በበጎ ሥራ በረከትን የመሰብሰብ ዘመቻ

ክረምት ነውና ሰዓቱ ሄዶ ከሥራቸው እንዳይስተጓጎሉ እንደሁም በዝናብ እንዳይመቱና ታክሲ እንዳያጡ ማልደው ይነሳሉ። ዛሬ ግን አነሳሳቸው ለሥራ አይደለም። ጤናቸውን በሕክምና ባለሙያዎች ለማረጋገጥና ነጋቸውን በተሻለ ጤንነት ለማየት ነው። ስለክረምት በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት መሰጠት የሰሙት ቀድመው ቢሆንም በሥራ ስለሚባክኑ ትኩረት ነፍገውት ነበር። እናም አንድ ወዳጃቸው ማታ ላይ ደውሎ ስላስታወሳቸው ነው በጠዋቱ ራሳቸውን አሰናድተው ለጉዞ የተነሱት።

መኖሪያቸው ሩቅ ነው። የታክሲ ወጪው ለርሳቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ግን ከጤናቸው የሚበልጥ የለም። በዚያ ላይ ለታክሲ በሚያወጡት ገንዘብ ብቻ መታከም አይችሉም። ስለዚህ ከቤታቸው እስከ አውቶብስ ተራ በዝናብ እየተመቱ ሜክሲኮ የምታደርሳቸውን አውቶቡስ ያዙ። ከዚያም አለርት ሆስፒታል ‹‹ያደርሰኛል›› ያሉትን መርጠው ገቡና ካሰቡት ቦታ በጊዜ ደረሱ። መርሐ ግብሩ በጠዋት ባይጀመርም እርሳቸው ግን አልተከፉም። ምክንያቱም የጠዋቷ ፀሐይ የማለዳውን ዝናብ አሸንፋ እያሞቀቻቸው ነው። የተሸመቀቀው እግራቸው በሙቀቱ እየተፍታታ እንደሆነ ተሰምቷቸው በደስታ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። አሁንም ቁጭ ብለው ፀሐይዋን እየሞቋት ነው።

የሕመማቸው መነሻ ከክረምቱ ብርድና ዝናብ ጋር ተያይዞ ነው። ለዚህ ደግሞ ውጪው ብቻ ሳይሆን ቤታቸው ጭምር አስተዋፅዖ ያደርጋል። ግርግዳው በጭቃ የተመረገ ቢሆንም በአግባቡ የተሠራ አይደለም። ከእንጨቶቹ መበስበስ የተነሳ አንዳንዱ ቦታ ላይ ክፍተት ይታይበታል። ብርዱን ደግሞ በከሰልና እንጨት ሙቀት ብቻ አይወጡትም። እንዲህ ምንም የማይከፈልባት ፀሐይ ስትወጣ በተፈጥሮ ፀጋ ራሳቸውን አፍታተው ኑሯቸውን ይገፋሉ። ዛሬ በዚህ ቦታ ሲገኙም ብዙ ተስፋን ሰንቀዋል። ምክንያቱም በበጎ ፈቃዱ ከጤናቸው አልፎ ቤታቸውም የሚጠገንላቸው እንደሚሆን ያስባሉና። ለዚህም ጥያቄ እንደሚያቀርቡ አጫውተውናል።

እንደሰማነው ይህ የሁለት ወር የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት የነፃ ጤና ምርመራና እንክብካቤ ብቻ አይደለም። ከዚያ የላቁ በርካታ ተግባራት ሊከወኑ የታቀዱበት ነው። አንዱ ባለታሪካችን እንዳሉት የችግረኞችና አቅመ ደካሞች ቤትም ይታደስበታል። እናም የእርሳቸውም ጥያቄ መልስ እንደሚያገኝ ይታመናል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ የሁለት ወሩ የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ‹‹ክረምት ይዞት የሚመጣው በረከት ብዙ ነው። ሀገርን ዜጎችን የመታደጉ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው። በተለይም ከጤናው አንጻር ክረምትን ተገን አድርገው የሚከሰቱ ነባርና አዲስ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር የማይተካ ሚናን ይጫወታል። ከዚያ ባሻገርም ሀገር ወጪ ልታደርጋቸው የሚችሉ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪዎችን ይታደጋል። ይህ ሲባልም በሕክምና መሣሪያዎች ጥገና፣ ወደ ውጭ ሄደው መታከም ያለባቸውን ዜጎች በሀገር ውስጥ እንዲታከሙ በማገዝና የመሰል ሥራዎች ወጪዎችን በመሸፈን ነው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕልውና እርካታን ይሰጣል። ጤና ላይ ሲሆን ደግሞ የተለየ መልዕክት አለው። ምክንያቱም ውጤቱ ሰው የማዳን ተግባር ነው። ለሰው ደስታውን መስጠትና ነገውን ጭምር ማብራት ነው። ይህ ተግባር በክረምት የሚከናወን ብቻም አይደለም። ክረምትን ለየት የሚያደርጉት ባሕሪያት ባለሙያዎች ከያሉበት ማለትም ውጪ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ተሰባስበው በተለያዩ ሙያዎች ተቀናጅተው የችግሩን እልባት መስጠት ስለሚችሉበት ነው። ለዚህም ማሳያው ባለፉት ዓመታት ከ2ሺህ በላይ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ዲያስፖራዎችንና በሀገር ውስጥ ያሉ የግልና የመንግሥት የጤና ተቋማትን በማስተባበር ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የነፃ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው።

ባለፈው ዓመት በነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የነፃ ሕክምና እንዳገኙ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ እስከአሁን ያለውን ተሞክሮ በማየት በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የነፃ ሕክምና ለመስጠት መታቀዱን ይናገራሉ። በተለይም ወቅቱ ክረምት በመሆኑ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች የሚከሰቱበት አጋጣሚ ሰፊ ነውና ይህንን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሠራ ያብራራሉ።

የወባ በሽታ መከሰቻ አጋጣሚው ብዙ ቢሆንም ዋና ተደርጎ የሚወሰደው በደለል የሚሞሉ ቦታዎች በስፋት ሲፈጠሩ ነው። ስለሆነም ይህ ሁኔታ እንዳያጋጥም እንደ ጤና ሚኒስቴር ችግሩ በስፋት ያጋጥማል በሚባሉና በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ውሃ የሚያቁሩ ረግራጋማ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራ ይከናወናል። ለዚህም 70 ሄክታር መሬት ላይ የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራዎች ይከናወናል ተብሎ በዕቅድ መያዙን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት የተሰጡ የነፃ ሕክምናዎች ከቀላል ሕክምናና ምርመራ እስከ ከፍተኛ ቀዶ ሕክምና ድረስ የዘለቁ ናቸው። ይህ ብቻ በቂ አይደለምና ይህንን ተግባር ለማጠናከር ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እናቶችንና በደም እጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገቡ ዜጎችን ለመታደግም ከአምናው በተሻለ መልኩ ይሠራል። ይህም የአምናው 40 ሺህ ዩኒት ደም የተሰበሰበ ሲሆን፤ ዘንድሮ 90 ሺህ ዩኒት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አንስተዋል።

ከረምቱ በጤናው ዘርፍ ሌሎች ተግባራትም የሚከናወንበት ይሆናል። አንዱ ጤናን እንዲሻሻል ከሚያደርጉ መካከል የመሣሪያዎች አቅርቦትና ጥራት ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ታስቧል። ለአብነት ባለፈው ዓመት 425 የሕክምና መሣሪያዎችን በመጠገን 48 ሚሊዮን ብር ከማዳን ታልፎ ዜጎች በመሣሪያው የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ሲሉም በቀረበው የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አፈጻጸምን አመላክተዋል። ይህ ቁጥር በዚህ ዓመት ወደ 400 የሕክምና መሣሪያ ከፍ እንደሚልም ተነግሯል።

ሌላው በዚህ ክረምት ይከናወናል የተባለው ጤና ተኮር ተግባር የጤና ተቋማትን ለታካሚዎች ፅዱ፣ ማራኪና ምቹ ማድረግ ነው። ከፅዳት አንጻር ባለፈው ዓመት የተጀማመሩ ሥራዎች ያሉ ሲሆን፤ ይህም በ11 ሆስፒታሎች ብቻ 21 ቶን ቆሻሻ ማስወገድ የተቻለበት ነበር። በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ደግሞ በ25 ሆስፒታሎች ላይ ሥራው ተሠርቶ 80 ቶን ቆሻሻ የማስወገድ ዕቅድ ተይዟል። ለዚህ ደግሞ የጤናው ዘርፍ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርባችኋል ሲሉ ተናግረው፤ ከዚህ በተጓዳኝ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አዲስ የሚጀመር ተግባር መኖሩን አመላክተዋል። ይህም 17 የጤና ተቋማትን የማደስ ተግባር ነው።

ክረምቱ ያለንን የምናጋራበትና አካባቢዎቻችንን የምናፀዳበት ነው የሚሉት ዶክተር መቅደስ፤ አገልግሎት የማይሰጡ መድኃኒቶችን ማስወገድ፣ መሣሪያዎችን መጠገንና ትርፍ የሆኑ ወይም የማያስፈልጉ ሆነው የተገኙ ነገር ግን ለሌሎች ተቋማት የሚጠቅሙ ንብረቶችን መስጠት የምንችልበት ይሆናል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ንፅሕናው የተጠበቀ ተቋምን መፍጠር እንችላለንና ይህንን የማድረጉ ሥራ አሁኑኑ ይጀምር ሲሉም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። በተደጋጋሚም ኦዲት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ጤናና ክረምት ከሚተሳሰሩባቸው ዓበይት ተግባራት መካከል አንዱ አረንጓዴ ዐሻራ ነው። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለምግብነትና ለሌሎች ዘርፎች ከሚያገለግሉት ባሻገር ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ባለፈው ዓመት እንደተከልን ሁሉ በዘንድሮውም ዓመት አጠናክረን የምንቀጥለው ይሆናል ያሉት ሚኒስትሯ፣ በ2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ250 ሺህ በላይ ችግኞች በጤናው ዘርፍ እንደሚተከሉና ከዚህ ውስጥም 25 ሺህ ያህሉ ለመድኃኒትና ለምርምር የሚያገለግሉ ችግኞች መሆናቸውን አመላክተዋል።

አረንጓዴ ዐሻራን በመድኃኒቱ ዘርፍ ማሳረፍ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የመድኃኒት ወጪን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ዜጎችን ፈጥኖ በመታደግና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠትም ሁነኛ መፍትሔን ያበጃል። ስለሆነም በዚህ ተግባር ላይ መሳተፉን ማንም ሰው እንደቀላል ሊያየው አይገባም ሲሉም አሳስበዋል።

በመጨረሻ በጤና ሚኒስቴር የሁለት ወር የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት ይሰጥበታል ያሉት በሆስፒታሎች ያለውን የምገባ ሥራ አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ መሥራትና የማዕድ ማጋራት ተግባራትን ማከናወንን ነው። ባለፈው በጀት ዓመት ማለትም በ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎች የነፃ የሕክምና አገልግሎት፣ የሕክምና መሣሪያዎችን መጠገን፣ ደም ልገሳና በሌሎችም ዘርፎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሥራት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል። ለአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ተደርጓል። ለበርካታ ወገኖችም ማዕድ የማጋራት ሥራ ተከናውኗል። በዘንድሮው ደግሞ ይህን ክንውን ከፍ አድርጎ ለመሥራት ታስቧል። ስለሆነም ሁሉም ለስኬቱ መረባረብ እንዳለበት አስረድተዋል።

የሁለት ወር የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎቱ ውጤት ገንዘብ የማይተመንለት ባይሆንም ባለፈው ዓመት 1ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ከመውጣት የታደገበት እንደሆነ መውሰድ ይቻላል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የነፃ ሕክምና አገልግሎቱ ነው። ቀጣዩ ወጪ ደግሞ የመሣሪያ ጥገናውን ይሸፍናል። በዚህ ዓመትም ይህንኑ ሥራ በተጠናከረ መልኩ በመከወን በአጠቃላይ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት አስበናል። ሲሉ አስረድተዋል።

በሁለት ወር የክረምት ጤና በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ባለፈው ዓመት ስኬታማ ተግባራት ያከናወኑ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ሚኒስትሯም ‹‹ይህ የእናንተ ስኬታማነትና ትጋት የሚታይበት በመሆኑ ድጋፋችሁ አይለየን›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እኛም በጎነት ለራስ ነውና ‹‹ይመለከተናል›› የምንል ሁሉ በቻልነው መጠን እንረባረብ በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You