“ዓለም ዘጠኝ ነው፤ አስር አይሞላ ምን አባቱ!” አድርገው ወይም ላድርገው ብለው በዚህ ዓረፍተ ነገር ብዙዎች ድፍረት ይላበሳሉ። ይሄን ባደርግ ምን ይመጣል? የሚል ሀሳብ በዚህ ዓረፍተ ነገር ያንፀባርቃሉ። የዓለም ዘጠኝ ናት ጨዋታ፤ ሰዎች አንድን ነገር መድፈር አለብኝ፤ ይሄን ባደርገው ምን ይመጣል! ካለው አይብስ! በሚል አንድን ተግባር ለማድረግ ሲያስቡ ይጠቀሙታል። ዓለም ዘጠኝ መሆኑ በብዙዎች ይነሳል።
በእርግጥ አንድ ሁለት ተብሎ ተቆጥሮ ሲያበቃ ዘጠኝ ሞልቶ ከአስር የጎደለው የዓለም ክፍል አይደለም እዚህ ጋር ሚነሳ። ዓለም እዚህ ጋር ኑሮ፣ህይወት በአጠቃላይ ዓለማዊ ሁነት ነው። ዓለም ሁሌም ጎደሎ መሆኑን ለመግለፅ ነው፤ ዓለም ዘጠኝ ነው። አስር አይሞላም፤ የሚሉት ብዙዎቹ። በልጅነቴ ስለ ዓለም ሳይገባኝ ሰዎች አባባሉን ሲሉት ስሰማ ልክ እንደ አፍሪካ ያሉ ሌሎች አህጉራት ተቆጥረው ቁጥራቸው ዘጠኝ ስለሆነ ይመስለኝ ነበር። ዓለም ሰፊ ትርጉም ያለው መሆኑ ቆይቶ ገባኝ።
አለም ግን ጎደሎ መሆን ቢሰለቸው ምን አለ? ጉድለቱ ቀርቶ ሞልቶ ሁኔታዎች ቢለወጡ ማለቴ ነው። በእርግጥም ዓለም ጉድለቷ እውነት ነው። ሙሉ የሆነ ፍስሀ፣ ጉድለት የሌለው ደስታ እክል የሌለው ነፃነት ሙሉ የሆነ ሙሉነት ፈፅሞ የለም። አንዱ ሲሞላ ሌላው ይጎላል። በእርግጥ የዓለም ጉድለትን ተረድቶ ለመሙላት ያለ ልክ መታገል፤ ከአቅም በላይ መወጠርም ተገቢነት የለውም።
ግና ደግሞ የዓለም ዘጠኝነትን አምኖ ተቀብሎ ጎዶሎውን ለማበጀት አለመጣርም ትክክል አይደለም፤ ስንፍና ነው። እንዲሁ በደንብ ሳያስቡበትና ሳያቅዱ ‹‹ምን አባቱ! አስር አይሞላም›› ብሎ በፉከራ ዘጠኙን ለማጉደል መጣር ልክ አይደለም። ምን አባቱ አስር አይሞላ! ብለን የምናደርገው ሁሉ ይበልጥ እንዳያጎለን ያሰጋል።
ዓውዳመት በመጣ ቁጥር ብዙ ሰዎች ወጪው ያሳስበናል። ቤታችን ደምቆ ምግብና መጠጡ ሞልቶ ማየት እፈልጋለን። ታዲያ ለዚህ ሙላት ኪስ መጉደሉ አይቀርም። የሚጎድለው ኪስ ከቶም እንዳያገግምና እንዳይሞላ ተሟጦ ከሆነ ይከብዳል።
በተለይ እንዲህ እንደኛ አገር በዓላት ተደራርበው ሲመጡ ኪሳችንን ማጉደላቸው አይቀርም። አዲስ አመት ነውና የተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ተነባብረው እኛን ለማራቆት በቀረቡን ጊዜ የአስር አይሞላም ምን አባቱ ጨዋታ አለ የምንለውንም ዘጠኙን ዓለም ሊያጎልብን ይችላል።
ማንም በዓውዳመት መደሰት ይፈልጋል። በዓሉን ከዘመድ አዝማድ ጋር ተሰባስቦ በጥሩ ሁኔታ እየበሉና እየጠጡ ማሳለፍ። ከጎረቤት ጋር ተጠራርቶ አምሮና አጊጦ ማሳለፍ፤ ነገር ግን አውዳመት አውዳመት ሆኖልን በማግስቱ ሂሳብ እንድናሰላ የሚያደርገን፤ እዳ ውስጥ የሚከተን መሆን የለበትም።
ሁሉ ነገር በአቅም ሲሆን መልካም ነው። እንደቤታችን ብናድር አይጨንቀንም። እንደ ኪሳችን ብንደግስ አይጠበንም። በእርግጥ በወጋችን በአቅም መኖርን የሚመክሩ በልክ ማደሩን የሚያበረታቱ ብዙ ብሂሎች አሉን። “አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፤ ታላቅ ችሎታ ነው” ተብሎም ተነግሮናል።
“ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” አይደል የሚባል። አዎ እንደ ቤታችን እንደር፣ እንደ አቅማችን በዓሉን በደስታ እናሳለፍ። ያለንን ለእኛ በሚሆን መልክ አመቻችተን ከአቅማችን ሳንጎድል፤ ከዚያም በላይ ሳንጠራራ ቤታችንን ማድመቅ ይገባል። አንደ ጎረቤታችን ሳይሆን እንደቤታችን ማደር ይገባል።
ጎረቤታችን ፍሪዳ ነው የተጣለው፤ ብለን እኛ ጋር ያለው ቅርጫ ወይም ዶሮ አናርክስ። ወዳጃችን ጋር ኬክ ነው የተቆረሰው ብለን እኛ ቤት የጋገርናት ቂጣ አናጣጥል። ሁለቱም በየራሳቸው ደስታን መፍጠር ይችላሉ። ቤታችን ቢጎልም ፍቅርን መሙላት እንችላለን። በእርሱ ነው ሌላውን መፎካከር። ያልጎደለ ቤተሰባዊ ፍቅር በመላበስ የጎደለን መሙላት ይቻላል።
እዚያኛው ቤት የሌለው ፍቅር እኛ ቤት ላይ ሞልተን ያለችን ትንሽ ነገር ተቃምሰን በፍቅር እንዋል። ወገኖቼ ፍቅር የሞላበት ቤት ላይ ያለ ጉድለት፤ የማይታይና እጅግ የተሰወረ ነው። ከቁስ ይልቅ እሱ ቤታችንን ከሞላ ተጎርሶ ይጠገባል።
አዎ በአቅም ነው ማደር። ዛሬ ላይ አስር አይሞላ ብለን ለወራት የቋጠርነውን ብንፈታ ነገ ብዙ የታሰሩ ጉዳዮች ሲገጥሙን መፍቻ እናጣለን። ዓውዳመቱን ስናስብ የፍስሀ ይሆንልን፤ እኛን የሚያስደስተን ባቅማችን፤ እንደ ቤታችን እናሳልፈው። አብዝተንም ሳንቋጥር ከአቅማችን በላይም የቋጠርናትን ጥሪት ሳንጨርስ አልፎ የሚሄደውን ቀን በአቅማችን ደምቀን በድምቀት እንለፈው።
ስለ ቁጠባ ሲነሳ ሁሌም የሚታወሱኝ የቀድሞ ስራ ባልደረባዬ ናቸው። ሰውየው አጅግ ቆጣቢ ናቸው። ያለምክንያት አንዲት ሳንቲም የማያበክኑ። በእርግጥ ቆጣቢነታቸው ባልከፋ ነበር፤ ችግሩ ትንሽ ያበዙታል እንጂ። ለሚበሉትና ለሚጠጡትም በስስት ነው ወጪ የሚያደርጉት። አንዴ በሻይ ሰዓት በመስሪያ ቤታችን መዝናኛ ክበብ ተሰብሰበን በተቀመጥንበት መጥተው ተቀላቅለውን አስተናጋጁን ጠርተው ያሉት ሁሌም እያሰብኩ ፈገግ እላለሁ።
“ና ማን ነህ አስተናጋጅ! ቁርስ በልቻለሁ ግን ርቦኛል። ዓለም አስር ሞልቶ አያውቅም ልብላ ባክህ አንድ ሻይና አንድ ዳቦ አምጣያልኝ” ብለው ሲያዙት ሰማን። አንድ ሻይ በዳቦ ለመብላት የዓለምን ጎደሎነት በማንሳት ሲፎክሩ ነው ፈገግ ያልን። ቀልዱ ብዙ ጊዜ ይባል ስለነበር አብረናቸው የነበርነው ሊያስቁን ፈልገው መስሎን ቀና ብለን አየናቸው። ሰውየው ግን ቆምጨጭ ብለው ነው የሚያወሩት፤ የምራቸውን ነው። ዳቦ በሻይ የመብላት ውሳኔያቸው አጀገኗቸው ተጀንነዋል።
ዞር ብለውም አላዩን፤ እኛን ለማሳቅ የሚሆን ጊዜም ቀልድም የላቸውም። በተለይ ስለወጪ እያወሩ ሊቀልዱ? ኧረ አይታሰብም! ሳያቸው በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተጠምደዋል።
ባልደረባችን ወጪን በተመለከተ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያራምዱትን አቋም ስለማውቅ ብዙውን ጊዜ በትዝብት መልክ ነው የማያቸው። በብዙ ጉዳይ ትዝብታችንን እሳቸው ላይ ስለምናበዛ ከመካከላችን ስስታም የሆነ ሲገጥመንና ቁን ቁን ሲልብን “አሁንስ ጋሽ…. መሰልከኝ” እንባባል ነበር።
ወጪ ላይ አብዝቶ ያለአግባብ መዝረክረክ መልካም ልምድ እንዳልሆነ ሁሉ፤ የበዛ ቁጥብነትም መልካም አይደለም። ከልክ በላይ በሆነ ስስት መሰረታዊ የሆነን ፍላጎት ማቀብም ተገቢ አይመስለኝም። ሰው ለሚበላውና ለሚጠጣው ሰስቶ ለምኑ ሊቆጥብ ነው? ባይሆን ለመብላትና ለመጠጣቱ የሚበቃ በቂ ጥሪት መቋጠሩ ላይ ይበርታ እንጂ በሆድ መቋጠር በጎም አይደል፤ የጤና ጉዳትም ያመጣል።
አዎ ሁሉ ነገር በልክና በትክክል እንዲሁም በተገቢ ቦታ ሲሆን ያምራል። ልክ ማወቅ ደግሞ ከእውቀቶች ሁሉ ቀዳሚው ነው።
የመስከረም ወር በዓላት ይበዙበታልና መልካም በዓል!
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015