በአካባቢው ‹‹እምቧ›› የሚሉት ጥጆችና የወተት ላሞች እንድ ላይ የሚያሰሙት ድምጽና በብዛታቸው የተለየ ስሜት ይፈጥራል:: ድምጹ እንኳንስ ለከተሜው፣ ለአርቢው አርሶ አደርም እንግዳ ሳይሆን አልቀረም::
በአንድ ሥፍራ ብዛት ያላቸው ጥጆች ተሰብስበው የተመለከተ ደራሽ እንግዳ የጥጆች ገበያም የተጀመረ ሊመስለው ይችላል፤ በእለተ ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም በሲዳማ ክልል ሥር በሚገኙ ቦና እና በንሳ ወረዳዎች በተገኘንበት ወቅት ነበር እንዲህ በህብረት ድምጻቸው የተደመምንባቸውን ጥጆችና የወተት ላሞች የተመለክትነው::
በሁለቱ ወረዳዎች ውስጥ በብዛት ያየናቸው ጥጆች በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ (ስንክሮናይዜሽን) ዘዴ የተገኙ ናቸው፤ የወተት ላሞቹ ደግሞ በማሻሻያ ዝርያ ለተጨማሪ የእርባታ ዘዴ በባለሙያዎች ዝግጁ ሲሆኑ ነው::
በዕለቱም በማሻሻያ ዝርያው ቀድመው በመጠቀም ውጤቱን ያሳዩት አርሶ አደሮች ጥጆቻቸውን በመያዝ፣ የቀደሙትን በማየት በእርባታው ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ ሰፊ ቁጥር ያላቸው አርሶአደሮች ላሞቻቸውን ይዘው ተገኝተዋል:: ባለሙያዎችም ላሞቹን ለተጨማሪ የዝርያ ማሻሻያ ዝግጁ ለማድረግ ከንጋቱ 12 ሰአት ጀምሮ ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነበር ::
በዕለቱም በ2014 በጀት ዓመት በዝርያ ማሻሻያ (ስንክሮናይዜሽን) ዘዴ የተወለዱ ጥጆች ቀን የማክበር እና በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ የአዲስ ዝርያ ማሻሻያ የማስጀመሪያ መርሃግብር በይፋ ተከናውኗል:: በመርሃ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሣን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተው አርሶአደሩን የንቅናቄ መርሃግብሩን አድምቀው ነበር የዋሉት::
ከእለቱ መርሃግብር መረዳት እንደቻልነው በክልሉ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስራ መካሄድ ከጀመረ ቆይቷል፤ በየዓመቱ ያለፈውን ውጤት የማሳየትና የቀጣዩን የማስጀመር መርሃግብር ማከናወንም ተለምዷል:: እንዲህ ያለው መርሃግብር በተወሰኑ የክልሉ ወረዳዎች ውስጥ የተጀመረውን የእንስሳት ዝርያ የማሻሻል ዘዴ ሥራና የተገኘውን ውጤት ተሞክሮ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ለማስፋት ንቅናቄ ለማካሄድ ሲባል በየዓመቱ ይካሄዳል:: የንቅናቄ መርሃግብሩ ዋና ዓላማም የወተት ምርታማነትን መጨመር ነው::
በግብርናው ዘርፍ በማይነጣጠሉት የሰብል ልማትና የእንስሳት እርባታ ስራዎች አርሶ አደሩ በተለይ እንስሳቱንና የእንስሳት ውጤቶችን ለገበያ በማቅረብ ይህ ነው የሚባል ገቢ እያገኘበት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል:: እንደ አገርም ኢትዮጵያ በከብት ሀብቷ ተጠቃሽ ብትሆንም፣ እንስሳቱ የወተትና የሥጋ ምርታማነታቸው ዝቅተኛ መሆኑ፣ በተለይም ደግሞ ከአገረሰብ ላሞች የሚገኘው የወተት መጠን እጅግ አነስተኛ እንደሆነና የተጠቃሚውን ፍላጎት ማሟላት እንዳልተቻለ ይታወቃል::
ከወተት አቅርቦትና የዋጋ መናር ጋር ያለው ነባራዊ ሁኔታም ይህንኑ ያሳያል:: ይህን ክፍተት መሙላት ወይንም ማሻሻል የሚቻለው ደግሞ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴን በመጠቀም እንደሆነ ታምኖበታል:: ዘዴው ውጤት እያስገኘ መሆኑንም በቦና እና በንሳ ወረዳዎች ያየነው ተሞክሮ ማሳያ ነው::
በተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎች በወተት ልማት ላይ የተሰማሩና ለሌላውም ሞዴል መሆን የቻሉ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ስለውጤታማነቱ ይመሰክራሉ:: በማቀነባበሪያ ማሽን ወይንም ደግሞ በመኖ መቆራረጫ ማሽን በመጠቀም በቤቱ ደጃፍ ላይ ለጥጆቹ መኖ ሲያዘጋጅ ያገኘነው በቦና ዙሪያ ወረዳ ቦና ዜሮ አንድ ቀበሌ ያገኘነው ወጣት ታገል ሽብሩ፣ከመኖ አዘገጃጀት ጀምሮ ለጥጆቹ የሚያደርግላቸውን እንክብካቤ አሳየን:: ወጣት ታገል ‹‹ላይፍስ›› ከሚባል የካናዳ የምርምር ማዕከል ያገኘውን ቾፐር የሚባል የመኖ ማዘጋጃ ማሽን በመጠቀም መኖ ያዘጋጃል::
የተሻሻለ ዝርያ ባላቸው ሁለት ጥጆች በ2006 ዓ.ም የጀመረው ይህ ስራ ወጣት ታገልን ውጤታማ እያደረገው ይገኛል:: ሥራውን የበለጠ በማስፋት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ‹‹በአንድ ዓመት አንድ ጥጃ››የሚል መርህ ይዞ እየሰራ ነው::
የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳት ከአገረሰብ እንስሳት በተሻለ ስላስገኙት ውጤትም ወጣቱ ሲያስረዳ እንዳለው፤ በተሻሻለ የዝርያ ዘዴ የሚወለዱ ጥጆች እድገታቸው ፈጣን ነው:: ከወተት ላሞቹ የሚገኘው የወተት መጠንም ከፍተኛ ነው::
የተሻሻለ ዝርያ ካላት የወተት ላም በቀን እስከ 25 ሊትር ወተት ይገኛል:: ይህም ከአገረሰብ ላም ከሚገኘው ወተትም በእጅጉ ይበልጣል:: ወጣቱ በአሁኑ ወቅትም ከ20 በላይ የወተትና የሥጋ ከብቶች ያሉት ሲሆን፣ ካሉት የወተት ላሞችም በቀን 150 ሊትር ወተት እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኗል::
የወተት ልማቱ ከእንክብካቤ፣ ከማለብና ለገበያ እስከማቅረብ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል የሚፈጥር በመሆኑም ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ይላል:: የወተት አቅርቦትና ፍጆታንም ከፍ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ስለመሆኑ እንደ ወጣት ታገል በልማቱ ከተሰማሩትና በሥፍራው ካገኘናቸው መገንዘብ ችለናል::
በክልሉ በተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ስላለው ጥረት የሲዳማ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ እንደሚሉት፤ የሲዳማ አርሶ አደር ማህበረሰብ ለእንስሳቱ ልዩ ቦታ ይሰጣል:: ሰላምታ ሲለዋጡ እንኳን ከልጆችና ቤተሰብ ቀጥሎ ስለእንስሳት ደህነነት የሚጠያየቀው:: እንስሳቱን ለገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጭ ያደርጋቸዋል፤ ለምግብ፣ ለመጓጓዣ፣ ለዋስትና የሚጠቀምባቸውም ናቸው::
ለእነዚህ እንስሳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል፤ ከመኖሪያ ቤቱ ውጭ ራቅ አድርጎ እንኳ አያሳድራቸውም:: እንዲህ ለእንስሳት ክብርና ቦታ የሚሰጥ አርሶ አደር ማህበረሰብ በእንስሳቱና በእንስሳት ውጤቶቹ የጎላ የገቢ ጥቅም እያገኘባቸው አይደለም:: የእንስሳቱ ዝርያ ምርታማነት አነስተኛ መሆን ብቻ አይደለም ችግሩ፤ ጤናቸው እንዲጠበቅ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ፣ አያያዛቸውና አስተዳደሩ ባህላዊ መሆን፣ የመኖ እጥረትና የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቃሚነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው በተለያየ መንገድ ተለይቷል::
የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለይም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተዋቀረ ወዲህ ግን ልዩ ትኩረት በመስጠትና ሰፊ ንቅናቄ በማካሄድ ወደ ውጤት የተቀየረ ሥራ መሰራቱን ነው አቶ ተክሌ የተናገሩት::
እርሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ከሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን በላይ የዳልጋ ከብቶች ይገኛሉ:: ከነዚህ ውስጥ 11 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ዝርያቸው የተሻሻለው::ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የዳልጋ ከብቶች ዝርያቸው ያልተሻሻለና በቀን ከአንድ ሊትር በላይ የወተት ምርት የማይሰጡ የወተት ላሞች ናቸው ያሉት:: በዚህ ሁኔታ አርሶ አደርን በገቢ፣ የምርት ተጠቃሚውን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም::
የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያን ለመጠቀምና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተፈጠረ ባለው መነቃቃት ሞዴል አርሶ አደሮችንና በማህበር ተደራጅተው ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ማፍራት ተችሏል:: በቦና ወረዳ አንድ ቀበሌ ውስጥ ብቻ ዝርያቸው የተሻሻለ ቁጥራቸው ከሶስት መቶ በላይ የሆነ ጥጆች ማርባት ተችሏል:: በአንድ ቀበሌ ይሄን ያህል ውጤት ማስመዝገብ ከተቻለ በቦና ወረዳ 20 ቀበሌዎች ውስጥ ብዛት ያላቸው የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ጥጆች መኖራቸውን መገመት አያዳግትም:: ይሄ ክልሉ ለሰጠው ትኩረትና ለተከናወነው ተግባር አንድ ማሳያ ይሆናል:: እንቅስቃሴው ቀጥሎ ተሞክሮውን በማስፋት ውጤማነቱን ማረጋገጥ ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ የወተትና የሥጋ ከብት ልማትን ማሳደግ ይቻላል::
ክልሉ ቦና እና በንሳ ወረዳዎችን ሞዴል አድርጎ ያቀረባቸው ባስመዘገቡት ውጤት ሲሆን፣ አርሶ አደሩ ዝርያቸው የተሻሻለ እንስሳትን ለማርባት ካለው ፍላጎት በተጨማሪ ለእንስሳቱ የሚሆን መኖ በማልማት፣ በአያያዝና በአስተዳደር ቁርጠኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው::ለውጤቱ ደግሞ ከወረዳ አመራሩ ጀምሮ እስከታች ካለው አርሶ አደር ጋር በመሥራት ያሳየው እንቅስቃሴም የሚበረታታ ሆኖ ተገኝቷል:: በአጠቃላይ ለሌላው አርአያ የሚሆን አፈጻጸም አስመዝግበዋል::
አቶ ተክሉ እንዳብራሩት፤ የዝርያ ማሻሻያው እየተካሄደ ያለው ከህንድ አገር በመጣ የተሻሻለ ኮርማ በመጠቀም ሲሆን፣ ኮርማው ሁለት አይነት ዝርያ ያለው ነው:: ሌላው ከኮሪያና ከህንድ ሴት ጥጃ በማስመጣት የተሻሻለ ዝርያ እርባታውን ለማካሄድ የሚያስችል ዝርያ ነው::
ዝርያዎቹን አርሶ አደሩ በደንብ አውቋቸዋል፤ በቀላሉ ጥቅም ላይ ያውላቸዋል:: ዝርያዎቹን የማሻሻል ሥራ የሚከናወነው በአካባቢው በተገነቡ የዝርያ ማሻሻያ ማእከላት ውስጥ ሲሆን፣ የማዳቀል ሥራውም ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች በስፍራው ይከናወናል:: ክልሉ ለዝርያ ማሻሻያ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ያሟላል:: አገልግሎቱ ነፃ በመሆኑ ከአርሶ አደሩ የሚጠበቀው የእንስሳቱን ዝርያ ለማሻሻል ዝግጁ መሆን ብቻ ነው::
ይህ አገልግሎት በገንዘብ ቢተመን የአንድ ከብት ዝርያን ለማሻሻል ከ30ሺ ብር ያላነሰ ውጭ ይጠይቃል:: አርሶ አደሩ ዝርያ ማሻሻል ያለውን ጠቀሜታና የሚያስፈልገውን ወጭም እየተገነዘበ በመምጣቱ ወደ ተጠቃሚነቱ እያደላ እንደሆነ በአንድ ቀን በአንድ ቀበሌ ውስጥ በተካሄደው የንቅናቄ መርሃግብር ላይ ከብቱን ይዞ ከተገኘው አርሶአደር ብዛት መረዳት ይቻላል:: ዝርያ የማሻሻሉ ስራ ቁጭት እየተፈጠረም ነው ማለት ይቻላል::
ክልሉ የዳልጋ ከብቶቹን ዝርያ በማሻሻል ምርታማነትን ለመጨመር እያከናወነ ባለው እንቅስቃሴ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፏል:: በአስር ዓመት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት እንስሳት ዝርያቸው የተሻሻለ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ ነው፤ በአጭር ጊዜ እቅዱም በተለይ በተያዘው በጀት ዓመት የአንድ መቶ አንድ ሺ እንስሳትን ዝርያ ለማሻሻልና 71ሺ ጥጆችን ለማግኘት እየተሰራ ይገኛል::
በክልሉ 30 የገጠር ወረዳዎችና 7 የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በሚገኙት 37 መዋቅሮች የተጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ሥራን ለማከናወን የግብአት፣የሰው ኃይል፣ የእቅድ፣ የመግባባት፣ አርሶ አደሩን የማሰልጠንና ሌሎችንም ተግባራት የማከናወኑ ስራ በቅድመ ዝግጅቱ ተሟልቷል::
በመርሃግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሣ እንደገለጹት፤ ክልሉ ሲዳማ በክልልነት ከተዋቀረ ወዲህ የህዝቡን የመልማት ጥያቄ በተለያየ መንገድ ለመመለስ ጥረት ከሚያደርጋቸው ተግባራቶቹ አንዱ የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ነው:: የመንገድ መሠረተ ልማት ሲሟላ በመንገዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የሚመላለሱበት የሰብልም ሆነ የእንስሳት ውጤቶች ለተጠቃሚዎች ማጓጓዣም ነው:: ሌሎችም የመሠረተ ልማት ሥራዎችም የህዝብን ኑሮ የሚቀይሩ ሆነው መሆን ይኖርባቸዋል::
ይህን ማሳካት የሚቻለው የእያንዳንዱን የክልሉ ነዋሪ ገቢን የሚያሳድግ ሥራ መሥራት ሲችል ነው:: የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል ዘመናዊ እርባታን የመፍጠር ጉዳይ የቤተሰብ ብልጽግናን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል:: በመሆኑም ውጤት ላይ መሠረት ያለው ሥራ ይጠበቃል::
ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አሁን ያለው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ መሆኑን ከእለቱ መርሃግብር መገንዘባቸውንም ተናግረዋል:: የግብርና ሥራን እንደከዚህ ቀደሙ በሰፊ መሬት ላይ ማከናወን ሳይሆን፣ በአነስተኛ መሬት ላይ ምርታማነትም ማሳደግ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል:: እንዲህ ያለው አካሄድ የመሬት ጥበት ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ለማስቀረት አይነተኛ ዘዴ እንደሆነም አስገንዝበዋል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም