ከስፖርት ማህበራት ዓመታዊ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ ለባለሙያዎች የአገር ውስጥ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችንም ማመቻቸት ነው:: ይህንን በማድረግ ረገድም መልካም የሚባል ተግባር ከሚያከናውኑት ማህበራት ቀዳሚው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው:: ፌዴሬሽኑ በራሱ አቅም በአሰልጣኝነትና ዳኝነት ላይ የአገር ውስጥ ስልጠናዎችን በተለያየ ደረጃ ከማዘጋጀትም ባለፈ፤ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ባለው መልካም ግንኙነት በየዓመቱ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸውን ያዳብራል::
በተያዘው ዓመትም በአሰልጣኝነት እና ዳኝነት ዓለም አቀፍ ዳኝነት በመስጠት ላይ ይገኛል:: ላለፉት አምስት ቀናት ሲከናወን የቆየው የደረጃ አንድ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ስልጠና ትናንት ተጠናቋል:: በአዲስ አበባ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ማዕከል ሲካሄድ የቆየው ስልጠናው ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ 20 የሚሆኑ ሰልጣኞች የተሳተፉበትም ነበር:: የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ዳኞች በአገር ውስጥ ሁለት ስልጠናዎችን ተከታትለው ለዓለም አቀፍ ስልጠናው ብቁ መሆናቸውን ያረጋገጡ አትሌቶች ናቸው::
ይህ ዓይነቱን ስልጠና በሌሎች አገራት ማግኘት አስቸጋሪ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜ በዞን ደረጃ አገራት በአንድ ማዕከል በኮታ በሚያገኙት ዕድል የሚሰጥ ነው:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ግን ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ባለው መልካም ግንኙነት እንዲሁም በተቋሙ መልካም ፈቃደኝነት ዓለም አቀፍ ስልጠናው በአገር ውስጥ እንደሚሰጥ በፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዮሃንስ እንግዳ ይገልጻሉ:: ስልጠናው በበላይነት የሚመራውና ቁጥጥርም የሚደረግበት በዚሁ ተቋም ይሁን እንጂ ስልጠናውን የሚሰጡት ግን ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች ናቸው:: ይህ ዕድል የመገኘቱ ዋነኛው ምክንያትም ኢትዮጵያ ባላት የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ እንዲሁም በአገር ውስጥ ስልጠናውን ሊሰጡ የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎች በመኖራቸው መሆኑንም አቶ ዮሃንስ ያስረዳሉ::
በዳኝነት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰለጠኑ በርካታ
ባለሙያዎች ባይኖሩም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው እያሰለጠኑ ያሉ ጥቂት ዳኞች አሏት:: በመሆኑም በዚህ ስልጠና የምስክር ወረቀት ያላቸውን አሰልጣኞች እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ትልልቅ ውድድሮችን መምራት የሚችሉ ባለሙያዎችን ቁጥር እና ጥራት ለመጨመርም ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተወካዩ ይጠቁማሉ:: በእርግጥ በአህጉር አቀፍ ደረጃ አፍሪካ እንዳላት የስፖርቱ እንቅስቃሴ በቂ ባለሙያዎች የሏትም፤ ምክንያቱ ደግሞ ስልጠናውን የማግኘት ዕድሉ ጠባብ በመሆኑ ነው:: ይሁንና ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚገኙት እድሎች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን በማፍራት በአገር ውስጥ ስልጠናዎችን ማሳደግ ይቻላል::
በተለያዩ አጋጣሚዎች አምና ለመስጠት ታቅዶ የነበረው የአሰልጣኝነት ስልጠናም እየተሰጠ ይገኛል:: ከመስከረም 04/2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ያለው ስልጠና 24 አሰልጣኞች የተካፈሉበት ሲሆን እስከ መስከረም 29/2015 ዓ.ም የሚቀጥልም ይሆናል:: ሰልጣኞቹ ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች ሲሰባሰቡ፤ ብቁ የሆኑና መስፈርቱንም የሚያሟሉም ናቸው:: ስልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት ደግሞ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ የአንደኛ ደረጃ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝነት ኢንስትራክተር የሆኑት አቶ አድማሱ ሳጂ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ የስልጠና፣ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር የሆኑትና በዓለም አትሌቲክስ የአንደኛ ደረጃ አሰልጣኝነት ኢንስትራክተር በሆኑት አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ናቸው።
ኢትዮጵያ የአትሌቶች አገር እንደመሆኗ በባለሙያዎች ረገድ እጥረት ባይኖርም ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ አንጻር ስፖርቱን የሚያዘምኑ ስፖርተኞች አስፈላጊ እንደሆኑ ተወካዩ ያመላክታሉ:: የባለሙያዎቹን አቅም መገንባት ለነገ የማይባል ስራ በመሆኑ ከዓለም አቀፉ ተቋም የተገኘውን ዕድል በመጠቀም ስልጠናው እየተሰጠ ይገኛል:: ከዚህ ባሻገር በቁጥር በርካታ የሆኑትን አሰልጣኞች የአገር ውስጥ ስልጠና ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ከፌዴሬሽኑ ባለፈ ክልሎች በራሳቸው አቅም የአንደኛ ደረጃ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ:: የሁለተኛ ደረጃ ስልጠናው ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ክልሎች የሚመድቧቸው ባለሙያዎች ስልጠናውን የሚከታተሉ ይሆናል:: በዚህም ከእቅድ በላይ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደተቻለና ቀሪው ዓለም ካለበት አኳያ አሰልጣኞችን የማዘመን ስራ መሆኑንም አቶ ዮሃንስ ያረጋግጣሉ::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም