
አዲስ አበባ፡- የድምፃዊ ማዲንጐ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።
የድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የክብር አሸኛኘት እና የቀብር አፈፃፀም ዙሪያ አስመልክቶ ለቀብር ሥነ ሥርዓት የተቋቋመው ኮሚቴ ትናንት በሰጠው መግለጫ እንዳለው፤የድምጻዊው ቀብር ሥነሥርዓት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 9 ሰዓት ይፈጸማል።
ኮሚቴውን ወክሎ መግለጫውን የሰጠው አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ እንደገለጸው፣ የማዲንጐ ህልፈተ ሕይወት ድንገተኛ በመሆኑ አስደንጋጭ ነው።
በሕይወት ዘመኑ የሠራቸው ሥራዎች ዘመን ተሻጋሪና ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖ የነበራቸው ናቸውም ብሏል።
የአርቲስቱ ሕልፈተ ሕይወት የመላው ኢትዮጵያ ኃዘን ነው ያለው አርቲስት አረጋኸኝ፤ ቀብሩ በዛሬው ዕለት በ9 ሰዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል። ከጠዋቱ አራት ሰዓት አስከሬኑ ከቤቱ በመውጣት ወደ አንድነት ፓርክ በማቅናት በቦታው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና የሥራ አጋሮቹ በሚገኙበት የክብር ሽኝት ይደረግለታል።
ሌላው የኮሚቴው አባል ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁን ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍና ማዲንጐን በሚመጥን መልኩ ሥርዓተ ቀብሩ እንዲፈጸም ማድረግ አለባቸው ብሏል። ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ጋዜጠኛ ሰይፉ ገልጿል። ኮሚቴው የሥራ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በስፍራው በመገኘት ሥርዓተ ቀብሩን እንዲያስፈጽሙ ጥሪ አቅርቧል።
ወርቃማው ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሲታወስ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ አዘዞ ተወልዶ በሦስት ወሩ ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ ሄዶ እዚያው አደገ። አብሮት የኖረው ስሙ ማዲንጎ ይሁን እንጂ ፥ እናትና አባቱ ያወጡለት መጠሪያ ስም “ተገኔ” ነበር፤ “ጠበቃዬ ፥ ጋሻ መከታዬ ማለት ነው” ብሎ ነበር ራሱ ማዲንጎ።
ማዲንጎ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው ቃለ ምልልሶች አባቱን ጨምሮ አብዛኛው ቤተሰቡ የቤተ ክህነት አገልጋይ የነበሩ መሆናቸውን ተናግሯል። በልጅነቱ የሙዚቃ ፍቅር እንዳደረበት ይናገር የነበረው ማዲንጎ፥ የሰባተኛ ክፍለ ጦር ካምፕ የ603 ኮር የሙዚቃ ቡድን ልምምድ ሲያደርግ ከተመለከተ በኋላ ድምጻዊ መሆን እችላለሁ በማለት እድል እንዲሰጡት ጠይቆ እንደነበርም ነው በቃለ ምልልሶቹ የተናገረው።
እናም በወቅቱ እድሉን አግኝቶ የድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩን ” ና ተላክ ልቤ ፥ ልላክህ ልስደድህ ልቤ” የተሰኘውን ሙዚቃ ተጫውቶ አድናቆት ተችሮታል።ተቀባይነትን አግኝቶም በዛው በወታደር ቤት ሙዚቃውን የቀጠለ ሲሆን፥ “ማዲንጎ” የሚለው ስሙም እዛው እንደወጣለት ነው የገለጸው።
ማዲንጎ በአንድ ወቅት ኤፍሬም ታምሩን እንደ አርአያ (ሞዴል) የሚመለከተው እና በዋናነትም የኤፍሬም ሥራዎች ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባት ምክንያት እንደሆኑት እና በብዛት የእርሱን ሥራዎች እንደሚጫወትም ነው ይናገር የነበረው።
በተጨማሪም ሙሉቀን መለሰን፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ይሁኔ በላይ፣ ኤልያስ ተባባልን እንደሚያደንቅ እና የእነሱን ሙዚቃዎች እንደሚጫወት አውርቷል።
ማዲንጎ በታዳጊ የኪነት ቡድን ከዚያም በወታደር ቤት ብዙ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ኑሮውን ባህርዳር ከተማ በማድረግ ድምፃዊ የመሆን ሕልሙን መስመር አስያዘ።በይፋ ወደ ሙዚቃው ዓለም በተቀላቀለባት ባህር ዳር ከተማም በ120 ብር ወርሐዊ ደመወዝ ተቀጥሮ ቤተሰቡን እያገዘ ይኖር ነበር።
በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የተለያዩ የሙዚቃ ባንዶችን በመቀላቀል የታዋቂ ሙዚቀኞች ሥራዎችን በማቀንቀን ተወዳጅነትን አገኘ። በሂደትም በ1987 ዓ.ም “ስያሜ አጣሁላት” የተሰኘውን እና እሱ የልጅነቴና ከሰው ጋር አስተዋወቀኝ የሚለውን አልበሙን ለሕዝብ ጆሮ አደረሰ።
በዚህም አድናቆትን እና የሕዝብ ፍቅርን ሲያገኝ ከዓመታት በኋላ “አይደረግም” የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሙን ለሕዝብ በማድረስ ተወዳጅነቱን ከፍ አደረገ። ይህ አልበሙም አይደረግም፣ የአፋሯ ቆንጆ፣ ሰው የለኝም ፣ ማህሌት፣ ሞኙ ልቤ እና ሌሎች ተወዳጅ ዜማዎችን ያካተተ ነው።
ድምፀ መረዋው አርቲስት ማዲንጎ፥ በመልዕክትም ሆነ በይዘት ጠንካራ መልዕክት ያላቸውን በሀገር፣ በፍቅር፣ በትዝታ እንዲሁም በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ቅኝቶች አቀንቅኗል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወርም ለአድናቂዎቹ ሥራዎቹን በማቅረብ በውጭ የሚኖሩ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል። በሂደትም “አይደረግም” የተሰኘውን ሁለተኛውን አልበሙን ካወጣ ከስምንት ዓመት በኋላ “ስወድላት” የተሰኘውን ሦስተኛ አልበሙን ለአድማጭ እንካችሁ አለ።
በዚህ የሙዚቃ አልበሙ ውስጥ ላላተርፍ፣ ስወድላት፣ አቅሜን፣ አይሆንልኝም፣ እባክሽ ታረቂኝ፣ ከተለያየን ፣ ውሰጃት፣ ዳኛ፣ ጎዳናው፣ ማተቧ፣ ማርማር የተሰኙና ሌሎች ሙዚቃዎች ተካተዋል። በስወድላት አልበምም በተለያዩ የሙዚቃ ውድድሮች እጩ እንዲሁም “ምርጥ የፍቅር አልበም“ ተብሎ መሸለም ችሏል።
“ ተንገበገበልሽ አረረልሽ ሆዴ፣
አትራቂኝ በእኔ ሞት አይብዛ መንደዴ፣
ያስታርቀን መውደዴ ፣
ልመናዬን ስሚኝ ይቅርታሽ ይድረሰኝ፣
ጥፋቴን ለመርሳት እኔ አቅም አነሰኝ፤…. “
የሚለውና በሦስተኛው አልበሙ ውስጥ የተካተተው የፍቅር ሙዚቃው ሕዝብ ልብ ውስጥ ከቀሩ ተወዳጅ ሥራዎቹ ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
“መቼም ከሀገሩ ከቀዬው ርቆ
ሰው ከሀገሩ ቢሄድ ርቆ ቢሄድ ርቆ
ልቡ ቀልብ ሃሳቡ መች ይረጋል (2x)
ልቡ ከሱ መች ሊረጋ መች ሊረጋ ፣
የሰው ሀገር የሰው ነው እንደራስ አይሆንም ፣
ቢከፋውም ቢቸገርም ቢያዝንም ብቻውን ነው ፤”
የተሰኘው ስለሚወዳት ሀገሩ ያዜመው ዜማ ደግሞ በተለይም ከሀገር ርቀው በሚኖሩ የሀገሩ ልጆች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ ነው።እንዲሁም ከአልበሞቹ በተጨማሪ “በላይ”፣ ከብርሃኑ ተዘራ ጋር የተጫወተው “ሰላም ያገር ሰው”፣ ለ“ዓባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም የሠራው ማጀቢያ ሙዚቃ ከሠራቸው ሥራዎቹ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ።
“በማንኛውም ሙያ ውስጥ ያላችሁ ወጣቶች፥ በጥረት እንጂ ከመሬት ተነስቶ የሚመጣ ነገር የለም፤ በድንገት የሚመጣ ነገርም ጠቃሚ አይደለም” በማለት ያስተላለፈው መልዕክትም የሚታወስ ነው። አርቲስት ማዲንጎ አራተኛ አልበሙን ለአድማጮች ለማድረስ በመሥራት ላይ እንደነበርም ነው የተሰማው። አይቀሬው ሞት ድንገት ፈጥኖ ቀደመው እንጂ።
በተለይም ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት እያመመው ግንባር ድረስ በመሔድና በማሰልጠኛ የሚገኙ ምልምሎችን በማነቃቃት የራሱን ታሪክ የሠራ ብርቅዬ አርቲስት ነበር። ግንባር ድረስ በመዝመትም ማዲንጎ አፈወርቅ በወርቃማ ድምጹ አገር ወዳድ ወጣቶችን ሳይሰስት አዝናንቷል።
ለዚህም በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅ እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶለታል። አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በወጣትነቱ እና ብዙ መሥራት በሚችልበት ዕድሜው ባደረበት ሕመም ምክንያት በትናንትናው ዕለት በሥጋ ተለይቶናል። ሆኖም በምርጥ አይረሴ የጥበብ ሥራዎቹና በፍሬ ልጁ ዘወትር ስናስታውሰው እንኖራለን፥።
አርቲስቱ የአንድ ሴት ልጅ አባትም እንደነበር ኤፍቢሲ ዘግቧል።የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በድምፃዊው ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ኃዘን በድጋሚ እየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2015 ዓ.ም