“ህሩይ” በግዕዝ ምርጥ ወይም የተመረጠ ማለት ነው። መጀመሪያ” ህሩይ” የሚል መጠሪያ የእርሳቸው ስያሜ አልነበረም። አባታቸው ወልደ ስላሴ ለሚወዱት ልጃቸው ያወጡላቸው ቀዳሚው ስም ገብረመስቀል ነው። በአባታቸው የወጣላቸው ገብረመስቀል የተሰኘ ስማቸውን የለወጡት አንድ መምህር ናቸው። የብላታ ህሩይ ብሩህ አዕምሮና በስነ ምግባር የላቀ መሆኑን የተመለከቱት መምህር ገብረመስቀል የሚለው ስም እስከመጨረሻው ድረስ የታወቁበትና ገናና የሆኑበት ስማቸው “ህሩይ” ብለው ለወጡት።
እኚህ አገር ወዳድ ድንቅ ኢትዮጵያዊ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ ደራሲ፣ ዲፕሎማትና የሃይማኖት አባት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተደጋግመው የሚነሱና ባበረከቱት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ተጠቃሽ ናቸው። እኚህ የአገር ባለውለታ ብላታ ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በዚህ ሳምንት መስከረም 9 ቀን 1931 ነበር። በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ አምዳችንም እኚህን የአገር ባለውለታ ልናነሳ ወደድን።
በሰሜን ሸዋ በመርሐ ቤቴ አውራጃ በታች ቤት ወረዳ ረመሸት ቀበሌ ደን አቦ ገዳም ከአባታቸው ወልደሥላሴ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወለተማሪያም በ1871 ዓ.ም የተወለዱት ብላታ ጌታ ህሩይ በሕይወት ዘመናቸው በተለያየ መስክ አገራቸውን በፅናት አገልግለዋል፤ ለህዝባቸው ነፃነትና ስልጣኔ ታግለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሆን አገራቸውን ያገለገሉት ህሩይ ወልደሥላሴ መሪ ብቻ ሳይሆኑ እውቅ ደራሲ፣ የታሪክ ተመራማሪና ጎበዝ ዲፕሎማት ነበሩ። ወደ ቀለም ትምህርት ቤት የገቡት በአባታቸው ወልደስላሴ ምክንያት ነው። አባታቸው በብዙዎች ባለመማራቸው ትችት ይደርስባቸው ስለነበር ይህ ቁጭታቸውን ልጃቸውን በማስተማር ለመወጣት ቆረጡ።ልጃቸው ህሩይ ለትምህርት ሲደርስ መጀመሪያ ያደረጉት ወደ ቀለም ትምህርት ቤት ማስገባትና ፊደል መቁጠር እንዲጀምር መርዳት ነበር፡፡
አባት ወልደሥላሴ ልጃቸው ህሩይን ገናቦ ገዳም በሚገኝ ትምህርት ቤት አስገብተው ትምህርት እንዲጀምር አደረጉ። በዚያም ፊደል ቆጥረው ንባብ ለይተው ከፍተኛው የቤተክርስቲያን ትምህርት መከ ታተል እንዲችሉ ከመረሀ ቤቴ እስከ ስላሴ ከዚያም እስከ ሽሬ መድኃኒዓለም ድረስ እየወሰዷቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ብርቱ ክትትልና ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር።
ታታሪና የቀለም ቀንድ የነበሩት ብላታ ጌታ ህሩይ፤ በዜማ ትምህርት እስከ መምህርነት ደረጃም ደረሱ። ቀጥለውም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንጦጦ ራጉኤል ቤተክርስቲያን የመፅሐፍን ትርጓሜና ልዩ ልዩ የሃይማኖት ትምህርቶችን በዘመኑ ከነበሩት የደብሩ ሊቃውንት ተምረዋል። ትምህርቱንም በከፍተኛ ደረጃ እና ውጤት አጠናቀቁ።
በወቅቱ የራጉኤል የደብር አለቃና የአፄ ምኒልክ የፅሕፈት ሚኒስትር የነበሩት ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደአረጋይ ከደብሩ ሊቃውንት ስለ ብላታ ህሩይ ዝና በተደጋጋሚ ሰምተው ወደሳቸው እንዲቀርቡ አደረጉ። ሚኒስትሩም ህሩይ ያላቸውን ድንቅ ችሎታና ታታሪነት ተመልክተው ከቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ ጋር ንጉሱ ዘንድ ቀርበው እንዲሸለሙም አድርገዋል፡፡
አፄ ምኒልክም በወቅቱ ለሽልማት ከቀረቡት በእድሜ ከሁሉም አነስተኛ የነበሩት ብላታ ህሩይ ወልደሥላሴን ተመልክተው “እንደው ይሄ ልጅ ትንሽና ገና ብዙ ስራ የሚጠበቅበት ሆኖ ሳለ ለሽልማት መቅረቡ እንዴት ነው” ብለው ሲጠይቁ የፅሕፈት ሚኒስትር የነበሩት ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልዳረጋይ “ጃንሆይ ልጁ እድሜው ነው እንጂ እውቀቱ ትልቅና አስገራሚ ነው፡፡” በማለት የነበራቸውን ብሩህ አዕምሮና ችሎታ መስክረውላቸዋል።
ከሽልማቱ በኋላ ህሩይ በተለይ በቤተ መንግስትና በቤተክህነት ስማቸው ተደጋግሞ ይጠራ ጀመር። ቀስ በቀስም በሁሉም ዘንድ መታወቅና ተወዳጅነት ማትረፍም ቻሉ። በተለይ በነበራቸው የስነ ፅሁፍ ችሎታ፣ የታሪክና የሃይማኖት እውቀት በብዙዎች ዘንድ አንቱታን አተረፉ፡፡
ወደ ጋብቻ የገቡትም በወጣትነት እድሜያቸው
ነበር። ወይዘሮ ሀመረ እሸቴን በቤተክርስቲያን ስርዓት አግብተው አራት ሴቶችና ሁለት ወንድ ልጆችን ማፍራትም ችለዋል። በኋላም በእንግሊዙ ንጉስ ጆርጅ 5ኛ የንግስና ስርዓት ላይ ለመገኘት ከኢትዮጵያ ከተወከሉ ሉዑኮች ጋር ወደ እንግሊዝ አቅንተው እግረ መንገዳቸውም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ፓሪስ፣ ሮም፣ ስክንድሪያና ካይሮ በመዞር ስለ ስልጣኔና አዳዲስ ሀሳቦችን መቅሰም ቻሉ። በዚህም በዘመኑ በአገራችን ከነበሩ ሰዎች የተለየ ዘመናዊ አመለካከት እንዲላበሱ አድረጓቸዋል።
ከተመለሱም በኋላ የመጀመሪያው የአማርኛ መፅሀፍ ትርጉም ከአለቃ ታዬ ጋር ለማዘጋጀትም በቅተዋል። ከዚያም በነበራቸው የተለየ ተስጥኦና የዳበረ ልምድ ህዝባቸው ይጠቅሙ ዘንድ የአዲስ አበባ አስተዳደር ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ።የከተማዋ ፕላንና ግብር እንዲሁም ልዩ ልዩ የአስተዳደር ስርዓቶችን በአዲስ መልክ በማስጀመር ታላቅ ውለታን የሰሩ ናቸው፡፡
በወቅቱ የከተማ አስተዳደር ስርዓትን “ማዘጋጃ ቤት” ብለው በመሰየም አዲስ አሰራር መዘርጋት የጀመሩት እሳቸው ናቸው። በዚህም የአስተዳደር ስርዓቱን ምቹ እንዲሆን አድርገዋል።
በ1914 ዓ.ም በኢትዮጵያያ የውጭ አገር ዜጎች ጉዳይን በሚመለከት ፍርድ ቤት ብላታ ተብለው ማዕረግ ተሰጣቸው ዳኛ ሆኑ።ከዚያም የኢትዮጵያ መንግስት የቅርብ አማካሪ በመሆንም አገልግለዋል። ከአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጋር በመሆንም በድጋሚ አውሮፓን ጎብኝተዋል። በ1919 ዓ.ም ደግሞ ብላቴን ጌታ ተብለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። ከ1922 ጀምሮ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገራቸውን ከውጭው ዓለም ጋር በማገናኘትና የአገሪቱን ጥቅም እንዲከበር በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
በተለይም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለጉብኝት ሲሄዱ ያዩትን አዲስና ለአገር ጠቃሚ ብለው ያሰቡትን ነገር በመቅሰም ወደ አገር ቤት ሲመለሱ እንዲተገበር የሚተጉና ለህዝባቸው ስልጣኔ እጅግ ጉጉም ነበሩ። የኢትዮጵያን ቀይ መስቀል ማህበር በማቋቋምና የመጀመሪያው መሪ በመሆንም አገልግለዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ለአገራቸው ይዋደቁ ለነበሩ ጀግኖች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦም አበርክቷል፡፡
ክቡር ብላቴ ጌታ ህሩይ ወልደሥላሴ በሄዱበት አገር ያገኟቸውን መፅሃፍት ይዘው ወደ አገር በመመለስ የማንበብና የሚውቁትን ነገር ለሌሎች የማድረስ መልካም ልምድም ነበራቸው። ይህም እጅጉን በጠለቀ የማንበብ ፍቅራቸው የበዛ እውቀትን መሸመት አስችሏቸዋል። የተለያዩ ስራ ሀላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰሩ በነፃነት አዳዲስ አሰራሮችና የስራ ሂደቶች እንዲከተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ ያስቻላቸውም ይህ ነው።
ብላታ ጌታ ህሩይ በተለይም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ በሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ በማህበረሰቡ ዘንድ እጅጉን ይወደዱም ነበር። ቤተሰባቸውን በስርዓትና በቤተሰባዊ ፍቅር በመምራት ልጆቻቸው አገራቸውን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ በብርቱ ይመክሩ ነበር።
እኚህ ታላቅ የአገር ባለውለታ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከንጉስ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር በመሆን በስደት ወደ እንግሊዝ አገር ሄዱ። እዚያም ኢትዮጵያ በወራሪዋ ኢጣሊያ ግፍና መከራ እየደረሰባት መሆኑንና የተለያዩ የዓለም አገራት ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው ወረራውን እንዲያወግዙ ለማድረግ ብዙ ጥረዋል። እኚህ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ባለስልጣንነት ያገለገሉት የአገር ባለውለታው ሰው ህሩይ ወልደ ስላሴ በአገሪቱ የስነ ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ባበረክትዋቸው ዘርፈ ብዙ የስነ ፅሁፍ ስራዎችም ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። ከ21 ያላነሱ ልዩ ልዩ መፅሐፍት አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡
በተለይ በብዙዎች ዘንድ የሚጠቀሱ በርካታ ስራዎችን ያበረከቱ ሲሆን ከነዚህም መሀከል፡- ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ ዓድዋ ዘመቻ(ታሪክ)፣ ኢትዮጵያና መተማ (ታሪክ፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስ (ታሪክ)፣ ደስታና ክብር(ታሪክ)፣ የሕይወት ታሪክ (ትምህርት)፣ ዋዜማ (ታሪክ)፣ ማኅደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን(ታሪክ)፣ በዕድሜ መሰንበት ሁሉን ለማየት(ታሪክ)፣ መጽሐፈ ቅኔ (ግጥምና ቅኔ)፣ ወዳጄ ልቤ(ልብወለድ)፣ የልብ ሐሳብ(ልብ ወለድ) አዲስ አለም(ልብ ወለድ)፣ጎሐ ጽባሕ(መልክ፣ ገድልና፣ ነገረ መለኮት)፣ ጥሩ ምንጭ(መልክ፥ ገድልና፣ነገረ፣ መለኮት)፣ ስኳርና ወተት( ተረቶችና ቀልዶች)፣ ለልጅ ምክር ላባት መታሰቢያ (ትምህርት)፣ ተጠቃሾቹ ናቸው።
በመጨረሻም ብዙ የደከሙላት አገራቸው በወራ ሪው ኢጣሊያ እንደተያዘች እዚያ በስደት በቆዩባት እንግሊዝ መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ.ም ሕይወታቸው አልፏል።
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ስለ ብላታ ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ እንዲህ ብለው ነበር።
“አሁን የአዳምን ልጆች ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ። በየጊዜው የጻፋቸው ከፍተኛ ባህሪውን የሚገልጹ መጻሕፍት፤ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈለግ አልመሰለኝም።
በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፤ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፤ እውነትን፣ ፍርድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።
አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለአገርህ ሥራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። በክፉ አድራጊዎች የሚገፋ የዓለምን ፀጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍ አልቻለም። ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ በተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ። ይህም ለእያንዳንዳችን የሚደርሰን ዕድል ነው። አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፣ አንቀላፋህም። በሥጋ ብትለየንም ስምህና ሥራህ በመካከላችን ይኖራሉ።
ኅሩይ! እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህና መንፈስህ የሚሰፍሩበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ሥፍራ በሰላም ዕረፍ።”
ምንም እንኳን ለአገራቸው ነፃነት ሲሟገቱ ያረፉት ብላታ ጌታ ህሩይ በእንግሊዝ አገር ስርዓተ ቀብራቸው ቢፈጸምም ከ9 ዓመት በኋላ አፅማቸው ወደ ኢትዮጵያ በንጉሱ አማካኝነት እንዲመጣ ተደርጎ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን መስከረም 11 ቀን 1940 ዓ.ም በድጋሚ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለአገራቸው እድገትና መሻሻል የራሳቸውን አሻራ ጥለው ያለፉ ታላቅ ምሁር ስለነበሩ በትውልድ ዘንድ ለዘለዓለም ሲታወሱ ይኖራሉ።ለስማቸው ማስታወሻ እንዲሆንም መኖሪያ ቤታቸው የሳይንስ አካዳሚ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2015 ዓ.ም