መስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል:: ንግሥቲቷ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ:: ይህ ደግሞ የሴቶች ተልእኮ ከአከባበሩ የሚጀምር እንደሆነ የሚያረጋግጥልን ነው:: ምክንያቱም በሴቶች መሪነት መስቀል ታሪክ ሆኗል::
በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘትን ይዞ በየአካባቢው ማኅበረሰብ ባህልና ወግም ሆኖ እንዲከበር በር ከፍቷል:: ከዚያም ሻገር ብሎ ዓለም እንዲያውቀውና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ሆኖ ሊመዘገብ ችሏል:: ይህ ደግሞ ለአገር ገቢ እስከመሆን የሚያበቃውን ታሪክ በሴቶች እንደተሰጠው ይነግረናል::
በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች ብንነሳ ቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ጉራጌ እንደሆነ ሁላችንም እንስማማበታለን:: በዚህም መሰረት ዛሬ ከአዲስ አበባ 215 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ጉራጌ ምድር ላይ እንከትማለን:: በምን ካላችሁ በሀሳብ ነው:: ስለዚህም በዚህ ሆነን ያንን እንቃኘዋለን:: እንደ ንግስት ኢሌኒ ለበዓሉ መሰረትና ድምቀት የሆኑትን ሴቶች እናነሳለን:: የሴቶችን የመስቀል ዝግጅት፤ ልፋትና ደስታ እንዲሁም አጠቃላይ ሁኔታ በአዲስ አበባ ቢሆኑም ባህሉን እየኖሩ፤ ሌሎችን እያደመቁ ያሉትንም በማነጋገር ነው ሁኔታውን የምናወሳላችሁ::
ያው እንደምታውቁት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና ነች:: ስለዚህም የማይኖርባት ማህበረሰብ የለም:: በባህሉ የማይደምቅባት ሰውም እንዲሁ:: ስለሆነም መስቀልና ሴቶችን ለማንሳት መገናኛ አካባቢ ባለው በአደብና ሆቴል ተገኝተናል:: ስንገባ ያገኘናት መጀመሪያ ወጣት ሲሳይ ሞንሹን ነው:: መስቀል የጉራጌ ብሔረሰብ ልዩና አውራ በዓሉ እንደሆነ ታነሳለች:: ጉራጌ ቡልቡላ አካባቢ የተወለደችው ወጣቷ ለሥራ ወደ አዲስ አበባ ከመጣች ብዙ ጊዜ ቢሆናትም ባህላዊ ምግቦችን የዘወትር ሥራዋ አድርጋ ቀጥላለች:: ለዚህ ደግሞ መስቀልን ለማክበር ወደ ሀገር ቤት በየጊዜው መሄዷ ጠቅሟታል:: ባህሉን ከነስርዓቱ ሁልጊዜ የመተግበር ልምድም አላት::
እንዳጫወተችን በዓሉን ለማክበር ስትሄድ ልብስ ፤ ጨው፤ ስኳር ፤ ለአባቶች ጠርሙስ አረቄን ጨምሮ እንደ ማንኛውም ከሀገር ቤት ለሥራ እንደወጣ የጉራጌ ልጅ ለወላጆቿ ይዛ ትሄዳለች:: ሴትም ሆነች ወንድ ይሄን ማድረጋቸው የማይቀር እንደሆነም ታስረዳለች። ኖራትም አልኖራትም ለበዓሉ የግድ ሀገር ቤት መሄድ አለባት። ካልሄደች እርግማን ስላለው በጣም መጥፎ ነው። ወላጆቿ አፍ አውጥተው ባይረግሟት የሌሎች ልጆች ሲመጡ ሲያዩ እሷ በመቅረቷ ያዝኑባታል። ስለሆነም ሁልጊዜ መስቀልን ከቤተሰቦቿ ጋር ታሳልፋለች::
ወላጆቿ ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤትም ይጠብቃታል። ሴት ስለሆነች በክትፎ ከተፋውና በበዓል ሥራዎች ሀገር ቤት ካሉት ሴቶች ጋር መሥራትና ማገዝ ይኖርባታልና ያ እንዲያልፋት አትፈልግም:: በእርግጥ በባህሉ ዘንድ እንግዳ ናት ብሎ ዝም የሚላት የለም። ‹‹ የቄስና የሴት እንግዳ የለውም›› አይደል የሚባለው:: እዚህም እንዲያው ነው:: ይህ ባይሆን እንኳን እሷ ምርቃቱን ስለምትፈልገው በረከቱን በማሰብ ከሥራ ወደኋላ አትልም::
ሲሳይ እንደምትለው፤ በተለይ ገጠር ያሉት ሴቶች ለወዲያኛው መስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምሩት የዚህኛው መስቀል እንደወጣ ነው። ፈጥነው በየግላቸው ከሚያጠራቅሙት ቅቤ በተጨማሪ በየአካባቢያቸው የቅቤ ዕቁብ ይገባሉ። ከየአካባቢው የሚመጡትንና በሥራ የሚያግዟቸውን ሴቶችም ሆነ ተወላጆች በሙሉ የሚጠብቋቸው ተዘጋጅተው ነው። በዓሉ ሳምንት ሲቀረው ቅቤው ይነጠራል። ዘንድሮ የተፋቀ ቆጮ ለዘንድሮ መስቀል ስለማይሆንም ቆጮ መፋቅ የሚጀምሩትም የዚህኛው መስቀል እንደወጣ ነው። ይቆረጥና ዓመት ሙሉ ታፍኖ ይቀመጣል። መስቀል ሊደርስ ሁለት ወር ሲቀረው በመጭመቅ ወደ ዝግጅት ይገባሉ።
ታፍኖ ረጅም ጊዜ የሚቆይበት ምክንያቱ ጣዕም እንዲኖረው ለማድረግ ነው።ለምሳሌ፡- ለዛሬ መስቀል ቆጮ መሥርያ የተጠቀምነው አምና ያዘጋጁትን ነው:: የቡላም ዝግጅት ተመሳሳይ ነው። በነገራችን ላይ ጉራጌ ላይ ወድቆ የተሰበረ ሰው ሴቶች በቅቤ ያበደ የቡላ ገንፎ እየሰሩ ስለሚመግቡት ሁለት ወር ሳይቆይ ከስብራቱ ይጠገናል:: በአጠቃላይ በበዓሉ ምክንያት በሴቶች ላይ የሚደርሰው የሥራ ጫና ከፍተኛ ነው። ነገር ግን እሷን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች ደስታ እንጂ ቅሬታ አይሰማቸውም። ምክንያቱም ያዘጋጁትን ክትፎም ሆነ ምግብ የሚመገበው ሁሉ ይመርቃቸዋል::
የሶዶ ጉራጌዋ ወይዘሮ የኔነሽ ታዬ እንዳወጉን ደግሞ፤ በጉራጌ የሴቶች ተብሎም መስቀል በልዩ ሁኔታ ይከበራል። የዚህ በዓል ወጪ በሙሉ በሴቶች ነው የሚሸፈነው። ሆኖም ይሄ በዋናው መስቀል በዓል ሴቶች ከጉልበት ውጪ በገንዘብ የሚያደርጉት አስተዋጾ የለም ማለት አይደለም። በዓላቸው የሚከበረው መስከረም 14 ሲሆን፤ በዕለቱ ሴቶች በልዩ ሁኔታ በራሳቸው የሚዘጋጀውን የጎመን ክትፎ የሚያቀርቡበት ነው:: ለማባያ የሚውል ቅቤ በዕቁብም ሆነ በሌላ መንገድ ማጠራቀም የሚጀምሩትም ነው:: ምክንያቱም በሴቶች እንደ ክትፎ ሁሉ ድቅቅ ተደርጎ የተከተፈው ጎመን ከሥጋ ክትፎ ባልተናነሰ ብዙ ቅቤ ይወስዳል።
የሚከተፈው ጎመን ብዙ በመሆኑ ሴቶች እንደ ሥጋው ክትፎ ሁሉ በየአካባቢው ተሰባስበውና ተጠራርተው በሕብረት ያደርጉታል:: ስለዚህም ይህ ቀን ለእነርሱ መሰባሰቢያቸውም ነው:: የመስቀል በዓል ሥራ ለሴቶች እጅግ አድካሚ ነው። ቆጮ ቆረጣና ጨመቃው ቀርቶ ወደ ምግብ ዝግጅቱ ከተገባ በኋላ ያለባቸው የሥራ ጫና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም:: ለምሳሌ ከአምቾ የሚወጣውን ተንጣሎ የቀረውን ቡላም መለየት አንዱ ነው። ሆኖም ይሄ ሁሉ ድካም ልዩ በሆነው የበዓሉ ድባብ ተኖ ይጠፋል:: በሳቅና ጨዋታው ፤ጭፈራው እንዲሁም በምግብና መጠጡ ሲሳተፉ ይረሱታል ይላሉ።
ለሥራ አዲስ አበባ መጥተው ለመስቀል በየዓመቱ ሀገራቸው በመሄድ የሚያከብሩት ወንድ የጉራጌ ተወላጆችም የመስቀል በዓል ሴቶችን የበለጠ እንደሚያደክም አይክዱም። ወጣት ሙሉጌታ ገብሬ አንዱ ሲሆን፤ ለበዓሉ ለመሄድ ቸኩሎ ቢሆንም ስለሴቶች የሥራ ጫና እንዳጫወተን፤ የተወለደው አሁን ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ከሚገኝበት አካባቢ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ኢዣ አገና በተሰኘ ከተማ ነው። በየዓመቱ የሚሄደው የቤረሰቡ ተወላጅ ያልሆኑትን ሁለት ሦስት እንግዶች ይዞ ነው። ለሦስት ቀን ብለው ሄደው መብላት መጠጣቱና ከቤተሰባቸው ጋር መገናኘቱ ስለሚያስደስታቸው 15 ቀን ይቆያሉ:: እናም በዚህ ቆይታቸው ሁሉም የሚመገቡትን ከቀን እስከ ሌት የሚያዘጋጁት ሴቶች እንደሆኑ ይመሰክራል::
አብዛኛው የጉራጌ ተወላጅ መንደሮች ይራራቃሉ። ሆኖም መቀራረብና አብሮ በዓሉን ማሳለፍ ግድ ነው:: በዚህም በባህሉ ሊስትሮም ቢሆን እየጠረገ ለእናት አባቱ ለመስቀል መዋያ ገንዘብ አጠራቅሞ የመጣው ተወላጅ ሁሉ እነዚህን ቤተሰቦችና ጎረቤቶቹን በሙሉ እየዞረ መጠየቅ ግዴታው ነው። በዞረበት ሁሉ ይበላል ይጠጣል፤ የቻለውን ያደርጋልም። የዚህ ጊዜ ደግሞ የሴቶች ልፋት እጅጉን ይጨምራል:: ምክንያቱም እንግዳ የሚበዛበት ወቅት በመሆኑ የተሰራው ባይበቃ እንኳን ዳግም መስራት ግዴታ ይሆንባቸዋል:: ሥጋ መፍጫ የገባባቸው ዘመናዊ አካባቢና ነዋሪዎች ቢኖሩም ሴቶች ክትፎውን በእጃቸው ነው የሚከትፉት። ስለዚህም የእነርሱ ውሎ የሚሆነው ክትፎዎቹ ሲሰሩ፤ ቅጠሉ ላይ ተጨልፎ ከተደረገ በኋላ ቅቤ ሲያፈሱ፤ ቤተዘመዱን ሲያስተናግዱ ነው::
ሌማት ሪስቱራንትና ባር ሥጋ ቤት ሥጋ ሻጩ ምህረት ሳህሌ እንደሚለው ደግሞ፤ መስቀል ለጉራጌ መገናኛው፤ ሀሳቡን መገላለጫው፤ የሕይወቱን ምሶሶ ማቆሚያው ነው:: አከባበሩ የሚጀምረው ከመስከረም 12 ሲሆን፤ እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ይቆያል:: በዚህ ውስጥ ታዲያ ሴቶች ከበዓሉ ዝግጅት ጀምሮ በልዩ ሁኔታ የሚያከብሯቸው ዕለቶች ይለያሉ:: ምክንያቱም ለበዓሉ ዝግጅት ሲደረግ ሥራ በጾታና በዕድሜ ይከፋፈላል:: እናም ሴቶች ለሚመጣው መስቀል በዓል የሚሆን ቅቤ ማጠራቀም አንዱ ተግባራቸው ተደርጎ ይሰጣቸዋል:: የወራት ዝግጅታቸው ቤት ማሳመርንም ያካትታል:: በዓሉ ሦስት ወራት ሲቀሩት መሰናዶውም ይጧጧፋል:: በተለይም ወጣት ሴቶች ቤት ቀለም መቀባት ጭምር ይሰራሉ:: ስለዚህም የቡሔ በዓል ከተከበረ በኋላ የመሰናዶውን ፍጥነት በየጊዜው እየጨመሩ ነው የሚሄዱት::
የጉራጌ ሴቶች የመስቀል በዓል መከበር በሚጀምርበት መስከረም 12 ቀን ለምግብ ማቅረቢያ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከግርግዳ ያወርዳሉ:: ዕለቱ ‹‹ሌማት የሚወርድቦ ቀነ›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በዕለቱ የመመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም ቤት ይፀዳል:: በየቤቱ አዳዲስ ጅባዎች ይነጠፋሉ:: ቀጣዩ ቀን ‹‹ወሬት ያሸና ወይም ወልቀነ›› የሚባል ሲሆን፤ ሴቶች የጎመን ክትፎ የሚያዘጋጁበት እለት ነው:: እናም ከቆት የሚበላበት ዕለት በመባል ይታወቃል::
ሌላው በጉራጌ ባህል መስከረም 14 የሚከበረው ደንጌሳት የሚባለው ቀን ሲሆን፤ የጎመን ክትፎ በሸክላ ጣባ ለመላው ቤተሰብ የሚቀርብበት ዕለት ነው:: በዕለቱ የሚወጣውን ወጪ በሙሉ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው:: ሴቶች ዓመቱን በሙሉ ለመስቀል ባጠራቀሙት ገንዘብ ሙሉ ዝግጅቱን ሸፍነው ቤተሰባቸውን ያስተናግዳሉ:: በደንጌሳት ማታ በየቤቱ ደመራ ይለኮሳል:: ሥርዓቱ የባዮፕ ኧሳት ቀን ይባላል:: ደመራው ሲቃጠል ሴቶች እልልታ ያሰማሉ:: ለበዓሉ በሰላም በመድረሳቸውም ፈጣሪን ያመሰግናሉ::
መስከረም 18 ሲደርስ ደግሞ ሴቶች የተለያዩ የስፌት ቁሳቁሶች ለማዘጋጀት የሚውል ስንደዶ መልቀም ይጀምራሉ:: ይህ ቀን የፊቃቆማይ ይባላል:: የአካባቢውን ባህላዊ ዜማ እያሰሙ ስንደዶ የሚለቅሙበት ጊዜ ነው:: ከመስከረም 17 እስከ መስከረም23 ያለው ደግሞ የጀወጀ ወይም የጀወቸ አማች መጠየቂያ ጊዜን ያከብራሉ:: በዚህ አማች መጠየቂያ ወቅትም ሴቶች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ፤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ይገዛሉ:: ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት ይሸምታሉ:: ወቅቱ ልጆች በወላጆቻቸው እንዲሁም ባለትዳሮች በአማቾቻቸው የሚመረቁበትም ነው::
የመስቀል በዓል አከባበርን ከሚያጎሉ ሥርዓቶች መካከል የአዳብና ባህላዊ ጭፈራ ሥነ ሥርዓት ተጠቃሽ ነው:: አዳብና ከመስከረም 16 ቀን እስከ ጥቅምት 5 በዓል ባሉት ቀናት ይከናወናል:: ከተማ ይቀበልህ፤ ቀና ይሁንልህ፤መንገድ ይክፈትልህ። ለሰው መልካም ሁን። ይስጥህና ለሰፈሩ ሕዝብ ለሁሉም መግብ ተብሎም በእናትና አባቶች ይመረቅና ወደየመጣበት ይበተናል። ሀገር ቤት የቀሩ ሴቶች በፊናቸው ወዲያው ለቀጣዩ መስቀል ቆጮ ዝግጅት እንሰት መረጣ ይሄዳሉ። እኛም ምርቃታቸው ደርሶን አገራችንን ሰላም ያድርግልን በማለት ለዛሬ ተሰናበትን:: መልካም በዓል
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም