መልክና ቁመናዋን ላስተዋለ ኑሮ አብዝቶ የፈተናት መሆኑ በግልጽ ያስታውቃል። ገጽታዋ ለቅሶና ሃዘን የበዛበት ይመስላል፤ ጠይሙ ፊቷ ብዙ ይናገራል፡፡ ጥቂት ላሰበ በወይዘሮዋ ውስጥ የተዳፈነ ችግር ስለመኖሩ መገመት አያስቸግርም፡፡ በየአፍታው በዓይኖቿ የሚመነጨው ዕንባ በሕይወቷ ብዙ መከራ ማለፏን ያሳያል፡፡
ወይዘሮ ትርሲት ሸዋ ውልደትና ዕድገቷ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ወትሮም ቢሆን ኑሮ ምቹ ሁኔታን ያልፈጠረላት ወይዘሮ ትርሲት ከደሃ ቤተሰብ መወለዷ ነገሮች ገና በጠዋት እንዲፈትኗት ምክንያት ሆኗል፡፡ ኑሮዋ ዛሬ ላይ ይበልጥ ከፋ እንጂ ለችግርና መከራ አዲስ አይደለችም፡፡ ኑሮ ከውልደቷ ጀምሮ ፊቱን ያዙርባት እንጂ እናት፣ አባት፣ እህትና ወንድም ነበራት፡፡ በሕይወት አለመገጣጠም እናትና አባቷ እሷን ጨምሮ የወለዷቸውን ልጆች በቅጡ ሳያሳድጉ ነው የተለያዩት፡፡ ትርሲት ሕይወቷን ከአባቷ ጋር ነው የገፋችው፡፡
ቀን ስራን እየሰሩ የሚያስተዳድሯት አባቷ ከእለት እለት እድሜያቸው እየጨመረ የኑሮ ጫናን ብቻቸውን መቋቋም እያቃታቸው ሲሄድ ትርሲት እኔም ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ? ከኔም ምን ይጠበቃል? ብላ ማሰቧ የእለት ተእለት ግዳጇ ሆነ፡፡
በዚህ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ምክንያት ትምህርቷን በአግባቡ መማር ያልቻለችው ትርሲት ገና ከጅምሩ ትምህርቷን አቋርጣ እሷንና አባቷን ሊያኖር የሚችል ሌላ አማራጭ ማማተር ጀመረች፡፡ ብዙ አሰበች አወጣች አወረደች ምን ብትሰራ እሷና አባቷ ቢያንስ የዕለት ጉርሳቸውን ሊያገኙ እንደሚችሉ አወጣች አወረደች መልሱን ማግኘት ግን ቀላል አልሆነላትም፡፡ ይህ ደግሞ በትምህርቷ ብቻ ሳይሆን በጤናዋ ጭምር መቃወስን አስከተለ፡፡ መኖር አስጠላት ደካማ አባቷ ተሯሩጠው የሚያመጡትን መብላት የኮሶ ያህል መረራት፡፡ እና ምን ላድርግ ብላ አሰበች፤ አሁንም ለራሷ በቂ መልስ አጣች፡፡ ከእናቷ ጋር ያሉት እህት ወንድሞቿ ከሷ የተሻሉ ባለመሆናቸው ‹‹እንረዳዳ›› ለማለት እንኳን አትችልም፡፡ ሌላ በሕይወቱ ተሳክቶለት እነሱን ሊደግፍ የሚችል ዘመድም ሆነ ጓደኛ አልያም የቅርብ ሰው የለም፤ ብቻ ለትርሲት ኑሮ ጠመመባት ፡፡
አንድ ቀን በአጋጣሚ ፒያሳ አካባቢ ሴቶችን ለስራ ወደአረብ አገር የሚልክ ደላላ መኖሩን ሰማች፤ በአስከፊ የሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ ያለችው ትርሲትም ይህን እድል በከንቱ ማባከን ወይም አጋጣሚውን ማለፍ አልፈለገችም፤ እናም ወደተባለበት ቦታ በፍጥነት በመሄድ ተመዘገበች፡፡ ክፍያ ያለመኖሩ ደግሞ ይበልጥ አጓጓት፤ ደስም አላት፡፡
በፍጥነት ጊዜ ሳታጠፋ ወደተባለው ቦታ አመራች፡፡ የሰማችው እውነት ነበር፤ እሷና መሰሎቿን ወደአረብ አገር በነጻ ለመላክ ደላላው ተፍ ተፍ ይላል፡፡ አሁን በሕይወቷ ትንሽ ተስፋ የፈነጠቀ መሰላት፡፡ ያ ከውልደቷ ጀምሮ ሲጫወትባት የኖረውን ድህነት ድል እንደምትነሳው አይነት ስሜት ተሰማት፡፡
ደላላው ያስፈልግሻል ያላትን ሁሉ እንደምንም በማሟላት ለጉዞ ዝግጁ ሆነች፡፡ ተጠርታ ለእሷ የተስፋ ምድር ወደምትሆናት ቤሩት እስክትገባ ድረስ አንዱ ቀን ሁለት እየሆነ ቆጠረችው፡፡ ያቺ በጉጉት የተጠበቀችው ቀን አልቀረችም መጣች፡፡ ትርሲትም ደካማ አባቷን ከቤት ትታ ለራሷም ለእሳቸውም ቀን አወጣለሁ ስትል ተመኘች፡፡ ያሰበችው አልቀረም የስደት መንገዷን በአውሮፕላን ጉዙ አንድ ብላ ጀመረች፡፡
ከቤቷ ከወጣችበት ቀን ጀምሮም ሰርታ አባቷን ለመጦር ለእሷም ቅርስ የሚሆን ነገር አድርጋ በአገሯ ላይ በሰላም መኖር ሃሳብ ህልሟ ሆነ፡፡ የሰው አገር ግን እንደ አሰበችው ያልተቀበላት ወይዘሮ ትርሲት አንገፍግፏት የሄደችው መከራና ስቃይ በሚገርም ሁኔታ ባህር አቋርጦም ተከተላት። አሁን ትርሲት ቤሩት ደርሳለች ቀጣሪዎቿም ከአውሮፕላን ማረፊያ መጥተው ወስደዋታል፡፡ እሷም አዲሱን የሕይወት መንገዷን ልትጓዝ ሰርታ ልታገኝ ሽማግሌ አባቷን ልትጦር ብዙ እቅድ ላይ ነች፡፡ ከዛ ሁሉ በላይ ደግሞ ጥሩ ተመግባ ጥሩ ኑሮን መኖር ትልቁ ህልሟ ነበር፡፡
የትርሲት ህልም እንዳሰበችው እየሄደ አይደለምⵆ እንደውም በሚገርም ሁኔታ ከነበረችበት ችግር የባሰ ሆነባት፡፡ የስራው መብዛት፣ እረፍት የለሹ ድካም የምግብ በቂ አለመሆንና አለመስማማት የአሰሪዎቿ ቀጭን ትዕዛዝና ቁጣ የደመወዝ በጊዜው አለመከፈል፤ ኧረ ! ምኑ ቅጡ ሁሉም ነገር ግራ አጋባት፡፡ይህ ነው እንዴ የቤሩት ኑሮ? ሰው እንዲህ ሆኖ ነው ሰርቶ የሚለወጠው? የሚሉት ጥያቄዎች ደግሞ ተመላልሰው ወደአእምሮዋ እየመጡ አስጨነቋት፡፡
እነዚህና ሌሎች ጭንቀቶች በአንድ ፊት አገሯ ላይ ጥላቸው የሄደችው ነገ ሰርቼ ገንዘብ ልኬ የእርጅና ዘመኑን በተሻለ ይኖራል ስትል ያሰበችላቸው አባቷ አሳሰቧት። ከምንም በላይ ደግሞ አባቷ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ የምትችልበት መንገድን ማጣቷ ከስራውና እረፍት ማጣት ጋር ተደማምሮ ህመም ሆነባት፡፡
አሁን ያለችው ሰው አገር ባህር አቋርጣ ብዙ ማይሎችን ተጉዛ ነው፤ በቃ አልፈልግም አገሬ ልግባ ብላ ብድግ የምትልበት ዕድል የለም፡፡ በዚህ መካከል የጤናዋ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ ከችግር እየገባ መታመም ይዛለች። ምንነቱን የማታውቀው በሽታ ስቃይዋን እያሳያት ነው፡፡ እንዳትታከም የሰራችበት በወቅቱና በአግባቡ አይከፈላትም፤ ወደቤሩትም የገባችበት መንገድ ህጋዊ ባለመሆኑ እንደልቧ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ይህ ተደራራቢ ችግር መፈጠሯን እንድትጠላ አደረጋት፡፡
ትርሲት በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልቻለችም፡፡ እናም የሆነ ነገር መወሰን እንዳለባት ተሰማት፤ ከምትሰራበት ቤት ደመወዟን እንኳን ሳትወስድ መጥፋትን ብቸኛው አማራጯ አደረገች፣ በዚህ ብቻ አልቆመችም ከምትሰራበት ቤት በድንገት ተሰወረች፣ ጠፋች፡፡
ትርሲት ከምትሰራበት ቤት ትጥፋ እንጂ ሌላ አማራጭ ኖሯት አይደለም፡፡ በእጇ ላይ አምስት ሳንቲም የላትም።ብቻ ካለችበት ፈታኝ ሁኔታ ለመውጣት ስትል ነው የጠፋችው፡፡
ተደራራቢ ስራ፣ እረፍት ማጣት፣ በወጉ አለመመገብ አስመርሯት ከአሰሪዎቿ ቤት ጠፍታ የወጣችው ትርሲት አሁንም ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑላትም፤ እንደውም ይባስ አስጨናቂ አስፈሪ ቀናትን ማሳለፍ አስገዳጅ ሆነባት፡፡
ከአንዱ ጓደኛ ወደሌላ እየተዘዋወረች ማደር ያገኘችውን ከፖሊስ እየተደበቀች መስራትና የእለት ጉርሷን መቻል ብቻ ሆነ አላማዋ ከአገሯ ስትወጣ ሰንቃው የነበረው ተስፋና ህልሟ ሁሉ አሁን አብሯት የለም፡፡ ከዛ ይልቅ እንዴት ከፖሊስ አምልጣ ዛሬን ማደር እንደምትችል ማሰላሰል ሆነ ስራዋ፡፡ የትርሲትን ችግር ተረድተው ያስጠጓት የነበሩት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም፤ ፊሊፒንስና ሱዳናዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምር እንጂ፡፡
ወይዘሮ ትርሲት ወትሮውንም ቢሆን በጤናዋ ላይ ሙሉነት አይሰማትም ነበር፤ በተለያዩ ጊዜያት ጎሸም እያደረጓት የሚያልፉ ህመሞችም አልጠፉም፤ ነገር ግን በዚህ የችግር ጊዜዋ ውስጥ ሆና ድንገታዊ የሆስፒታል አልጋ የሚያስይዝ ህመም አጋጠማት፤ ህጋዊነትን ባልያዘችበት አገር ከጎኗ የእኔ የምትለው ሰው ሳይኖራት መታመሟ አሳዛኝም አስደንጋጭም ሆነባት፡፡ “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ ወይዘሮ ትርሲት በህመሟ ምክንያት ከፍ ያለ ጭንቀት ውስጥ ብትገባም ህጋዊ ወረቀቱን ተጠቅሞ ወደሆስፒታል የሚወስዳት አሳክሞ የሚያድናት ደግ ሱዳናዊ አገኘች፡፡ ይህ አጋጣሚ ፈጣሪ የተላከላት እንደሆነ አሰበች። የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ ለእኔ ልትገልጽልኝ ያልፈለገችውን ህመም በሰው አገር በኦፕሬሽን አውጥታ ታክማ አገገመች።
አሁን ወይዘሮ ትርሲት ከበሽታዋ አገግማ በአካል ጎልብታለች፡፡ ዛሬም ግን ከጎኗ የሚሆን ዕንባዋን የሚያብስ ዘመድ የላትም፡፡ አባቷንም በተለያዩ ጊዜያት በተለይም አመት በዓል ሲሆን ያላትን ታካፍላቸው እንጂ እንደ ልጅ ያሳበችውን ያህል ልታግዛቸው አልቻለችም፡፡ ማንም እንደሌላት የምታውቀው ወጣት አጋር እንደሚያሻት ልቧ ሹክ እያላት ነው፡፡
ትርሲት በህመሟ ምክንያት ድንገት ካወቀችው ሱዳናዊ ጋር መግባባት ይዛለች፡፡ ሱዳናዊው እንደእሷ እንጀራ ፈልጎ ከአገሩ የተሰደደ ወጣት ነው፡፡ ስደት ቢያመሳስላቸውም እሱ ህጋዊ ነው፡፡ እሷ ደግሞ ህገወጥ ስደተኛ መሆኗ ያለያያቸዋል፡፡ ህክምናዋን በእሱ አማካይነት ካደረገች በኋላ አብረው መዋል ማደር ጀምረዋል፤ እሱን ባገኘችው ቁጥር ጎዶሎዋ የሞላ፣ ቀኗ የፈካ ይመስላታል፡፡
ዓይኑን የጣለባት ሱዳናዊ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ልቧን ተረክቦ ልቡን አስረከባት፡፡ የሁለቱ ግንኙነት ፍቅር ቢያሸንፍ ቁምነገር አሰቡ፡፡ ትዳር ይዘው ጎጆ ቀልሰው መኖር ጀመሩ፡፡
ጥንዶቹ በትዳር ዘልቀው ቤት ሲያቀኑ መተሳሰባቸው ነገን የሚያሻግር ሆነ፡፡ የአብሮነታቸቸው መስመር ጠንክሮ ዓመታትን በአንድ ኖሩ፡፡ ፍቅራቸው በመኖር ብቻ አልተጋመሰም፡፡ ሁለቱን በአንድ የሚያጣምር፣ ሕይወት ኑሯቸውን የሚያሳምር ፍሬ አገኙ፡፡ ትዳራቸው በልጅ በረከት ታደሰ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን በፍቅር እያዩ አቅፈው ሳሙ፡፡ ወይዘሮ ትርሲትም ዳግም ነገ የመኖር ተስፋዋ ለመለመ፡፡ አሁን የምኖርለት ከጎኔ ሆኖ ችግር ደስታዬን የሚካፈለኝ የእኔ ሰው አለኝ ማለት ጀመረች፡፡
ትርሲት ከልጇና ከባለቤቷ ጋር ሕይወትን ቀጥላለች። ምንም እንኳን የስደት መንገዷ በዚህ መልኩ ይሆናል ብላ ባታስብም በተለይ ልጇን ስታይ ደስ ይላታል፡፡፡፡ ተስፋዋ ይለመልማል፡፡ ነገ የተሻለ እንደሚሆን ታስባለች፤ ብቸኛ የሆነችባቸው ዓመታት አሁን በእጥፍ የደስታ ቀናት እያጣጣመቻቸው ነው፡፡ ዛሬ ልጇና ባለቤቷ ጎዶሎዋን ሞልተዋል፣ ዓለሟን አሳምረዋል፣ ዕንባዋን አብሰው ፈገግ ታዋን መልሰዋል፡፡
ወይዘሮ ትርሲት በአንድ ልጅ አላበቃቸም ከአመታት ቆይታ በኋላ ሁለተኛ ልጅ ደገመች፡፡ አሁን የእሷም ሆነ የሱዳናዊው የትዳር አጋሯ ደስታ ከፍ ብሏል፡፡ በልጅ በረከት መባረኳ ልዩ ስሜትን ፈጥሮባታል፡፡
አሁን ላይ ትርሲት እንደሌሎች ሰዎች ወጥታ አትሰራም ባለቤቷ ሰርቶ የሚያመጣውን እየተቀበለች ልጆቿን ነው የምታሳድገው? ስለጤናቸው አመጋገባቸው ብቻ በየሰዓቱና በየደቂቃው ስላላቸው ሁኔታ ከመከታተል በእነሱ ውስጥ ነገን አሻግራ ከማየት የዘለለ ሃሳብም ስራም የላትም፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አንድ በሕይወቷ ያጋጥመኛል ብላ ያላሰበችው ዱብ እዳ ወደቤቷ ገባ፡፡ ወይዘሮ ትርሲት በጣም አዘነች አብቦ የነበረው ተስፋዋ እንደጉም ሲበን እንደጤዛ ሲረገፍ ተሰማት፤ እሷን ካለችበት የጤና ችግር አላቆ አሳክሞና አድኖ በትዳር ይዞ የሁለት ልጆች እናት ያደረጋት ሱዳናዊው ባሏ በድንገታዊ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ እጅግ ከባድ ጊዜ ሆነባት፡፡ እድሜዋን ሙሉ ችግር እየተከተለ ለምን እንደሚያሳድዳት አልገባ አላት። የሁለት ህጻናት ሴት ልጆቿ ነገ አስጨነቃት ምን ላድርግ ምን ልሁን ብላ አሰበች፡፡ ለጊዜው ከማልቀስ በቀር ይህ ነው የሚባል መፍትሔን ለራሷ መንገር ሳትችል ቀረች፡፡
ሆድ ቀን አይሰጥም፣ በተለይ ምኑንም የማያውቁት ህጻናት ስለችግር ቢነግሯቸው፣ በያባብሏቸው አይገባቸ ውም፡፡ ወይዘሮ ትርሲት ልጆቿን ለማብላት ስትል የተወችውን እዚህም እዚያም የማለት ስራ ጀመረች፡፡ እሱም ቢሆን ቀላል አልነበረም፡፡ ልጆቿ ላይ ቤት ዘግታ በየሰው ቤት በመዞር ጽዳትና ያገኘችውን ስራ እየሰራች የእለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ጣረች፡፡
“የአገሬው ሰው መልካም ነው ፤ ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያቴ ልጆቼ እንዳይራቡ ሁሌም የሚችለውን ያደርግ ነበር ትምህርት ቤትም አስገብተውልኝ ይማሩም ነበር በዚህ በጣም አመሰግናቸዋለሁ” ትላለች ስለነበራት ቆይታ ስታስታውስ፡፡
“የሰው ቤት ቢያመሹበት አያድሩበት” ነውና ወይዘሮ ትርሲትም ምንም እንኳን ከአገሯ ተሰዳ የሄደችበት አላማ ግቡን ባይመታም ሁለት ልጆችን ግን አግኝታለች። እረዳሃለሁ ብላ ትታቸው የሄደቻቸው አባቷም በችግር ምክንያት በገቡበት የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን ሰምታለች፡፡
ችግርና ሃዘን ሕይወቷን ሙሉ የሚያሳድዷት ትርሲት የአባቷን ሃዘን በሰው አገር ልትወጣው ግድ አላት። ሃዘኗን ከጨረሰች በኋላ ግን ቤሩት ላይ የሚያቆያት አንዳች ምክንያት አጣች፡፡ ልጆች ጥላ እንደልቧ መስራት አልቻለችም፡፡ ልጆቿን የሚይዝላትም አላገኘችም፤ በመሆኑም አገሯ ገብታ የሆነችውን ለመሆን ወሰነች፡፡
አገሯ ስትገባም የት አርፋለሁ የሚለው ጉዳይ አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ሆነ፡፡ አባቷ በሕይወት ዘመናቸው የኖሩባት አንዲት ክፍል የቀበሌ ቤት እንዳለች ታውቃለች፡፡ ቢያንስ ልጆቼን ይዤ አንገቴን አስገባበታለሁ ብላ በማሰብ ደጋግ ኢትዮጵያውያን ከነልጆቿ ወደአገሯ እንዲልኳት ለምና ወደትውልድ አገሯ ተመለሰች፡፡
ወይዘሮ ትርሲት አገሯ መድረሷ ቢያሰደስታትም ሸብ ረብ ብሎ የሚቀበላት እንደማይኖር ታውቃለች፡፡ በእጇ ኢትዮጵያውያኑ አዋጥተው ከሰጧት ጥቂት ገንዘብ በቀር ምንም የለም፤ ከአውሮፕላን ወርዳ ወደዛች የምታውቃት የአባቷ አንድ ክፍል የቀበሌ ቤት አመራች፡፡ ያየችውን ማመን አልቻለችም፡፡ ቤቱ ተተኪ የለውም በሚል በወረዳው አካላት ታሽጓል፡፡ ሌላ ንዴትና ተስፋ መቁረጥ ውስጧ ገባ። ያሳደጓት የሚያውቋት ጎረቤቶቿ ግን ከነልጆቿ ሰብስበው ቢያንስ የመንገድ ድካሟን አራግፋ ወደቀጣዩ የሕይወት መስመር ትገባ ዘንድ አገዟት፡፡
ዋል አደር ብላ ወረዳው ጽህፈት ቤት ሄዳ ልጅነቷን በመናገር ቤቱ እንዲከፈትላት ጠየቀች፤ እነሱም መልካም ፈቃዳቸው ሆነ፡፡ ቤቱን በመክፈት ወይዘሮ ትርሲት ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ የሆኑ ልጆቿን ማሳረፍ ቻለች፡፡
ትርሲት አመታትን በችግር በገፋችበት የስደት ሕይወት ያተረፈችው ነገር ቢኖር ልጆቿ ብቻ ናቸው፡፡ በልጆቿ ተስፋ ታደርጋለች፡፡ ዛሬም በአንዲት ክፍል ቤቷ ውስጥ ልጆቿ የማያውቁትን ባህልና የችግር ኑሮ ይኖሩ ዘንድ ፈርዳባቸው አብረዋት እየተኮራመቱ ነው፡፡ ብርድና ውርጩ ያስቸግራታል፡፡
የልጆቿ አባት አሁን ከእሷ የለም፡፡ ልጆቹም አባታቸው ያደርግላቸው የነበረውን ነገር ዛሬ ላይ ማግኘት አይችሉም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ያስከፋታል፡፡ መፈጠሯንም እንድትጠላ ያስገድዳታል፡፡ የትናንትናው ሁኔታ ዛሬ አብሯት የለም። ቢያንስ የሚበሉት የማያጡት ልጆቿ በደጋጎች እርዳታም ቢሆን ጥሩ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩት ልጆቿ ዛሬ ላይ ሳይበሉ ለማደር ተገደዋል፡፡ አፍ መፍቻቸው ባልሆነ ቋንቋ እየተቸገሩ ከእናታቸው እቅፍ ለመውጣት ሲቸገሩ ስታይ ሁሉም ነገር ከባድ ይሆንባታል፡፡
የቀደመ ታሪኳን የሚያውቁና ችግሯን የተረዱ አንዳን ዶቹ በማጽናናትና በምክር እንዲሁም የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ያግዟታል፡፡
ትርሲት አገር ቋንቋ የማያውቁ ልጆቿን የመንግስት ትምህርት ቤት አስገብታለች፤ ከሁኔታዎች ጋር ተስማምተው ኑሮን ይገፉ ዘንድ ትጥራለች፡፡ ነገር ግን ብዙም ጤንነት ስለማይሰማት እንደልቧ ያገኘችውን ሰርታ መኖር እየከበዳት ነው፡፡ ‹‹የእኔስ ይሁን እነዚህን ህጻናት ግን ምን ላድርጋቸው? ስትል ትጠይቃለች፤ ማንነቷን የተረዱ የወረዳ ስራ አስፈጻሚዎች አሽገውት የነበረውን የአባቷን ቤት ከፍተው ስላሳረፏት ምስጋና ታቀርባለች፤ ነገር ግን ጣሪያ ግድግዳ እንጀራ ሆኖ አይቆረስ ወጥ ሆኖ ፈሰስ አይደረግ ነገር ሆኖባት ከልጆቿ ጋር ተፋጣለች፡፡
ነገን ከልጆቿ ጋር በጤና ለመኖር ዛሬ ላይ ደጋግ ኢትዮጵያውያን በእኔ አቅም የሚሰራ ስራን ቢሰጡኝ ሰርቼ ልጆቼን ባስተምር እኔ ባለፍኩበት ባያልፉ ስትልም ትማጸናለች፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2015 ዓ.ም