራት ባላቸው የቴክኖሎጂ ቁስ ስብስብ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ ቴክኖሎጂን የመረዳት፣ የመጠቀም፣ የማሻሻል ብሎም የመፍጠር አቅምን ታሳቢ በማድረግ ነው። የተለያዩ ሀገራት ላሉባቸው ጉድለቶች ነባራዊ ሁኔታን በመቃኘት ተገቢ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከመለየት ጀምሮ ቀጣዩን የሀገራቸውን ብሎም የአለማችንን ሁኔታ ሊቀይሩ ለሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ ይስተዋላል።
በአገራችን ወቅታዊ ክፍተቶችን በማጥናት መፍትሄ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከመለየት ባለፈ ቀጣዩን የአለማችንን ጉዞ በመገምገም መፃኢ ቴክኖሎጂዎች ላይ መስራት ባደጉትና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ያለውን የቴክኖሎጂ ልዮነት ለማጥበብ የጎላ አስተዋፅኦ አለው። ይሄም ማለት <> ብሎ በመክፈል አለም የሚግባባበት መመዘኛ የሀገራት ኢንዱስትሪያቸው ባለው የቴክኖሎጂ አቅም ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የተቆራኘ በመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያም በምን መልኩ ቴክኖሎጂዎችን በተሳካ መንገድ በማሸጋገር ለእድገቷ ልትጠቀመው እንደምትችልና ዘርፉ ለሀገር እድገት ያለው አስተዋፅዎ ምን እንደሚመስል በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካልና ኢንዱስትሪያል ትምህርት ክፍል ተመራማሪናና መምህር ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ጋር ቆይታ አድርገናል።
ቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት ምን ማለት ነው
ቴክኖሎጂን በተሳሳተ መንገድ ትርጉም በመስጠት ቴክኖሎጂን እንደ ማሺን፣ መሳሪያ በማየትና አንዳንድ ጊዜ የሳይንስን ጽንሰ-ሐሳብ እንደ ቴክኖሎጂ የመውሰድ የተዛባ የአመለካከት ችግሮች ይስተዋላሉ። ነገርግን ቴክኖሎጂ ማለት ሸቀጦችን ለማምረት እና አገልግሎቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያገለግሉ የእውቀት፣ የክህሎት፣ መሳሪያዎች፣ ልምድና ድርጅታዊ አወቃቀር ስርዓት ሲሆን፤ ቴክኖሎጂ የሚያካትታቸው የምርትና የምርት ሂደት ንድፍ እውቅትን፤ በምርት ተቋማት ውስጥ ውጤታማ የሆነ የአመራር ስርዓቶችን ሲሆን፤ ቴክኖሎጂ ማለት የመሣሪያዎችና የእውቀት ድምር ነው።
በመሆኑም የቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት አንድን የዳበረ ቴክኖሎጂ ካደገበት ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂያዊ አውድ ወስዶ ወደ ሌላ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቴክሎጂያዊ አውድ ማላመድ ሲሆን፤ አንድ ቴክኖሎጂ ተሸጋገረ የሚባለው ተጠቃሚው ቴክኖሎጂውን በደንብ አውቆ በሚገባ ሲጠቀምበት፤ ለአካባቢው ተስማሚ አድርጎ ሲቀዳው፤ ቴክኖሎጂው ሲበላሽ መጠገንና መስራት ሲቻል፤ ማሻሻያ (ሞዲፊክ) ሲያደርግና በተቀባዩ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቴክሎጂያዊ አውድ ውስጥ ማላመድና ማሰራጨት ሲቻል ነው።
ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ቅድመ ሁኔታን የሚያመለክቱት ቁሳቁሶችና እቃዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ተቋማዊ መሰረተ ልማት፤ ግልጽ የሆኑ የልማት ግቦች፤ ተስማሚ የሆነ ተቋማዊ ማዕቀፍ፤ የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ ለተቋሞችና ህጎች ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ አስተዳደራዊ አካሄዶችን ማቋቋም ሲቻል ነው። በአጠቃላይ በዋናነት ሁለት የቴክኖሎጂ ሽግግር መንገዶች ሲኖሩ፤ የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ (vertical transfer or adaptation process) የቴክኖሎጂ ፍሰት ከምርምርና ጥናት ደረጃ ሂደት (መሰረታዊ ምርምር) ወደ ፈጠራ ምርቶች (ሀገር በቀል ቴክኖሎጂን) ያካትታል። ሁለተኛው ዓለም አቀፍ (horizontal adoption process) የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ከአንድ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቴክሎጂያዊ አውድ ስርዓትና ዘዴዎች ወደ ተለያዩ ባህሎችና ስፍራዎች እንዲተገበሩ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው።
የቴክኖሎጂ ሽግግር በኢትዮጰያ ምን ይመስላል?
እንደ እኔ የቴክኖሎጂ ሽግግር በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን ቢያሳይም በተሳካ ሁኔታ እየተሸጋገረ ያለ አይመስለኝም። ለአብነት የሲሚንቶ ፋብሪካን ብንወስድ ቴክኖሎጂውን በደንብ እናውቀዋለን ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ምክንያቱም ቴክኖሎጂውን ለእኛ በሚስማማ መልኩ አላላመድነውም አላሰራጨነውምና። እንዲሁም ቴክኖሎጂውን ስላልቀዳነውና ስላላሻሻልነው ማሸጋገርም አልቻልንም። ስለዚህ መሰል ቴክኖሎጂዎችን በሀገራችን ለዘመናት ብንጠቀምም ወደ እኛ ነባራዊ ሁኔታ ቀይረን እየተጠቀምንበት ስላልሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግራችን በኔ እይታ ዝቅተኛ ነው።
ነገር ግን ከዛሬ 20ና 30 ዓመታት በፊት ወደ ሀገር ቤት ገብተው ካየኋቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል የብየዳ ማሽንን ይጠቀሳል፤ ይህ ቴክኖሎጂበወቅቱ በጣም ብርቅ ነበር፤ አሁን ግን ማህበረሰቡ በደንብ ይጠቀምበታል፣ ያውቀዋል፣ ይጠግነዋል፣ ቀድተዋቸውም አሻሽለዋቸዋል። ስለዚህ አሁን ላይ በሀገራችን ይሄን ማሽን ተጠቅሞ የተለያዩ የብረታ ብረት ስራዎችን መስራት ከከተማው እስከ ገጠሩ ድረስ የተለመደ ሲሆን፤ በእኔ ጥናትና የስራ ዘርፍ ካየኋቸው ቴክኖሎጂዎች በዚህ ደረጃ የተሸጋገረ አለ ለማለት አያስደፍርም።
በተጨማሪም በሀገራችን በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ዘርፍ አያሌ ቴክኖሎጂዎች እየተሸጋገሩ ሲሆን፤ በአግሮ ኢንዱስትሪው ላይ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቴክኖሎጂ ግንባታው ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ድረስ የሚያስተሳስር ስለሆነ የተሻለ ሽግግር ይታይበታል።
የሀገራችን የቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅፋቶችና ቁልፍ መፍትሄዎች
የሀገራችን የቴክኖሎጂ ሽግግር ችግሩ አንድ አይደለም እንቅፋቶቹም ብዙ ናቸው።ስለዚህ ማንኛውም ሽግግሩን የሚያዘገይና የሚያግድ ነገር እንቅፋት እንደሆነ ይቆጠራል። ስለዚህ የህግ፣ የመሠረተ ልማት፣ የተግባቦትና የባህል ተጽዕኖዎች ዋና ዋና እንቅፋቶች ሲሆኑ፤ የፋይናንስ ችግር፣ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ በድርጅት ውስጥ ያለ የግል ግንኙነት፣ የተንዛዛ አሰራር፣ ውሳኔ ሰጭ የሆኑ አመራሮች ውሳኔ ለመስጠት በቂ እውቀት አለመኖር፣ የአዋቂዎች እምቢተኝነት እና ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ተግዳሮቶች የተሳካ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዳይኖር ተጨማሪ እንቅፋቶች ናቸው።
በአጠቃላይ የአመለካከት ችግር ሀገሪቱ በዘርፉ ዳዴ እንድትል ያደረጋት በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት በሀገራችን የተሳካ ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ይኖርብናል።በሌላ በኩልም የቴክኖሎጂ በር ጠባቂዎችን ማደራጀት ያስፈጋል ሲሆን፤ እነዚህ ግለሰቦች ባካበቱት እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ባላቸው ብሔራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ትስስርና ግንኙነቶች ለቴክኒካዊ መረጃዎች ቅርብ በመሆናቸው በፍጥነት የሚለዋወጠውን ቴክኖሎጂ ንቁዎች ናቸው፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ምክር ይሰጣሉ፤ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ ገበያ ተመጣጣኝነቱንና ተስማሚነቱን አይተው ተወዳዳሪ ጥቅሙን ያጣራሉ፤ ልብ የሚያማልሉ ማስታወቂያዎችን በብስለት ይመዝናሉ።በመሆኑም ዘለቄታዊ ዕድገት እንዲኖርና በትንሽ ሀይል ከፍተኛ ምርት በማምረት ሰፊ የሆነ የሀብትሥርጭት እንዲኖር ያደርጋሉ።
በሀገሪቱ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች እነዚህን እድሎችና ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ባላቸው ቁርጠኝነትና የቴክኖሎጂ አስተዳደር ችሎታ ስኬታማነትን እንዲጨምሩ የሚያደርግ ሲሆን፤ ነባርና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዋና ተዋናዮች መሆን አለባቸው። ወደ ሀገር የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ምርት የመተካት ሥራ የፖሊሲዎቻችን ተቀዳሚ ዓላማ ከሆነ እንደ ቻይና በአጭር ጊዜ አመርቂ ዕድገት ማምጣት ይቻላል፤ የሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ለማሻሻል የመሠረተ ልማት፣ የብድር አገልግሎት፣ የምርምር በጀትና ሌሎች መመቻቸት አለባቸው፤ በምህንድስና ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ ምርምሮች ሀገር በቀል እውቀቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማሻሻል ትኩረት ያድርጉ። በአጠቃላይ በሀገሪቱ በእውቀት ላይ የተመሰረተና በምርምር የተደገፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊኖር ይገባል።
የሌሎች ሀገሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተሞክሮ
አንድን ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር መጀመሪያ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። ምክንያቱም አዳዲስ ነገሮችን ለማፍለቅ ካለመነሳሳታችንም በላይ ተቀብሎ በለውጡ ለመጓዝ ያለመፍቀድና በለመድነው አሰራር መቀጠል ነው የምንመርጠው። ለአብነት ሲንጋፖርን ብንመለከት እ.ኤ.አ በ1980 የነበሩበት ሁኔታና እ.ኤ.አ በ 2001 የነበሩበት ሁኔታ ሰማይና ምድር ነው። ይሄም የሆነበት ምክንያት መጀመሪያ ህዝባቸውን ለመቀየር ለውጥ ያስፈልጋል የሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጡ። በሁለተኛ ደረጃ ወደ ተግባር ገብተው ሰርቶ ማሳየት ጀመሩ። በሶስተኛ ደረጃ ስራውን የራሳቸው አድርገው የማላመድ ደረጃ የደረሱ፤ በእነዚህ ሶስት ደረጃዎች ተጫባጭ እድገትና ለውጥ ለማምጣት ችለዋል። ይህን ወደ እኛ ስናመጣው ትልቁ ችግራችን ስራዎችን በእቅድና በጥናት ሳይሆን በዘመቻ የምንሰራ መሆኑ፤ ባለን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ልክ ለውጥ ልናመጣ አልቻልንም።
የቴክኖሎጂ ሽግግር ስልቶች
ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ደረጃ ለመድረስ ሊወሰዱ የሚገባቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር ስልቶች አሉ፤ የቴክኖሎጂ ዱካዎችን መከተል ፤ አንዳንዶቹን ደረጃዎች መዝለል ወይም ሌሎች መንገዶች በመጠቀም አሻሽሎ መስራት ቴክኖሎጂዎችን በተሳካ ሁኔታ ማሸጋገር ያስችላል። በዚህ መሰረት ለእኛ ምቹ የሚሆነው መንገድ ደረጃዎችን መዝለልና አሻሽሎ መስራት ነው የሚል እምነት አለኝ።
ስለዚህ በዘመቻና በፖለቲካዊ ውሳኔ ሳይሆን በጥናትና በእቅድ ተመርኩዘን ስልቶቹን አጣጥመን ብንሰራባቸው በቴክኖሎጂ ሽግግሩ እንደ ሀገር ውጤታማ መሆን እንችላለን። በጥናት ተመርኩዘን የሚዘለለውን በመዝለል ማሻሻል የሚገባንን በማሻሻል የተሻለ ደረጃ መድረስ እንችላለን። በአጠቃላይ በሀገሪቱ የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የትምህርት ሚኒስቴር፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በ ”ሶስትዮሽ ትስስር” እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት ይኖርባቸዋል።
የቴክኖሎጂ ሽግግር ጥቅም
ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተሻሻለ ጥራትና አቅም በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባለፈ ፖለቲካዊ ተቀባይነትም ይጨምራል። በመሆኑም ቴክኖሎጂ ማለት ሁሉም ነገር ስለሆነ በቀላሉ የአለምን ገበያ ለመቆጣጠር ያስችላል። ስለዚህ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት፣ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት፣ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር፣ ጽዱና መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ከተሞች ለመመስረት ያስችላል። በአጠቃላይ ሀገራችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ብሔራዊ አቅማችንን በመገንባት ፈጣን ዕድገት በማምጣት ከአደጉ ሀገሮች ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
ሶሎሞን በየነ