1977 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ነው:: ወቅቱ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በርሃብ የተጠቃበትና ሺዎች የረገፉበት ፤ ከርሃብ የተረፉትም ቀያቸውን ትተው እግር ወደ መራቸው የተሰደዱበት ወቅት ነው:: ኢትዮጵያም የዓለም መገናኛ ብዙኃን የወሬ ማድመቂያ ሆና የሰነበተችበትና ብዙኃንም እጃቸውን ለእርዳታ የዘረጉበት ጊዜ ነበር::
ይህ ክፉ ወቅት ግን ለአሸባሪው ሕወሓትና መሰሎቹ ግን የደስታ ጊዜ ነበር:: ከተራቡ አፎች እህል በመንጠቅ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን አጋብሰዋል:: ለተራቡ ዜጎች ከዓለም ሕዝብ ከተሰበሰበው 100 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 95 ሚሊዮን ዶላሩን ለመሣሪያ ግዥ በማዋል ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ሠርተዋል:: ሺዎች በየቀኑ እየረገፉ ባሉበት ወቅትም የየቡድኑ አባላት በደስታና በፌሽታ ዳንኪራ ሲወርዱ ተስተውለዋል::
የ1977 ዓ.ም ርሃብ በፈጠረላቸው መልካም አጋጣሚም እራሳቸውን በጦር መሣሪያ አደራጅተዋል:: የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለማግኘት ችለዋል:: በዚህም ቀደም ካለው ጊዜ በተሻለ መልኩ በጦር ሜዳ ድል ቀንቷቸዋል:: ህልውናቸውንም በርሃብ ላይ አጽንተዋል:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሕወሓት ርሃብና ድህነትን እንደዋነኛ በሥልጣን የመቆያ ስልት በመውሰድ የአገዛዙ አንዱ አካል አድርጎት ኖሯል::
አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ባስተዳደረባቸው 27 አመታት በአገሪቱ ልማትን ከማረጋገጥ ይልቅ የድሃ ድሃ በሚል መርጃ ግብር ሴፍትኔት ፕሮግራምን እንደዋነኛ የልማት መሣሪያ አድርጎ ሲያስተዳድር ቆይቷል:: አገሪቱ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶችና የሰው ኃይል ቢኖራትም ሕወሓት መራሹ አስተዳደር እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ አስተባብሮ መምራት ባለመቻሉ ዜጎች ሴፍትኔት ጥገኛ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸው ቆይቷል::
አሸባሪው ቡድን ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ሕዝብ እንኳን ለውጥ ማምጣት አልፈለገም:: ትግራይን ሲስተዳድር በነበረበት ወቅትም 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ በሴፍትኔት ይተዳደር ነበር:: ቡድን መራሹ አገዛዝ ሕዝብ በራሱ የተፈጥሮ ሀብትና እውቀት መጠቀም ከጀመረ ኋላቀር የሆነውን የኢህአዴግ አስተዳደር የመቀበል ፍላጎት ስለማይኖረው አደህይቶና አቆርቁዞ የመግዛት ስልትን ሲከተል ኖሯል:: በዚህም አገዛዙ በነበረባቸው የስልጣን አመታት የድህነት ምጣኔው ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱም በላይ በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከሚገኙ 50 አገራት በመበደር ተወዳዳሪ ያልተገኘላት አገር ለመሆን በቅታለች::
በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ማብቂያም የኢትዮጵያ የዕዳ መጠን ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርቷ እስከ 60 በመቶ የደረሰ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር ሆነ ተቋማት መበደር የማትችልበት ደረጃ ደርሳለች:: በዚህም በድህነቷ የዓለምን ትኩረት የሳበች አገር እንድሆን አድርጓታል:: ይህም ድህነትን እንደ አንድ ስኬት ለሚያየውና ኢትዮጵያን የማደህየትና የማቆርቆዝ አላማ ለነበረው የአሸባሪው ሕወሓት አስተዳደር እንደትልቅ ስኬት የሚታይ ነበር::
ድህነትንና ርሃብን እንደ አንድ የፖለቲካ መሣሪያ የሚጠቀመው ቡድን ከሥልጣን ተወግዶ መቀሌ ከመሸገ በኋላም የትግራይን ሕዝብ በማስራብ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል:: በተለይም ጥቅምት 20 ቀን 2013 በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላና በአፀፋውም ኢትዮጵያውያን በ15 ቀናት ውስጥ ቡድኑን ጠራርገው ተንቤን በርሃ ከከተቱት በኋላ በጦር ሜዳ ያጋጠመውን ሽንፈት በዲፕሎማሲ ለማሸነፍ በርካታ ሙከራዎችን አድርጓል::
ከእነዚህ ሙከራዎች ዋነኛው ደግሞ ትግራይ ሕዝብ ተርቧል የሚል የሀሰት ትርክት በማሰራጨት የውጭ ደጋፊዎቹና በእነሱ የሚታዘዙ መገናኛ ብዙኃን እንዲያስተጋቡለት ማድረግ አንዱ ስልት ነበር:: የኢትዮጵያ መንግሥት የመጀመሪያውን ዙር ጦርነት አገባዶ ከመቀሌ ሲወጣ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ የትግራይ ሕዝብ እንዳይራብ በቂ የምግብ እህል ክምችትና የነዳጅና የመድኃኒት አቅርቦት በመጋዘኖች ውስጥ አስቀምጦ ወጥቷል::
ሆኖም ከሥልጣኑ ውጪ ለሕዝብ ሕይወት ደንታ የሌለው የሽብር ቡድኑ መንግሥት ትቶት የሄደውን የእርዳታ እህልና ነዳጅ ለጦር ኃይሉ ተጠቅሞበታል:: በምትኩም የትግራይ ሕዝብ ተራበ በማለት የቁራ ጩኸት ሲያሰማ ቆይቷል:: ይኸው ጩኸትም ዛሬም ድረስ ቀጥሏል:: መንግሥት በጦርነትም ውስጥ ሆኖ ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ በርካታ የሰብአዊ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ቢሆንም ርሃብን እንደጦር መሣሪያ የመጠቀም ልምድ ያለው ይኸው አሸባሪ ቡድን የትግራይ ሕዝብ በርሃብ አለቀ የሚል የስላቅ ለቅሶ ሲያሰማ ቆይቷል::
በተለይም ይኸው ለቅሶው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተአማኒነትን እንዲያገኝ የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ በርካታ መሰናክሎችን ሲፈጥር ቆይቷል:: የእርዳታ እህል የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ ከማድረግ ጀምሮ የገቡትም እንዳይመሱ በማድረግ የጦር ኃይሉን ለማመላለሻነት እየተጠቀመበት ይገኛል::
እንደ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን መረጃ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስም የእርዳታ እህል የጫኑ 6ሺ631 መኪኖች ወደ ትግራይ የገቡ ሲሆን መመለስ የቻሉት 4ሺ599 ብቻ ናቸው:: 2ሺ32 መኪኖች የአሸባሪ ቡድኑን ታጣቂዎች በማመላለስ ተግባራት ውስጥ ተጠምደው ይገኛሉ:: ይህ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ የራሱን አሉታዊ ጎን እንደሚያሳርፍ ቢታወቅም ርሃብን ዋነኛ የፖለቲካው መሣሪያ ማድረግ ለሚፈለግው አሸባሪው ሕወሓት ግን ከዚህም የከፋ እንዲመጣ ምኞቱ ነው::
«ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ» እንደተባለውም መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ሲል አሸባሪ ቡድኑ እንደሚጠቀምበት እያወቀ በርካታ ሰብአዊ ዕርዳታዎችን ወደ ትግራይ ሲልክ ቆይቷል:: ከሐምሌ 1 ቀን 2014 እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ባለው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ240 ሺ በላይ ሜትሪክ ቶን ምግብ፤ 52ሺ 645 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች፤ 258 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት፤ 7ሺ275 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንዲሁም 2ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል:: ይህ እንግዲህ አሸባሪ ቡድኑ ለጦርነት አቆብቁቦ በነበረባቸው ቀናት ዋዜማ ነው::
በትግራይ ሕዝብ ርሃብና ጉስቁልና ላይ ማትረፍና ዕድሜውን ማራዘም የሚፈልገው አሸባሪው ሕወሓት መንግሥት የላካቸው ሰብአዊ ዕርዳታዎች ወደ ኅብረተሰቡ እንዳይደርስ በማሰብ ከ547ሺ ሊትር በላይ ነዳጅ ከተባበሩት መንግሥታት መጋዘን ውስጥ በመስረቅ የእርዳታ ማቅረቡን ሥራ አስተጓጉሏል::
የሽብር ቡድኑ መቀሌ ወደሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን በኃይል በመግባት 12 የነዳጅ ቦቴዎችን በአጠቃላይ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ በዘረፈበት ወቅትም የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌ የቡድኑ ድርጊት አሳፋሪና አስጸያፊ መሆኑን መግጻቸው የሚታወስ ነው::
አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ተግባር ከዚህም በላይ የሚያስብለው ቢሆንም ቡድኑ ዝርፊያ፤ ውንብድና ሌብነት እና ውሸት ያደገበት በመሆኑ አሳፋሪና አስጸያፊ ተግባራቱን ግብአተ መሬቱ እስኪፈጸም ድረስ የሚቀጥልበት ይመስላል:: ይህንን የትግራይ ሕዝብ በአግባቡ ተገንዝቦ ቡድኑን በቃህ ሊለው ይገባል።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም