በአስር አመቱ እቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል የማእድን ዘርፍ አንዱ ነው። የማእድን ዘርፉን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ሥራው በቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል እያለ እንደ ሀገር በተቀናጀና በተናበበ መልኩ እንዲከናወን የሚያስችል መዋቅር ተዘርግቶለታል ። ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንደሚባለው በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን እያንዳንዱ መዋቅር የየራሱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ። እያንዳንዱ መዋቅር እንደ ሀገር የተያዘውን የዘርፉን እቅድ ማሳካት ከቻለ የዘርፉን አልሚዎች፣ ማእድኑ ያለበትን አካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የሀገርን የኢኮኖሚ ማሳደግ ይቻላል ።
እስከ አሁን ካለው የዘርፉ እንቅስቃሴ መረዳት የሚቻለው ግን በዘርፉ አንዳንድ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ የተዘረጋው መዋቅር ሁሉ በሚፈለገው መልኩ የማይገኝና ችግሮችን እየፈታ የማይጓዝ መሆኑን ተከትሎ በዘርፉ እንደሚጠበቀው ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ ነው። ለዚህም ማሳያዎቹ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የበጀትና የሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች አለመሟላት ናቸው ። በክትትልና ቁጥጥር በኩልም ተመሳሳይ ችግር ይታያል ።
ዘርፉን በተመለከተ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የማእድን ሥራው የሚከናወነው ታች ሆኖ ሳለ፣ የማእድን ሀብቱም የሚገኘው በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ሆኖ፣ በሥራው ቦታ ጠንካራ በሆነ አደረጃጀት ሥራዎች እንዲሰሩ አለማድረግ የዘርፉን እድገት ጎድቶታል፤ ሁኔታው ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል አቅም እንዳይፈጠርም ምክንያት
ሆኗል ።
ዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድል በማስገኘት ኑሮአቸውን ለመለወጥ እንዲያስችላቸው ከማድረግ ባለፈ የማዕድን ውጤቶች ለዓለም ገበያ ውለው የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት፣ ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬ በማዳን የሀገር ኢኮኖሚን ከፍ ለማድረግ ያለው አበርክቶ የጎላ መሆኑን ተገንዝቦ ትኩረት ሰጥቶ አለመስራት ይስተዋላል፤ ስራው ብዙ የስራ እድል ሊፈጠርበት ሲገባ በጥቂት ተጠቃሚዎች ብቻ የሚከናወን መሆኑም ሌላው ክፍተት ነው ።
ማእድኑ ለሚገኝበት አካባቢ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ማእድናት በምርምርና ጥናት ለይቶና ሰንዶ ለመንግስትና ለአልሚዎች በማመቻቸት ረገድ ኃላፊነት ካለባቸው ተቋማት መካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኙበታል ። ተቋማቱ በዘርፉ በየጊዜው ጥናትና ምርምር ቢያካሂዱም፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎቹ መደርደሪያ (ሼልፍ) ከማድመቅ በዘለለ የፈየዱት የለም የሚሉ ጥቆማዎች ይደመጣሉ ።
የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር በመቀየር በኩል እስከታች የተዘረጋው የዘርፉ መዋቅርም የየድርሻውን በመወጣት ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል በመፍጠር፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እና እንደ ሀገር የተያዘውን ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ራእይን ማሳካት ይጠበቅበታል፤ ይሁንና በስራ አጋጣሚ በአንዳንድ አካባቢዎች ካለው ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው በማእድን ልማቱ ለመሰማራት እየሞካከሩ ያሉ ኩባንያዎችን በመደገፍ በኩል በተለይ በላይኛው መዋቅር በኩል ክፍተቶች ይስተዋላሉ ።
እኛም በዚህ ቅኝት እያንዳንዱ የቀበሌ፣ የወረዳና የዞን መዋቅር በማዕድን ዘርፍ በመንቀሳቀስ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እያከናወነ ስላለው ተግባር በደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ስላሉት የማዕድን አይነቶች፣ የማእድን ሀብቶቹ ጥቅም ላይ ውለው አልሚዎቹን እና የየአካባቢውን ማህበረሰብ እንዲሁም ሀገሪቱን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል እየተከናወነ ስላለው ተግባር የጉራጌ ዞን ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ዳምጠውን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል ።
አቶ ፍሰሐ እንደገለጹት፤ ጉራጌ ዞን ለግንባታ፣ለኢንዱስትሪና ለሌሎችም ግብአቶች የሚውል የማዕድን ሀብት በስፋት ከሚገኝባቸው የደቡብ ክልል ዞኖች መካከል ይጠቀሳል ።ለአብነትም በዞኑ የምሥራቅ ክፍል አካባቢ ላይምስቶን፣ግራናይት የመሳሰሉት የማዕድን አይነቶች፣በምዕራቡ ክፍልም ተመሳሳይ ሆነ ሀብት አለ፤ ከእነዚህም መካከል ለኢንደስትሪ በተለይም ለሲሚኒቶ ፋብሪካዎች ግብአት የሚውል የድንጋይ ከሰል፤ኖራ ድንጋይ፣ከከበሩ ማዕድናት ደግሞ ኦፓል ማዕድናት ይጠቀሳሉ ።
ለኢንደስትሪ ግብአት የሚውሉትን ማዕድናት ሀብት ክምችት በጥናት ለይቶ በተደራጀ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውል በክልሉ የተለያየ ድጋፍ ተደርጎ የዲላና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት እንዲያካሂዱ ተደርጓል ። በጥናት ግኝቱም በተለያየ መንገድ ከሚታወቁት የማዕድን አይነቶች በተጨማሪ ሌሎች ማእድናት በዞኑ እንደሚገኙ ተረጋግጧል ። ተጨማሪ የጥናት ሥራዎችን የሚጠይቁ የማዕድን አይነቶች መኖራቸውም ተደርሶበታል ።
በተለይም በክልሉና በዞኑ መካከል በተደረገ የውል ስምምነት በክልሉና በዞኑ የማዕድን ባለሙያዎች በጋራ በተካሄደ ጥናት በመጀመሪያው ዙር በተከናወነ የናሙና ውጤት በዞኑ እኖር ወረዳ ውስጥ የወርቅ ማዕድን መኖሩን የሚያሳይ ምልክት ማየት ተችሏል፤ ነገር ግን ያለውን የወርቅ መጠንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እርግጠኛ ከመሆን በተጨማሪ በጥልቀት የጥናት ሥራ ማድረግ ያስፈልጋል ።
የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናትንም በተመለከተም ኦፓል የሚባለው ማዕድን በዞኑ የምሥራቁ ክፍል በሶዶ፣ በምዕራቡ ክፍል ደግሞ በእኖር አካባቢዎች ስለመኖራቸው በተመሳሳይ በናሙና ጥናት ተረጋግጧል ።ተጨማሪ ጥልቅ የጥናት ሥራ የሚያስፈልገው የወርቅና የኦፓል ማዕድኖች የሚገኙባቸው በዞኑ የምዕራቡ አካባቢ ነው ።
የከሰል ድንጋይ ሀብትን በተመለከተም አቶ ፍሰሐ እንዳስረዱት፤ ማእድኑ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ቢገኝም፣ በተለይ በዞኑ አበሽጌ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በስፋት ይገኛል ። በአበሽጌ ወረዳ በጊቤ ይበሬ ቀበሌ አስተዳደር በ2013ዓም በኢንዱስትሪ ማዕድን የድንጋይ ከሰል የምርመራ ፈቃድ የወሰደው ሰን ማይኒንግ የተባለው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባቱ ልማቱን ከማጓተቱም በላይ ሁለት ቀበሌ የሚሆን ሰፊ ቦታ አጥሮ መያዙ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል ።
ወደ ልማቱ ባለመገባቱም የአካባቢው ማህበረሰብ ቅሬታውን እየገለጸ ይገኛል ። ኩባንያው ወደ አካባቢው ሲመጣ ልማቱ ወደፊት የሚያስገኘውን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ማህበረሰቡ ደስታውን መግለጫም እርድ አከናውኖ ነው ኩባንያውን በበጎ የተቀበለው ። የኩባንያው ወደ ስራ አለመግባት ግን የማህበረሰቡን ተስፋ አመንምኖታል ።
ችግሩን የተገነዘበው ክልሉ ለኩባንያው ፍቃድ ለሰጠው የማዕድን ሚኒስቴር በጽሁፍ ቢያሳውቅም፣ እስካሁን የተወሰደ እርምጃ ግን የለም ። ዞኑም ሆነ ክልሉ የኩባንያውን ፈቃድ መሰረዝ ባለመቻሉ እንጂ ፈጣን ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ።
ሌሎች በከሰል ማልማት የምርመራ ፈቃድ ለመውሰድ ሁለት ኩባንያዎች በሂደት ላይ ይገኛሉ ። በነዚህ ኩባንያዎችም ላይ ተስፋ ተጥሏል ። ደቡብ ሶዶ በሚባለው ወረዳ ላይ ከሁለት ወር በፊት አንድ ኩባንያ በይፋ ተመርቆ ወደ ማምረት ሥራ ውስጥ ገብቷል ። ግራናይት በሚባለው ማዕድን አይነት ላይም በአበሽጌሌና ሶዶ ወረዳዎች ውስጥ ለማልማት ፍቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ ።
በራስ አቅምና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጋራ ትብብር የጥናት ሥራ በዞኑ ውስጥ የማዕድን ሀብት ስለመኖሩ ከማረጋገጥ ባለፈ ሀብቱን ወደ ጥቅም በመለወጥ ላይ የሚሰራው ሥራ ሀብቱ አለ የሚባለውን ያህል እንዳልሆነ ይነገራል፤ የዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ከዞናቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዘው ምላሽ የሰጡን አቶ ፍስሃ እንዳሉት፤ የጉራጌ ዞን ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት መምሪያ ዋና ተልእኮና ተግባር በዞኑ ያለውን የሀብት መጠን ወይንም አቅም መለየት ነው ። በዚህ ረገድ በተለይ በ2014 በጀት አመት ሰፊ ተግባር ተከናውኗል ። የዞኑና የክልሉ ባለሙያዎች፣የዲላና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናቶችን አካሂደዋል ።
እንደ አቶ ፍሰሐ እምነት በጥናት የመለየቱ ሥራ ቢከናወንም፣ ወደ ልማት የገቡ ኩባንያዎችም ቢኖሩም፣ በድምሩ የሚያሳየው ውጤት ወደፊት ሰፊ የቤት ሥራ መኖሩን ነው ።በተያዘው በጀት አመት ለውጤት የሚያበቃ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚኖር እምነት አላቸው ።
ከነክፍተቶቹም ቢሆን ዞኑ እንደውጤት የሚጠቅሰው ነገር ይኖር እንደሆንም አቶ ፍሰሐ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ ዞኑ ለኢንዱስትሪ ግብአት በሚሆኑ ማዕድናት ላይ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም በጅምር ደረጃ የሚጠቀስ እንጂ ስላስገኘው ጥቅም ለመናገር የሚያስችል አይደለም ። ይህ ሲባል ግን ተስፋው የተሟጠጠ አይደለም ።ለግንባታው ዘርፍ በሚውለው ማዕድን ላይ ግን ጥሩ የሚባል ሥራ ተሰርቷል ።
በማህበር ተደራጅተው ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ወጣቶችንም ማፍራት ተችሏል ። የባለሀብቱ ተሳትፎም የተሻለ ነው ። በዚህኛው ዘርፍ ጥሩ የሚባል ነገር ቢኖርም ህጋዊ ሆኖ ከመሥራት ይልቅ ህገወጥነትን የመምረጡ ሁኔታ፣የአካባቢ ሥነመህዳርን ጠብቆ ለማምረት ያለው ፈቃደኝነት ማነስና በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ባለመሆኑ የበለጠ መሥራት ይጠበቃል ።
የዞኑ የ2015 በጀት አመት የእቅድ የትኩረት አቅጣጫን በተመለከተም አቶ ፍሰሐ እንዳብራሩት፤ ከጥናትና ምርምር አኳያ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናቀቁና ውጤቱን ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይህም ስራውን በጋራ የሚሰሩትን ወላይታ፣ዲላና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎችን ያካትታል ። ከማልማት አኳያም በተለይ ለግንባታ ግብአት የሚውሉ ማዕድናት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሀብት ክምችቱ በስፋት በሚገኝባቸው የዞኑ ወረዳዎች በትኩረት ለመሥራት በእቅዱ ተካትቷል። በግንባታ የማዕድን ዘርፍ በ2014 በጀት አመት ወደ 48 በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ወጣት ተጠቃሚ መሆን የቻለ ሲሆን፣ በዚህ በጀት አመትም የበለጠ በመስራት ወጣቶቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴው ተጠናክሯል ።
ያለፉ ክፍተቶችን አርሞ በመሙላት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብም ሆነ በእቅድ የተያዙትን ከግብ ለማድረስ የማስፈጸም አቅም ወሳኝ ነው፤ ከዚህ አንጻር ቢሮአቸው ከአደረጃጀት ጀምሮ ሥራውን በብቃት ለመወጣት የሚገኝበትንም በተመለከተ አቶ ፍሰሐ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ የማዕድን ዘርፉን የሚመራ ክፍል ተደራጅቷል ።እሳቸው በሚመሩት መምሪያ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ያካሄዱት የሥራ ግምገማ የሚያሳየው የማስፈፀም አቅም ዝቅተኛ ሆኖ መገኘትን ነው ። ዘርፉ ላይ የሚገኙትን ባለሙያዎች ክህሎት ማሳደግ ይጠበቃል ።
በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ወይንም ማነቆዎችን እንዲሁም መልካም ስለሚባሉት ተግባራትም አቶ ፍሰሐ ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ የማስፈጸም አቅም ውስንነትን መቅረፍ ያስፈልጋል፤ ባለሙያዎች የጥናት ሥራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው፣የታችኛውን መዋቅርም መደገፍ ከባለሙያው እንደሚጠበቅ እንዲሁም የሰው ኃይል መጨመር እንደሚያስፈልግ በሥራ ግምገማ ከተለዩት መካከል ይጠቀሳሉ ።
በዚህ መልኩ በተከናወኑ የማስፈጸም አቅምን የማሳደግ ተግባራት በ2015 በጀት አመት የተሻለ አፈጻፀም ለማስመዝገብ ይረዳል የሚል ተስፋ አሳድሯል ። በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያና የተሟላ ቴክኖሎጂ ቢኖር ግን የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል ። በአቅም ውስንነት ሳቢያ እነዚህን ማሟላት አለመቻሉ አንዱ ተግዳሮት ቢሆንም፣ በተቻለ አቅም ጥረት እየተደረገ ነው ። ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን አንዳንድ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንም ቢጠየቅ ፈቃደኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለም፤ ሁሉንም አማራጭ ማየት ግን ከአስፈጻሚው አካል ይጠበቃል ።
ዞኑ ከፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባይኖረውም ሚኒስቴሩ ፍቃድ የሚሰጣቸው ኩባንያዎች በዞኑ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው በዞኑ የማዕድን ዘርፉን የሚመራው አካል ሥራቸውን በመከታተል ያለውን ሁኔታ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት የሚሉት አቶ ፍሰሐ፣ ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ የማይገቡ ኩባንያዎች አዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንቅፋት መሆናቸውን ይገልጻሉ ። የኩባንያዎቹ ስራ አለመጀመር የአካባቢው አርሶ አደር ‹‹ቦታ ሊይዙብኝ ነው ። ሳያለሙ ለራሳቸው ሊጠቀሙ ነው›› የሚል ስጋትና ጥርጣሬ ሊያድርበት እንደሚችል ይጠቁማሉ ። የፌዴራል መንግስት ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ፈጣን ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው አስምረውበታል ።
በአጠቃላይ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘውን የማዕድን ሀብት በተመለከተ የሀብት ክምችት ይገኝባቸዋል በተባሉ በተወሰኑ የክልሉ ወረዳዎች ጥናትና ምርምር በማድረግ ባለፈው አመት ሲሰራ የቆየው ዲላ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ውጤቱን ለሚመለከተው ክፍል ማስረከቡን በዚሁ አምዳችን ለንባብ ማብቃታችን ይታወሳል ። ጥናቱን መሠረት አድርጎ ወደተግባር መለወጥ የማዕድን ዘርፉን የሚመራው አካል ስልጣንና ኃላፊነት ነው ።
የምርምር ሥራውን በመምራትና በማስተባበር በቅርበት ሲሰሩ የነበሩት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍል ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ደረጄ ክፍሌ እንደሚሉት፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለክልሉ ያስረከበው የጥናት ሰነድ ወደ ሥራ ስለመለወጡ መረጃ ጠይቀው በዞን ደረጃ ዘርፉን የሚመሩ አካላት ስለጥናቱ መረጃ እንደሌላቸው መገንዘባቸውን ተናግረዋል ።
ዘርፉን የተመለከተ ማንኛውም መረጃ እስከታችኛው መዋቅር መድረስ ይኖርበታል፤ ላይ ብቻ የሚቀር ከሆነ ሥራውን ተናብቦ ለመሥራት ያስቸግራል ። ይሄ መታረም አለበት ያሉት ዶክተር ደረጄ፣ ዩኒቨርሲቲው ከአንድ ወር በፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ መድረክ ማካሄዱን ይገልጻሉ ። በመድረኩም በማዕድን ዘርፉ ባለፈው በጀት አመት የተከናወነውንና አፈጻጸማቸው፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት መጠናከር ያለበት መሆኑ እንዲሁም ቀጣይ የጋራ ሥራ አቅጣጫ መነሳቱን ያብራራሉ ። በቀጣይ እቅዳቸው ከዩኒቨርሲቲዎች የሚፈልጉትም ጭምር በሪፖርቱ መቅረቡን አመልክተዋል ።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ውጤቱን ካስረከበ በኃላ ወደተግባር መለወጥ የነርሱ ተግባር እንደሆነ ቢገነዘብም ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ የጠቀሱት ዶክተር ደረጀ፣ በተለይም ወደሥራው የሚሰማሩ ወጣቶች ሥልጠና እንዲያገኙ ዩኒቨርሲቲው ባለሙያ በመስጠት እገዛ አንደሚያደርግ ገልጸዋል ።በዩኒቨርሲቲው በኩል እንዲህ ያሉ ተግባራት በተከታታይ የሚከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀው፣ የጥናትና ምርምር ሥራውም ቢሆን ዩኒቨርሲቲው በራሱ ከሚያከናውነው በተጨማሪ ክልሉ ፍላጎት ሲያቀርብ አብሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም