የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች በተሻሻለው አዲስ የውድድር መርሃግብር መሰረት ነገ በባህርዳር ስቴድየም በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል። የጣና ካፕ ውድድር ዋንጫ ከቀናት በፊት ባህርዳር ስቴድየም ላይ ማንሳት የቻለው ወልቂጤ ከተማ በአርባምንጭ ከተማ ቀን ሰባት ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ የውድድሩ መክፈቻ ሲሆን አስር ሰአት ላይ ባህርዳር ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን እንደሚገጥም አዲስ ከወጣው መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ዕጣ የማውጣት ፕሮግራምን ባሳለፈው ሐምሌ 26 ቀን በፅ/ቤቱ አዳራሽ ቀንና የውድድር ቦታውን ሳይገልፅ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በወቅቱ በወጣው ፕሮግራም መሠረት በ5ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በ6ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በ14ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከተማ ጋር እንደሚገናኙ ተገልፆ ነበር።
ይሁን እንጂ አዲስ ይፋ በተደረገው የውድድር መርሀ ግብር የ2015 የውድድር ዘመን የ1ኛው ዙር መርሐ-ግብር ከላይ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ታውቋል። ይህ መሆኑ ደግሞ በስፖርት ቤተሰቡ ዙሪያ የመቀየሩ ምክንያት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄን አስነስቷል። ለዚህም ጥያቄ ለሶከር ኢትዮጵያ ምላሽ የሰጡት የሊጉን አክስዮን ማኅበር ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፣ “ የሁለት ዓመት የውድድር ዘመናችን ምን እንደሚመስል ከሱፐር ስፖርት ጋር ግምገማ አድርገናል። ብዙ ጠንካራ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ሦስት ነገሮች ላይ አተኩረን መስራት እንዳለብን ተስማምተን አቅጣጫም ተሰጥቶበት ተለያይተናል። አንደኛው በጨዋታዎች ላይ ስታዲየም የሚገኙ ተመልካቾች ውስንነትን አይተናል። እግር ኳስ ያለ ተመልካች ምንም አይነት መስብ እንደሌለው በማሰብ በርከት ያሉ ደጋፊዎች ያሏቸውን ክለቦች ውድድሩ ለሚዘጋጅበት ከተማ ቅርብ ማድረግ እንዳለብን ተስማምተናል። በዚህም መሠረት የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አስቀድሞ በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት በ5ኛ ሳምንት ባህር ዳር ላይ ቢሆንም የሚኖረው ተመልካች ውስን ነው። አዳማ ብታደርገው ግን ጨዋታው በብዙ ሺ ተመልካች ታጅቦ የሚካሄድ በመሆኑ ለመቀየር ተገደናል” ብለዋል።
በተመሳሳይ ፋሲል ከነማ ከቅዱስ በ6ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ቢደረግ የሚኖረው ተመልካች ጥቂት መሆኑ ነው። ባህር ዳር ቢሆን የሚኖረው ተመልካች በርካታ መሆኑን ከግምት በማስገባት መርሃግብሩ ተስተካክሏል። አሁን ፋሲል ከጊዮርጊስ ነው ባህር ዳር የሆነው በቀጣይ ደግሞ ሁለተኛው ዙር ሲመለስ የጊዮርጊስን ጥቅም በጠበቀ መልኩ አዲስ አበባ ከሆነ ሊያገኘው ይችላል። ካልሆነ ግን ቅርብ በሆነው በርከት ያሉ ደጋፊዎቹን በሚያገኝበት ከተማ አዳማ ሊያገኘው ይችላል። በዚህ ውድድሮች ተመልካች ሊኖራቸው ይገባል። ተመልካች ሊኖራቸው እንዲገባ ደግሞ ተመልካች ያለበት ቦታ ውድድር ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ መነሻነት መርሐ-ግብሩ ላይ ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደቻሉ ስራአስኪያጁ አብራርተዋል። ወደ ፊትም ገበያውን መሠረት ባደረገ መልኩ ተመሳሳይ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
እንደ ስራአስኪያጁ ገለጻ፤ ይህ አይነት አሰራር ለሊግ ካምፓኒው ሳይሆን ጥቅሙ ለክለቦች ነው። ለምሳሌ ባህር ዳር ከተማ ከፋሲል ከነማ አስቀድሞ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ከሆነ በ14ኛ ሳምንት አዳማ መጫወት ነበረባቸው፤ ግን ይሄ ብዙ ተመልካች ሊኖረው የሚችል ጨዋታ በመሆኑ ወደ 3ኛ ሳምንት በማምጣት ባህር ዳር ላይ እንዲካሄድ ተደርጓል።
ሁለተኛ ማሻሻያ የተደረገበት ጨዋታ መጀመሪያ ሰዓቱ ለተመልካች አመቺ አለመሆኑን በመረዳት የተቀየረ ነው። አቶ ክፍሌ እንደገለጹትም፤ ለምሳሌ የአራት ሰዓት ጨዋታ ከዚህ በኋላ የሚቀር ይሆናል። ይህ ሰዓት ሊጉ እንደ መጀመሪያ መሆኑ መጠን ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል። ከዚህ በኋላ ግን ተመልካች የሚስብ ብዙ ተመልካች ያለው ውድድር መሆን እንዳለበት በማመን ሜዳቸው መብራት የሌላቸው ከተሞች ጨዋታዎቹ ሰባት እና አስር ሰዓት እንዲሆኑ እና መብራት ያላቸው ሜዳዎች ደግሞ ዘጠኝ እና አስራ ሁለት ሰዓት እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሦስተኛው ማሻሻያ የተደረገው ውድድሩን የሚያዘጋጁ ከተሞች ከዚህ ቀደም የመክፈቻ ጨዋታዎችን አያደርጉም ነበር። አሁን በተደረገው ለውጥ ሦስቱም ከተሞች ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና አዳማ የመክፈቻ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ ነው። ይህም ከሱፐር ስፖርት ጋር በተደረገው ውይይት መሰረት የመጣ መልካም ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ውድድሩን የሚመራው አክሲዮን ማህበሩ ዘንድሮ በጠንካራ ሁኔታ ወደ ገብያ የሚገባበት ጊዜ እንደሚሆን አቶ ክፍሌ የጠቆሙ ሲሆን፤ በዚህም ከፍተኛ የሆነ የቅስቀሳ ስራዎችን በተለያዩ መንገዶች እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የሊጉን ጥራት እና ዕድገት ለመጠበቅም ሰፊ ስራ ይሰራል ብለዋል። በዚህ ስራ ውስጥ አንዱን ክለብ ለመጥቀም ሌላውን ለመጉዳት የሚሰራ ስራ አለመኖሩን ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባም አክለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም